ፒጣና

ከውክፔዲያ

ፒጣና በጥንታዊ አናቶሊያ (ሐቲ) ታሪክ የኩሻራ ንጉሥ ነበር።

የሚታወቀው ከልጁ አኒታ አዋጅ ነው። በዚያ ሰነድ ዘንድ ፒጣና የኩሻራ ንጉሥ ሲሆን በ1662 ዓክልበ.. ግድም ካነሽን ያዘ። ያሸነፈው ንጉሥ ምናልባት ዋርሻማ ነበር። በዚያም ዓመት ልጁ አኒታ ወደ ካነሽ ዙፋን ተከተለው።

«...የነሻ (ካነሽ) ንጉሥ በኩሻራ ንጉሥ ተማረከ። የኩሻራ ንጉሥ ፒጣና ከከተማው በብርታት ወጣ፤ ነሻ ከተማ በሌሊት በኃይል ያዘ። የነሻን ንጉሥ ማረከ፤ በነሻ ኗሪዎች ላይ ግን ክፋትን አላደረገም። ይልቁንም የሱ አባቶችና እናቶች አደረጋቸው። »

የአኒታ አዋጅ በሕንዳዊ-አውሮፓዊ ቋንቋኬጥኛ ስለ ተጻፈ፣ ፒጣና «የኬጥያውያን መንግሥት» (ሂታይት) የሚባለው ግዛት መሥራች እንደ ነበር ይታመናል። ይህ ቋንቋ ከከተማው ካነሽ ስሙን «ነሺሊ» አገኘ፤ ከሐቲ ቋንቋ (ሐትኛ) የተለየ ነበረ። ኬጥኛ የተጻፈው በመስጴጦምያ በተደረጀው በኩነይፎርም ጽሕፈት ስለሆነ፣ የሕንዳዊ-አውሮጳውያን ተናጋሪዎች ከዚህ በፊት ለራሳቸው ፊደላት እንደ ፈጠሩ የሚሉ ትውፊቶች አጠያያቂ ናቸው።

ቀዳሚው
ዋርሻማ
ካነሽ ንጉሥ
1662 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
አኒታ