ቅድመ-ታሪክ

ከውክፔዲያ
(ከቅድመ ታሪክ የተዛወረ)
ፋርስ ቅድመ-ታሪክ (ከመዝገቦች በፊት) የተገኘ የእሪያ ሸክላ ቅርጽ

ቅድመ-ታሪክ ማለት ከታሪክ ወይም መዝገቦች ከተጻፉ በፊት ያለፈው ጊዜ ነው።

በአለም ደረጃ መጀመርያው የታወቁት የጽሑፍ ቅርሶች ከ3125 ዓክልበ. ያሕል ሲሆኑ ከጥንታዊ ግብጽ ሥነ ቅርስ ታውቀዋል። ለምሳሌ የመንደሮቹ መኳያ ሰሌዳ እና የጊንጥ ዱላ ከዚህ ዘመን ናቸው። ስለዚህ ከ3125 ዓክልበ. በፊት ያለፈው ሁሉ የአለም «ቅድመ-ታሪክ» ነው። ከ3125 ዓክልበ. በፊት ደግሞ የድንጋይ ዘመን እየሆነ ከዚያ ወቅት ጀምሮ የናስ ዘመን ሆነ።

ከግብጽ ውጭ፣ በሌሎች አገራት የቅድመ-ታሪክ መጨረሻና የታሪክ መጀመርያ የሚወሰንበት ጊዜ መዝገቦች ለመጻፍ የጽሕፈት ችሎታ በዙሪያው እንደ ታወቀ ይለያያል። ለምሳሌ በመስጴጦምያ ዙሪያ ታሪክ በ2400 ዓክልበ. ግድም ይጀምራል፤ ከዚያ በፊትም ቅድመ-ታሪክ ሊባል ይችላል። በአውሮጳ ግን ከሁሉ ቀድሞ ማንበብ የምንችልበት ጽሑፎች በ«ሚውኬናይ ጽሕፈት» ግሪክ አገር ከ1400 ዓክልበ. ግድም ናቸው። በአሜሪካዎችም በሜክሲኮ ዙሪያ ጽሕፈቶች ቢያንስ ከ900 ዓክልበ. ጀምሮ እንደ ታወቁ ቢመስልም፣ ከ300 ዓክልበ. በፊት የሆኑት ቅርሶች ግን ማንበብ ገና አልተቻለም። በአውስትራሊያ1780 ዓም አስቀድሞ ምንም ጽሕፈት ወይም መዝገብ ባለመገኘቱ የአውስትራሊያ ቅድመ-ታሪክ እስከ 1780 ዓም እንግሊዞች እስከ መጡ ድረስ ቆየ ይባላል።

የብሔሮችና የሰዎች ስሞች ሊነበቡባቸው የሚችሉ መዝገቦች ሳይኖሩ ቢሆንም፣ ከሥነ ቅርስ ስለ ቅድመ-ታሪክ ሌሎች መረጆች ሊታወቁ ይቻላል። ለምሳሌ በስሜን አውርስያ እስከ 2000 ዓክልበ. ያሕል ድረስ የድሮ ዝሆን ወይም «ቀንደ መሬት» በአዳኞች እንደ ተገደለ ይታወቃል። በሳይቤሪያ ለሥነ-ቅርስ የታወቀው የማልታ-ቡረት ሥልጣኔ የነዚህን አዳኞች አኗርኗር ይገልጻል።

በስሞችና በተወሰኑ ጊዜ አሀዶች ጉድለት፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ ሃይማኖት ትምህርቶች ወይንም በአፈ ታሪክ ብዛት፣ ብዙ ጊዜ ስለ ቅድመ-ታሪክ በትክክል ምን እንዳለፈ ወይም መቼ በርካታ ተቃራኒ አስተሳስቦች አሉ። አንዳንዴም የቅድመ-ታሪክ መጨረሻ ለመወሰን ይከብዳል። በአይርላንድ ልማዳዊ ታሪክ መጻሕፍት ውስጥ የአይርላንድ ነገሥታት ዝርዝር እና የአይርላንድ ታሪክ ከ2300 ዓክልበ. ጀምሮ ይዘግባል፣ ዳሩ ግን ከ370 ዓም ያህል በፊት ለነበረው ሁሉ ምንም ሌላ ማስረጃ ስላልተገኘ፣ ያው ሁሉ ከ370 ዓም በፊት የአይርላንድ «አፈ ታሪክ» እንዲሁም «ቅድመ-ታሪክ» ተብሏል። ከዚህም በላይ የግሪክ ተጓዥ ፒጤያስ ዘማሢሊያ በ325 ዓክልበ. ግድም አይርላንድን «ኢየርኔ» ሲለው እንደጎበኘው ይታወቃል፤ የአይርላንድ ታሪክ ከነዚህ መዝገቦች ጀምሮ እንደ ተከፈተ ሊከራከር ይቻላል። በቻይናም እንደዚህ ነው፣ የተጻፉት ቅርሶች ከ1200 ዓክልበ. ቢገኙም የታሪክ መዝገቦች ከ2400 ዓክልበ. አካባቢ ጀምሮ ላለፈው «አፈታሪካዊ ዘመን» ብዙ መረጃ ያቀርባሉ።