ታምራት ሀይሉ ሀይሌ-Tamerat Hailu Haile

ከውክፔዲያ
Jump to navigation Jump to search

- ታምራት ሀይሉ ሀይሌ-Tamerat Hailu Haile

         ታምራት-- ቁምነገር 
    
    

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸውን ሰዎች ጠቁሙን ፤ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪካቸዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ጥቆማዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ በሚድያ ዘርፍ በተለይም ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች በሚያጋጥምበት የህትመት ስራ ወይም የመጽሄት ህትመት ውስጥ ከ20 አመት በላይ የዘለቀው ታምራት ሀይሉ ሀይሌ / ታምራት ቁምነገር/ ቁምነገር መጽሄትን 20 አመት ያለማቋረጥ ያሳተመ ነው፡፡ ብዙዎችን ቃለ-መጠይቅ ያደረገው ታምራት ማነው? በምን መንገዶች አልፎ እዚህ ደረሰ?

            ጅማሬ

‹ታላቅ ወንድሜ ብርሃኑ ኃይሉ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ከሚሰራበት መስሪያ ቤት አዲስ ዘመን ጋዜጣን ወርሃዊ ደንበኛ በመሆን በየዕለቱ ይዞ ይመጣ ነበር፡፡ በየዕለቱ የሚመጣውን ጋዜጣ ከዳር እስከ ዳር በማንበብ የሥነ- ጽሑፍ ዝንባሌዬን እያሳደግሁ መጣሁ› ይላል ጋዜጠኛ ታምራት ኃይሉ አሁን ስላለበት ሙያው ጅማሬ ሲያስታውስ፡፡

           ትውልድና እድገት
      

ታምራት ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ በተለምዶ 22 ማዞሪያ በሚባለው አካባቢ ነው፡፡ለቤቱ የመጨረሻ ልጅ ሲሆን 4 ወንድሞችና 3 እህቶችም አሉት፡፡ እናቱ ወ/ሮ በለጡ ሄይ፤ አባቱ አቶ ኃይሉ ኃይሌ ይባላሉ፤ የጥረት፤የፅናትና የፍቅር ተምሳሌቶች ናቸው ጥንዶቹ፤ ታምራት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን የተማረው መገናኛ አካባቢ በሚገኘው ምስራቅ በር ሲሆን የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በምስራቅ አጠቃላይ ተምሯል፡፡

     ‹‹…..ጉቶ ላይ በጉልበቴ ወደቅሁ ››

ታምራት አንደኛ ክፍል እስኪገባ ደረስ ስሙ ታምራት አልነበረም፤በየጊዜው የሚያጋጥመውን ህመም መነሻ በማድረግ የሰፈሩ ሰዎች ‹ተረፈ› ብለው ነበር የሚጠሩት ፤ ‹እናቴ እንደነገረችኝ ከሆነ› ይላል ታምራት ‹ገና ከ3 ዓመቴ ጀምሮ ህመም የማያጣኝ ሰበበኛ ልጅ ነበርኩ፤ በሶስተኛ ዓመቴ ቤት ውሰጥ ድክ ድክ ስል ከከሰል ላይ ወጥቶ መሬት የተቀመጠ የብረት ድስት ወጥ ላይ ሄጄ ተቀመጥኩበት፤ በስንት የህክምና እርዳታ ባገገምኩ በዓመቱ ግቢ ውስጥ ያለ ዛፍ ላይ ዥዋዥዌ እጫወታለሁ ብዬ ስወዛወዝ ገመዱ ተበጥሶ ጉቶ ላይ በጉልበቴ ወደቅሁ፤እግሬ አበጠ፤ እንደገና ወደ ሀኪም ቤት፤ ብዙም ሳልቆይ በፀና ታምሜ ሆስፒታል ገባሁ፤ በዚህ ህመም ግን እንደበፊቱ ቶሎ ድኜ ወደቤት መግባት አልቻልኩም፤የመዳኔ ነገር ተስፋ አስቆራጭ ከመሆኑ የተነሳ የሰፈሩ ሰዎች የእድር እቃዎቻቸውን ማዘገጃጀት ጀመሩ፤በየዕለቱ ጠዋት ጠዋት ከወደ ሆስፒታል የሚመጣ የመርዶ ዜና መጠባበቅ ጀመሩ፤ ‹ተረፈ ግን ተርፎ ቤት ገባ፤› ይላል ታምራት የኋላ ታሪኩን በማስታወስ፡፡

           3ኛ ክፍል
       

ሰፈር ውስጥ ይማርበት ከነበረው የ‹ዘውዱ ቄስ ትምህርት ቤት› ወደ መደበኛ የመንግስት ትምህርት ቤት አንደኛ ክፍል ሲገባ ስሙን ከተረፈነት ወደ ታምራትነት ተቀየረ፤ ያም ሆኖ የተረፈ መንፈስ ብዙም አልራቀውም ነበርና 3ኛ ክፍል እንደገባ እናቱ ከሚያረቧቸው ከብቶች መሀከል አንዷን ጊደር ከታላቅ ወንድሙ ጋር ሰውነቷን ለማጠብ አንገቷ ላይ የታሰረውን የፕላስቲክ ገመድ ወገቡ ላይ አስሮ ወደ ቧንቧ ለመውሰድ ሲጎትታት ደንብራ ከቤታቸው ጀርባ ባለው የጓሮ በር ወጥታ ወደ ሜዳ ስትሸመጥጥ ታምራትን እንደ ፈረስ ጋሪ እየጎተትች ወስዳ አውራ መንገድ ላይ በሰዎች ጩኸት እንድትቆም ይደረጋል፤ ህይወቱን ለማትረፍ አንጀቱን ሰርስሮ የገባውን የፕላስቲክ ገመድ ከሆዱ ላይ በቢላ መበጠስ ነበረባቸው፤

‹ጊደሯ በሰዎች እርዳታ ተይዛ ገመዱ ቶሎ ባይቆረጥ ኖሮ ገመዱ አንጀትህን ለመበጠስ ጥቂት ጊዜ ብቻ ነበር የቀረው › ብላኛለች እናቴ የሚለው ታምራት፤ ‹ከዚህ ዕድሜዬ በኋላ ግን ወደ ሆስፒታል የሚወስድ ባስ ያለ ህመም አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡›ይላል፡፡ 

