ሶሀባ (sahabah)/አኢሻ (ረ.ዐንሀ)

ከውክፔዲያ


እናታችን አዒሻ (ረ.ዐ)

“በኢስላም የመጀመሪያው የፍቅር መግለጫ ነብዩ ለአዒሻ የነበራቸው ፍቅር ነው።”

ከሥረ መሠረቱ ኢስላምን ከንጹህ ምንጭና ከትክክለኛው አካባቢ የመረዳት ምሳሌ ናት። ከመምህራኖቹ ሁሉ ምርጡ መምህር (ከነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)) እንደመማሯም አንድ ሙስሊም ሊደርስበት የሚያስበው የፅድቅ ደረጃ የደረሰች አርአያ ሴት ነች።

በመሠረቱ የአዒሻ ምሳሌነት ዘርፈ ብዙ ነው። ከግል ሕይወት እስከ ሕዝባዊ፣ ከቤት ውስጥ ኑሮ እስከ ምሁራዊ ጉዞ፣ ወዘተ። ከነዚህ የአርኣያነት ምሳሌነቶች ውስጥ ወሳኝ ድርሻ ያለው ደግሞ የምዕመናን እናትነቷ ነው። በቁርኣን የተገለጸውን ምርጥ ኢስላማዊ ምግባር በማሟላትም ምሥጉን ስብእና ነበራት። ቸርነት፣ ቅንነት፣ ታማኝነትና እውነትንና ፍትህን መፈለግ የአዒሻ ዋነኛ መገለጫዎች ነበሩ።

አዒሻ እንደተማሪ ከጎበዝ ወጣትነት በተጨማሪ በጠያቂና ተመራማሪ ጭንቅላት ወደ ስኬታማና የተከበረ አዋቂ፣ መምህርና ዳኛ ሆና፤ በተፍሲር፣ በፊቅሂ፣ በሐዲስ፣ በታሪክና በዐረብኛ ቋንቋ ዘርፎች ከፍተኛ ደረጃ ከመድረሷም በላይ በምትሰጣቸው ደፋር፣ ቀጥተኛና የበሰሉ ምሁራዊ ትንተናዎች ትታወቃለች። የአዒሻ ለምታምንበት ነገር ሁሉ ደፋር፣ ግልጽና ቀጥተኛ መሆንን ከፍተኛነት፤ በአሁኑ ሰዓት በሙስሊሙ ዘንድ እንኳ ሴት ልጅ በጾታዋ ምክንያት ብቻ ከማህበረሰቡ የእለት ተዕለት ሕይወት የተገለሉትን ሙስሊም ሴቶች በማየት እንኳ ማረጋገጥ ይቻላል።

አዒሻ ከማንም በበለጠ ኹኔታ በነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የእለት ተዕለት ሕይወት የነበራት ቦታ እንዲሁም የአስተሳሰብና የባሕሪይ ነጻነቷ በዘመኗ ከነበሩ ታላላቅ ስብዕናዎች ሁሉ የበለጠ ትኩረት እንድትስብ አድርጓታል።

የአዒሻ የኋላ ታሪክ (Background)

አዒሻ ሙሉ ስሟ፤ አዒሻ ቢንት አቡበከር አስ-ሲዲቅ ቢሆንም አዒሻ ቢንት ሲዲቅ በመባል በብዛት ትታወቃለች። ይበልጥ የምትታወቀው ግን አስ-ሲዲቃ ቢንት አስ-ሲዲቅ (እውነተኛዋ የእውነተኛው ልጅ) በሚለው ነው። ነብዩም የእህቷን ልጅ አብዳላህ ኢብኑ ዙበይርን እጅግ በመንከባከቧ ምክንያት (ኡሙ አብደላህ) የአብደላህ እናት በሚል ቅጽል ሥም ይጠሯት ነበር። ሁለቱም ወላጆቿ ኢስላምን ገና በጠዋቱ የተቀበሉ በመሆናቸው አስተዳደጓ በንጹህ ኢስላማዊ ከባቢ (environment) ውስጥ ነበር ማለት ይቻላል። እሷም ስትናገር “ገና ከጨቅላነቴ አንስቶ ወላጆቼ ኢስላምን ሲተገብሩ ለማየት ታድያለሁ” ትል ነበር። ገና ከጠዋቱ ስታስተውለው የኖረችው ኢስላማዊ አኗኗር በኋላ ላዳበረችው የአዕምሮ ንቃትና ሠብዕና ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል። ከልጅነቷ አንስቶ በኢስላም ላይ ከፍተኛ እምነት ስታሳድር ለእውነት መስዋዕት መሆንን ደግሞ አስተምሯታል። በተመሳሳይ ኹኔታም ክህደትና መሃይምነትን ትጠላለች።

