ጾመ ፍልሰታ

ከውክፔዲያ

ጾመ ፍልሰታ

(ከዋርካ የተወሰደ፦)

<ፍልሰታ > የሚለው ቃል የሚገልጸው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለቆ መሔድን መሰደድን መፍለስን ያመለክታል። ይህም የእመቤታችንን ሥጋ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መፍለሱን በኋላም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት ይነገራል።

ጾመ ፍልሰታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፷፬ ዓመት በዚች ምድር ኖራ እንደ አንድ ልጇ መሞቷን መነሣቷንና ማረጓን ያዩ ዘንድ ሐዋርያት የጾሙት ጾም ነው። ጾሙ ከነሐሴ ፩ ቀን እስከ ነሐሴ ፲፮ ቀን ሲጾም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዐዋጅ ከደነገገቻቸው ሰባቱ አጽዋማትም አንዱ ነው።

ሃይማኖታዊ መሠረት[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

እመቤታችን ከአባቷ ከኢያቄም እና ከናቷ ከሐና ነሐሴ ፯ ቀን ተፀንሳ ግንቦት ፩ ቀን በሊባኖስ ተወልዳለች። <እምሊባኖስ ትወጽዕ መርአት ፦ ከሊባኖስ ሙሽራ ትወጣለች > እንደተባለ ። እመቤታችን በእናት አባቷ ቤት ሦስት ዓመት፤ በቤተ መቅደስ አሥራ ኹለት ዓመት፤ ከልጇ ከወዳጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ፡ ከዮሐንስ ወልደዘብዴዎስ ዘንድ አሥራ አራት ዓመት ከዘጠኝ ወር ቆይታ በ ፷፬ ዓመት ዕድሜዋ በ፵፱ ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች። የእመቤታችንን ስም የሚገልጹ የውዳሴ ጽሑፎችም በዕድሜዋ ልክ ተደርሰዋል። ለምሳሌ የውዳሴ ማርያም ቁጥር ፷፬ ነው፤ የመልክዐ ማርያም ቁጥርም ፷፬ ነው።[1]

ባረፈች ጊዜ ቅዱሳን ሐዋርያት ተሰባስበው አስከሬኗን ይዘው ወደ ጌቴሴማኒ መቃብር ለማሳረፍ ሲሄዱ አይሁድ ለተንኮል አያርፉምና ተተናኮሏቸው። ቀድሞ ልጇ ሞቶ ተነሣ፣ ዐረገ እያሉ ሲያስቸግሩን ይኖራሉ: ደግሞ አሁን እሷም ተነሣች፣ ዐረገች ሊሉ አይደል በማለት አይሁድ ተሰባስበው አስከሬኗን ለማቃጠል ሲተናኮሉ እግዚአብሔር በተአምር ከነዚያ አይሁዶች አድኗቸዋል ። የእመቤታችንንም አስከሬን ነጥቆ ከሐዋርያው ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አኑሮታል። ከዚያ በኋላ ሐዋርያት ሥጋዋን አግኝተው ይቀብሩት ዘንድ በዐረፈች በስምንተኛው ወር ከነሐሴ ፩ ጀምሮ እስከ ነሐሴ ፲፬ ቀን ድረስ ኹለት ሱባዔ ይዘው በአሥራ አራተኛው ቀን ሥጋዋን ከጌታ ተቀብለው በጸሎትና በምህላ በፍጹም ደስታ በጌቴሰማኔ አሳረፉት ። በሦስተኛውም ቀን ተነሥታ ስታርግ ከሰኡቃዊያን ወገን የሆነው ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ አያት። እርሱም በቀብር ሥርዓቱ ጊዜም አልነበረም። ሀገረ ስብከቱ ህንድ ስለነበር ሊያስተምር ወደዛው ሂዶ ነበርና። በዚያም ሲያስተምር ሰንብቶ በደመና ተጭኖ ሲመጣ ያገኛታል። ትንሣኤዋን ከርሱ ሰውራ ያደረገች መስሎት አዝኖ «ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ አሁን ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀርቼ ነውን ?» ብሎ ቢያዝንባት እመቤታችንም ከርሱ በቀር ማንም ትንሣኤዋን እንዳላየ ነግራ አጽናናችው። ለሌሎቹ ሐዋርያትም እንዲነግራቸው ለምልክትም /ለምስክርም እንዲሆነው ሰበኗን /መግነዟን ሰጥታው ዐረገች። ቶማስም ኢየሩሳሌም ደርሶ ሐዋርያትን «የእመቤታችን ነገርስ እንደምን ሆነ?» ሲል ቢጠይቅ «አግኝተን ቀበርናት እኮ» አሉት። እርሱ ምስጢሩን አዉቆ ደብቆ «ሞት በጥርነሐሴ መቃብር» እንዴት ይሆናል ? አይደረግም ይላቸዋል። ሊያሳያቸውም መቃብሩ ዘንድ ሂደው ቢከፍቱት አጧት። እርሱም «አታምኑኝም ብዬ እንጂ እርሷስ ተነሥታ ዐርጋለች» በማለት ኹኔታውን ተረከላቸውና ለምስክር ይሁንህ ብላ የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው። ከዚህ በኋላ ለበረከት ይሆናቸው ዘንድ ሰበኑን ተካፍለው ወደየአህጉረ ስብከታቸው ሄዱ። ዛሬ በቅዳሴ ጊዜ ዲያቆኑ በሚይዘው የመጾር መስቀል ላይ በሁለት ቀዳዳዎች አልፎ ተጠምጥሞ የምናየው መቀነት መሰል ጨርቅ የዚያ ሰበን ምሳሌ ነው።