           የስነ- ፅሑፍ ጅማሬ

ታምራት የ9ኛ ክፍል ተማሪ እያለ በኢትዮጵያ ራዲዮ ዘወትር ቅዳሜ ጠዋት ይቀርብ በነበረው ‹ከልጆች ዓለም› በተሰኘው ፕሮግራም ላይ መሳተፍ ጀመረ፡፡ በወቅቱ ከፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ ጋሽ ሰለሞን ገ/ስላሴ ጋር ያገናኘችው አርቲስት እመቤት ወ/ገብርኤል ናት፤ እመቤት እና ታምራት ጎረቤታሞች ብቻ ሳይሆኑ አብሮ አደጎች ናቸው፡፡ እመቤት ቀደም ብላ ከልጆች ዓለም ፕሮግራም ላይ ትሰራ ስለነበር ወንድ አቅራቢ ሲፈለግ ታምራትን ጠቆመች፤ ከትምህርት ቤት መልስ ታምራትና እመቤት ዘወትር ሀሙስ ከሰዓት በኋላ ባንቢስ አካባቢ ይገኝ ወደነበረው የቀድሞው ብስራተ- ወንጌል ራዲዮ ጣቢያ በማምራት ከእነ አስካለ ተስፋዬና ቅድስት በላይ ጋር ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን አቅርበዋል፡፡

     ‹አስጀምሮ ላስጨረሰኝ ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ይግባው!›
   

ታምራት ከ 12 ዓመቱ ጀምሮ ከጋዜጦችም ይሁን ከመፅሄቶች፤ ከመፅሐፍትም ይሁን ከማናቸውም የመረጃ ምንጮች ሲያነብ ያገኘውን ማናቸውም ስሜት ነኪ ግጥሞች፤አባባሎች፤ጥቅሶች፤ጠቅላላ እውቀት፤ የሰዎች ንግግሮች፤ድንቃ ድንቅ ሁነቶች፤ቀልዶችና ታሪካዊ ክስተቶች ወዘተ በቸልታ አያልፋቸውም፡፡ በእዚያ እድሜው ለዚሁ ዓላማ ብሎ ባዘጋጀው የማስታወሻ ደብተሩ ላይ ከእነ ምንጩ መዝግቦ ይይዛል፡፡ከእያንዳንዱ ፅሑፍ ግርጌ ‹አስጀምሮ ላስጨረሰኝ ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ይግባው!› ከሚል ጥቅስና ፊርማ ጋር፤ይህቺ ታሪካዊ የማስታወሻ ደብተር የትምህርት ቤቱ ምስራቅ አጠቃላይ የሚኒ ሚዲያ ሲከፈት ብዙ ተጠቅሞበታል፡፡በተለይም በእረፍት ሰዓት በሚኒ ሚዲያ ለተማሪዎች መረጃዎችን ለማቅረብ ሌሎች ተማሪዎች የሚነበብ ነገር ፍለጋ ወደ ቤተ- መፅሐፍት ሲያመሩ ታምራት ማስታወሻ ደብተሩን በመክፈት ብቻ የመረጃ ‹በየአይነቱን › ያቀርብ ነበር፡፡ ማስታወሻ ደብተሩ በቅርቡ 30ኛ ዓመቷን ደፍና ራሷን ወደ ቅርስነት መለወጧን በኩራት ይናገራል፡፡


         30 እና 40 ብር 
       

12ኛ መልቀቂያ ፈተና እንደወሰደ በክልል 14 ባህልና ስፖርት ቢሮ ስር ለወጣት አማተር የስነ-ፅሑፍ አፍቃሪያን የሚሰጠውን ስልጠና ለመከታተል በሳምንት ለ3 ቀናት ከ22 ማዞሪያ አምስት ኪሎ የሚገኘው ባህልና ስፖርት ቢሮ በእግሩ መመላለስ ነበረበት፡፡ ይህም ከተለያዩ ፀሐፍትና ታዋቂ ሰዎች ጋር ለመገናኘት ዕድል ፈጥሮለታል፡፡ በወቅቱ የግሉ ፕሬስ ጋዜጦች ያበቡበት ወቅት ስለ ነበር የመፃፍ ፍላጎቱ ላለው እንደ ታምራት ላሉት ወጣቶች ጥሩ መድረክ ነበር፡፡ እናም አንዳንድ ፅሑፎችን እየጻፈ በወቅቱ ለነበሩ የግል ጋዜጦች መስጠት ጀመረ፡፡ መብረቅ፤ ሰይፈ ነበልባል፤ ዋኖስ፤ቤዛ፤ ሞገድ፤አዲስ ድምፅ፤ አንደበት፤አቢሲኒያ፤አፍሪካ ቀንድ፤ አሌፍ ወዘተ እጁን ያፍታታባቸው ጋዜጦችና መፅሔቶች ነበሩ፡፡አንዳንድ የጋዜጣ አዘጋጆች የታምራትን ፅሑፍ እየተቀበሉ አትመው ‹ ዝም› ቢሉትም ሌሎች ጋዜጦች ግን ለታክሲም ቢሆን በማለት 30 እና 40 ብር ይሰጡት ነበር፡፡ እየቆየ ሲሄድ ግን በጋዜጣ ላይ የሚወጡት ፅሑፎች ይዘት የሚወሰነው በፀሐፊው ስሜት ሳይሆን በአንባቢው ፍላጎት ላይ እየተመሰረተ መጣ፤ በጋዜጣ ላይ የሚወጡት ጽሑፎች ገበያ ተኮር በመሆናቸው መንግስትን የሚተቹ አለፍ ሲልም እንዲቆጣ፤ ጦር እንዲሰብቅና ሀር እንዲነቀንቅ የሚጋብዙ እንዲሆኑ ይፈለግ ነበር፤ገበያውን እየተከተለ መፃፍ ለታምራት አልሆንለት ሲለው ፊቱን ወደ መንግስት ጋዜጦች አዞረ፡፡ የመንግስት ጋዜጦች አዲስ ዘመን፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣና አዲስ ልሳን ጋዜጦች ምንም እንኳን የፖለቲካ ፅሑፍ ተቀብለው የሚያወጡ ባይሆኑም በማህበራዊ ጉዳይ ላይ ለሚፅፍላቸው ሰው በራቸው ክፍት ነበር፡፡ እናም በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በመፃፍ ብዙ ልምድ አገኘ፤ ለፅሑፎቹ ምንም ክፍያ ባያገኝም ዛሬ ላለበት ደረጃ መሠረት የሆነውን ስለ ጋዜጠኝነት ሙያ ሀሰሳ እውቀት ማካበቱን ይናገራል፡፡