የምዕመናን እናት አዒሻ ከነብዩ ባለቤቶች መካከል ብቸኛዋ ልጃገረድ ናት። የሁለቱ ትዳር የተፈጸመው በአላህ ትዕዛዝ ነበር። አዒሻም ስታገባ በወቅቱ በነበሩት በዐረቦች፣ በእብራውያንና በሌሎች ሕዝቦች ባህል እንደተለመደው ትንሽ እድሜ ነበራት። ይህንን የዕድሜ ሁኔታ አሁን ከ1400 ዓመታት በኋላ ባለው ባህልና ዝንባሌ ለመገምገም መሞከርም ስህተት ነው። የነብዩ የትዳር ሁኔታ ከሳቸው ተልዕኮ ተለይቶ ሊታይ አይችልም። ተልዕኮዋቸውም የዐረቦችን አንድነት መፍጠርና እውቀትና ጥበባቸውን ለሠው ዘር ማስተላለፍ ናቸው። ካለፉትም ከአሁኖችም ምሁራን አስተያየት ማረጋገጥ እንደሚቻለው አዒሻ (ረ.ዐ) በአስተዳደጓም ሆነ በተፈጥሮዋ ምርጥ የተባለችው ምርጫ ነች። ይህንን ተግባርም በወሳኝ እድሜዋ ከነብዩ ጎን በመኖር እየኖረችው በብቃት ፈጽማዋለች።

አዒሻ ለነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በነበራት ፍቅርና እርሳቸውን የግሏ ብቻ ለማድረግ ባላት ጽኑ ፍላጎት ምክንያት በሌሎቹ ሚስቶቻቸው ላይ ትቀና ነበር። ነብዩም ይህን ፍቅሯን ተመሳሳይ መጠን ያለውን ፍቅር በመስጠት መልሰውላታል። የሳቸው ፍቅር ለሰሃቦችም ምሳሌ ነበር።

አነስ (ረ.ዐ) እንደዘገቡትም፤ “በኢስላም የመጀመሪያው የፍቅር መግለጫ ነብዩ ለአዒሻ የነበራቸው ፍቅር ነው።” ነብዩ ለሷ የነበራቸው ፍቅር ከአካላዊ ውበቷ ጋር የተሳሳረም አይደለም። ይልቅስ፤ አዒሻ ከተሰጣት አምላካዊ ተልዕኮና የነብያዊ ተግባሩን ቀጣይነት ከማረጋገጥ ጋር የተቆራኘ ነው። የዚህ የማይታለፍ ሚና ማሳያ ነብዩ (ሶ.ዐ.ወ) ከሌሎች ሚስቶቻቸው ጋር የማይገጥማቸው ወህይ ከኢዒሻ ጋር ከተቀመጡባቸው ወቅቶች ሲሆኑ ጅብሪልን አይተዋል። ይህ ደግሞ በነብዩ (ሶ.ዐ.ወ) እንደተነገረው የሠማያዊው ክብር ሥጦታ መገለጫ ነው።

