ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ

ከውክፔዲያ

ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ አፄ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የጻፉት የሕይወታቸው ታሪክ ነው። በሁለት መጻሕፍት ታትሟል።

መጀመርያው መጽሐፍ ስለ ሕይወታቸው ከልደታቸው ከ1885 ዓም ጀምሮ እስከ 1929 ዓም እስከ ፋሺስት ወረራ ድረስ ይተርካል። በባስ፣ እንግላንድ በስደት ሳሉ ጽፈውት ከዚያው በፊት ስለ ነበረው የኢትዮጵያ አስተዳደርና ሥልጣኔ ደረጃ ከፍ ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።

በአንዱ ወሳኝ ምዕራፍ ፴ «የሕገ መንግሥትን ትርጓሜ ስለ ማስረዳት።» የበጅሮንድ ተክለ ሐዋርያትን ቃላት በሙሉ ጠቀሱዋቸው።

ሁለተኛው መጽሐፍ ከ1929 እስከ 1934 ዓም ያለውን ወቅት ይዘርዝራል፤ ይህም ኢትዮጵያ ከጣልያን ነጻ ሆና ወደ ዙፋናቸው የተመለሱበት ዘመን ነው።

የታተመው በ1965 ዓም ነበር።

ከመቅደም፣ የጻፉባቸው ምክንያቶች በሙሉ ይዘርዝራሉ፣ ለምሳሌ፦

«ማናቸውም ሥራ ቢሆን በጊዜና በዕድሜ ይፈጸማል እንጂ ፡ በምኞትና በችኰላ ሊፈጸም የማይቻል መሆኑን ሰው ሁሉ እንዲያውቀውና እንዲረዳው ነው። »

ከምዕራፍ ፳፱ «ሕገ መንግሥት ስለ ማቆማችን» ያለው ፍሬ ነገር፦

«ሕግ ለሰው ሁሉ የበለጠ የሚጠቅም መሆኑን ማንም አይስተውም። መከበርም መጠቀምም የሚገኙት ከሕግ መተካከል የተነሣ ነው። መዋረድም መጐዳትም የሚመጡት ከሕግ መጓደል የተነሣ ነው። ግፍና በደልም የሚበዙት ሕግ ባለመቆሙ ነው።
እግዚአብሔር ከፍጥረት ሁሉ በላይ ሆኖ፤ በቃሉ ብቻ ማዘዝ የማይቸግረው ሲሆን ፡ ሕግን መሥራቱ ሕግ ለዓለም ሁሉ የበላይ ገዥ እንዲሆን ስለ ዐወቀ ነው።
ከሰውም ትክክለኛ ለመባል የሚገባው በማናቸውም ረገድ ቢሆን፤ ዋናውን አሳብ አዝልቆ ሲሆን ሰውን ሁሉ በሙሉ፤ ሳይሆንም የሚበዛውን ለመጥቀም በተሰጠው ዕውቀት የሚጣጣርና የሚችል ሲሆን ነው።»