       የስራ ዓለም ሀ
       

ታምራት፣ በ1988 መጨረሻ የአዲስ አበባ መስተዳደር ባህልና ማስታወቂያ ቢሮን በመቀላቀል በአዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ በባህልና ጥበብ አምድ አዘጋጅነት ተቀጠረ፡፡በወቅቱ የጋዜጣው ባልደረባ የነበረችው ጋዜጠኛ አለም ፀሐይ ደሳለኝ ‹እፎይታ › ጋዜጣ ላይ በተሻለ ደሞዝ ስትቀጠር ጋዜጣው የእርሷን ቦታ ለመሙላት ላወጣው ማስታወቂያ ከታምራት የቀረበ ብቻ ሳይሆን የተሻለ ሪፖርተር አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ታምራት ምንም ክፍያ ሳያገኝ በሳምንት ሁለት ቀናት ማለትም ረቡዕ እና ቅዳሜ በሚወጣው አዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ ያለመታከት ይፅፍ ነበርና ‹ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያ እስኪወጣ ተጠባበቅ› ተብሎ ስለነበር ለውድድር ሲቀርብ ‹ማነህ እስኪ ራስህን አስተዋውቅ› አልተባለም፡፡ ሳይከፈለው ለዓመታት ይፅፍበት በነበረው ጋዜጣ ላይ አሁን ተቀጣሪ ጋዜጠኛ ሆነ፡፡ ከእነ ጋዜጠኛ አለምሰገድ ዘውዴ፤ ታየች ኦርጌቾ፤ በትሩ ላቀው፤ ተስፋዬ መክብብ፤ለጋወርቅ አስፋው፤ሳሙኤል ፍቅሬ፤ ሲሳይ ወርቅነህ፤ ባሲጥ አብዱል ከሪም፤እያደር አዲስ፤ ለምለም በቀለ፤ ይልማ ደምሰው ወዘተ ጋር ተቀላቀለ፡፡አዲስ ልሳን ጋዜጣ የአዲስ ከተማ አስተዳደር ልሳን እንደመሆኗ መጠን በመዲናይቱ ይደረጉ የነበሩ አበይት ክንውኖች በጋዜጣዋ ይዘገቡ ነበር፡፡ ታምራትም በመዲናይቱ የሚደረጉ የጥበብ ጉዳዮችን በወጉ በመዘገብ ለጋዜጣዋ ተነባቢነት ትልቅ ሚና አበርክቷል፡፡ በተለይም በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት እና በከተማ መስተዳድሩ ስር ባሉ የጥበብ ማዕከላት የሚደረጉ የኪነ-ጥበብ ዝግጅቶች ላይ በመታደም ታምራት ዝግጅቶቹ የከተማዋ መነጋገሪያ አጀንዳ እንዲሆኑ ተገቢውን ሽፋን ይሰጥ ነበር፡፡ በጊዜው በአዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ በዋና አዘጋጅነት ትሰራ የነበረችው አንጋፋዋ ጋዜጠኛ ታየች ኡርጌቾ እንደምትናገረው ‹ታምራት ስራውን ጥንቅቅ አድርጎ የሚሰራ ታታሪ እና በጥሩ ስነ-ምግባር የታነጸ ›ስትል ትገልጸዋለች፡፡ ታምራትም የሚዲያ ቋንቋ አጠቃቀምንና የአርትኦት ስራን ምንነት የተማርኩት ከስነ- ልሳን ባለሙያዋ ታየች ኦርጌቾ ብዕር ስር ‹ኩስ ኩስ › እያልኩ ነው በማለት ይመሰክራል፡፡

ታምራት በአዲስ ልሳን ጋዜጣ ቆይታው ገና 2 ዓመት ሳይሞላው ለሀላፊነት መታጨቱ የሚገርም አልነበረም፡፡ የከተማ መስተዳድሩ ከጋዜጣ ህትመቱ በተጨማሪ የራሱን የራዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ለመጀመር ኮሚቴ ሲዋቀር ታታሪው ጋዜጠኛ ታምራት አባል ተደረገ፡፡፡ በወቅቱ ታምራት የባህልና ጥበብ አምድ አዘጋጅ ሲሆን የባህልና ማስታወቂያ ቢሮ ሃላፊው አቶ ሰለሞን አበበ ነበሩ፡፡ የፕሬስ መምሪያ ሃላፊው ደግሞ አቶ አለምሰገድ ዘውዴ፡፡ ታዲያ ታምራት በወቅቱ ምንም እንኳን ገና 20ዎቹ መጀመሪያ ላይ ጋዜጠኛ ቢሆንም እንደ አምድ አዘጋጅ ብቻ ሳይሆን በምክትል አዘጋጅ ደረጃ የጋዜጣውን ስራ እየተቆጣጠረ ከሃላፊዎች ጋር የኤዲቶሪያል ኮሚቴ አባል ሆኖ ሀሳብ ያዋጣ ነበር፡፡ በዚህም በወቅቱ ከነበሩ ወጣት የሚዲያ ባለሙያዎች የተሻለ የመምራት ብቃትና ስነ-ምግባር የተላበሰ መሆኑ አብረውት በሰሩ ሰዎች ሳይቀር ይመሰከር ነበር፡፡ አዲስ ከገቡትም ሆነ ከነባር ባልደረቦቹ ጋር በቀላሉ በመግባባት የሚታወቀው ታምራት ስራን በጊዜ ከማድረስ ባለፈ ሌሎች ጋዜጠኞችን በማስተባበርና በመምከር ጥሩ ሰብእና የተላበ ሰው እንደሆነ በስፋት ይነገርለታል፡፡ ታምራት ከ1988-1992 ባሉት 4 አመታት በአዲስ ልሳን በሰራበት ጊዜ ብዙ እውቀት መቅሰሙን ይናገራል፡፡ በተለይ የመንግስት ቤት ውስጥ ሃላፊነትን ተረክቦ መስራትን በእድሜ ታላላቆቹ ከሆኑ ሰዎች ጋር መስራቱ ዛሬ ቆም ብሎ ሲያስበው ብዙ እውቀት እንዲቀስም አድርጎታል፡፡