አዒሻ (ረ.ዐ) የገጠሟትን ፈተናዎች፣ የነበራትን እጅ የመስጠት (የኢስቲስላም) አመለካከት ምክንያት በማድረግ የወረዱትን የቁርኣን አንቀፆች በመመልከት “የአላህ እዝነት መፍሰሻ” ትባላለች። ምክንያቱም፤ እነዚህ አንቀፆች ከሷም በኋላ ላለው ትውልድ ሁሉ የሚያገለግል ነው። አንዳንድ ሶሃባዎች የአዒሻን የአላህ እዝነት መገለጫነት ለመግለጽ ከሚጠቀሙት ነገሮች አንዱ የተየሙም ድንጋጌ በአዒሻ ምክንያት መውረዱን ነው። ከዚህም አልፎ አላህ (ሱ.ወ) ይህች እናታችን ስሟ በመናፍቃን በሐሰት በመወሳቱ ምክንያቱ በሱረቱ አን-ኑር ምዕራፍ 24 በተለይም አንቀጽ 23 እና 26 ላይ ክብሯን በመመለስ አንቀጹን ያነበበ ሁሉ ትምህርት እንዲሆነው አድርጓል።

ﺇِﻥَّ ﺍﻟْﻤُﺴْﻠِﻤِﻴﻦَ ﻭَﺍﻟْﻤُﺴْﻠِﻤَﺎﺕِ ﻭَﺍﻟْﻤُﺆْﻣِﻨِﻴﻦَ ﻭَﺍﻟْﻤُﺆْﻣِﻨَﺎﺕِ ﻭَﺍﻟْﻘَﺎﻧِﺘِﻴﻦَ ﻭَﺍﻟْﻘَﺎﻧِﺘَﺎﺕِ ﻭَﺍﻟﺼَّﺎﺩِﻗِﻴﻦَ ﻭَﺍﻟﺼَّﺎﺩِﻗَﺎﺕِ ﻭَﺍﻟﺼَّﺎﺑِﺮِﻳﻦَ ﻭَﺍﻟﺼَّﺎﺑِﺮَﺍﺕِ ﻭَﺍﻟْﺨَﺎﺷِﻌِﻴﻦَ ﻭَﺍﻟْﺨَﺎﺷِﻌَﺎﺕِ ﻭَﺍﻟْﻤُﺘَﺼَﺪِّﻗِﻴﻦَ ﻭَﺍﻟْﻤُﺘَﺼَﺪِّﻗَﺎﺕِ ﻭَﺍﻟﺼَّﺎﺋِﻤِﻴﻦَ ﻭَﺍﻟﺼَّﺎﺋِﻤَﺎﺕِ ﻭَﺍﻟْﺤَﺎﻓِﻈِﻴﻦَ ﻓُﺮُﻭﺟَﻬُﻢْ ﻭَﺍﻟْﺤَﺎﻓِﻈَﺎﺕِ ﻭَﺍﻟﺬَّﺍﻛِﺮِﻳﻦَ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻛَﺜِﻴﺮًﺍ ﻭَﺍﻟﺬَّﺍﻛِﺮَﺍﺕِ ﺃَﻋَﺪَّ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﻟَﻬُﻢ ﻣَّﻐْﻔِﺮَﺓً ﻭَﺃَﺟْﺮًﺍ ﻋَﻈِﻴﻤًﺎ “ሙስሊሞች ወንዶችና ሙስሊሞች ሴቶች፣ ምእምናንና ምእምናትም፣ ታዛዦች ወንዶችና ታዛዦች ሴቶችም፣ እውነተኞች ወንዶችና እውነተኞች ሴቶችም፣ ታጋሾች ወንዶችና ታጋሾች ሴቶችም፣ አላህን ፈሪዎች ወንዶችና አላህን ፈሪዎች ሴቶችም፣ መጽዋቾች ወንዶችና መጽዋቾች ሴቶችም፣ ጿሚዎች ወንዶችና ጿሚዎች ሴቶችም፣ (ካልተፈቀደ ሥራ) ብልቶቻቸውን ጠባቂዎች ወንዶችና ጠባቂ ሴቶችም፣ አላህን በብዙ አውሺዎች ወንዶችና አውሺዎች ሴቶችም፣ አላህ ለእነርሱ ምሕረትንና ታላቅን ምንዳ አዘጋጅቶላቸዋል።” (አል-አህዛብ 33፤ 35)

