አቢሜሌክ

ከውክፔዲያ
አቢሜሌክ አብርሃምን ሲገስጽ (1650 ግድም እንደ ተሳለ)
ይስሐቅና አቢሜሌክ (1650 ግድም እንደ ተሳለ)

አቢሜሌክ (ዕብራይስጥ፦ אֲבִימֶלֶךְ ፣ אֲבִימָלֶךְ /አቢሜሌክ/ ወይም /አቢማሌክ/) በኦሪት ዘፍጥረት ዘንድ የፍልስጥኤማውያን ከተማ ጌራራ ንጉሥ ነበር። የስሙ ትርጉም «አባቴ ንጉሥ ነው» እንደ ሆነ ይታሰባል።

መጀመርያው የሚጠቀሰው በምዕራፍ ፳ ሲሆን አብርሃም በጌራራ ንጉሥ አቢሜሌክ ግዛት እየኖረ ሚስቱ ሣራ እኅቴ ነች በማለት አቢሚሌክን እንዳታለለ ይወራል። ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ታሪክ ስለ ሣራና የግብጽ ፈርዖን አለ።

ከዚያ በኋላ በምዕራፍ ፳፮ ይስሐቅ ደግሞ በአቢሜሌክ ግዛት ሲኖር ሚስቱ ርብቃ እኅቴ ነች በማለት እንዲህ ያደርጋል።

በመጽሐፈ ኩፋሌ መሠረት ግን፣ የአብርሃምና ሣራ ታሪክ ከፈርዖን ጋር፣ የይስሐቅና ርቅቃም ታሪክ ከአቢሜሌክ ጋር ብቻ ይሰጣል። የአብርሃምና ሣራ ታሪክ ከአቢሜሌክ ጋር በኩፋሌ ስለማይታይ፣ ከሌሎቹ ሁለት ታሪኮች በመቀላቀል እንደ ተሳተ የሚል ሀሣብ አለ። በዚህ መጽሐፍ የከተማው ስም «ጌራሮ» የንጉሡም ስም «አቤሜሌክ» ተጽፈዋል።

አይሁድ መጽሐፍ «ሃጋዳ» ግን፣ በአብርሃምና በይስሐቅ ዘመናት ሁለት አቢሜሌኮች በጌራራ ገዙ። በይስሐቅ ዘመን የነበረው የሌላው አቢሜሌክ ልጅ ሲሆን ንጉሥ በሆነው ጊዜ ስሙን ከ«ቤንሜሌክ» (የንጉሡ ልጅ) እንደ አባቱ ወደ «አቢሜሌክ» ቀየረው ይላል። እነዚህ ስያሜዎች ደግሞ ምናልባት ማዕረጎች (እንደ አልጋ ወራሽ ያሕል) ሊሆኑ ይቻላል።

አማርና ደብዳቤዎች ዘመን (1340 ዓክልበ. አካባቢ) የጢሮስ ግብጻዊ ገዥ ወይም ከንቲባ ስም አቢሚልኪ ሲሆን ይህ ምናልባት ግንኙነት እንዳለው ተብሏል።

በሌላ ልማድ በኪታብ አል-ማጋል፣ በመዝገቦች ዋሻ እና በየአዳምና የሕይዋን ትግል በተባሉት መጻሕፍት እንደሚጻፍ፣ የጌራራ ንጉሥ አቢሜሌክ በአብርሃም ዘመን ለመልከ ጼዴቅ ኢየሩሳሌምን ከሠሩት ፲፪ ነገሥታት አንዱ ነው።

ሌላ አቢሜሌክ (መሳፍንት)መጽሐፈ መሳፍንት ፱፡፩-፮ ከአባቱ ጌዴዎን በኋላ እስራኤልን ገዛ።

በ"Wikimedia Commons"
(የጋራ ፎቶዎች ምንጭ)
ስለ አቢሜሌክ የሚገኛኙ
ተጨማሪ ፋይሎች አሉ።