መላኩ ብርሃኑ ተስፋዬ-MELAKU BERHANU TESFAYE

ከውክፔዲያ
Jump to navigation Jump to search

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸውን ሰዎች ጠቁሙን ፤ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪካቸዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ጥቆማዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ በሚድያ ዘርፍ አሁን ታሪኩን የምንሰንድለት ሰው መላኩ ብርሀኑ ነው፡፡ መላኩ ማነው?


ትውልድ እና ልጅነት

ጋዜጠኛ መላኩ ብርሀኑ አዲስ አበባ ከተማ በቀድሞው አጠራር ወረዳ 18 ቀበሌ 18 በተለምዶ ‹‹ኦሎምፒያ›› ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በትንሳዔ ብርሃን አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በቦሌ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። መላኩ ከተማሪነት ዘመኑ ጀምሮ ላደላበት የስነ-ጽሁፍ ፍቅር የተሸነፈው በጊዜ ነው። የጋዜጠኝነት ሙያን ከልጅነቱ ሲመኘው መኖሩ ኋላ ላይ አድጎ በዘርፉ መሰማራት ሲችል የፍላጎቱን ያህል እንዲሰራበትና በዘርፉ አንቱታን ለማግኘት ከቻሉ የርሱ ዘመን የሙያ ባልደረቦቹ ተርታ ለመሰለፍ አስችሎታል።መላኩ እንደሚናገረው ጋዜጠኛ የመሆን ህልሙን ለማሳካት ከምኞት ባሻገር እጁን ያሟሸባቸውና መንደርደሪያዎቹ የነበሩት የተማረባቸው ትምህርት ቤቶች ሚኒ ሚዲያዎች ነበሩ። ለዚህ ደግሞ ገና 9ኛ ክፍል ሳለ የመጀመሪያ ልብ-ወለድ ስራውን አይተው ወደሚኒ ሚዲያ እንዲመጣ ብርታት የሰጡትን የ9ኛ ክፍል የአማርኛ መምህሩን አቶ አለማየሁ የስጋትን በእጅጉ ያመሰግናል።


የንባብ ፍቅር-የመጻፍ ክህሎት

መላኩ፤ ግጥሞችና አጫጭር ድርሰቶችን ከመሞነጫጨር ፣ በትምህርት ቤቱ ሚኒሚዲያዎች ከመሳተፍ እና ኋላም ተምሮ ጋዜጠኝነትን ከመስራቱ አስቀድሞ ረጅም የሚባሉ አመታትን በንባብ አሳልፏል። እንደአብዛኛው የ1960ዎቹ ትውልድ አባል የመላኩ አባት የማርክሲስት ሌኒኒስት ርዕዮተ ዓለም አራማጅና እና በዘመኑ የኮሙኒዝም አቀንቃኝ ነበሩና ብዙ ጊዜያቸውን በንባብ ያሳልፉ ነበር። መላኩ እንደሚናገረውም አባቱ ሲያነቡ እያየ እንደመኖሩ የሚያነቧቸውን መጽሃፍት በማገላበጥ ከእድሜው የቀደሙ መጽሃፍትን በልጅነቱ ለማንበብ እድል አግኝቷል።አባቱ ከማሌ ርዕዮተ አለም ተንታኝ መጽሃፍት ውጪ የዘመኑ ልብወለድ መጽሃፍትንም ያዘወትሩ ስለነበር መላኩም ‹‹ጣምራ ጦር›› የሚለውን የገበየሁ አየለ መጽሃፍ ገና የ3ኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ አንብቦ መጨረሱን ያስታውሳል። ‹‹ስደተኛው››፣ ‹‹ደራሲው››፣ ‹‹የቀይ ኮከብ ጥሪ››፣ ‹‹ብቀላ›› ፣ ‹‹ፊልድ ማርሻል ሞንትጎመሪ››፣ ‹‹ሌኒን፣ ስለሰላም እና ጦርነት››፣ ‹‹እናት መሬት››፣ ‹‹የ6ቱ ቀን ጦርነት››፣ ‹‹የኛ ሰው በደማስቆ››፣ እና ሌሎችም በርካታ ዳጎስ ያሉ መጽሃፍትን ገና በልጅነቱ አንብቧቸዋል።የፖለቲካው ርዕዮት ባይገባውም፣ ከእድሜው የላቁ የህይወት ፍልስፍና የታጨቀባቸው ልብወለድ ድርሰቶቹ ሙሉ ስዕል ባይሰጡትም ሲያነባቸው ቢያንስ አንድ ቁምነገር ከማግኘት አልፎ የንባብ ክህሎቱንም እንዳሳደገባቸው ነው የሚገልጸው። መላኩ የማንበብ ፍቅሩ እጁን ማፍታታት እስከጀመረበት እስከ 10 ኛ ክፍል ድረስ ያለማቋረጥ ዘልቋል። "ለማትሪክ ዝግጅት ስል እረፍት አድርጌባቸዋለሁ" ካላቸው ሁለት አመታት ውጪ የወጣትነት ዘመኑን በአብዛኛው በንባብ እንዳሳለፈ ሲናገር ደስ እያለው ነው። "ፌስቡክ ባልነበረበት፣ ቴሌቪዠን ብርቅ በሆነበት በዚያ ዘመን ብቸኛ ጊዜ ማሳለፊያ ንባብ መሆኑ የዘመኑ ወጣቶች ብስል እና አስተዋይ እንዲሆኑ ረድቷቸዋል ብዬ አምናለሁ" ይላል መላኩ። “በዘመኑ የታተሙ ፣ እኔ ያላነበብኳቸው የልብ ወለድ መጽሃፍት የሉም” ይላል መላኩ እኮራበታለሁ ስለሚለው የንባብ ፍቅሩ በሙሉ ልብ ሲናገር። መላኩ እነዚያ የዚያ ዘመን መጽሃፍት የዛሬ ማንነቱንና አስተሳሰቡን የቀረጹለት በመሆናቸውም አሁን ድረስ በልጅነቱ ማንበብ መጀመሩን እንደአንድ የህይወቱ ፍሬያማ ጊዜ ይቆጥረዋል። እንደንባብ ክህሎቱ ሁሉ ስነጽሁፍን የጀመረውም በልጅነቱ የሰላምታ ደብዳቤና ለቀበሌ የሚገቡ ማመልከቻዎች በመጻፍ መሆኑን ነው በፈገግታ የሚያስታውሰው። አባቱ ለስራ ጉዳይ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍላተ ሃገራት ይዞሩ ስለነበር ለእርሳቸው የሰላምታ እንዴት እንደሚጻፍ ያስተምሩት እንደነበር ይገልጻል። በዚያ መፍታታት የጀመረ እጁ ቃላት መቀመር ሲችል የስነጽሁፍ ችሎታውን ያዩ ጎረቤቶቹና የአካባቢው ሰዎችም ጉዳይ ሲኖራቸው ለቀበሌ ማመልከቻ የሚያጽፉት እርሱን እንደነበር እየሳቀ ስታውሳል።