የአዒሻ ኃይማኖተኛነትና ዙሕድ ከተከበረ፣ ሃብታም፣ ዝነኛና ከፍ ካለ ቤተሠብ ብትወለድም ከሃብታሙ አቡበከር (ረ.ዐ) ተወልዳ በምቾት ብታድግም፤ ከነብዩ (ሶ.ዐ.ወ) ጋር ችግርን በትዕግስት አሳልፋለች፤ ሕይወትን በዙህድ (ቀለል ያለና የምድራዊውን ዓለም ሕይወት የናቀ የአኗኗር ዘይቤ) መርታለች ቀለል ባለ ኑሮ ኑራለች። አላህም ለሁሉም የነብዩ ሚስቶች አላህን፣ መልዕክተኛውን እና የመጨረሻውን ዓለም በመምረጥ ከነብዩ ጋር የችግር ህይወት መምራትና ምድራዊ ደስታን በመምረጥ መካከል ምርጫ አስቀመጠላቸው። እነሱም የመጀመሪያውን መረጡ።

አዒሻም ቀለል ያለ የዙህድ (ምድራዊውን ሕይወት የናቀ) ሕይወት በመምረጧ ምክንያት ጥቂት እየተመገበች፣ ጥቂት እየጠጣች፣ የተጣጠፈ እየለበሠች ካላትም ትንሽ ላይ እየለገሠች ለመኖር ተገደደች። እዚህ ጋር ሳይጠቀስ የማያልፈው ነገር የአዒሻ አለጋገስ ነብዩ (ሶ.ዐ.ወ) እንዳሉት ቀኟ ሲለግስ ግራዋ አያውቅባትም። ተምሳሌታዊ ለጋስነቷ አንዳንድ ጊዜ የራሷን አንገብጋቢ ፍላጎቶች እስከመርሳት ያደርሳል። ይህ ሁኔታዋ አላህ በቁርኣን “የራሳቸው አንገብጋቢ ፍላጎት ቢኖርባቸውም እንኳ ሌሎችን ከራሳቸው ያስበልጣሉ” እንዳለው ነው። ከአዒሻ ተማሪዎች መካከል የነበረው ታላቁ የኢስላም ምሁር ዑርዋ ኢብን ዙበይር አዒሻ በየቦታው የተጣጣፈ ልብስ ለብሳ ሰባ ሺህ ዲርሃም ለምስኪኖች ስትሰጥ ማየቱን ተናግሯል።

እናታችን ምንም እንኳ እድሜዋ ለጋ ቢሆንም ለአላህ ካላት መተናነስና ለነብዩ (ሶ.ዐ.ወ) ካላት ክብርና ለተልዕኮዋቸው ካላት ጽኑ እምነት የተነሳ ነበር ቀለል ያለ ሕይወትን ለመኖር የመረጠችው። ይህ ምርጫዋ ደግሞ ብዙ የሕይወት ስንክሳሮችን እንድትጋፈጥ አድርጓታል። ከነብዩ (ሶ.ዐ.ወ) ኅልፈት በኋላም አዒሻ በዙህድ መኖር፣ መጾም መጸለይ እና ለወላጅ አጦች እንዲሁም ለድሆች መርዳቷ ቀጥላለች።

እውቀቷና ብልህነቷ

የአዒሻ የአዕምሮ ብስለትና ፍጥነት ለጥቂቶች ብቻ የተሠጠ የሚባል ዓይነት ነበር። ከመምህራኖች ሁሉ ምርጡ መምህር ዘንድ የምትማር የኃይማኖት ተማሪ ብትሆንም እንዲሁ የተሠጣትን ብቻ ተቀብላ የምትነፍስ አልነበረችም። ይልቅ፤ ተመራማሪ ጭንቅላትና ጠያቂ አዕምሮ ነበራት። መታወቂያዋም ይኀው ነው። ነብዩ እየመለሱ እሷ ግን መላልሳ እየጠየቀች የምትታይባቸው ብዙ አጋጣሚዎችም ነበሩ። ለአብነት ያህልም፡- በአንድ አስፈሪ ሌሊት እርሳቸው ለሞቱ ሶሃባዎች ዱዓእ ሊያደርጉ በወጡበት ሳያውቁ እርሷ ግን ተከትላቸው መምጣቷን ሲያስተውሉ “ለምን በዚህ አስፈሪ ጨለማ ተከተልሽኝ? ጂኒሽ ጎብኝቶሽ እንዴ?” አዒሻ ግን ይህን አጋጣሚ እንኳ ጥያቄ ለመጠየቅ ተጠቀመችበት። ምን አለች? “ሁሉም ሰው የሚከታተለው ጂን አለ እንዴ?” ነብዩም (ሰ.ዐ.ወ) “አዎ እኔን ጨምሮ ጂን ይከታተለናል። ነገር ግን የኔውን አላህ አስልሞታል (በክፉ አያዘኝም)” አሏት።

