ካራን

ከውክፔዲያ
Traditional mud brick "beehive" houses in the village of Harran, Turkey

ካራን (አካድኛ፦ ሐራኑ፣ ግሪክ፦ Κάρραι /ካራይ/፤ ሮማይስጥCarrhae /ካራይ/) በዛሬው ቱርክ አገር ሻንልዩርፋ አውራጃ ውስጥ የሚገኝ ሥፍራ ነው።

እጅግ ጥንታዊ ከተማ ሲሆን በአብርሃም ዘመን መኖሩ በኦሪት ዘፍጥረት ይጠቀሳል። የአብርሃም አባት ታራ ከነቤተሠቡ ጋር ከከለዳውያን ዑር ከተማ ተነሥተው ሁላቸው ወደ ካራን እንደ ፈለሱ ይላል። የካራን ዙሪያ አገር በእብራይስጥ ትርጉም ፓዳን-አራም (የአራም መንገድ) ወይም አራም ናሓራይም (አራም ከሁለቱ ወንዞች መካከል ወይም መስጴጦምያ) ይባላል። ካራን በባሊኅ ወንዝ ላይ ነው።

ከዚህ በላይ በኤብላ የተገኙት ጽላቶች (2127-2074 ዓክልበ. ግድም ኡልትራ አጭር አቆጣጠር) የካራንን ጥንታዊነት ይመሰክራሉ። በነዚህ መዝገቦች መሠረት፣ አንድ የካራን ከንቲባ የኤብላን ልዕልት ዙጋሉምን አግብቶ ነበርና እርሷ ከዚያ «የካራን ንግሥት» ተባለች። ካራንም ከዚያ ዘመን ከኤብላ ጋር የሚነግድ ነጻ ከተማ እንደ ነበር ይታወቃል።[1]

ቢያንስ ከ1800 ዓክልበ. ካራን (እንደ ዑር) የጨረቃ ጣኦት የሲን ቤተ መቅደስ መኖርያ እንደ ነበረ በማሪ መዝገቦች ይነገራል። የአራማውያንና ሆራውያን መኖርያ ከ1500 ዓክልበ. በኋላ በሚታኒ (ሃኒጋልባት) መንግሥት ነበረ፤ ኬጢያውያን ግን በ1320 ዓክልበ. ግድም አቃጠሉትና ያዙት። ከዚህም በኋላ ዙሪያው በአሦር ሥልጣን ውስጥ ሆነ። አሦርም በ621 ዓክልበ. እየወደቀች ለጥቂት አመታት እስከ 617 ዓክልበ. ድረስ ካራን የአሦር መንግሥት መጨረሻ ዋና ከተማ ሆነ።

  1. ^ Kazane Hoyuk and Urban Life Histories in Third Millennium Upper Mesopotamia, Andrew Theodore Creekmore, 2008 p. 93.