መላኩ ለእናቱ ያለውን ፍቅር ሲገልጽ "ቃላት ይህንን እውነት ለመመስከር አቅም የላቸውም" ይላል። በርሱ የዛሬ ህይወት ውስጥ ዋናውን ድርሻ የሚወስዱ መሆናቸውን የሚናገርላቸው እናቱ “ለእኩዮችህ አርአያ ሆነህ ማደግ አለብህ” እያሉ ለቁምነገር ብቻ አልሞ እንዲኖር አድርገው እንዳሳደጉት ነው የሚገልጸው። "እናቴ ዘመናዊ ትምህርት ባትማርም የህይወቴ አብዛኛው ፍልስፍና የተቀዳው ከርሷ አባባሎች እና ህይወትን ከምትመለከትበት የተረጋጋ አተያይ ነው" ይላል። መላኩ ያንን ቃል ለማክበርና ቤተሰቦቹ በሚፈልጉት ቦታ ለመገኘት ህይወቱን በስርዓት አስገዝቶ በልጅነት እና ወጣትነት ጨዋታዎች ሳይታለል ያሰበበት ለመድረስ ጉዞ የጀመረውም በልጅነቱ መሆኑን ይናገራል።

መላኩ ለልጅነቱ ፣ ለትውልድ ሰፈሩ እና እና ላደገበት ማህበረሰብ ያለውን ልዩ ፍቅርና ህይወቱን ሙሉ የማይዘነጋውን ናፍቆትና ትውስታ ተናግሮ አይጠግብም። ዘነበ ወላ “ልጅነት” የሚለውን መጽሃፍ ቀድሞኝ ባይጽፍ ኖሮ የልጅነት ታሪኩን የሚጽፍ አንደኛ ደራሴ እኔ መሆኔ አይቀርም ነበር” በማለት ነው የሚናገረው። የአለማየሁ ገላጋይን “የብርሃን ፈለጎች እና የዘነበ ወላን ልጅነት የራሴ የልጅነት ዘመን ማስታወሻ አድርጌ ስለምቆጥራቸው ከሁሉም መጽሃፍት የበለጠ ዋጋ እሰጣቸዋለሁ” ነው የሚለው መላኩ። መላኩ መደበኛ ትምህርቱን ከማጠናቀቁ አስቀድሞ በተለያዩ የስነጽሁፍ ውድድሮች እየተሳተፈ ችሎታውን ያዳብር ነበር።በዚህም ሽልማቶች አግኝቷል። የስነጽሁፍ እና ግጥም አስተዋጽዖ በሚፈለግበት ቦታ ሁሉ ስራዎቹን እያቀረበ ነው ልጅነትና ወጣትነቱን ያሳለፈው።