ሌላም የአዒሻን ጠያቂ ባህሪ የሚያሳይ ምሳሌ ማሳየት ይቻላል። ነብዩ ስለ ዕለተ ትንሳዔ ሲናገሩ ሁላችንም ራቁታችንን ያልተገረዝን ሆነን እንደምንቀሰቀስ ሲገልጹ አዒሻ (ረ.ዐ) እንደተለመደው “ታዲያ ሁሉም እርቃኑን ሆኖ ሲነሳ አንዱ የአንዱን ኃፍረተ-ገላ ሊያይ ነው?” ስትል ጠየቀች። ነብዩም “አዒሻ ሆይ! የእለቱ ችግር አንዱ የአንዱን ኃፍረት ለማየት የሚያስችለው አይደለም” ሲሉ መለሱላት።

ለከፍተኛው ብልሃቷ ምስጋና ይግባውና አዒሻ ኢ-ምክንያታዊ ለሆኑና ከቁርኣን አስተምህሮ ጋር የሚጋጩ “ኃይማኖታዊ” ተግባራትን ታግሳ የምታልፍበት ልብ አልነበራትም። እሷ በምንም ሁኔታ የቁርኣን አስተምህሮ ከምክንያታዊነት ጋር አይጋጭም የሚል ጽኑ እምነት ነበራት። እንዴት ሆኖስ ይጋጫል አላህ ራሱ “በቁርኣኑ ውስጥ ምንም መጋጨትን አታገኙም” እያለ? በዚህ እይታዋ ምክንያት የአብደላህ ኢብኑ ዑመርን “አንድ ሠው ሲሞት ቤተሰቦቹ በሚያለቅሱት መረን የለቀቀ ለቅሶ ምክንያት ይቀጣል” የሚለውን ሐዲስ ሳትቀበል ቀርታለች። ምክንያቷም፤ “ቁርኣን ‘ማንም ነፍስ የማንኛይቱንም ኃጢያት አትሸከምም’ እያለ ነብያችን እንዴት እንዲህ ይላሉ?” የሚል ነው።

ሌላኛው የአዒሻ ተመራማሪነት ማሳያ የሚሆነው ነብዩ “ውሻ፣ አህያና ሴት እነዚህ ሶስት ነገሮች ሶላት ያበላሻሉ።” ብለዋል መባሉን አለመቀበሏ ነው። አዒሻ ይሄንን አባባል ስትሰማ “ምን ያህል ብትደፍሩን ነው እኛን ከውሻና ከአህያ ጋር የምታነፃፅሩን? ነብዩ እንኳ እኔ ተኝቼ ለሊት ሲሰግዱ ሱጁድ ማድረጊያ ቦታቸው ላይ እግሬን ዘርግቼ ሲያገኙ እግሬን ቀስ አድርገው ይገፉትና ሱጁዳቸውን ያደርጋሉ” አብደላህ ኢብኑ ዑመር ሴቶቹን በትጥበት (ጉስል) ወቅት ጸጉራቸውን እንዲፈቱ ማዘዙን ስትሰማ “ታዲያ አንድነቱን ጸጉራቸውን እንዲላጩ አያዛቸውም ነበር? እኔኮ ከነብዩ ጋር በአንድ የውሃ መያዣ ስታጠብ ጸጉሬ ላይ ሶስት ጊዜ ውሃ ከማፍሰስ ውጪ ፀጉሬን አልፈታውም ነበር።” ማለቷ ይነገራል።