        እለታዊ አዲስ ጋዜጣ

ታምራት በ1992 ሰኔ ወር የመጀመሪያ የግል እለታዊ ጋዜጣ ሲመሰረት የ4 አመት የአዲስ ልሳን ቆይታው በዚሁ አብቅቶ በተሻለ ደሞዝ እለታዊ አዲስ ጋዜጣን በረዳት አዘጋጅነት መደብ ተቀላቀለ፡፡ እለታዊ አዲስ ጋዜጣ ሰኞን ጨምሮ በየእለቱ ይወጣ የነበረ በዶክተር ፍስሀ እሸቱ የተመሰረተ ጋዜጣ ሲሆን ያኔ ዶክተር ፍሰሀ እሸቱ የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ባለቤት ነበሩ፡፡ በወቅቱ ጋዜጣው ከፍተኛ ደሞዝ እከፍላለሁ በሚል ከልዩ ልዩ ሚዲያዎች ከ60 በላይ ጋዜጠኞችን ሲቀጥር ያኔ አዲስ ልሳንን ለቀው ዕለታዊ አዲስ ከገቡ 6 ጋዜጠኞች መካከል ታምራት ሀይሉ አንዱ ነበር፡፡

ለታምራት ትልቅ የጥንካሬ መሰረት የሆነው ቤት እለታዊ አዲስ መሆኑ ራሱም የሚመሰክረው ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ዜናም ሆነ ፊቸር የሚሰራው በየቀኑ ነው፡፡ ስለዚህ ታምራት ደግሞ ሃላፊ ሆኖ ስለሆነ የተቀጠረው በአንድ በኩል የጋዜጣውን አምድ ጥራት እያስጠበቀ በሌላ ደግሞ ከስሩ ያሉ ሰዎችን እየመራና እያሰራ የሚወደውን ስራ ደስ ብሎት ሲሰራ እንደነበር ይናገራል፡፡ በጊዜው የጋዜጣው ዋና እና ምክትል አዘጋጆች የነበሩት ሰሎሞን አባተና ደረጀ ደስታ በወቅቱ እለታዊ አዲስ የተቀጠሩ ጋዜጠኞችን ብቁ ለማድረግ የተቻላቸውን አድርገዋል፡፡ ታምራትም ልክ እንደ አዲስ ልሳን ሁሉ በጋዜጣው ምክትል ዋና አዘጋጅና የቅርብ አለቃው ጌታቸው ማንጉዳይ ስር ሆኖ የጥበብና ባህል ዲፓርትመትን የስራ መሪነቱን በከፍተኛ ሀላፊነት ተወጥቷል፡:

            ዘ ፕሬስ ጋዜጣ
     
እለታዊ አዲስ ጋዜጣ በየዕለቱ ስትታተም ቆይታ በስምንተኛው ወር ላይ በኮሌጁ ባለቤት በ‹ኪሳራ› ምክንያት ስትቋረጥ እንደ አንድ ቤተሰብ ይተያዩ የነበሩት የጋዜጣው ባልደረቦች ተበተኑ፡፡ አንዳንዶች ቀደም ሲል ይሰሩበት ወደነበረው ሚዲያ ተመልሰው ሲገቡ፤ ሌሎች ሀገር ጥለው ተሰደዱ፡፡ ጥቂቶች ፊታቸውን ወደ ሌላ የስራ መስክ አዞሩ፡፡ ሌሎች የራሳቸውን ጋዜጣ በመመስረት አማራጭ ሚዲያ ለመሆን ሲሞክሩ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ የነበሩት የዛሬዎቹ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ጋዜጠኞች ሰሎሞን አባተና ደረጀ ደስታ ‹ዘ ፕሬስ› የተባለ ጋዜጣ ሲመሰርቱ ታምራት የጋዜጣው ምክትል ዋና አዘጋጅ ሆኖ ስራ ጀመረ፡፡

በወቅቱ ዘ ፕሬስ ጋዜጣ በተለይ በ1993-1995 ከፍተኛ ተነባቢነት ከነበራቸው የህትመት ውጤቶች መካከል አንዷ የነበረች ሲሆን ያኔ ዘፕሬስ ይሰሩ ከነበሩት ጋዜጠኞች መካከል ሕብረት ሀረገወይን፤ ኤርሚያስ ስዩም ፤ኤልሳቤጥ እቁባይ፤ ራሄል አዳነ እና አለማየሁ ገበየሁ ይጠቀሳሉ፡፡

             ጉዞ ወደ ቁም ነገር
      

ታምራት ከበፊት ጀምሮ የራሱን ስራ መስራት ምኞት ነበረው፡፡ ይህን ምኞቱንም ገና ማዘጋጃ ቤት ሳለ ይናገረው ነበር፡፡ የራስን መጽሄት ወይም ጋዜጣ ከፍቶ መስራት ትልቅ ህልሙ ነበር፡፡ ይህን ህልሙን ለማሳካት የፊታችን መስከረም 20ኛ ዓመቷን የምትደፍነውን ‹ቁም ነገር› መጽሄትን ማሳተም የጀመረው እዛው ዘ ፕሬስ ጋዜጣ ላይ ሆኖ ነበር ከሙያ ጓደኞቹ ራሔል አዳነ እና ኃይለገብርኤል ይመር ጋር፡፡ ፡፡ ቁምነገር መጽሄት በኢትዮጵያ የህትመት ታሪክ ለተከታታይ 19 አመት አንድም ጊዜ ሳትቋረጥ የዘለቀች መጽሄት ናት፡፡ መጽሄቷ በጥበብ እና በማህበራዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት በማድረግ ስትታተም የቆየች ስትሆን ለብዙዎች ፀሐፍት ከአንባቢያን ጋር መገናኛ መድረክ ሆና አገልግላለች፡፡