የጋዜጠኝነት አለም

መላኩ 12ኛ ክፍልን አጠናቅቆ ከመደበኛ ትምህርት ቤት ከወጣ በኋላ የመጀመሪያውን የጋዜጠኝነት ስልጠና ከፎቶግራፍ ሙያ ጋር አጣምሮ የወሰደው በቀድሞው የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅ በዛሬው የፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው። በስልጠና ላይ እያለ “ኮርስ ሜቶቼ” የሚላቸው የኮሌጅ ባልደረቦቹ መላኩን የሚያውቁትና ሁሌም የሚያስታውሱት በስነጽሁፍ ስራዎቹ ነው። መላኩ ወደመደበኛ የጋዜጠኝነት ስራ የገባው ከፖሊስ ኮሌጅ ምረቃ በኋላ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ የጋዜጠኝነት ሙያ አገልግሎቱን በወንጀል ዘገባ ዘርፍ አሃዱ ብሎ ጀመረ። በጊዜው ለፖሊስና ርምጃው ጋዜጣ እንዲሁም ለፖሊስና ህብረተሰብ የራዲዮና ቴሌቪዠን ፕሮግራሞች የአዲስ አበባ ሪፖርተር ሆኖ መስራት ጀመረ። በፖሊስ ሚዲያ ውስጥ ትክክለኛውን የጋዜጠኝነት ዘርፍ እንዳውቀውና እንድተገብረው መሰረት የሆነኝ ሰው የመጀመሪያ አለቃዬ ቀድሞ የፖሊስና እርምጃው ጋዜጣ አዘጋጅና ኋላም የአዲስ አበባ ፖሊስ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የነበረው የስነጽሁፍ ሰው መቶ አለቃ ሃይሉ አበበ ነው ይላል። መላኩ በጊዜው ከፖሊስና ህብረተሰብ ራዲዮ፣ ቴሌቪዠንና ጋዜጣ ሪፖርተርነቱ በተጨማሪ ዘወትር ማክሰኞና ሃሙስ ምሽት በአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን (የቀድሞው ኢቲቪ 2) ላይ የሚተላለፈውን “አዲስ ፖሊስ” የሚባል የቴሌቪዠን ፕሮግራም ከቡድን አባሎቹ ጋር በማስጀመር በዋና አዘጋጅነት ሰርቷል።አዲስ ፖሊስ የተባለ መጽሄትም መስራችና አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል።


  መማር-መማር አሁንም መማር


የቀድሞው ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የአሁኑ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በሃገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት በመክፈት በዲፕሎማ መርሃግብር ጋዜጠኞችን ማሰልጠን ሲጀምር መላኩ ‘የነፍሴ ጥሪ ነው’ የሚለውን የጋዜጠኝነት ሙያ ሳይንሱ በሚፈቅደው ትምህርት ለማገዝ ወደዚያው አቀና። የሶስት ዓመት የጋዜጠኝነት ስልጠናውንም በ1997 ዓ.ም በማዕረግ ተመራቂነት አጠናቀቀ።

መላኩ የዩኒቲን የትምህርት ዘመን “የህይወት ዘመኔ የሙያ መሰረት” ብሎ ይጠራዋል። ከዛሬዎቹ የቪኦኤ ዘጋቢ ጽዮን ግርማ ጀምሮ የዛሬው ሪፖርተር ጋዜጣ ዋና አዘጋጁ ታምሩ ጽጌ፣ የቀድሞው ጦቢያና ልሳነ ህዝብ መጽሄት አዘጋጅ ታዬ በላቸው ፣ በፍቃዱ በሻህ እና እንዲሁም ሌሎች በርካታ የዘመኑ ታዋቂ የግል ፕሬስ ጋዜጠኞች ለመላኩ የዩኒቲ ኮሌጅ ባቾቹ/ በአንድ ዘመን አብረውት የተማሩ ጓዶቹ / ናቸው። መላኩ ዩኒቲን ከተሰናበተ በኋላ በዚያው ዓመት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤትን ከፍቶ ጋዜጠኝነትን በዲግሪ ፕሮግራም መስጠት በመጀመሩ ወደዚያው በማቅናት በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን በብሮድካስት ጆርናሊዝም ስፔሻላይዝድ ዘርፍ በቴሌቪዠን ጋዜጠኝነት የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። ሮዝ መስቲካ፣ መሰለ ገብረህይወት ፣ ታምሩ ጽጌ፣ የትነበርክ ታደለ፣ ጸዳለ ለማ፣ አንዱአለም ሲሳይ እና ሌሎችም የእርሱ ባቾች ዛሬ ድረስ ጋዜጠኝነትን አክብረው ያስከበሩ የዚያ ዘመን ተመራቂ ጓዶቹ መሆናቸውን ይመሰክራል። ከዚህ ዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ከወጣ በኋላ መላኩ ሙያውን በዕውቀት ለማበልጸግ የነበረው ፍላጎት ከአንድ አመት በላይ ከትምርት ርቆ እንዳይቆይና ትምህርቱን እዚህ ላይ እንዳያቆም አድርጎታል። ቀጣዩ የትምህርት ጉዞው ሲኪም ማኒፓል ዪኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክኖሎጂካል ሳይንስስ ወደተባለ ዩኒቨርሲቲ ነበር። በተልዕኮና በአካል በወሰዳቸው የሁለት አመት ኮርሶችም በጆርናሊዝም እና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ በኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ልዩ ሙያ (specialization) የማስተርስ ኦፍ አርትስ ኢንተርናሽናል ዲግሪውን ተቀብሏል። መላኩ ከኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ መደበኛ ትምህርቶቹ ባሻገር ከ21 በላይ አጫጭርና ረጃጅም የጋዜጠኝነት ስልጠናዎችን በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት ተከታትሎ ሰርተፍኬቶችን አገኝቷል። በርከት ያለ የስራ ዘመኑን በጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን ስራዎች ላይ ያሳለፈው መላኩ ከእድሜው እኩሌታ የላቀ ዘመኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ላይ አገልግሏል። ለ9 ዓመታት በፖሊስ መገናኛ ብዙሃን ውስጥ ከሪፖርተርነት እስከዋና አዘጋጅነት በደረሱ መደቦች ላይ በፖሊስ ራዲዮ፣ጋዜጣና ቴሌቪዠን እንዲሁም በአዲስ ፖሊስ ቴሌቪዠን ፕሮግራም እና መጽሄት ላይ ነው የሰራው። በተጨማሪም በአዲስ ልሳን ጋዜጣ እና ቀድሞ ኢቲቪ 2 ይባል በነበረው የአ/አ መገናኛ ብዙሃን ቴሌቪዠን ፕሮግራም ላይ በአምድ ጽሁፍ አዘጋጅነትና እና በወንጀል ዘገባዎች አቅራቢነት ሰርቷል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ከተቀላቀለ በኋላም ለ7 ዓመታት ያህል በዜና አገልግሎቱ ከከፍተኛ ሪፖርነትነት እስከዜና ኤዲተርነት ከዚያም የፕሮግራም ፕሮዳክሽን ክፍል ሃላፊነት ድረስ በደረሱ የጋዜጠኝነት ሙያ መደቦች ላይ እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ አገልግሏል። “በዜና አገልግሎት ቆይታዬ ብዙም ያልተለመደ ዘርፍ የነበረውን የዲፕሎማቲክ ኮሙኒቲውን ወደሚዲያ ለማምጣት በቀረጽኩት ዘርፍ በቢት ሪፖርተርነት ሰርቻለሁ። የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ቢት ሪፖርተር በመሆን ሰርቻለሁ። በኤዲተርነት እና በፕሮግራም ፕሮዳክሽን ዘርፍ የሰራሁት ስራም መልካም ነበር። ዜና አገልግሎቱ ለዚህ አስተዋጽዖዬ የመልካም የስራ አፈጻጸም ሽልማት ሰጥቶኛል። የጋዜጠኝነት ህይወቴን ሳስብ ከአንጋፋና አዳዲስ ጋዜጠኞች ጋር የሰራሁበትና የሙያዬን አበርክቶ ያካፈልኩበት በመሆኑ ለዜና አገልግሎት ቆይታዬ ልዩ ከበሬታ እና ፍቅር አለኝ.” ይላል- መላኩ።


