ሁሴን ከድር መሐመድ/ hussen kedir mohammed /

ከውክፔዲያ
Jump to navigation Jump to search

ሁሴን ከድር መሐመድ/ hussen kedir mohammed /ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ   መስፈርቱን ያሟላሉ  የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን  ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ6 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ከስነ-ጽሁፍ ዘርፍ ዘርፍ ታሪኩ የሚቀርብለት ሰው ሁሴን ከድር መሐመድ ይሆናል፡፡
               ትውልድ እና ዕድገት


ሁሴን ከድር መሀመድ በጥቅምት 1967 በሲዳሞ ክፍለ- ሀገር ይርጋጨፌ ፤ ወጊዳ ማርያም የተባለ ቦታ ተወለደ። የ7 አመት እድሜውን ሲያከብርም በ1974 መሆኑ ነው ከይርጋ ጨፌ ወደ አዲስ አበባ  መጣ፡፡


በ1975 በዑመር ሠመተር ት/ቤት የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ጀመረ። በኑር መስጂድ(በኒን መስጅድ) አሊፍ ብሎ ቁርዓን ጀመረ።

ታዳጊው ሁሴን በ10ዓመቱ 30ጁዝ (30ምዕራፍ) ቁርዓን አጠናቀቀ። በአንዋር መስጅድ የፊቂህ ኪታቦችን በሻፍኢያ መዝሃብ እስከ ስምንተኛ ክፍል ዘመናዊ ትምህርትን እየተማረ ሃይማኖታዊውን ጎን ለጎን አጠናቀቀ።
ሁሴን የ14 አመታ ልጅ ሳለ በአንዋር መስጅድ በ1981-82 ከቀህ መሐመድ ጎን የቁርአን አስተማሪ በመሆን በርካታ ልጆችን ከ10-2 ሰዓት ያስተምር ነበር። በዚያው ተመሳሳይ ሰዓትም የራሱን የኪታብ ትምህርት በተለያየዩ ሸኾች አንዋር መስጅድ ተምሯል።


በ1983 በከፍተኛ ሰባት አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሆነ። በዚያው ዓመት በት/ቤቱ የድራማ ክበብ ተመዝግቦ "ሞገደኛው ነውጤ"" ቴአትር ላይ አንደኛ ምስክር ሆኖ ሠራ። በ1984 የት/ቤቱ የድራማም የጋዜጠኛም ክበብ ባልደረባ ሆነ። በዚህም ትምህርቱን ችላ በማለቱ በ1985 የ10ኛ ክፍል ትምህርት እንዲደግም በክፍል ኃላፊው ተፈረደበት። 10ኛ ክፍልን አንገቱን ደፍቶ ተማረ። 11ኛ ክፍልን በተፈሪ መኮንን (እንጦጦ አጠቃላይ) መማር ጀመረ። በት/ቤቱ የጸረ- ኤድስ ክበብ፣ የሥነጽሑፍ ክበብ ተመዘገበ። በት/ቤቱ የመድረክ ሥራዎች ላይ ጎልቶ መታየት ጀመረ።

በ1986 በክልል 14 ባሕልና ስፖርት ቢሮ በክረምት የቴአትር ኮርስ ተመዝግቦ በነተስፋዬ ሲማ፣ በኃይሉ መንገሻ በቴአትር ሰለጠነ።

በ1987 የት/ቤቱ የሥነጽሑፍ ክበብ ሊቀመንበር ሆነ። በኢትዮጵያ ሬዲዮ የቅዳሜ መዝናኛ ግጥሞችና ጭውውት ማቅረብ ጀመረ። በዚህ ሰአት ሁሴን የ20 አመት ወጣት ነበር፡፡

በ1988 በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የት/ቤቱን የሥነጽሑፍ ክበብ አሠራር በመተንተን ማብራሪያ ሰጠ። ሁሴን በስነ-ጽሁፍ እና የጋዜጠኝነት ዝንባሌው እየቀጠለ ሄዶ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጽሁፍ ወደመጻፍ አመራ፡፡

በ1989 በአዲስ ዘመን በደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር ገጽ "ኢሥራእና ሚዕራጅ" የሚል ጽሑፍና ለሁለት ሳምንታት አሳተመ። ይህም ሁሴንን በጣም ያበረታታ አጋጣሚ ነበር፡፡

ሁሴን በ1989 የሐመረኪን የሥነጽሑፍ ማኅበርን በመመሥረት በሊቀመንበርነትና ሕዝብ ግንኙነት ሠራ።

በ1990 በተለያዩ የግልና የአዲስ ልሣን ጋዜጣ ጽሑፎቹን ማቅረብ ጀመረ። ይህም የበለጠ እጁን እንዲያፍታታ ትልቅ እገዛ አድርጎለታል፡፡

