አኒታ

ከውክፔዲያ
የአኒታ ነሐስ ጩቤ በካሩም ካነሽ ተገኝቶ

አኒታ በጥንታዊ አናቶሊያ (ሐቲ) ታሪክ የኩሻራና የካነሽ (ነሻ) ንጉሥ ነበር።

አባቱ ፒጣና የኩሻራ ንጉሥ ሲሆን በ1662 ዓክልበ.. ግድም ካነሽን ያዘ። በዚያ ዓመት ልጁ አኒታ ወደ ካነሽ ዙፋን ተከተለው። ይህ ሁሉ «የአኒታ ዐዋጅ» በተባለው ጽሑፍ እንዲህ ይተርካል፦

«...የነሻ (ካነሽ) ንጉሥ በኩሻራ ንጉሥ ተማረከ። የኩሻራ ንጉሥ ፒጣና ከከተማው በብርታት ወጣ፤ ነሻ ከተማ በሌሊት በኃይል ያዘ። የነሻን ንጉሥ ማረከ፤ በነሻ ኗሪዎች ላይ ግን ክፋትን አላደረገም። ይልቁንም የሱ አባቶችና እናቶች አደረጋቸው። ከአባቴ ፒጣና በኋላ፣ በዚያም ዓመት፣ እኔ አመጽ ሰበርኩ። ወደ ጸሐይ መግቢያ የሚቀመጡት ማናቸውንም አገራት ሁላቸውንም አሸነፍኩ። «ኡላማ ከተማ<...> የሐቲ ንጉሥ ተመለሰ <...> በተሽማ ከተማ አሸነፍኩት <...> ነሻ ከተማ፣ እሳት(?) <...> ሐርኪዩና ከተማ በመዓልት ወሰድኩ፤ ኡላማ ከተማ በሌሊት በኃይል ወሰድኩ፣ ተነንዳ ከተማ በመዓልት ወሰድኩ። ለነሻ ጣኦት ሸጠኋቸው። ዋጋው ለጣኦቱ ተሰጠ። ከኔ በኋላ የሚነግሥ ሁሉ፣ ኡላማ ከተማ፣ ተነንዳ ከተማ፣ ሃርኪዩና ከተማ፣ የነሻ ጠላቶች፣ ዳግመኛ የሚሠፍራቸው ማናቸውም ሁሉ፣ ጣኦቱ ይቃውመው! <...> «ከአባቴ አንድ አመት በኋላ <...> ወደ ዛልፑዋ ባሕር (ጥቁር ባሕር) ሄድኩ፤ ጠረፌ ሆነ። እነኚህን ቃላት ከደጄ ጽላት ቅጂ አደረግሁ። ካሁን ወዲያ ለጊዜ ሁሉ ማንም ይህን ጽላት አይሰርዝ! የሚሰርዘው ማንም ሁሉ፣ የነሻ ጠላት ይሁን። «ዳግመኛ የሐቲ ንጉሥ ፒዩሽቲ መጣ። በዛላምፓ ከተማ ያመጣቸውን ትርፍ ሥራዊቱን አሸነፍኩ። «በባሕር አጠገብ የዛልፓንም ምድር ያዝኩ። በቀድሞ፣ የዛልፓ ንጉሥ ኡሕና ጣኦታችንን ከነሻ ከተማ ወደ ዛልፓ ከተማ ወስዶ ነበር። በኋላ ግን እኔ አኒታ ታላቁ ንጉሥ ጣኦታችንን ከዛልፓ ወደ ነሻ መለስኩት። የዛልፓን ንጉሥ ሑዚያን ወደ ነሻ አመጣሁት። ሐቱሳሽ በኔ ላይ በክፋት ተባብሮ ስላልሆነ፣ ተውኩት። በኋላ ግን ረሃብ በደረሰበት ጊዘ ጣኦቷ ከተማውን ሰጠችኝ። በሌሊት በኃይል ወሰድኩት። በሥፍራው ፌጦ ዘራሁ። ከኔ በኋላ የሚነግሥ ሁሉ፣ ሀቱሳሽን ዳግመኛ የሚሠፍረው ማናቸውም ሁሉ፣ ጣኦቱ ይመታው! «ፊቴን ወደ ሻላቲዋራ ከተማ አዛወርኩ። ሻላቲዋራ እንጨት <...> እና ሥራዊቱን አመጣብኝ። ወደ ነሻ ወሰድኳችቸው።<...> «በማደን ሂጄ በአንድ ቀን ፪ አናብሥት፣ ፸ እሪያዎች፣ መቶ ሃያ አውሬዎች፣ ወይም ነብርአጋዘን ወዘተ፣ ሁላቸውን ወደ ነሻ አመጣሁ። «በሚቀጥለው ዓመት ወደ ሻላቲዋራ ከተማ ለውግያ ሄድኩ። የሻላቲዋራ ሰው ከነልጆቹ ተነሡ። በኔ ላይ መጣ። ምድሩንና ከተማውን ትቶ የሑላና ወንዝ ያዘ። የነሻ ሥራዊት ወደ ኋላው ሄዶ መንደሮቹን አቃጠሉ። ወደ ከተማው የሰበሰባቸው፦ 1400 ወታደሮች፣ 40 የፈረሰኛ ቡድኖች ነበሩ፤ <...> ስቦ ወጣ። «በዘመቻ ስሂድ<...> የቡሩሻንዳ ሰው የብረት ዙፋንና የብረት ምርኳዝ እንደ ስጦታዎች አመጣልኝ። ወደ ነሻ በተመለስኩበት ጊዜ የቡሩሻንዳ ሰው ከኔ ጋር ወስድኩ። ወደ ግቢው ሲገባ፣ በቀኜ ይቀመጣል።»

ይህ ዐዋጅ በኬጥኛ ተጽፎ ከሁሉ መጀመርያው የታወቀው የሕንዳዊ-አውሮጳዊ ቋንቋዎች ቤተሠብ ናሙና እርሱ ነው። የሐቲ ዋና ከተማ ሃቱሳሽን አፍርሶ ዳግመኛ የሚሠፍረውን ንጉሥ ሁሉ ቢረግምም፣ እንዲያውም ከመቶ ዓመት ያህል በኋላ የኬጥያውያን መንግሥት ንጉሥ 1 ሐቱሺሊ ዳግመኛ ሠፈረው።

አኒታም የካነሽ ንጉሥ ሲሆን የአሦር ነጋዴዎች ወደ ካሩም እንዲመልሱ አስቻለ። ከሐቲ ብዙ ስላሸነፈ «ታላቅ ንጉሥ» የሚለውን ማዕረግ ወሰደ። የአኒታ ተከታይ ምናልባት ዋና አለቃው ፐርዋ ሲሆን፣ ከትንሽ በኋላ «የአሕላዚና ታላቅ ሰው» ዙዙ ተከተለው። «አሕላዚና» ባይታወቅም የካነሽ መንግስት ስያሜ እንደ ነበር የሚል አስተያየት አለ።

ቀዳሚው
ፒጣና
ካነሽ ንጉሥ
1662-1637 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
ዙዙ