አባል:Eliasab

ከውክፔዲያ
ከአለት የተፈለፈለ
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን
ዋሻ ሚካኤል ቤተክርስቲያን

[[ስዕል:
የዋሻ ሚካኤል የተሻሻለው ንድፈ-ዲዛይን [1]
|250px]]
Eliasab
አገር ኢትዮጵያ
ሌላ ስም {{{ሌላ ስም}}}
ዓይነት ፍልፍል ዓለት ውቅር ቤተክርስቲያን
አካባቢ** አዲስ አበባ
የቅርስነት ታሪክ
ቅርሱ የተሰራበት ዘመን 4ኛው ወይም 12ኛው ክፍለ ዘመን 
አደጋ የመፈራረስ እና ጥንታዊ መዋቅሩን ማጣት
* የአለበት ቦታ
** የዩ.ኔ.ስ.ኮ. ክልል ክፍፍል


ዋሻ ሚካኤል ቤተክርስቲያን[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዋሻ ሚካኤል (Washa Mikael, English) ከአዲስ አበባ በስተምስራቅ በኩል የካ ከፍለ ከተማ ውስጥ ያለ ጥንታዊ እና በከፊል ወጥ ከሆነ ዓለት ተፈልፍሎ የተሰራ ቤተ-ክርስቲያን ነው:: አዲስ አበባ ከሚገኘው የእንግሊዝ ኢምባሲ በስተጀርባ ቲንሽ ራቅ ብሎ በሚገኘው ከፍታማ ቦታ ላይ ይገኛል::[2] ምንም እንኳ የአካባቢው ቄሶች በ4ኛው ክፍለ ዘመን እንደተሰራ ቢናገሩም በአብዛኛው ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚገመተው ግን በ12ኛው ክፍለ ዘመን እንደተሰራ ነው::[3][4] ቤተክርስቲያኑ የላሊበላ ውቅር ቤተክርስቲያን አይነት ስልት የያዘ ነው። ምንም እንኳ የህንጻው አወቃቀር ባልታወቀ ምክንያት ሳይጠናቀቅ የቀረ ቢሆንም ስራው ቢገባደድ ኑሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት የአለት ውቅር ቤተክርስቲያኖች በትልቅነቱ ሁለተኛ ይሆን እንደነበር ተመራማሪዎች ይዘግባሉ (ታላቁ የላሊበላ መድሃኒ አለም ነው::)[1]

ታሪካዊ ዳራ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የአክሱም መንግስትና የዋሻ ሚካኤል ውቅር ቤተክርስቲያን:- አብርሃና አጽብሃ የአክሱም መንግስትን በጋራ ይገዙ እንደነበር የተለያዩ መጽሃፍት ይገልፃሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጽሁፍም ይሄንን በተለያዩ መረጃዎች ይጠቅሳል፡፡ ክርስትናን ከተቀበሉ በኋላ እንደተፃፈ በሚነገረው የድንጋይ ላይ ፅሁፍ አብርሃና አፅብሃ የሚያስተዳድሩት አገር ግዛት ዝርዝር ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ ዝርዝር እንደምንረዳው ግዛታቸው ሳባን /የመንን/፣ ኑባ /ሱዳንን/ እና ቤጃ /ደቡብ ግብጽ/ ድረስ ይደርሳሉ፡፡ ይህም እጅግ ሰፊ ግዛት እንዳላቸው ያስረዳል፡፡ ከየካ ሚካኤል የተገኘው /ያልታተመ/ መረጃ ይህንን ሀሳብ እንደሚከተለው ያጠናክራል::[5]

“በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ ወሰን በጣም ሰፊ ስለነበር ሁሉቱ ወንድማማቾች አክሱም ላይ ሆነው ሕዝባቸውን በቅርብ ለማስተዳደር ስለተቸገሩ እጣ ተጣጥለው ንጉስ አብርሃ አክሱም ላይ በመሆን ሰሜን ኢትዮጵያን፣ ንጉስ አጽብሃ ደግሞ ደቡብ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ሸዋ ውስጥ የረር ተራራ ላይ ቤተ መንግሥቱን ሰራ፡፡ በወቅቱ ቤተመንግሥቱን ለመሥራት ሲመጣ ማዕቀበ እግዚእ በሚባል ካህን ታቦት ሚካኤልን አሸክሞ አስመጥቶ ነበር፡፡ ይህንን አሸክሞ ያስመጣውን ታቦት ከየረር ተራራ በስተ ሰሜን አቅጣጫ ባስፈለፈለው ዋሻ ውስጥ እንዳስገባው ይገልፃል፡፡”