አዎንታዊ ምልከታዋ

የአዒሻን አስደናቂ ባህሪና ጥንካሬ ለመግለጽ በሕይወቷ እጅግ አስቸጋሪ የሆነውን አጋጣሚ፣ በሀሰት የዝሙት ክስ ሲቀርብባት እንዴት እንዳለፈችው መግለጹ ጠቃሚ ነው። ይህ ክስ ሲቀርብባት አዒሻ እጅግ አዘነች በጣም ኃይለኛ ድብርት ውስጥ ገባች። ሆኖም፤ ፈጽሞ አላፈገፈገችም፤ ለማንምም አላጎበደደችም። ይልቅስ፤ መተማመኛዋን አላህን በማድረግ እሱ ራሱ ንጽህናዋን እስኪገልጽ ድረስ በጽናት ቆመች። አላህ ንጽህናዋን እንደሚገልፅ እርግጠኛ ብትሆንም ቅሉ በሷ ምክንያት አላህ ለመልክተኛው ወህይ (ራዕይ) ያወርዳል ብላ ግን አልጠበቀችም ነበር። ዳሩ ግን፤ አላህ ሙሉ ሱራ (ምዕራፍ) ሲያወርድ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሷን ንጽህናና ታማኝነት ሲገልጽ ነብዩን ለማመስገን ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረች። አላህን ብቻ ነው የማመሰግነው በማለት በአቋሟ ጸናች። ይህን ያለችው ግን ነብዩ ላይ ሥርኣት ለማጣት ሳይሆን የአላህን መብት ለርሱ ብቻ ከመስጠት አንጻር ነው። ይህ ተግባሯ ለሁሉም ሙስሊሞች እንደ ምርጥ ምሳሌ ሊቀርብ የሚችል ጉዳይ ነው። ምድራዊ ኃይላት የቱንም ያህል ቢሆኑ ከአላህ ጋር አይወዳደሩም። ለነገሩ ይህ አይነቱ ውስጣዊ ጥንካሬ ቀደምት ሙስሊሞች የነበራቸው ኃብት ነበር።

አሁንም ለአዎንታዊ አመለካከቷ ምስጋና ይግባውና አዒሻ ኢ-ፍትሃዊነት፣ ኢ-ሞራላዊና ውሸት ያለችውን ነገር ከመጋፈጥ ወደ ኋላ ብላ አታውቅም። አንዳንዶች አቡበከር ሲዲቅ ከሞተ በኋላ እርሱ ላይ አቃቂር ለመፈለግ ሲሞክሩ ጠራቻቸውና አቡበከር በሕይወት ዘመኑ የፈጸማቸውን ተግባራት፤ ያደረጋቸውን ገድሎች እና ስኬቶቹን በመግለጽ ከርሱ ላይ ያገኙት ምን አይነት ሥህተት እንደሆነ ጠየቀቻቸው አንዳቸውም መልስ አልነበራቸውም።

በኸሊፋዎቹም ላይ (ሙዓውያን ጨምሮ) አንድ የፖሊሲ ስህተት ካየች ሳትናገራቸው አልፋ አታውቅም ነበር። አንዴ ሴቶች ቀብር ዚያራ እንዳያደርጉ እቀባ ነበር። እሷ ታዲያ መካ በሄደችበት የወንድሟን ቀብር ለመዘየር በቆመችበት አንድ ሠው መጣና “ነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) ሴቶች ቀብር እንዳይዘይሩ ከልክለዋል” አላት። እሷም “ነብያችን ቀብር መዘየርን ለወንድም ለሴትም ከልክለው የነበረ ቢሆንም በኋላ አንስተዋል።” አለችው። በሷ ግንዛቤ መሠረት እቀባው ለሁለቱም ጾታ እኩል ተነስቷል። ለሴቶች አልተነሳም የሚባልበት አንዳችም ማረጋገጫ የለም። በሷ ጥንካሬም የእናታችን ሰፍያህ ፍላጎት ተሳክቷል። እናታችን ሰፍያህ ለአይሁዱ ወንድሟ የሃብቷን አንድ ሶስተኛ ለመስጠት ብትፈልግም ኸሊፋው ግን “ከነብዩ አስተምህሮ ውጪ ነው” በሚል ሊፈቅድላት አልቻለም። ሆኖም፤ በአዒሻ ያላሰለሰ ጥረት የእናታችን ሰፍያህ ፍላጎት ሊሳካ ችሏል።

