ታራ

ከውክፔዲያ
ታራ በ1545 ዓ.ም. ለሳለው ለጊዮም ሩዊ እንደ መሰለው

ታራ (ዕብራይስጥ፦ תָּרַח /ታረሕ/) በኦሪት ዘፍጥረት መሠረት የናኮር ልጅና የአብራም (አብርሐም) አባት ነበረ።

ዘፍጥረት 11፡26-32 ስለ ታራ በአማርኛ እንደሚለው፣ የታራ ዕድሜ 100 ዓመት ሲሆን አብራም፣ 2 ናኮርሐራን የተባሉትን ወንድ ልጆች ወለደ። ከዚያ በኋላ ሐራን የሎጥ አባት ሆነ፣ ዳሩ ግን ታራና ቤተሠቡ በከለዳውያን ዑር ገና እየኖሩ ልጁ ሐራን ሞተ። አብራም ሚስቱን ሦራን (ሣራን) አግብቶ እስዋ ግን መካን ነበረች። ከግዜ በኋላ ታራ ልጁን አብራምን፣ የአብራምንም ሚስት ሦራንና የልጁን ልጅ ሎጥን ወሰዳቸው፣ ከከለዳውያን ዑር ወደ ከነዓን አገር ለመዛወር ተጓዙ። ሆኖም ካራን የሚባለውን ከተማ በደረሱ ጊዜ መንገዳቸውን ተዉና በዚያ ተቀመጡ። በጠቅላላ የታራ ዕድሜ 205 ዓመታት ነበረ። (በዕብራይስጥግሪክና በሳምራዊው ትርጉሞች ዘንድ፣ ታራ ልጆቹን ሲወልድ እድሜው 70 አመት ብቻ ነበረ። በተጨማሪ፣ በሳምራዊው ትርጉም ዘንድ የታራ እድሜ በጠቅላላ 145 ዓመታት ብቻ ደረሰ።)

መጽሐፈ ኩፋሌ 10፡28-11፡16 ዘንድ፣ ታራ ከአባቱ ናኮርና ከእናቱ ኢዮስካ በ1806 አመተ አለም ተወለደ። በዚያን ጊዜ ክፉ አዕዋፍና በተለይ ቁራዎች የሰው ልጅ የዘራውን የአትክልት ዘር ከከላውዴዎን እርሻዎች ይበሉ ነበር። በ1870 አ.አ. ታራ ሚስቱን ኤድናን አገባት፤ እርሷም የሴሮሕ ልጅ አብራም ልጅ ነበረች። በ1876 አ.አ. ኤድና ልጁን አብራምን ወለደችለት፤ ስለዚህ የታራ እድሜ 70 ዓመታት ነበረ። የታራ ቤተሠብ እንደ ሰው ልጅ ሁሉ ጣኦታትን ያመለኩ አረመኔዎች ነበሩ፤ ታራም እራሱ የጣኦታት መቅደስ ቄስ ነበረ። አብራም ግን በወጣትነቱ ከአባቱ ታራ እምነት መለየት ጀመረ፣ የአብራምም እድሜ 15 አመታት ሲሆን አዕዋፍን ለመከላከል ማረሻን ፈጠረ፤ ስመ ጥሩ ሆነ። በ1903 አ.አ. ግን አብራም አባቱን ስለ ጣኦታት እንዳያመልካቸው፤ ሕያው እግዚአብሔርን ብቻ እንዲያመልክ ለመነው። ታራም እውነትህ ነው፣ ግን የጣኦታት መቅደስ ቄስ ሆኔ እውነቱን ብነግራቸው ሕዝቡ ይገድሉናል እንዳይገድሉህ አንተም ዝም በል ብሎ መለሰው። በ1936 አ.አ. ግን አብራም መቅደሱን ጣኦታቱንም በሙሉ አቃጠላቸው። ወንድሙም ሐራን ጣኦታቱን ለመጠብቅ ሲያስብ በዚሁ እሳት ሞተ። ስለዚሁ ድርጊት ታራና ቤተሠቡ ወደ ከነዓን አገር ለመሸሽ ተጓዙ፤ ሆኖም በካራን ከተማ ደርሰው ተቀመጡ። በ1953 አ.አ. በካራን ሲቀመጡ ታራ ልጁን አብራም፣ የአብራምም ሚስት ሦራንና የልጁን ልጅ ሎጥን ወደ ከነዓን አገር አሰናበታቸው።

ለዚህ ተመሳሳይ ታሪክ በአይሁድ ረቢዎች መጻሕፍት እንዲሁም በእስልምና ቁርአን ይገኛል። በቁርአን የአብርሐም አባት ስም «አዛር» ቢባልም መታወቂያው ከታራ (ታረሕ) ጋር አንድላይ መሆኑ አይጠራጠርም።