ታምራት ባለፉት 20 ዓመታት ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንቶች ፤ጠቅላይ ሚኒስትሮች፤ከፍተኛ መንግስት ባለስልጣናት፤ አርቲስቶች፤ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን ጀምሮ እስከ ጉሊት ነጋዴዎችና ጎዳና ተዳዳሪዎችን ጠይቋል፡፡ማንም የቁም ነገር መፅሄት አንባቢ የሆነ ሰው ወደ ኋላ መለስ ብሎ የቁም ነገር መፅሔቶችን ቢያገላብጥ ከፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ እስከ ፕሬዚዳንት ነጋሶ ገዳዳ፤ ከፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፤ ከኃይለማርያም ደሳለኝ እስከ ዶ/ር አብይ አህመድ የቀረቡ ጥያቄዎችን ማግኘት ይችላል፡፡ከአንጋፋው ጥላሁን ገሠሠ እስከ መሀሙድ አህመድ፤ ከአለማየሁ እሸቴ እስከ ማሪቱ ለገሰ፤ ከሙሉቀን መለሰ እስከ ኤፍሬም ታምሩ፤ ከንዋይ ደበበ እስከ ፀሐዬ ዮሐንስ፤ ከቴዲ አፍሮ እስከ ዘሪቱ ከበደ፤ ከጎሳዬ ተስፋዬ እስከ ማዲንጎ አፈወርቅ፤ ወዘተ ከኮሜዲያን ልመንህ ታደሰ እስከ አለባቸው ተካ ከደረጀና ሀብቴ እስከ ክበበው ገዳ፤ ከእንግዳዘር ነጋ እስከ ጥላሁን እልፍነህ ወዘተ ከአትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ እስከ ደራርቱ ቱሉ፤ ከቀነኒሳ በቀለ እስከ ጥሩነሽ ዲባባ፤ከወርቅነሸ ኪዳኔ እስከ ገብረ እግዚአብሔር ገ/ማርያም ወዘተ ከአሰልጣኝ ስዩም አባተ እስከ ካሳሁን ተካ፤ከሰውነት ቢሻው እስከ አስራት ሀይሌ፤ ከካሳዬ አራጌ እስከ መሠረት ማኔ ወዘተ ከመድረክ ተዋንያን ከፍቃዱ ተ/ማርያም እስከ ሽመልስ አበራ፤ ከፍቅርተ ጌታሁን እስከ ወለላ አሰፋ፤ ከአለማየሁ ታደሰ እስከ ጀማነሽ ሰለሞን፤ ከአዳነቸ ወ/ገብርኤል እስከ ሀረገወይን አሰፋ ወዘተ ከጋዜጠኞች ከአለምነህ ዋሴ እስከ ሳምሶን ማሞ፤ ከዳግማዊ ታሪኩ እስከ ሳሙኤል ፍቅሬ፤ ከበላይ በቀለ እስከ ሃይለራጉኤል ታደሰ ከትዕግስት በጋሻው እስከ እፀገነት ላቀ ወዘተ፤ ኳስ ተጫዋቾች፤ የህክምና ባለሙያዎች፤ መምህራን፤ የፈጠራ ባለሙያዎች፤ሞዴሎች፤ ወዘተ ቁም ነገር መፅሔት ታሪካቸውን ዘግባ ለታሪክ ካኖረቻቸው ኢትዮጵያውያን ሲቪል ጀግኖች ጀርባ ታምራት አለ፡፡

ባለፉት 20 ዓመታትም በመፅሔቱ ላይ ከ1000 በላይ እንግዶች ሀሳባቸውን እንዲያካፍሉ ሲደረግ ከ450 በላይ አንጋፋና ወጣት ደራሲያንና ጋዜጠኞች የብዕር ትሩፋታቸውን እንዲያቀርቡ ዕድል ፈጥሯል፡፡ በቁም ነገር መፅሔት ላይ ተከታታይ ፅሑፎቻቸውን በማቅረብ በዓመቱ ሰብስበው ወደ መፅሀፍት ጥራዝ እንዲቀይሩ ታምራት ብዙዎችን አግዟል፡፡ አበረታቷልም፡፡ እንደአብነትም ኮሜዲያን ደረጀ ሀይሌ፤ታገል ሰይፉ፤ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ፤ ደረጀ በላይነህ፤ ኃይለጊዮርጊስ ማሞ ጲላጦስ/ ዘላለም ጌታቸው/ዶክተር/ እመቤት ስጦታው፤አቦነህ አሻግሬ/ተባባሪ ፕሮፌሰር/መኩሪያ መካሻ/ተባባሪ ፕሮፌሰር/ ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡

ታምራት ቁም ነገር መጽሄትን ማሳተም ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍሎ ይሰራ ነበር፡፡ በጊዜው የመጽሄቶች የማከፋፈልና የመሸጥ ስራ ፈታኝ በነበረበት ጊዜ ቁም ነገርን ገበያ ውስጥ እንድትገባ ማድረግ ቀላል አልነበረም፡፡ ለታምራት ግን ተችሎ ነበር፡፡ በተለይ በርካታ የኪነ-ጥበብ ሰዎችን በማስተዋወቅ ቁምነገር ሚናዋን ትወጣ ዘንድ ታምራት የተጫወተው ሚና በቀላሉ የሚነገር አልነበረም፡፡ አዳዲስ መፅሐፍት፤ፊልሞችና ቴአትር ለህዝብ ሲቀርቡ ቁም ነገር መፅሔት በነፃ በማስተዋወቅ በኩል ቀዳሚ ናት ፡፡በበጎ አድራጎት ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን አፈላልጎ በመፅሔቱ ላይ በማውጣትና በነፃ በማስተዋወቅ ማህበረሰቡ ለበጎ ፈቃደኝነት ስራ ትኩረት እንዲሰጥ የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ሜሪ ጆይ፤ስለ እናት፤መቄዶኒያ፤ጌሪጌሴኖን፤ሙዳይ፤ወዘተ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

20ኛ ዓመቷን ለመድፈን እየተንደረደረች ያለችው ቁም ነገር መፅሔት የመዝናኛ እንደመሆኗ መጠን በመጀመሪያዎቹ 4- 5 ዓመታት ቃለ-መጠይቅ ከሚደረግላቸው ሰዎች ጋር አብሮ የሚወጣው የካርቱን ምስል ዛሬ ድረስ በአንባቢያን ዘንድ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በጊዜው እነዚህን ካርቱን ስእሎች በመሳል ሚና የነበራቸውን ሰአሊዎች ሮማን ታደሰን እና ብርቱካን ደጀኔን ዕድል በመስጠት ሙያው ከስነ- ፅሁፉ ጋር ተቆራኝቶ እንዲታይ በር ከፍቷል፡፡ ታምራት ቁምነገርን በሚሰራበት ጊዜ በአንድ በኩል የድርጅቱ መስራች እና ባለቤት ነው፡፡ በሌላ ጎኑ እንደ ጋዜጠኛ ባለሙያዎችን ቃለ-መጠይቅ ያደርጋል፡፡ ርዕሰ -አንቀፅ ይፅፋል፤ በተለይም የቁም ነገር መፅሔት መለያ ከሆኑ ዓምዶች መሀከል ላለፉት ሃያ ዓመታት ሳይታክት የጻፈው ርዕሰ- አንቀፅ ማህበረሰብን የሚያነቃ፤ መንግስትን የሚሸነቁጥና የኪነ- ጥበብ ቤተሰቦች ራሳቸውና ሙያቸውን አሻግረው እንዲያዩ የሚጋብዙ ሲሆኑ ከዘፈን ግጥም ጋር ተሰናስለው የሚፃፉ ናቸው፡፡ መፅሔቷ በኪነ-ጥበብና በማህበራዊ ህይወት ውስጥ ያደረገችውን አስተዋጽኦ የተመለከቱ ከ20 በላይ የተማሪዎች የመመረቂያ ፅሑፎች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በሌሎች ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል እንዲሁም በቋንቋና ስነ ፅሑፍ ተማሪዎች ዘንድ ጥናት እንደተሰሩበት የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች ተረድተዋል፡፡