ያወቁትን እያሳወቁ ትውልድን መገንባት

መላኩ በስራ ዘመኑ በተግባርም በአካዳሚክስም ያከማቸውን ዕውቀት ለሌሎች ለማካፈል ተግቷል። ከዘርፉ ጋር በተያያዙ ብዙ የስልጠና ማዕከላት ላይ አሰልጣኝ እና መምህርም ነበር። በዚህም ለብዙዎች እውቀቱን አካፍሏል። ለአዲስ አበባ ፖሊስ ማሰልጠኛ ማዕከል አራት ዓመት ተከታታይ ዙር ሰልጣኞች የህዝብ ግንኙነት ትምህርት መምህር ሆኖ አገልግሏል። እንደኢስት አፍሪካ ጆርናሊዝም አሊያንስ፣ ግሎባል ሄልዝ፣ ሲአርዲኤ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤትና የመሳሰሉ ዓለምአቀፍና አህጉራዊ ተቋማት እንዲሁም የሃገር ውስጥ ድርጅቶች ለጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ባዘጋጁት የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን፣ የጤና ጋዜጠኝነት ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የጋዜጠኝነት አስተዋጽዖዎች ፣ እንዲሁም የምርመራ እና የወንጀል ዘገባ ት ስልጠናዎች ላይ በዋና አሰልጣኝነት አገልግሏል።የምስራች የጋዜጠኝነት ስልጠና ማዕከል ለሚሰጣቸው ስልጠናዎችም የኮሙኒኬሽን፣ የወንጀልና የትራፊክ አደጋ ዘገባዎች አሰልጣኝ ሆኖ አበርክቶውን አካፍሏል።

መላኩ በተለያዩ ጊዜያት ከሚሰራቸው መደበኛ የሚዲያ ስራዎቹ በተጨማሪ ጦማር ፣ ሮዝ ፣ ዘ ፕሬስ እና ዕለታዊ አዲስ ለተሰኙ የያኔው ዘመን ታዋቂ ጋዜጦችና መጽሄቶች ፍሪላንስ ዘጋቢ ሆኖም ሰርቷል። በተለይም በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በሚጽፋቸው ፅሁፎች እንዲሁም በወንጀል እና በምርመራ ዘገባዎቹ በርካታ አንባቢዎችን አፍርቷል። በዕለታዊ አዲስ ጋዜጣ "የሸዋጌጥ ተካልኝ"፣ በዘ ፕሬስ እና ግዮን ጋዜጣና መጽሄቶች ላይ " መላከ ብርሃን" በሮዝ እና አዲስ ጉዳይ መጽሄቶች ላይ ደግሞ “ኮከብ አሳየ” መላኩ ስራዎቹን የሚያቀርብባቸው የብዕር ስሞች ሆነው ዘልቀዋል።በተለይ "ኮከብ አሳየ" ብዙዎች የሚያውቁት፣ መላኩም መጽሃፍ ሲጽፍ የተጠቀመበት ፣በአንባቢዎች ዘንድ የሚታወቅ የወንጀል ጉዳዮች ጸሁፉ የሚቀርብበት የመላኩ ብርሃኑ የብዕር ስም ነበር።


