ጋምብሪቪዩስ

ከውክፔዲያ
ንጉሥ ጋምብሪኑስ፣ የመጥመቅ አስተማሪ - ከ1890 ዓ.ም. መጽሔት

ጋምብሪቪዩስ (ወይም ጋምበር) የጀርመን መምኅር ዮሐንስ አቬንቲኑስ ባሳተመው ዜና መዋዕል ዘንድ፣ የጀርመንና ሳርማትያ ፯ኛው ንጉሥ ነበረ። ከአባቱ ማርሱስ ቀጥሎ ለ44 ዓመታት (ምናልባት 2019-1975 ዓክልበ. ግድም) ነገሠ። ኪምብሪ የተባለው ጀርመናዊ ነገድ ከርሱ እንደ ተወለዱ ይላል። የሮሜ ጸሀፍት ታኪቱስስትራቦን «ጋምብሪቪ» ወይም «ጋማብሪቪ» የተባለ ጎሣ ይጠቅሳሉ። አኒዩስ ዴ ቪቴርቦም ያሳተመው ጽሑፍ እንዳለው፤ ጋምብሪቪዩስ «የአውሬ አመል» ነበረው።

አቬንቲኑስ እንደ ጻፈው፣ በጋምብሪቪዩስ ዘመን ኦሲሪስ አፒስጣልያን ተነሥቶ ወደ አገሩ ወደ ግብጽ ተመለሠ። ከጊዜ በኋላ ግን ኦሲሪስ በወንድሙ በቲፎን ተገደለ። የኦሲሪስ ልጅ ሄርኩሌስ ሊቢኩስ ያን ጊዜ የአባቱን ቂም በቅሎ ቲፎንን ገደለ። ከዚያ በኋላ ሄርኩሌስ በአውሮፓ ዞሮ የጊጋንቴስ (ኩሬቴስ) ወገን ከየአገሩ ያስወጣ ነበር። ይህ ሄርኩሌስ የጋምብሪቪዩስ ሴት ልጅ አራክሳን አግብቶ አራት አለቆች ወለደችለት፦ ቱስኩስ (በኋላ የጣልያን ንጉሥ የሆነው)፣ ትንሹ ስኩቴስ፣ አጋጡርሲስ፣ ፔውኪንገር፣ ጉጦ። በተጨማሪ በጋምብሪቪዩስ ዘመን፣ ከአሁኑ ፈረንሳይእስፓንያ አገራት መካከል በተገኙት ፒሬኔ ተራሮች ላይ ታላቅ ቃጥሎ እንደ ተከሠተ ይለናል። ጋምብሪቪዩስ በልጁ ሷይቩስ ተከተለ።

በአንድ ትውፊት ንጉሥ ጋምብሪቪዩስ የቢራ መጥመቅን አስተማረ። ይህን ዕውቀት ከኦሲሪስና ከኢሲስ ተምሮ ነበር። ስለዚህ ጋምብሪቪዩስ በዚህ አፈ ታሪክ የመጥመቅ አባት እንደ ሆነ ይቆጠራል። በዚህ ትውፊት አብዛኛው ጊዜ ስሙ «ጋምብሪኑስ» (Gambrinus) ይጻፋል። ሆኖም አሁን ስለ «ጋምብሪኑስ» መታወቂያና ትርጉም አዳዲስ ተረቶች ወይም ሃሳቦች ተነስተዋል። በተረቶቹ ብዙ ጊዜ «የፍላንደርስ ንጉሥ» ወይም «የብራባንት ንጉሥ» (የአሁን ሆላንድ አካባቢ) ይባላል።

በሌላ ምንጭ ዘንድ ጋምብሪቪዩስ ካምብሬ (በአሁኑ ፈረንሳይ) እና ሃምቡርግ (በአሁኑ ጀርመን) ከተሞች የሠራ ነው።[1]

ቀዳሚው
ማርሱስ
የቱዊስኮኔስ (ጀርመን) ንጉሥ
2019-1975 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
ሷይቩስ
  1. ^ [1]