       የሥራ ዓለም

በ1991 ሐምሌ ወር ውስጥ "የዕለታዊ አዲስ" ጋዜጣ ሪፖርተር ሆኖ ተቀጠረ። በርግጥ ደሞዝ የለመደው የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ ሁለት ልጆችን በማስጠናት በወር 50 ብር እየበላ ነበር። በ1989 በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር "ደመና" የሚባል ቴአትር ላይ የጎዳና ተዳዳሪና የደብተራ ገጸ-ባሕሪ ተላብሶ በመጫወት በሳምንት 25ብር ሳሙና እና ሶፍት ይከፈለው ነበር። ዕለታዊ አዲስ ግን 950ብር ደሞዝ እየበላ ለስምንት ወር ሠራ። ድርጅቱ ሲዘጋም ወደ ተለያዩ ጋዜጦች ጽሑፍ በመሸጥ፣ ሐመረ-ኪንን በማጠናከር፣ በቴአትር ሥራ በመጠመድ ቆየ። የክልል 14 ባሕልና ስፖርት ኮርስ ተመራቂዎቹ ጋር በመሆን የተለያዩ ቴአትሮችን ሠርቷል። ከእነዚህ ም ውስጥ

"የእምዩ ገመና" 1986 "በአገርህን እወቅ የቴአትር ክበብ "የዘር ጉዳይ" 1987 ውልብኝ የቴአትር ክበብ "ውድቅት" በጎሕ የቴአትር ክበብ 1989 "ወርቃማው ፍሬ" 1989 "ርዕሱን የረሳው" 1990 "ማን ያግባት" 1993 በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ዝግጅት አስተባባሪ ሆኖ "የተከፈለ ልብ" በሀገር ፍቅር ቴአትር ዝግጅት አስተባባሪ ሆኖ "አዳብና" 1994 በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ይገኙበታል፡፡

እንግዲህ ሁሴን ከድር የቴአትር የሥነ-ጽሑፍና የጋዜጠኝነት ሥራውን እኩል እያስኬደ ሳለ "ሩሕ ጋዜጣና መጽሔት በቋሚነት በሪፖርተርነት ቀጠረው። 

1994 በ400ብር ሩሕ ተቀጠረ። ቤተሰቦቹ የኑሮ አቅማቸው ደካማ የነበረ በመሆኑ እነርሱን ለመርዳት ነበር ሥራን አጥብቆ የያዘው። በሩሕ ለ5ወራት ሠርቶ በ1995 "አክፓክ የጦቢያ ጋዜጣና መጽሔት አዘጋጅ ድርጅት በ600 ብር ተቀጠረ። በ1996 አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ዲፓርትመንት በዲፕሎም ለመማር ገባ፡፡ በ1998 ጦቢያ ሲዘጋ ወደ Abbi weekly በ1000 ብር ደሞዝ ተቀጠረ። 1998 ነሐሴ 22 ትዳር መሠረተ። በ2001 በነጃሺ ማተሚያ ቤት የ"አሃድ" መጽሔት ም/አዘጋጅ ለመሆን ተቀጠረ። ሆኖም መጽሔት ሳይጀመር ቆመ። ማተሚያ ቤቱ ወደ አርታኢነት በ2500 ብር አዞረው።

ሁሴን አሁን በብዙ ህይወት አልፎ ህይወት ብዙ ነገር እያስተማረችው መጣች፡፡ ራሱን በብዙ ነገር ለመለወጥም ቁርጥ ውሳኔ አደረገ፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ በትምህርትም በሥራም አደገ። 

የቴአትር ትምህርቱን በዲፕሎም ጀምሮ በዲግሪ አጠናቀቀ። ከዚህ በኋላ የሚወደውን የሚድያ እንዲሁም የቴአትር ፤ የስነ-ጽሁፍ ስራን አጥብቆ ያዘው፡፡ ይህን የውስጥ ስሜቱን ለማርካትም ወደ ነጃሺ ማተሚያ ቤት አቀና፡፡ የነጃሺ ማተሚያ ቤት ኦዲዮ ቪዥዋል ሥራ አስኪያጅ ሆኖ በ2003 መሥራት ጀመረ። ተመልሶ ውጤታማ ወደሆነበት አርትኦት በማምራት በ2004 በማተሚያ ቤቱ በአርትኦት ሥራ ቀጠለ። ከ250 በላይ የድርጅቱን መጽሐፍት ፣ ከ70 በላይ የአልተውባ አሳታሚ ድርጅት ከ50 በላይ የተለያዩ ግለሰቦችን መጽሐፍት አርትኦት ሠርቷል። ይህም በብዙ ጉዳዮች ላይ በተለይ በእስላማዊ ስነ-ጽሁፍ ላይ የበለጠ ግንዛቤ እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ ከ2005 በኋላ በግሉ መሥራት ጀመረ። ከ2000 ጀምሮ ለ13 ዓመታት የሸገር ሬዲዮ የሙስሊም በዓላት ልዩ ዝግጅት ሠርቷል። ከ2003 ጀምሮ በአፍሪካ ቲቪ በፍሪላንስ ኪነጥበባዊና የፍልስፍና ዝግጅቶችን እስከ 2009 ሠርቷል። በዘፕሬስ በማትሚኖ በአቴና በአዲስ ዜና በዕንቁ በጠይም መጽሔት (ለተወሰነ ጊዜ ተቀጣሪ) በቁምነገር በግዮን በሌሎችም በርካታ የግል ጋዜጦችና መጽሔቶች ከ500 በላይ ጽሁፎችን አሳትሟል።