 በ አዲስ ጉዳይ-የመላኩ አሻራ

አዲስ ጉዳይ መጽሄት ሲጠነሰስ ከምሮ እስኪዘጋ ድረስ መላኩ በብርቱ ሃይሉና ጉልበቱ ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ የሰራበት መጽሄት ነው። መላኩ ዋናውንና በህይወቴ ትልቅ ቦታ የምሰጠው የጋዜጠኝነት አበርክቶዬ በዚህ መጽሄት ላይ አለ ነው የሚለው። አዲስ ጉዳይ መጽሄት ሲጀመር ጀምሮ በማኔጂንግ ኤዲተርነት የመራው መላኩ በመንግስት ትዕዛዝ እስኪዘጋ እና ባልደረቦቹ ስደት እስኪበተኑ ድረስ ለህዝብ እና ለሃገር ትልቅ ፋይዳ ያላቸው የመማህበራዊ ችእና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የተዳሰሱበት ፣ የተተነተኑበት እና መፍትሄም የመነጩበት መጽሄት እንደነበር ይናገራል። "የመጽሄት ህትመትን እና ፕሮፌሽናል የህትመት ውጤትን ጉዳይ ካነሳን በታሪክ ትልቅ ቦታ ሊይዝ ይገባዋል የምለው "አዲስ ጉዳይ መጽሄት" ነው ይላል መላኩ።አዲስ ጉዳይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ2004 ጀምሮ በኢትዮጵያ በየሳምንቱ በሙሉ ቀለም ታትሞ ለህዝብ በመድረስ ፈር ቀዳጅ የሆነ ፣ በብዙሃን አንባቢያን ዘንድ እጅግ የሚከበርና ተፈልጎ የሚነበብ፣ በበሳል ጽሁፎቹ እና በሚዛናዊ ዘገባዎቹ የሚወደድ ፣ የኢህአዴግ መንግስት በተቃራኒው ይፈራው የነበረና በመጨረሻ በመጨረሻም በአሉታዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ፈርጆ ሆን ብሎ በፍትህ ሚኒስቴር ክስ እና መግለጫ ካፈረሳቸው መጽሄቶች ግንባር ቀደሙ መጽሄት ነበር።ይህ መጽሄት በዚህ ሁኔታ ቢያከትምም አንባቢዎች ዛሬም ድረስ ኮፒዎቹን በቤታቸው አከማችተው ዘወትር የሚጠቅሱት ተወዳጅ የዘመኑ በሳል መጽሄት ነበር።

  የግሉ ፕሬስ ዋና ሰው እንዳልካቸው ተስፋዬ

መላኩ “የማይታየው የወቅቱ የግል ፕሬስ ዋና ሰው” ይለዋል እንዳልካቸው ተስፋዬን፡፡ እንዳልካቸው በኢትዮጵያ የህትመት ስራ ውስጥ የመጽሄት እና ጋዜጣ ህትመት ስትራተጂስት፣ የሃገሪቱ ዋነኛ የጋዜጣ እና መጽሄት አከፋፋይ ተቋም መስራች፣ በግል ፕሬሱ የትግል ጉዞ ውስጥ ወሳኝና ጉልህ ድርሻ ያበረከተ ሰው ነው፡፡ እንዳልካቸው ሮዝ መጽሄትን ወደሃገራዊ ጉዳዮች እና ማህበራዊ ችግሮቻችን መፍቻ ቁልፍ ሚዲያነት ከፍ ለማድረግ ረጅም እቅድ ይዞ በመጨረሻ አዲስ ጉዳይ መጽሄትን ወለደ። ይህንኑ መጽሄት በሮዝ አሳታሚ ድርጅት አማካኝነት ማሳተም ሲጀምር ከመላኩ ጋር ብዙ መሰረቶችን ጥለው ፣ ከሮዝ አንጋፋ ባልደረቦች ዮሃንስ ካሳሁን፣አስማማው ሃ/ጊዮርጎስ፣ እንዳለ ተሺ፣ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ፣ ከኤዲተሮቹ ዘሪሁን አሰፋ እና መስፍን አድነው ጋር በመሆን እውን ብዙዎች ያልደረፈሩትን በመድፈር መጽሄቱን እውን አድርጎታል። አዲስ ጉዳይ ከሮዝ መጽሄት በኋላ ተሻሽሎና በጥናት ተቀርጾ ለለውጥ እና ለማህብረሰብ እውቀት የተፈጠረ ፣ እንደዘመን አቻው ‹‹አዲስ ነገር›› ጋዜጣ በብዙ ባለሙያዎች የተደራጀ ባለራዕይ መጽሄት ሆኖ እንዲቀጥል መላኩ ሙያዊ አስተዋጽኦውን በፍቅር አበርክቷል።

