ተስፋዬ ሳህሉ
ተስፋዬ ሳህሉ (1924 እ.ኤ.አ. ተወልደው) በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ ስመጥርና የተወደዱ ተዋናይና በተለይም የሕፃናትና የልጆች ተረተኛ ናቸው። ፕሮግራማቸው የልጆች ጊዜ ከ1965 እ.ኤ.አ. ጀመሮ ታይቷል። ከዚያ ጀምሮ አባባ ተስፋዬ ተብለው አዲስ ስማቸውን ተቀበሉ። በ1998 ዓ.ም. ከ42 አመታት አገልግሎት በኋላ ከሥራቸው ተለቀቁ። በተወለዱ በ፱፬ አመታቸው ሃምሌ ፪፬ ፪፻፱ ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል። በትዳር ሕይወታቸውም ከባለቤታቸው ደብሪቱ አይታገድ ጋር አንድ ልጅ ያፈሩ ሲሆን አምስት የልጅ ልጆችንም አይተዋል።
አቶ ተስፋዬ ከአባታቸው ኤጀርሳ በዳኔ እና ከእናታቸው ዮንዢ ወርቅ በለጤ ሰኔ ፳፣ ፲፱፻፲፮ ዓ.ም በቀድሞ ባሌ ክፍለ ሃገር ከዶ የተሰኘ አካባቢ ተወለዱ። አምስት ዓመት ሲሞላቸው አባታቸው ወደ ጎባ የተጓዙ ሲሆን ጎባ ላይ ቄስ ትምህርት ቤት ገብተው የትምህርት ጅማሯቸው ተጠነሰሰ። ወላጆቻቸው ለስራ የተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በመዘዋወራቸው አባባ ተስፋዬ በጊኒር ከዛም በሐረርም የፈረንሳዮች ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በ፲፬ አመታቸው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ትምህርታቸውን በኮከበ ፅባህ ትምህርት ቤት መከታተል ጀመሩ።
የአዲስ አበባ መስተዳደር ባህል እና ቲያትር አዳራሽ ማስታወቂያ ካወጣ በኋላ በተዋናይነት ማገልገል የጀመሩት አቶ ተስፋዬ በወቅቱ የሴት ተዋንያኖች ባለመኖራቸው የሴቶችንም ገጸባህሪ ወክለው ይጫወቱ ነበር። ‘ሀ ሁ በስድስት ወር’ ፣ ‘ኤዲፐስ ንጉስ’፣ ‘አሉላ አባነጋ’፣ ‘ዳዊትና ኦርዮን’፣ ‘ኦቴሎ’፣ ‘አስቀያሚዋ ልጃገረድ’ና ‘ስነ ስቅለት’ ተስፋዬ ሳህሉ ከተጫወቷቸው ተውኔቶች ዉስጥ የሚጠቀሱ ሲሆን ‘ብጥልህሳ’፣’ ነው ለካ’ ፣ ‘ጠላ ሻጯ’ በድርሰት ያበረከቷቸው ተውኔቶች ሲሆኑ አራት የተረት መጻሕፍት ለልጆች አድርሰዋል።
በ፲፱፻፶፯ ዓ.ም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲቋቋም የልጆች ጊዜ የተሰኝ ፕሮግራም እንዲኖር ሃሳቡን አቅርቦ በማፀደቅ የራሳቸውን የአቀራረብ መንገድና የፈጠራ ችሎታ በመጠቀም ለመላው የኢትዮጲያ ህዝብ ያስተዋወቃቸውን ዝግጅታቸውን ለ፵፪ ዓመታት በአባትነት ስሜት አቅርበዋል። ለልጆች የሚሆኑ የተዋዙ ተረቶችን፣ ጨዋታዎችን እና አስተማሪ ዝግጅቶችን የሚያቀርቡት አባባ ተስፋዬ ያበረከቱት መተኪያ የሌለው አስተዋጾ ብዙዎች ያነሱታል።
አባባ ተስፋዬ ከ፲ በላይ የሆኑ ሙያዎች ባለቤት የነበሩ ሲሆን ከነዚህም መካከል ተዋናይ፣ ድምጻዊ፣ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋች፣ የውዝዋዜ አሰልጣኝ፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ፣ ደራሲ (የልጆች ተረት)፣ ተረት ተናጋሪ፣ የዜማና ግጥም ደራሲ፣ የምትሃት ባለሙያ ይጠቀሳሉ። በገና፣ መሰንቆ፣ ክራር፣ አኮርዲዮን፣ ትራምፔት፣ ትርምቦን እና ጃስ የሙዚቃ መሳሪያዎችን የሚጫወቱ ሲሆን ከዛም በተጨማሪ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ጣልያንኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋን ተናጋሪ መሆናቸውም ተነግሯል።
አባባ ተስፋዬ በኢትዮጲያ ቴሌቪዢን የልጆች ጊዜ ፕሮግራም ላይ የሚያቀርቡትን ተረት ሲጀምሩ የሚናገሩአት ታዋቂ ንግግር "ደህና ናችሁ ልጆች የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች እንደምን አላችሁ ልጆች። አያችሁ ልጆች የኢትዮጲያ ቴሌቭዥን የልጆች ጊዜ ዝግጅት ክፍል እናንተን ለማስደሰት ልክ በሰአቱ ይገኛል። እናንተስ ዝግጁ ናችሁ? አዎዎ አባባ ተስፋዬ ሸንተረሩን አቋርጠው ዳገቱን ወጥተው ቁልቁለቱን ወርደው በጓሮ በኩል ከተፍ ሲሉ እናንተ ደሞ ቆማችኋል አይደል? አዎዎ በቃ አሁን ተቀመጡ እንዳትጋፉ ታዲያ ትንንሾች ወደፊት ትልልቆች ወደኋላ አዎዎ።"
ጅምር! ይህ አጭር ጽሑፍ መሠረት ወይም መዋቅር ነው። አሁን ሊያስፋፉት ይችላሉ! |