Jump to content

መዓዛ ብሩ

ከውክፔዲያ
(ከመዓዛ የተዛወረ)

መዓዛ ብሩ መዓዛ የተወለደችው እዚህ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሲሆን ዘመኑም 1951 ዓ.ም ነበር፡፡ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ክፍል በሐረርጌ ክፍለ ሀገር በሒርና ከተማ ተምራ፣ ከአራተኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርቷን ደግሞ በቅድስት ማርያም ትምህርት ቤት (Saint Mary School) ተከታትላ ፈጽማለች፡፡ መዓዛ በትምህርት ቤቷ በክፍል ውስጥ አጫጭር ታሪኮችን ለተማሪዎች በማንበብ ከመታወቋም ሌላ ከፍ ያለ የሥነ - ጽሑፍ ዝንባሌ እንደነበራት የሚያስታውሱት መምህራኗ “አንድ ቀን ታላቅ የጥበብ ሰው እንደሚወጣት እናውቅ ነበር” ይላሉ፡፡ መዓዛ በ1971 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ - ቋንቋ ጥናት ተቋም ውስጥ በሥነ -ልሣን (Linguistics) ትምህርት ክፍል ተመደበች፡፡ ሥነ - ልሣን መዓዛ የምትፈልገው ጥናት ባለመሆኑ በምደባው ቅር ብትሰኝም፤ በንዑስ ትምህርት ደረጃ (minor study) የምትወስደው የውጭ ቋንቋና ሥነ - ጽሑፍ በመሆኑ ለነበራት ቅሬታ እንደማካካሻ ሆኖላታል፡፡ በዚህ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ሳለች የተፈጠረ አንድ አጋጣሚ ደግሞ መዓዛንና ሬዲዮንን የሚያስተሳስር ይሆናል፡፡ ይኸውም የኢትዮጵያ ሬዲዮ የፕሮግራሞች ኃላፊ የነበረው አቶ ታደሰ ሙሉነህ ለሚያዘጋጀው የእሁድ የሬዲዮ ፕሮግራም ድራማ የሚጫወቱ ሸጋ ድምጽ ያላቸው ወጣቶችን ሲያፈላልግ ከመዓዛ ጋር ይተዋወቃል፡፡ ድራማው አስታጥቃቸው ይሁን ያሰናዳው ሲሆን የመዓዛ ድምጽ ለሙከራ በስቱዲዮ ተቀርጾ ሲሰማው፣ ታደሰ ሙሉነህ የሚፈልገውና የሚወደው ድምጽ ሆኖ ስላገኘው ይደሰታል፡፡ ከዚህ በኋላም ለእሁድ ፕሮግራም የሚሆኑ ጽሑፎችን በየሳምንቱ እንድታነብለት ያግባባትና የመዓዛና የሬዲዮ ፍቅር በኢትዮጵያ ሬዲዮ ይወለዳል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የመዓዛ ድምጽ በእሁድ የሬዲዮ ፕሮግራም አድማጮች ዘንድ የተለመደና የተወደደ ሆነ፡፡ መዓዛም የሌሎችን ጽሑፎች በማንበብ ብቻ ሳትወሰን የራሷን ጽሁፎች እያዘጋጀች የምታቀርብ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ከሬዲዮ ፕሮግራሙ ቤተሰቦች እንደ አንዱ ሆነች፡፡ በ1974 ዓ.ም ከዩኒቨርሲቲ ተመርቃ ትምህርቷ ፍጻሜውን እስካገኘ ድረስም መዓዛ ሬዲዮና ትምህርትን ጎን ለጎን ስታስኬድ ቆይታለች፡፡ የመዓዛ የሥራ ዓለም የተጀመረው ግን በምትወደውና በምትፈልገው በኢትዮጵያ ሬዲዮ ውስጥ ሳይሆን መንግስት በመደባት በባህል ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ ነበር፡፡ ስራዋም ባህልና ስፖርት የተባለው የመስሪያ ቤቱ መምሪያ በሚያሳትመው “መርሐ ስፖርት” የተሰኘ ወርሃዊ የስፖርት መጽሔት (በኋላ ጋዜጣ) ላይ ሆነ፡፡ ምንም እንኳ አዲሱ ስራዋ ከራዲዮ የሚያርቃት ቢሆንም መዓዛ ግን ሳትሸነፍ ሬዲዮን በትርፍ ጊዜ ሥራነት ተያያዘችው፡፡ ሬዲዮ ጣቢያው የሚሠጣትን አነስተኛ ክፍያ እየተቀበለችም ልዩ ልዩ ጭውውቶችን እና መጣጥፎችን በግልና በጋራ በማቅረብ ተወዳጅ ሥራዎቿን ለሕዝብ አበርክታለች፡፡