እነበእውቀቱ ስዩም፣ ዳንኤል ክብረት፣ ረ/ፕ አበባው አያሌው፣ ሰለሞን ተሰማ ጂ. ፣ ቀሲስ ኤፍሬም፣ ዶክተር ብርሃኔ ረዳኢ፣ ሰርጸ ፍሬ ስብሃት፣ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ፣ሃብታሙ ስዩም ወዘተ የሚጽፉበት የወቅቱ የምሁራንና የአዋቂዎች ድምጽ የሚሰማበት መጽሄት አዲስ ጉዳይ ነበር ያስታውሳል። መላኩ እንዳልካቸው ተስፋዬን “የምንጊዜም የኔ ምርጥ ሰው ነው” የሚለው ይህንን ሁሉ ምሁርና አዋቂ ሰው በየዘርፉ አሰባስቦ ለሃገሪቱ በታሪክ የማይዘነጋ ምርጥ የህትመት ውጤት መፍጠር የቻለ ሰው በመሆኑ ነው ይላል። ለ4 አመታት ከ100 በላይ እትሞችን ለአንባቢ በማቅረብ የዘለቀው አዲስ ጉዳይ ደረጃውን ጠብቆ መጓዙን በርካታ አንባቢዎች ይመሰክራሉ፡፡ ነፍስ ሄር ኢብራሂም ሻፊ ፣ ዮሃንስ ካሳሁን፣ አስማማው ሃይለጊዮርጊስ፣ እንዳለ ተሺ የመላኩ የሙያ ባልደረቦች ሲሆኑ ከቴዎድሮስ ተክለአረጋይ ውጪ በመጨረሻ ዘመኑ አዲስ ጉዳይን የተቀላቀሉት የስታፍ አባላት እነአዚዛ መሃመድ እና መድሃኒት ረዳን ጨምሮ ሁሉም ከአዲስ ጉዳይ መዘጋት ጋር በተያያዘ ዛሬ በውጭ ሃገራት በተለያየ ስራና ህይወት ላይ ይገኛሉ። መላኩ ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ ዛሬን በህይወት ቆሞ አለማየቱ ይቆጨኛል ይላል። ኢብራሂም ሻፊ በሁሉ ልብ ውስጥ የእግር እሳት የሆነ፣ ስደት ላይ ሳለ ህይወቱ ያለፈ ምርጥ ማንም የማይስተካከለው አዋቂ የስፖርት ጋዜጠኛ ነው ይላል መላኩ። መላኩ ስለእንዳልካቸው ተስፋዬ ሲናገር “እንዳልካቸው ተስፋዬ ለዚህች ሃገር የፕሬስ ነጻነት ማበብ እና አንባቢ የሚገባውን ክብር እንዲያገኝ ሙሉ ነገሩን አጥቶም ቢሆን ከአደጋ ጋር ተጋፍጦ የታተረ ሊሸለም የሚገባው ታላቅ ሰው ሰው ነው” ይላል ።ሁሌም የአዲስ ጉዳይ ባልደረቦቹንና ጓደኞቹን ሲያስታውስ ያንን ወርቃማ የፕሬስ ዘመን አብሮ እንደሚያወሳው ነው የሚናገረው መላኩ።

   የአዲስ ጉዳይ አበርክቶዎች

መላኩ ይህንን መጽሄትነት መንግስት እስኪዘጋው ድረስ በማኔጂንግ ኤዲተርነት መርቷል። የታፈኑ እውነቶች፣ ፍቅርና ወንጀል፣ ቢዝነስቴይመንት፣ ትዳር እና ፍቅር፣ ማንን እንማ የመሳሰሉትን በጊዜው ከፍ ያለ አንባቢ የነበራቸውን አምዶችን በባለቤትነት ይዞ ሰርቷል። በተለይ “ዐቢይ ጉዳይ” በተሰኘ አምድ ላይ ይቀርቡ ከነበሩ በርካታ የፖለቲካ ትንታኔዎች ውስጥ የርሱ ስራዎችም ብዙ ናቸው። በታፈኑ ዕውነቶች አምድ ስር የሚቀርቡ በማህበራዊ ችግሮች ላይ ያተኮሩና በተግባር ለውጥ ያመጡ ዘገባዎችን እንዲሁም የወንጀል አምድ ስር የሚቀርቡ እውነተኛ ታሪኮችን እያዘጋጀ መጽሄቱ በመንግስት እስከተዘጋበት 2007 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ አዲስ ጉዳይ ላይ ለአንባቢ አቅርቧል። መላኩ በዚህ መጽሄት በጊዜው የነበረውን የፖለቲካ ስርዓት ችግሮች ገንቢ በሆነ መንገድ በማሳየት የህዝብ መብት እንዲከበር እና መንግስትም ተገቢ የአስተዳደር ተግባሩን በብቃት እንዲወጣ የመልካም አስተዳደር እና የፖለቲካ ባህል ለውጥ እንዲመጣ የበኩሉን ሙያዊ ድርሻ ተወጥቷል።ለዚህም ነው “በጋዜጠኝነት ህይወቴ ለአላማ የሰራሁበትና የሙያ መስዋዕትነት የከፈልኩበት ዘመን ያ ጊዜ ነው” ብሎ የሚኮራው።

   ጉዞ ወደ አርትስ ቲቪ

አዲስ ጉዳይ ከተዘጋ በኋላ መላኩ በዘመኑ በፕሬስ ላይ በነበረው ጫና እና ምቹ ያልሆነ ከባቢ ለሶስት አመታት ያህል ጋዜጠኝነትን በመደበኛነት ከመስራት አርቆት ነበር። ያንን "የጥሞና" ብሎ የሚጠራውን ሶስት አመት በኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ስራ ላይ አሳልፏል። ከለውጡ ጋር ተያይዞ አዲስ ጮራ በፈነጠቀው የሃገሪቱ ፕሬስ ላይ ዳግም ለመስራት በቀረበለት ጥያቄም መላኩ ከመስከረም 2019 ጀምሮ በአፍሪካ ሬይነሰንስ ቴሌቪዠን ሰርቪስ (አርትስ ቴሌቪዠንን) በዜና ክፍል ሃላፊነት ተቀላቅሏል። በዚያም የጣቢያው ቺፍ ኦፕሬሽን ኦፊሰርነት ድረስ በደረሰ የሃላፊነት ቦታ አገልግሏል። በርካታ አዳዲስ ፕሮግራሞችንና የዜና ፎርማቶችን ቀርጿል። በብዙሃን ዘንድ እውቅና ያገኘበትን “ዐቢይ ጉዳይ” በመባል በሚታወቀውን የውይይት ፕሮግራም በመቅረጽና በአዘጋጅነትና አቅራቢነት በመስራት የሃገራችንን የፖለቲካ እና ማህበራዊ ዲስኮርስ ባህሎች ከፍ አድርጎ ልዩነትን ወደውይይት እና መግባባት ባህል ለማምጣት የበኩሉን ሙያዊ ሃላፊነት እየተወጣም ይገኛል።ዐቢይ ጉዳይ ዛሬ ድረስ ብዙሃን በተረጋጋ ፣ ሚዛናዊ በሆነና በበሳል ሁኔታ በሚዘጋጅ የቴሌቪዠን ዝግጅትነት የሚመሰክሩለት፣ አርትስ ቴሌቪዠንም ከሚታወቅበት ፕሮግራም አንዱ ነው።