በዓመቱ ሐዋርያት ከያሉበት ተሰባስበው ቶማስ ትንሣኤሽን አይቶ እኛስ እንዴት ይቀርብናል ብለው ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምርው ሱባዔ ቢይዙ ከኹለት ሱባዔ በኋላ እንደገና ትንሣኤዋንና ዕርገቷን ለማየት በቅተዋል። ሐዋርያዊት የሆነች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናም ምእመኖቿ ከእመቤታችን በረከትን እንዲያገኙ ይጾሙ ዘንድ ይህን ሐዋርያት የጾሙትን ጾም እንዲጾሙ ዐዉጃለች። ምእመናንም በተለየ መልኩ በጾም በጸሎት በሱባዔ ጽሙድ ሆነው ይህን ወቅት ያሳልፋሉ።

የእመቤታችን ትንሣኤ ድንገት እንደእንግዳ ደራሽ እንደ ውሃ ፈሳሽ የተደረገ ሳይሆን በቅዱሳት መጻሕፍት በትንቢተ ነቢያት የተገለጸ ነው። ነቢዩ ዳዊት በመዝሙር ፻፴፩ ቁጥር ፲ ላይ «አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦትም» ይላል። በዚህም ምእመናንን ወደ ምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰማያት የመቅደስህ ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነሥ አለ። ታቦት የጽላት ማደርያ እንደሆነ ሁሉ እመቤታችንም ለክርስቶስ ማደርያ በመሆኗ አማናዊት ታቦት ትባላለች።

ንጉሥ ሰሎሞንም በመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ምዕራፍ ፪ ቁጥር ፲ ላይ «ውዴ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፤ ወዳጄ ሆይ ተነሽ፡ ውበቴ ሆይ ነይ» ብሏል። እዚህ ላይ «ወዳጄ ...ውበቴ»" የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት ። ክቡር ዳዊት መዝሙር ፵፭ ቁጥር ፱ ላይ «በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች» እንደሚል ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ቤዛነቱን ከፈጸመ በኋላ ወደ ቀደመ ክብሩ እንዳረገ እመቤታችን ቅድስት ድንገል ማርያምም በቀኙ ትቀመጥ ዘንድ «ተነሽ ነይ» አላት ። እንግዲህ ይህንና የመሰለዉን ሁሉ ይዘን የእናታችንን ዕረፍቷንና ትንሣኤዋን እንዘክራለን እንመሰክራለንም።

ዋቢ ምንጮች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  1. ^ ሥርዓተ አምልኮ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ http://ethiopianorthodox.org/amharic/archivee/seasonal/filsetapict.pdf