መዓዛ በእሁድ የሬዲዮ ፕሮግራም ታቀርባቸው የነበሩት ሥራዎች ይዘት ማህበራዊ ሕይወት እንዲሠምር በመጣር ላይ ያተኮሩ ሆነው ግልጽ፣ ቀላልና ለዛ ያልተለያቸው ስለነበሩ ከሶስት አሥርት ዓመታት በኋላም ትውስታቸው ከአድማጭ ህሊና አልጠፉም፡፡ በዚሁ ፕሮግራም ላይ መዓዛ ካበረከተቻቸው የፈጠራ ሥራዎቿ ውስጥ ጎልቶ የሚታወሰው “የአዲሱ ቤተሰብ” የተሰኘ ባለ ሰማንያ ስድስት ክፍል ድራማ ሲሆን በዘመኑ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉም የሚያደምጠው ተወዳጅ የቤተሰብ ድራማ ነበር፡፡ መዓዛ በ “መርሀ ስፖርት” እና በሬዲዮ መካከል ሆና ከአራት ዓመት በላይ ከቆየች በኋላ በ1979 ዓ.ም የባህል ሚኒስቴርን ለቃ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቀጠረች፡፡ አዲሱን መስሪያ ቤቷን ከተቀላቀለችበት ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከሬዲዮ እየራቀች መጣች፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የቆየችው ለሶስት ዓመታት ያህል ሲሆን ከዚያ በኋላ የግሏን የማስታወቂያ ሥራ ድርጅት መሥርታ የራስዋ ተቀጣሪ ሆናለች፡፡ ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1992 ዓ.ም ባሉት የአስራ ሶስት ዓመታት ጊዜ ግን መዓዛና ሬዲዮ ተራራቁ፡፡ መዓዛና ሬዲዮ ዳግም የተዋደዱት ከላይ እንደተገለጸው በ1992 ዓ.ም ሳምንታዊውን የ “ጨዋታ” ፕሮግራም በኤፍ ኤም 97.1 ከተፈሪ ዓለሙ ጋር በጋራ ማቅረብ ሲጀምሩ ነበር፡፡ የ “ጨዋታ” ፕሮግራም እስከ 1999 ዓ.ም ድረስ በአድማጮቹ እንደተወደደ በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ላይ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት የኤፍ ኤም ሬዲዮ ፈቃዶችን ለግሉ ዘርፍ ለመስጠት ሲዘጋጅ፣ ዝርዝር የሥራ እቅድ አቅርባ ባመለከተችው መሠረት፤ ከረጅም ጊዜ ቆይታ በኋላ ከአስር አመልካቾች መካከል አንዷ ሆና የመጀመሪያ የግል የኤፍ ኤም ሬዲዮ ባለቤት ያደረጋትን ፈቃድ ተቀበለች፡፡ መዓዛ የሬዲዮ ማሰራጫ መሳሪያዎችን ውድነት፣ የማሰራጫ ቦታ እና የባለሙያ እጦትን ተቋቁማ ሸገር 102.1 ኤፍ ኤም ሬዲዮን በታህሳስ 1999 ዓ.ም አበረከተችልን፡፡ ባለትዳርና የሶስት ልጆች እናት የሆነችው መዓዛ እንደ ባለቤት፣ ሥራ አስኪያጅና ጋዜጠኛ በመሆን በኢትዮጵያ ተወዳጁንና የመጀመሪያውን የግል የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ትመራለች፡ “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!”እያለች

https://www.facebook.com/thisdayinethiopianhistory