  “ፍቅርና ወንጀል” የመላኩ መጽሀፍ

መላኩ በጋዜጠኝነት የስራ ዘመኑ በመደበኛነት ከሰራባቸው ከላይ የተጠቀሱ ሚዲያዎች ባሻገር ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ በወንጀል እና በማህበራዊ ጉዳዮች አምደኝነት እንደ ጦማር፣ ዕለታዊ አዲስ እና ዘ-ፕሬስ እንዲሁም ጽጌረዳ እና ሮዝ የመሳሰሉ በዘመኑ ተነባቢ ጋዜጦችና መጽሄቶች ላይ ሰርቷል። በተለይም ኮከብ አሳየ በሚል የብዕር ስም “ፍቅርና ወንጀል” እንዲሁም “የታፈኑ ዕውነቶች” በተሰኙ አምዶች ላይ ያቀርባቸው በነበሩ በወንጀል እና ማህበራዊ ችግሮች ላይ ያተኮሩ የምርመራ ዘገባዎች ብዙ አንባቢያን ያውቁታል። እነዚህን ታሪኮች በማሰባሰብ በ2009 ዓ.ም “ፍቅርና ወንጀል” የተሰኘ አንድ መጽሃፍም ለንባብ አብቅቷል። የበርካታ መጽሃፍትም አርታኢ ነው። በቅርቡም ግዮን በተባለ መጽሄት ላይ በፍሪላንስ ለብዙ ዕትሞች የዘለቀ የከቨር ስቶሪዎች ጸሃፊ ሆኖም ሰርቷል።

  የሙያ ሽልማቶች እና የውጭ ሃገራት ጉዞዎች  

መላኩ ብርሃኑ በስራ ዘመኑ ከጋዜጠኝነት ሙያው ጋር ለተያያዙ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች እና ስልጠናዎችና ጥናታዊ ጉብኝቶች 11 ወደሚጠጉ የአፍሪካ፣የአውሮፓ፣የእስያ እንዲሁም የመካከለኛውና የሩቅ ምስራቅ ሃገራት ተጉዟል። እስራኤል፣ ህንድ፣ቻይና፣ፖላንድ፣ቱርክ፣ኢንዶኔዢያ ፣ ግብጽ፣ ሞሮኮ፣ ዛምቢያ፣ ታንዛኒያ፣ ኬንያ በተደጋጋሚ ጊዜ ለጥናታዊ ጉብኝት እና ለተለያዩ ስልጠናዎች የተጓዘባቸው ሃገራት ናቸው።ከዚህ በተጨማሪም የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያቤት ከዓለም ዙሪያ ለተመረጡ ጋዜጠኞች በሚሰጠው Edward R. Murrow Program for Journalists IVLP ዕድል መላኩ ከኢትዮጵያ የ2021 ብቸኛ ተመራጭ በመሆን ፕሮግራሙን የመካፈል እድል አግኝቷል።

መላኩ በተለይም በጤና ዘገባ ፣ በተጨማሪም በህገ-ወጥ ስደት እና በሌሎች ርዕሶች ላይ በተዘጋጁ የሚዲያ ዘገባ ውድድሮች ተሳታፊ በመሆን ለንባብ ባበቃቸው ስራዎቹ ከ International Centre For Journalists የአለምአቀፍ ሽልማት አሸናፊ ነው። በተጨማሪም ከ Africa Media Initiative የአንድ አህጉራዊ 2nd place AMI award ሽልማት አሸናፊ ሲሆን በሃገር ውስጥ ውድድሮችም የ IOM, PANOS, EAJA , ICFP ENHIA እና MoH ሃገር አቀፍ የጋዜጠኝነትና ሚዲያ ዘገባዎች ሽልማቶች እና ግራንቶች አሸናፊ ባለሙያ ነው።

  የሙያ ማህበራት ተሳትፎ

በሙያ ማህበራት ተሳትፎ በኩልም መላኩ ቀዳሚው የኢትዮጵያ ፕሬስ ካውንስል ሲመሰረት በአካባቢ ጋዜጠኞች ማህበር ተወካይነት ፈራሚ ሲሆን የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጋዜጠኞች ህብረት ፣የኢትዮጵያ አካባቢ ጋዜጠኞች ማህበርም የቦርድ ሰክረታሪ ሆኖ አገልግሏል። በቀድሞው የኢትዮጵያ ጤና ጋዜጠኞች ኢኒሺየቲቭ እና የአፍሪካ የጤና ጋዜጠኞች ማህበርም በአባልነትና በተጨማሪም በኢትዮጵያ የቤተሰብ ጤና ጋዜጠኞች ማህበር ውስጥ በልዩ አባልነትም አገልግሏል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጰያ አርታኢያን ማህበር የስራ አስፈጻሚ አባል እንዲሁም በኢትዮጲያ ሚዲያ ሴክተር አሊያንስ ውስጥ አባል ነው።