       '     ፋሽን መፅሔት 

ታምራት ቁም ነገርን ማሳተም ከጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላም በገበያው ላይ ያለውን ክፍተት በመረዳት በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነችውን ፋሽን የተባለች መጽሄት ማሳተም ጀመረ፡፡ በወር አንድ ጊዜ መፅሔት በሚወጣበት ሀገር በወር ሁለት መፅሄቶች በግሉ አዘጋጅቶ ማውጣቱ ሰፊ አንባቢና ተቀባይነትን እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡ በወቅቱ አዲስ የፕሬስ ህግ መውጣት ምክንያት አንድ ሰው ሁለት የህትመት ውጤት እንዳይኖረው የሚደነግገው አዋጅ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ፋሽን መፅሄትን ለ10 ዓመታት ያህል አሳትሟታል፡፡ ፋሽን መጽሄት በውበት ኢንዱስትሪው ላይ ያበረከተችው ሚና ትልቅ እንደነበር ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡ በተለይ የተለያዩ የውበት ባለሙያዎች እውቀትና ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ፋሽን ጥሩ መድረክ ፈጥራ ነበር፡፡ ይህ የፋሽን መጽሄት ሚና ግምት ውስጥ ገብቶ ከኔክስት ዲዛይን ኮሌጅ ታምራት ሽልማትና እውቅና ሊያገኝ ችሏል፡፡ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ታምራት ሁለቱን መፅሔቶቸች እያሳተመ ፋርሚድ በሚባለው የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች አስመጪ በሆነው የመንግስት የልማት ድርጅት ውስጥ በህዝብ ግንኙነት ሀላፊነት ሰርቷል፡፡በዚህ ቆይታውም ‹ዜና ፋርሚድ› የተሰኘች መፅሔትን ያዘጋጅ ነበር፡፡

ታምራት እርሱ ጋር ተቀጥረው የሚሰሩ ሰዎች የራሳቸውን ስራ እንዲፈጥሩም ይመክር ነበር፡፡ በ1995 -1996 የቁምነገር መጽሄት እና የፋሽን ምክትል ዋና አዘጋጅ የነበረው እዝራ እጅጉ ተወዳጅ ሚድያን እንዲመሰርት ሀሳቡን ያፈለቀው እና ያበረታታው ታምራት ነበር፡፡ የመጀመሪያዋ የተወዳጅ ጋዜጣ የንድፍና የጽህፈት ስራ የተከናወነው በቁምነገር መጽሄት ውስጥ ነበር፡፡ በኋላም ተወዳጅ ሚድያ አድጎ ታሪክን በሲዲ የተሰኘውን ፕሮጀክት ነድፎ ከ40 በላይ ታሪኮች በሲዲ ለማሳተም የቻለ ድርጅት ሆኗል፡፡ ታምራት በማንኛውም ሰአት የተወዳጅ ሚድያን ፕሮጀክቶች በሙሉ እምነት በመደገፍ እስከዛሬ ዘልቋል፡፡

‹‹ታምራት እጅግ ልዩ የሚዲያ ሰው ነው፡፡ ከማንም ጋር መሥራት የሚያስችል ጸባይ አለው፡፡ ካጠፋህ ወይም በእርሱ ፍጥነት ካልሄድክ ሥራህን ቀድሞ ይሸፍንና ጥፋትህን ሌላ ጊዜ ይነግርሃል፡፡ በቀላሉ አቅምህን የመረዳት ችሎታም አለው፡፡› ይላል ለ4 ዓመታት ያህል አብሮት የሰራው ጋዜጠኛ ሳምሶን አብደላ፤ ‹‹የእርሱን ያህል ሚዲያ የሚከታተል ሰው አላውቅም፡፡ ለመረጃ እጅግ ቅርብ ስለሆነ የሐሳብ ሀብታም ነው፡፡ለኤዲቶሪያል ስብሰባ ስንቀመጥ ስለሁሉም ነገር አቅጣጫ መስጠት ይችላል፤ የስፖርቱን፣ የኪነ- ጥበቡን፣ የፖለቲካውን፣የጤናውን ፤ የሚዲያውን፣ የንግዱን ዓለም ሰዎች ጠንቅቆ ያውቃቸዋል፡፡ ›› ሲል ይመሰክራል፡፡

ታምራት ላለፉት አመታት ቁምነገርን ሲመራ በመጀመሪያ መጽሄቷ ወርሀዊ የነበረች ሲሆን ከዚያም በየ15 ቀኑ አሁን ደግሞ ወደ ሳምንታዊ ተሸጋግራለች፡፡የህትመት ስራ አታካችነትና የንባብ ባህል ደካማነት በሀገራችን የሚታይ እውነታ ቢሆንም ‹በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ የምወደውን ስራ እሰራለሁ› በሚል ታምራት አሁንም በሀሴት ተሞልቶ ስራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ታምራት በቁም ነገር መፅሔትም ሆነ በፋሽን መፅሔቶች ላይ የፃፋቸውን በርካታ ፅሑፎች ወደ መጻሕፍትነት ለመቀየር ተጠቀርዘው የተቀመጡ ቅፆች አሉት፡፡ ወደተለያዩ ሀገራት ጉዞ ሲያደርግ የተመለከተውን ከ12 በላይ ሀገራትን የጉዞ ማስታወሻ አዘጋጅቶ የህትመት ብርሃን እየጠበቁ ስለመሆናቸው ይናገራል፡፡ በእንዳለ ጌታ ከበደ አርታኢነት በተዘጋጀው ‹ደቦ› በተሰኘው የ60 አንጋፋና የወጣት ፀሀፍት መድብል ውስጥ አንድ አጭር ልቦለድ አሳትሟል፡፡ ከዚህ ሌላ ‹ምን ያህል ያውቃሉ?› የተሰኘውን የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ መጽሀፍ ያሳተመው ታምራት ይህ መጽሀፍ ለብዙ ጊዜ በተደጋጋሚ በማሳተም በየዓመቱ የተለያዩ ሀገራትን የሚጎበኝበትን ገቢ መፍጠሩ እርካታን ይሰጠዋል፡፡ በኢቢኤስ ቲቪ ላይም ‹ካምቦሎጆ› የተሰኘ የስፖርት መዝናኛ ፕሮግራም ከሙያ ጓደኛው ሐብታሙ ደጀኔ ጋር በመሆን እያዘጋጀ ሲያቀርብ የነበረው ታምራት አሁን ደግሞ ለዛና ቁምነገር የተሰኘውን የሬድዮ መሰናዶ በአሐዱ ሬድዮ ላይ ከአንጋፋው ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ ጋር እያቀረበ ይገኛል፡፡