በውርስ ህግ ላይ የነበራት ከፍተኛ ብቃትና በራስ መተማመን በሌሎች ጉዳዮች ላይም እንድትሳተፍና ሴቶች በሙስሊም ማኅበረሰብ ውስጥ ስላላቸው ሚና ያለውን አስተሳሰብ የሚለውጥ ነው። ለአብነት ያህል ሴቶች ከሶላተል ጀናዛ ስግደት እንዲታቀቡ መደረጉን መቃወሟ ነው። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ጀናዛውን አስመጥታ መስጂድ በማስገባት የነብዩ ባለቤቶች እንዲሰግዱበት ታደርግ ነበር።

በሁሉም የህይወት መስክ ተሳታፊ አዒሻ ለሴቶች ማኅበራዊ ተሳትፎ አቻ የማይገኝላት ድንቅ ምሳሌ ናት። ምክንያቱም፤ አዒሻ ከነብዩ ሞት በኋላ እንኳ በየትኛውም ኢስላማዊ ሕይወት ውስጥ ከመሳተፍ ወደ ኋላ ብላ አታውቅምና። በነብዩ የሕይወት ዘመን ደግሞ ጦር ሜዳ ድረስ በመሄድ የተሳትፎዋን ጥግ አሳይታለች። በዐሊይ ላይ በተካሄደው ፍልሚያም “የዑስማንን (ረ.ዐ) ገዳዮች ለመበቀል ዐልይ ቸልተኝነት አሳይቷል” በሚለው የተሳሳተ ድምዳሜዋ ምክንያት ዐሊይን ለመውጋት የተሠለፈውን ጦር መርታለች። በኋላ በዚህ አቋሟ ብትጸጸትም ዋናው ጉዳይ ግን ሴት ብትሆንም ሐሳቧን ለማሳካት እስከ ጦርነት ድረስ ለመሄድ እንደማትመለስ ማወቁ ነው። በሷ እይታ ሴት በኢስላም ያላት ሚና ቤት ውስጥ የታጠረ አይደለም። ስትፀፀትም የተጸጸተችው በዐልይ ላይ በያዘችው አቋም እንጂ በነበራት ተሳትፎ አልነበረም። ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጎን ሳይሆን ከእህቶቿ (ከሌሎቹ የነብዩ ባለቤቶች) ጎን በጀነት አል-ባቂ ለመቀበር የመረጠችውም ነብዩን በዐልይ ላይ በነበራት አቋም አፍራቸው ነው። እውቀት በማምረት ረገድ የነበራት ተሳትፎ አዒሻ ተፍሲር፣ ሐዲስ፣ ፊቅሂ እና ታሪክን በመሳሰሉ ኢስላማዊ የዕወቀት ዘርፎች እንዲሁም በዐረብኛ ቋንቋ እና በሕክምና የነበራት እውቀት በሶሃባዎችና በተከታዮቻቸው በሠፊው የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ሌላው ቀርቶ ታላላቆቹ የነብዩ ባልደረቦች አቡበከርና ዑመር እንዲሁም የተቀሩት የነብዩ ባለቤቶች የአንድን ጉዳይ የመጨረሻ ውሳኔ አዒሻን ያማክሯት ነበር።

ከሰባቱ ታላላቅ የመዲና ቃዲዎች መካከል አንዱ የሆነው አቡ ሰለማህ ቢን አብዱራህማን “በሕይወቴ የአዒሻን ያህል ሠፊ የሐዲስ ግንዛቤ፣ ለሙስሊሞች አስፈላጊ በሆኑ አጀንዳዎች ላይም ጥልቅ የፊቅሂ ዕውቀት ያለው እና የቁርኣን አንቀጾችንም መችና ለምን እንደወረዱ አብጠርጥሮ የሚያውቅ በውርስ ህግጋት ላይም የሚወዳደራት ሠው አላየሁም” ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል።