መላኩ በኮሚዩኒኬሽን ዘርፎች

በመላኩ ለተለያዩ የሃገር ውስጥና የውጭ ሃገር ኩባንያዎች የኮሚዩኒኬሽን፣ ስልጠናና ሚዲያ ግንኙነቶች አማካሪነት ስራዎችን ሰርቷል።የጣሊያኖቹ ፕሮራስ ኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ እና ኮንሰርዚዮ ኢታሊ፣ የኮሪያው ኤምሲኤም ዲቨሎፕመንት፣ የቻይናው Shenzhen LEMI (Shenzhen LEMI Technology Development Co. Ltd.) ወዘተ መላኩ የኮሚዩኒኬሽንና ሚዲያ ሪሌሽን ስራዎቻቸውን ከሰራላቸው ድርጅቶች ጥቂቶቹ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም NOVE Consulting plc በተባለ የጣሊያን Export promotion ኩባንያ ውስጥ በቺፍ ኮሙኒኬሽን ስፔሻሊስትነት፣ እንዲሁም በጊፍት ቢዝነስ ግሩፕ በኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን እና ፕሮሞሽን ስራ አስኪያጅነት ሰርቷል። በአሁኑ ወቅትም የቡና ባንክ የኮሙኒኬሽን እና ፕሮሞሽን ስራ አስኪያጅ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል።

መላኩ ሁለት አስርተአመታትን በዘለለ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ህይወቱ ለአንዲትም ቀን ቢሆን አቅሙን ሳይቆጥብ ሰርቷል፡፡ አብረውት ይሰሩ የነበሩ በግልጽ እንደተናገሩት መላኩ ለሌሎች አርአያ የሚሆን ሁለ-ገብ እውቀትን የተላበሰ ባለሙያ ነው፡፡ ይህን ክህሎቱንም ስራዎቹን በመመልከትና ጽሁፎቹን በጥልቀት ከማንበብ መረዳት ይቻላል፡፡ መላኩ ለማንኛውም ስራ በቅድመ-ዝግጅት ያምናል፡፡ ስለ አንድ ጉዳይ ምንም ነገር ከመጻፍ፣ ከመስራትና ከመናገሩ በፊት በበቂ ሁኔታ ይዘጋጃል፡፡ ይህን በማድረጉም ስራዎቹ ብስለትን የተላበሱና በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ ሊሆኑ ችለዋል፡፡

  ቤተሰባዊ ህይወትና ቀሪ ዘመን

መላኩ ከወይዘሮ ሊዲያ ተስፋዬ ጋር ትዳር በመመስረት ሰንፔር መላኩ፣ ሚካኤል መላኩ እና አሜን መላኩ የተባሉ 3 ልጆችን አፍርቷል። “ቀሪው ዘመን በኮሙኒኬሽን ለውጥ የማመጣበት፣ በጋዜጠኝነቴም ሃገሬን የምጠቅምበት፣ በመምህርነት ትውልድ የምቀርጽበት ዘመን ነው” ይላል መላኩ። መላኩ ብርሃኑን በየዕለቱ ጽሁፎቹንና ምልከታዎቹን በሚያጋራበትና በርካታ ተከታዮች ባሉት የፌስቡክ አድራሻው https://www.facebook.com/melaku.berhanu1 ማግኘት ይቻላል


የመላኩ በጤና ጉዳዮች ዘገባ በዓለም አቀፍና በሃገር አቀፍ ደረጃ ተወዳድሮባቸው አሸናፊ ከሆኑ ዘገባዎቹ ጥቂቶቹ በሚከተሉት ሊንኮች ይገኛሉ

• CAN’T PAY THE BILL: Why people in Ethiopia can’t afford pain relief Published originally on www.newbusinessethiopia.com and shared on many websites like merja.com Dire tube and others https://mereja.com/forum/viewtopic.php?f=2&t=91365

• ማህበራዊ የጤና መድህን በረከቶች፣ ስጋቶችና መልካም አጋጣሚዎች Published originally on Addis Guday magazine then shared on websites like maghedere tena Link http://www.mahderetena.com/amharic/archives/2114 • ከአረንጓዴ ውበት ፈጣሪዎች የምንማረው አለ Published on Addis Zemen newspaper Link

www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/addiszemen/economy?start...

• የተዳፈነው ፍም

Originally published on Addis Guday magazine and shared on websites like ‘mahederetena’ Link www.mahderetena.com/amharic/archives/2118

• ጥቂት ቀናት የሚታደጓቸው እድሜ ልኮች

Originally published on Addis Guday magazine and ICFJ website http://www.icfj.org/news/winners-vaccine-reporting-contest-focus-barriers-and-successes-eradicating-polio http://www.icfj.org/files/Melaku%20Berhanu%20Tesfay.pdf And shared on other websites like mahedere tena and satenaw Link

• የተጣበቁት መንትዮች እና አስጨናቂው የ 6 ሰዓታት ቀዶ ህክምና

LINK http://www.mahderetena.com/amharic/archives/2096