     የምርምር ሥራዎች

ድኅረ ኢህአዴግ የኢስላማዊ ሥነ ጽሑፍ ሂደት ገጸ- ሙስሊም በኢትዮጵያ ቴአትር ገጸ ሙስሊም በአማረኛ ልቦለዶች ከ1966 እስከ2010 የኢስላማዊ ሥነጽሑፍ ቅኝት ከ1950 እስከ, 2010 (ያልተቋጨ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ታሪክ በጦቢያ መጽሔት በሶስት እትም የታተመ የራስ ቴአትር ታሪክ 1992 የወሎ ዑለሞች ታሪክ ከ1800- 1967 ያልታተመ የኢትዮጵያ ዑለሞች ታሪክ (ያልታተመ)

የግለሰቦች የሕይወት ታሪክ የዑስታዝ መሐመድ ጀማል በሕይወቱና ሥራዎቹ ዙሪያ 500 ገጽ ያልታተመ

        በፊልም ሥራ

ከ10 ያላነሱ ፊልሞች ላይ በተዋናይነት በአዘጋጅነት እና በደራሲነት ተሳትፏል። "በእጅ የያዙት" በትዳር ቀውስ ላይ ያተኮረ ፊልም ጽፎ ተውኖ በሲዲ አሳትሟል ምራት ጀዛእ ሊነጋሲል ፍላጎት በመሪ ተዋናይነት የሠራበት የቪዲዮ ድራማዎች ናቸው። "እፎይ" በዳንኤል ወርቁ ተጽፎ የተዘጋጀ 1997 የሠራው የመጀመሪያው ፊልሙ ነው።

በመጽሐፍት ሕትመት ረገድ የወላጅ ሐቅ አደገኛ የቀልብ በሽታ ፍጻሜ አልባ ሕይወት የሁለት ግመሎች ወግ (የልጆች) ኢትዮጵያውያን ሶሐቦች (ከመሐመድ አሊ ጋ) ትዳርና ሕይወት (ከመሐመድ አሊ ጋ) በይበልጥ በሥነምግባርና ማኅበረሰብ የሚያንጹ መጽሐፍትን በብዛት አዘጋጅቶም የአርትኦት ሥራ ሠርቷል።

           ወቅታዊና ቤተሰባዊ ሁኔታ 
 

ሁሴን በአሁኑ ጊዜ ከጓደኞቹ ጋር በአክሲዮን ማኅበር በከፈቱት ሚንበር ቲቪ በባለቤትነትና የፕሮግራም ክፍል ኃላፊ በመሆን እየሠራ ይገኛል። ባለፉት ሁለት ዓመታት "ምርኩዝ" የተሰኘ እጅግ ተወዳጅ ፕሮግራምም አዘጋጅ ነው። ሁለተኛ ዲግሪውን በሥነጽሑፍ በ2007 ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተቀብሏል። ሁሴን ከድር ከባለቤቱ ከወይዘሮ ሙና ሙሀመድ 5 ልጆችን ያፈራ ሲሆን ስማቸውም አይመን ሁሴን ዳኒያ ሁሴን ሪሃን ሁሴን ሳራ ሁሴን መሐመድኑር ሁሴን (ሚያዝያ 27 2013 ከምሽቱ አንድ ሰዓት ነው የተወለደው መሐመድ) ባለቤቱ ሙና ሙሐመድ አካውንታንት እና የአንድ ሆስፒታል ፋይናንስ ሃላፊ ነች።

ሁሴን "የአማርኛ ጥበበ ቃላት ታሪክ" ጋሽ አስፋው ዳምጤ ከ1972 ጀምረው በተለያዩ መጽሔቶች ያወጧቸውን "የጥበበ ቃላት" ሥራዎቻቸውን ወደ መጽሐፍ ቀይሮ ለሕትመት አዘጋጅቷል። በቅርቡ የኅትመት ብርሃን ያገኛል።
ሁሴን ቅንነት፣ ለሰዎች መልካም መዋል በእጥፍ ይከፍልሃል ብሎ ያምናል። ሰዎችን በክፉ መጠርጠር የውስጥ በሽታን ያመጣል ስለሚልም ሰውን ከመጠርጠር ማመን ይቀለዋል።

‹‹…… በመስጠትህ ታተርፋለህ እንጂ አይጎድልብህም። ስጥ ምስጥ ወደማይበላው የፈጣሪ ካዝና ነው የምታስቀምጠው።›› ይላል ሁሴን መስጠት ላይ ያለውን እሳቤ ሲገልጽ፡፡

ሁሴን በዚህ አመለካከቱ አተረፈ እንጂ አልከሰረም።

‹‹ሌላ አገር የለኝም በኢትዮጵያ ጉዳይ ቀናዒ ነኝ። መንግሥት ይመጣል መንግስት ይሄዳል አገር ቋሚ ናት። የአገራችን ጉዳይ ከምንጣላበት የብሔርና የሃይማኖት ጉዳይ ይበልጣል። ባይ ነኝ።›› ሲል ሁሴን ሀሳቡን ይገልጻል