አዒሻ ከአላህ መልክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሞት በኋላ የመምህራን መምህርት (አሰልጣኝ) ሆና አገልግላለች። በነብዩ መስጂድ ውስጥ የሚያስተምሩ ሠዎችንም ሲሳሳቱ ስታይ ታርማለች ጥያቄ ሊጠይቃት የመጣውንም መልስ ትሠጠዋለች። ከሷ ትምህርት ከቀሰሙ ሠዎች ውስጥ ጥቂቶቹ አብደላህ፣ ቃሲም፣ ዑርዋህ እና ዑምራህ ቢንት አብዱራህማን አል-አንሳሪ ይገኙበታል።

ጥልቅ የሆነው የፊቅሂ ዕውቀቷ ብቻዋን ኢጅቲሃድ እንድታደርግ አስችሏታል። አል-ቃሲም እንደዘገበውም ከራሷ ኢጅቲሃድም በመነሳት በአቡበከር፣ በዑመርና በዑስማን ዘመን ከዚያ በኋላም እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ ትምህርቶችን ስትሰጥ ኖራለች።

ከላይ እንደተገለጸውም የአዒሻ ኢጅቲሃድ የተመሠረተው ባላት ጥልቅ የቁርኣን እውቀት ላይ የተመሠረተ ነው። አንድ ሠው ስለአለማግባት ሲጠይቃት “አግባ አላህ ‘በርግጥ ከአንተ በፊት መልክተኞችን ልከናል፤ ለሁሉም ሚስቶችንና ልጆችን ሠጥተናል’ የሚለውን የአላህ ቃል አልሰማህምን? ስለዚህ፤ ከማግባት ረስህ አታቅብ” አለችው።

ኢጅቲሃዷ ከማንምና ከምንም ነጻ መሆኑን የሚያሳየን አንዳንድ ጊዜ እይታዋ ከሌሎቹ ሶሃባዎች እይታ ጋር ቀጥታ የሚቃረን መሆኑ ነው። አንዱ መጣና “አንዲት ሴት ረጅም መንገድ ስትሄድ ሁሌ መህረም (ባል ወይም የቅርብ ዘመድ) ሊከተላት ይገባልን?” ሲል ጠየቃት። እሷም “ሁሉም ሰው ሙህረም ይኖረዋልን?” ስትል መለሠችለት።

ማጠቃለያ

በተለይም፤ የአዒሻ ሕይወት አስደማሚ የሚሆነው የነበረችበትን ዘመን በትኩረት ስናጤን ነው። በዚህ ዘመን የሚኖሩ ሴቶች እንኳ አላህ የሠጣቸውን ችሎታ መጠቀም በማይችሉበት ኹኔታ አዒሻ በ6ተኛውና በ7ኛው ክፍለ ዘመን ያን የመሠለ ሕይወት መምራቷ ልዩ ምሳሌና ፋና ያደርጋታል። ገና ከልጅነቷ አንስቶ በንጹህ እስላማዊ አየር ውስጥ አደገች፤ ሆኖም እስረኛ አልሆነችም። ሐሳቧን በልበ-ሙሉነት ከመግለጽና በማኅበረሠቡ ጉዳዮች ከመሳተፍ የማህበረሰቧም መሪ ከመሆን ያገዳት አንዳችም ነገር አልነበረም። በቀላሉ ለማስቀመጥ አዒሻ ለአላህና ለመልክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) የተሰዋ ክቡር ሕይወትን መርታለች። ይህን አጭር መጣጥፍ በራሷ በእናታችን ንግግር እንዘጋዋለን። ምን አለች? “ሠዎችን ለማስደሰት ብሎ አላህ ያስከፋ አላህ ለሠዎች አሳልፎ ይተወዋል፤ አላህን ለማስደሰት የፈለገ ግን አላህ ይበቃዋል።”