            ታምራትና የበጎ ፈቃደኝነት
   

ብዙዎች የድሆች አባት ሲሉት የነበረው ኮሜዲያን አለባቸው ተካ በድንገተኛ የመኪና አደጋ ህይወቱ ሲያልፍ በእውቅናው ዘመን ሰብስቦ ያሳድጋቸው የነበሩ ወጣቶች መውደቂያ አጥተው ተቸግረው ነበር፡፡ የባለቤቷን አርአያነት አንግባ ስሙን ለማስቀጠል ባለቤቱ ወ/ሮ ሳባ ሀይሌ ወደ አደባባይ ስትወጣ ‹አለሁ› ብሎ ከጎኗ የቆመው ታምራት ነው፡፡ ‹አለቤ የበጎ ፈቃደኞች ማህበር›ን ሳባ ስትመሰርት ከምስረታው ጀምሮ በቦርድ አባልነት ሀላፊነቱን በመወጣት ሊበተኑ የነበሩ ወጣቶች ራሳቸውን የሚችሉበትን ስልጠና እንዲያገኙ መንገድ አመቻችቷል፡፡ በሲስተር ዘቢደር ዘውዴ በሚመራው የሜሪጆይ የልማት ማህበርም መውደቂያ ያጡ አዛውንቶችና ህፃናትን ለመጦር የበጎ አድራጎት ተግባራትን ሲያከናውን ታምራት በሙያው ከድርጅቱ ጎን ቆሟል፡፡ በማህበሩ ዓመታዊ የጠቅላላ ጉባኤ ላይም አባል ሲሆን የሜሪጆይ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር በመሆን የበኩሉን ሙያዊ አስተዋፅኦ እየተወጣ ነው፡፡ የሚውዚክ ሜይዴይ መስራችና አርቲስት የነበረውን የአርቲስት ሽመልስ አራርሶን የህይወት ታሪክ የያዘ ቪዲዮ አዘጋጅቶም አስመርቋል፡፡

ታምራት የአንጋፋውን ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ ልደትን በመኖሪያ ቤቱ አክብሯል፡፡በሚሊኒየሙ ዋዜማ በብሔራዊ ደረጃ የሱዳኑ አንጋፋ አርቲስት ሰይድ ከሊፋ በዊልቸር ላይ እየተገፋ መጥቶ እንዲዘፍን ሲጋበዝ የሀበሻው የሙዚቃ ንጉስ ጥላሁን ገሠሠ ግን አስታዋሽ አልነበረውም፡፡ የጥላሁን ገሠሠ አድናቂ ወዳጅና ታሪኩን ሲዘግብ እንደኖረ ወጣት ጋዜጠኛ መስከረም 17 የሚከበረውን የ68ኛ ኣመት የልደት በዓሉን ለማክበር ወደ መኖሪያ ቤቱ ሲገባ ጥላሁን በመኖሪያ ቤቱ አንድ ክፍል ብቻውን ተቀምጦ ሲተክዝ ነበር ያገኘው፤በስንት ታላላቅ መድረኮችና አብያተ- መንግስታት ሳይቀር ቆሞ ሲያዜም ለኖረ ሰው እንደ መረሳት ያህል ከባድ ፈተና የለም፤ ታምራት በዕለቱ ሌሎች የሙያ ጓደኞቹንና አርቲስቶችን ጋብዞ በመኖሪያ ቤቱ ደመራ ደምሮ ልደቱን አክብሯል፡፡ ታምራት እነዚህና ሌሎች በቁም ነገር በሚሰራቸው ስራዎች ሳቢያ የአባቱን ስም አስቀይሮ ‹ታምራት ቁም ነገር› በሚል የክበብ ስም እንዲጠሩት አስችሏል፤ ኮሜዲያን ደረጄ ኃይሌ፤አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ፤ አርቲስት ዳዊት ፍሬው፤ደራሲ እንዳለ ጌታ ከበደ፤ አርቲስት ኤልያስ መልካ/ነፍስ ኄር/ አርቲስት ሽመልስ በቀለና አርቲስት ተስፋዬ ማሞ የአባቱን ስም ከረሱትና ዘወትር በዚሁ ስያሜ ከሚጠሩት የቅርብ ሙያተኞች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ለጋዜጠኞች የሙያ ስነ- ምግባር መከበር ጥብቅና የመቆም ዓላማ ያለው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ምክር ቤት እንዲመሠረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ካደረጉ ባለሙያዎች መሀከል የሚጠቀሰው ታምራት ትልቁን ሚና እየተጫወተና አሁንም በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት ካውንስሉን እየመራ መሆኑን በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ፡፡

ታምራት ‹መፃፍ የቻለ ሁሉ ጋዜጠኛ አይደለም፤ እንዲያማ ቢሆን ኖሮ መተኮስ የቻለ ሁሉ ወታደር ይባል ነበር› ይላል ዘመኑን ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሚታየውን መደበላለቅ በመጥቀስ፡፡‹ሀገራችን ለሚዲያ ትኩረት ብትሰጥ ሙያው የማደግ እድሉ ከፍተኛ ነው› የሚለው ታምራት ይህንኑ መሠረት በማድረግም ወጣት ጋዜጠኞችን የጋዜጠኝነት ስልጠና በመስጠት ለሙያቸው ታማኝ ሆነው ህዝብን ማገልገል እንዲችሉ የሚያግዝ ‹ቁም ነገር የጋዜጠኞች ማሰልጠኛ ማዕከል›ን አቋቁሞ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት ፍላጎቱና ዝንባሌው ያላቸው ከ200 በላይ ወጣቶችን አሰልጥኗል፤ አንዳንዶቹ በአሁኑ ወቅት የራሳቸውን ፕሮግራም በማዘጋጀት በተለያዩ የኤፍ ኤም ራዲዮ ጣቢያዎች ላይ በመስራት ላይ ናቸው፡፡

