ቢግ ባንግ

ከውክፔዲያ
ዓለም ጭፍግ ካለ ትንሽ ጠጣር ነገር ተነስቶ እየሰፋ አሁን ያለንበትን ሁኔታ ስለመውለዱ እሚያሳይ ስዕል። በአጠቃላይ መልኩ የቢግ ባንግ ኅልዮት!

"ቢግ ባንግ" ወይንም ዐቢይ ፍንዳታ በሳይንቲስቶች ዘንድ የመላው ዓለም መነሻ ኩነትን ይገልጻል ተብሎ የሚታመንበት ኅልዮት ነው። አጠቃላይ አንጻራዊነት የተባለውን የአልበርት አይንስታይን ሳይንሳዊ ቀመር በመጠቀም ከአሁን ከአለንበት ጊዜ ወደኋላ ስንምለስ አንድ ወቅት ላይ ዓለም በሙሉ ተጨምቆ፣ አንዲት ትንሽ እኑስ እንደነበር እንረዳለን። ይህ እኑስ በውስጡ ምንም አይነት አቶምመዋቅርም ሆነ ቅጥ አልነበረውም። ይልቁኑ እጅግ ሞቃት፣ እጅግ ትንሽ እና አዕላፍ ጭፍገት ነበረው። ከዛሬ 13.7 ቢሊዮን ዓመት በፊት፣ ይህ ጥንጥ ጠጣር ነገር ድንገት በመፈንዳት በመበታተኑ ኅዋ እና አቶሞች ተፈጠሩ። እንዲሁም አቶሞቹ እየጓጎሉ ኮኮቦችን ፈጠሩ። በዚህ ሁኔታ ከፍንዳታው በኋላ የተፈጠረው ዓለም እየሰፋና እና እየቀዘቀዘ በመሄዱ እንደ መሬት ያሉ ፈለኮች (ፕላኔቶች) በሂደት ቀስ እያሉ ተፈጠሩ። በአሁኑ ወቅት፣ ምንም እንኳ ቀስ ብሎ ቢሆንም፣ ኅዋ እና በውስጡ ታቅፎ ያለው ቁስ እየተለጠጠና ሙቀቱም እየቀነሰ ይገኛል። ይህን እሚያጠናው የሳይንስ ክፍል ኮስሞሎጂ ሲባል በዚህ የጥናት ዘርፍ ተቀባይነት ያገኜው የ ቢግ ባንግ ኅልዮት በብዙ ሳይንቲስቶች ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቷል።