ሳሮን (አፈታሪካዊ ንጉሥ)

ከውክፔዲያ

ሳሮን1490 ዓ.ም. አኒዩስ ዴ ቪቴርቦ የተባለው ጣልያናዊ መነኮሴ ባሳተመው ዜና ማዋዕል ዘንድ፣ የኬልቶች (በጋሊያ፣ አሁንም ፈረንሳይ አገር) ሦስተኛ ንጉሥ ነበረ። የማጉስ ልጅና ተከታይ ሲሆን ለ61 ዓመት (ምናልባት 2214-2153 ዓክልበ. ግድም) እንደ ነገሠ ተብሏል። ዜና መዋዕሉም እንደሚለው፣ ንጉሥ ሳሮን የሰውን ልጅ ጸባይ ለማሰልጠን ጽሕፈትንም ለማስተምር በጋሊያ ትምህርት ቤቶች መጀመርያ የመሠረተ ነው።

ዲዮዶሮስ ሲኩሉስና ሌሎች የታሪክ ጸሐፍት ስለ ድሩዊዶች (የጥንታዊ ኬልቶች አረመኔ ቄሳውንት) ሲገልጹ፣ ከክፍሎቻቸው አንዱ «ሳሮኒዴስ» እንደተባለ ጽፈዋል። በብሪታንያ ደግሞ ሲገዛ ሳሊስቡሪ ከተማ (ኦልድ ሳሩም ወይም ጥንታዊ ሳሩም) እንዳቆመ አንዳንድ ጸሐፊ አስቧል። እንዲሁም በስቴፋኑስ ፎርካቱሉስ (ፈረንሳዊው ኤትየን ፎርካዴል) ዘንድ ሳሮን ጋሊያን እስከ ጋሮን ወንዝ ድረስ ገዛ፤ በቱሉስ ከተማ አንድ ዩኒቨርሲቴ እንደ መሠረተ የሚል ልማድ አለ። ለግብጽም ንግሥት ኢሲስ ጉብኝት አድርጎ ሲመለስ በጉዞው ላይ በቆሮንቶስ ልሳነ ምድር (ግሪክ አገር) አጋዘን አሳድዶ በሳሮኒክ ወሽመት ሰመጠና ልጁ (ወይም እንደ አኒዩስ ሓረግ በሞት የቀደመው የልጁ ናምኔስ ልጅ) ድሩዊስ ተከተለው።

በግሪክ አፈታሪክ ደግሞ ንጉሥ ሳሮን አጋዘን አሳድዶ በሳሮኒክ ወሽመት እንደ ሰመጠ ይታወሳል። በዚህ ትውፊት ግን የትሮይዜና (የፔሎፖኔሶስ ከተማ) ንጉሥ ይባላል።

ቀዳሚው
ማጉስ
የሳሞጤያ (ጋሊያ) ንጉሥ
2214-2153 ዓክልበ. ግድም (አፈታሪክ)
ተከታይ
ድሩዊስ