ታምራት ከጋዜጠኝነትና ከሚዲያ አመራር እንዲሁም ከኮሚዩኒኬሽን ጋር የተያያዙ በርካታ ስልጠናዎችን በሀገርና በውጭ ሀገራት ተከታትሏል፤በተለይም በውጭ ሀገራት ከቬይና እስከ አመስተርዳም፤ ከጄኔቩ እስከ ቤይጂንግ የተሳተፈባቸው ዓለም አቀፍ ስልጠናዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ይህንኑ ልምዱንም መሠረት በማድረግ በተለያዩ ሀገራዊና ሚዲያ - ነክ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ስራዎችን በማቅረብና ስለ ጋዜጠኞች የሙያ ሥነ ምግባር አተገባበር ስልጠና በመስጠት የድርሻውን በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡

              የትምህርት ዝግጅት

ታምራት ‹ተማር ታውቃለህ፤ ሞክር ትችላለህ!› የሚል መርህ አለው፡፡ ለዚህም ነው የመጀመሪያ ዲግሪውን በቋንቋ እና ስነ-ጽሁፍ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ እየተማረ ከዩኒቲ ኮሌጅ የህግ ዲፕሎማውን ማግኘት ችሏል፡፡ የማስተርስ ዲግሪውን ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ፅሁፍና ፎክሎር በሚሊኒየሙ ዋዜማ ተቀብሏል፡፡ ታምራት በዩኒቨርሲቲ ቆይታው መጨረሻ የሰራቸው የመመረቂያ ጥናቶች በመምህራኑ ከፍተኛ አድናቆት አስገኝተውለታል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪውን የሟሟያ ጥናታዊ ፅሁፍ የሰራው በ40 እና በ80 ቀን መታሰቢያ የሀዘን እንጉርጉሮ ግጥሞች ባህሪያት ላይ ሲሆን በተለይ በ1990ዎቹ አጋማሽ የታተሙ ከ100 በላይ የሀዘን እንጉርጉሮ ግጥሞችን በመሰብሰብ ተንትኗል፡፡ እንደዘበት ለመታሰቢያ ተብለው በየቤታችን የሚመጡት የመታሰቢያ ካርዶችን ላየ ሰው የሚፃፉት የሀዘን እንጉርጉሮ ግጥሞች ይዘቶቹ ሀዘን ለማጫር ተብለው የሚፃፉ የመሆናቸው ነገር እንደተጠበቀ ሆኖ ምሳሌያዊ ንግግሮችን፤ ስነ- ቃሎችን፤ ልዩ ዘይቤዎችንና ቅኔዎችን የያዙ ስነ- ፅሑፋዊ ይዘት ያላቸው ስለመሆናቸው በጥናቱ አመላክቷል፡፡

የሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ ጥናታዊ ፅሑፉ ደግሞ በብራና መፅሐፍት አዘገጃጀት ዙሪያ ያደረገ ሲሆን በብራና መፅሀፍት ዝግጅት ዙሪያ ያሉ ማህበረሰባዊ እምነቶችን ፈትhDል፡፡ ታምራት ለዚሁ ጥናቱ በማለት አንድ ፍየል ታርዳ ቆዳዋ ወደ መፃሕፍትነት ተቀይሮ ተጠርዞና ተደጉሶ ለአገልግሎት እስከ ሚቀርብበት ጊዜ ድረስ ያለውን ሂደት የብራና መፅሐፍት ዝግጅት አሁንም ድረስ በሚካሄድባቸው በደቡብ ጎንደር እስቴ ወረዳ እና የቁም ፅሕፈት ትምህርት ቤት እስከሚካሄድበት በደብረ ሊባኖስ ገዳም ድረስ ተቀምጦ ተመልክቷል፡፡ በዪኒቨርሲቲው የፎክሎር ጥናት መስክ በብራና ላይ የተደረገ የመጀመሪያ ጥናት መስራቱን የጥናቱ አማካሪ የሆኑት አንጋፋው የስነ- ፅሑፍ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘርይሁን አስፋው በቁም ነገር መፅሔት 10ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ በተገኙበት ወቅት መመስከራቸው ይታወሳል፡፡ታምራት እነዚህን ጥናታዊ ፅሑፎቹን በሚውዚክ ሜይዴይ የመፅሐፍ ንባብና የውይይት ክብብ ላይ አቅርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

                  ትዳር
          

ታምራት ባለትዳርና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነው፡፡ ባለቤቱ ወ/ሮ ራሔል ዘውዱ ‹ባልና ሚስት ከአንድ ባህር ይቀዳሉ› እንዲሉ እንደእርሱ ልታይ ልታይ የማትል ነገር ግን ከቁም ነገርም ሆነ ከፋሽን መፅሔቶች ጀርባ የነበረች ጋዜጠኝነትን እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ የተማረች የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ ናት፤ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ኤምባሲ የኢንፎርሜሽ ስፔሻሊስት ሆና እየሰራች ያለች ስትሆን የራሔል ታሪክ ራሱን ችሎ በሚዘገብበት ወቅት በስፋት እንመለስበታለን፡፡

           ማጠቃለያ 
    

ታምራት ቁምነገር / ታምራት ሀይሉ/ ገና በልጅነቱ አሀዱ ብሎ የጀመረው የጋዜጠኝነት ሙያ ዛሬ ላይ አድርሶታል፡፡ በአሁኑ ሰአት ለተከታታይ 20 አመት ያለ አንዳች መቋረጥ ለህትመት የበቃ መጽሄት ቁምነገር ነው፡፡ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስናይም አጠቃላይ በኢትዮጵያ የመጽሄት ህትመት ታሪክ የግል ሆኖ ለ20 አመት የታተመ ከቁምነገር በቀር የለም፡፡ ይህን የታምራትን የዊኪፒዲያ ታሪክ ባጠኑ ሰዎች እይታ ከቁምነገር ጀርባ ያለው ታላቅ ሰው ታምራት ሀይሉ ነው፡፡ ታምራት ምንጊዜም ከዚህ ሙያ መራቅ ብቻ ሳይሆን ያለ ጋዜጠኝነት ሌላ ስራ መስራት አይሆንለትም፡፡ ቀን ሌትም እየሰራ ፤ትልቅ ዋጋ እየከፈለ ያከበረው ሙያ ዛሬ ታምራትን አስከብሮታል፡፡ ታምራት ለዚህ ደረጃ የበቃው ግን ትእግስት በማሳየትና ለሙያው ታላቅ ፍቅር በመስጠት ነው፡፡ የኢትዮጵያ የህትመት ኢንዱስትሪ ማደግ ላይ ታምራት የራሱን ትልቅ አሻራ ማስቀመጥ ችሏል፡፡ ይህንንም ታሪክ ትውልድ እንዲያውቀው አስፍረናል፡፡