አይጊያሌዎስ

ከውክፔዲያ

አይጊያሌዎስግሪክ አፈ ታሪካዊ ዜና መዋዕል ዘንድ የሲክዮን መንግሥት መሥራች ነበረ። አውሳብዮስ (317 ዓ.ም. ጽፎ) ካስቶርን (150 ዓክልበ. ግድም) ሲጠቅስ፣ የአይጊያሌዎስ ዘመን 52 ዓመታት ሲሆን በአሦር ንጉሥ ቤሉስ 15ኛው ዓመት ጀመረ፤ ይህም በግሪክ መጀመርያው መንግሥት (ምናልባት ከ2360-2308 ዓክልበ. ግድም) ነበር ይላል። ከዚህ በላይ ፔሎፖኔሶስ መጀመርያ በእርሱ ስም «አይጊያሌያ» ይባል ነበር፣ ተከታዩም ኤውሮፕስ ነበር ይለናል።

ፓውሳንዮስ (107 ዓ.ም. ግድም) እንደ ጻፈ፣ «ሲክዮንያውያን፣ በዚሁ ጠረፍ ክፍል የቆሮንቶስ ሰዎች ጎረቤቶች፣ ስለ ራሳቸው አገር እንደሚሉ አይጊያሌዎስ መጀመርያው ኗሪ ነበረ፣ እስካሁን አይጊያሎስ የተባለው የፔሎፖኔሶስ አውራጃ እርሱ ስለነገሠበት ስለርሱ ተሰየመ፣ በሜዳውም ላይ አይጊያሌያ የተባለውን ከተማ መሰረተ።[...] በተጨማሪ አይጊያሌዎስ ኤውሮፕስን ወለደ፣ ኤውሮፕስም ቴልቂንን ወለደ፣ ቴልቂንም አፒስን ወለደ።»

ቢብሊዮጤኬ የተባለው መጽሐፍ (ከ150 ዓክልበ. በኋላ፣ በአፖሎዶሮስ ተጽፎ እንደተባለ) እንደ ጻፈ፣ «ኢናቆስ (የውቅያኖስጤቲስ ልጅ) እና ሜሊያ (የውቅያኖስ ልጅ) ወንድ ልጆች ፎሮኔዎስና አይጊያሌዎስ ነበሯቸው። አይጊያሌዎስ ያለ ልጅ አርፎ መላው አገር አይጊያሊያ ተባለ፤ ፎሮኔዎስም በኋላ ፔሎፖኔሶስ በተባለው አገር ሁሉ ነግሦ አፒስንና ኒዮቤን በሴት አድባሩ ቴሌዲኬ ወለዳቸው።»

ቀዳሚው
የለም (መሥራች)
የአይጊያሌያ (ሲክዮን) ንጉሥ
2360-2308 ዓክልበ. ግድም (አፈ ታሪክ)
ተከታይ
ኤውሮፕስ