በትግራይ ክልል በአብርሃና አፅብሃ ቤተ ክርስትያን ውስጥ ከጅማ የአፅብሃ ሬሳ የመጣበት ነው የሚባለው የጠፍር አልጋ ይገኛል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ደቡብ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረው አፅብሃ እስከ ጅማ መድረሱን ነው፡፡ ውቅር ቢተክርስቲያን መስራት ለአጽብሃ አዲስ አይደለም፡፡ በትግራይ ከውቁሮ ከተማ 20 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ገረአልታ ውስጥ ገማድ በተባለ ስፍራ አብርሃና አጽብሃ ያሰሩት ነው የሚባል አብርሃ አጽብሃ በመባል የሚታወቅ ውቅር ቤተክርስቲያን ይገኛል፡፡ ቤተክርስቲያኑ ገዳም ነው፡፡[5]

ከየካ ሚካኤል የተገኘው /ያልታተመ/ መረጃ እንደሚገልፀው በትግራይ ውቅሮ አካባቢ የሚገኘው የአብርሃና አፅብሃ ውቅር ቤተክርስቲያን ከዋሻ ሚካኤል ውቅር ቤተክርስቲያን ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው በመግለጽ ታሪኩን እንደሚከተለው ዘርዝሯል፡-[5]

“ከንጉስ አጽብሃ ጋር የመጣው ታቦት የገባበት ዋሻ የተፈጥሮ ዋሻ ሳይሆን በሰሜን ኢትዮጵያ እንደሚገኙት ከአንድ ቋጥኝ ድንጋይ ተፈልፍለው ከታነፁት ጥንታዊ ቤተክርስቲያን ዓይነት በኢትዮጵያ ፊደል “ሀ” ቅርጽ የታነፁ ሲሆን በቤተክርስቲያን የፊደል ትርጉም “ሀ” ማለት “ህልዎቱ ለአብ እምቅድም ይትፈጠር ዓለም” ወይም “የአብ መኖር ከአለም አስቀድሞ ነው” ማለት ነው የሚለውን አባባል ለማስረዳት ተብሎ የታነፀ ነው ይላል፡፡” በሌላ በኩል አንዳንድ የታሪክ ተመራማሪዎች የዋሻ ሚካኤል ውቅር ቤተክርስቲያን በደቡብ ሸዋ ከአዲስ አበባ በስተ ምዕራብ በአለምገና ቡታጅራ መንገድ አቅጣጫ ከአዲስ አበባ 66 ኪሎ ሜትር አካባቢ ከምትገኘው አዳዲ ማሪያም ውቅር አብያተ ክርስቲያን ጋር በመመሣሠሉና ይህ ደግሞ በንጉስ ላሊበላ ዘመን እንደ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በዚያ ዘመን የተሰራ ነው ይላሉ፡፡[5]

በአዳዲ ማሪያም የሚገኘው የታሪክ ማስታወሻ ንጉስ ላሊበላ የአዳዲ ማሪያምን ከቋጥኝ ድንጋይ እንደፈለፈለውና ሥራውን ሲጨርስ በራዕይ ተመርቶ ወደ ላሊበላ እንደተመለሰና እዚያ ሲደረሰ እንደሞተ ይተርካል፡፡[5]

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየሶስት ወሩ በሚያሳትመውና ሰላምታ ተብሎ በሚጠራው ቋሚ የበረራ መፅሄት ዊሊያም ዴቪድሰን የተባሉ የታሪክ ተመራማሪ የዋሻ ሚካኤል ውቅር ቤተክርስትያን የ700 ዓመት እድሜ እንዳለውና አሰራሩም ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አሰራር ጋር እንደሚመሳሰል ይገልፃሉ፡፡[5]

በየትኛው ዘመን እንደተሰራ ለማወቅ የአርኪዎሎጂ ጥናት መደረግ ስላለበት የነሱን የወደፊት የጥናት ውጤት መጠበቁ ወሳኝ ቢሆንም ከየካ ደብረሳህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያን ያገኘነው ያልታተመ ፅሁፍ የዋሻ ሚካኤል ውቅር ቤተክርስትኑ ከላሊበላ ጋር በማመሳሰል ማቅረብ የኢትዮጵያን ሀይማኖት ጥንታዊነት በሚፃረሩ ሀይሎች የሚወራ ነው በማለት ይቃወማሉ፡፡[5]

አብርሃና አፅብሃ ከአባታቸው ታዜር ከእናታቸው ሶፍያ (አይዋል) ታህሳስ 19 ቀን 312 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡ አባ ሰላማ (አባ ከሣቴ ብርሃን) በ28ኛ ዓመታቸው አጠመቁዋቸው፡፡ አብርሃና አጽብሃ ከአባ ሰላማ ጋር በመሆን ክርስትናን በግዛታቸው አስፋፍተዋል፡፡ በዘመናቸው 6ዐ አብያተ ክርስቲያናትን እንዳሳነፁና ከዚህም ውስጥ 44 ቤተክርስቲያናት ፍልፍል ቤተክርስቲያናት ናቸው፡፡ በስማቸው ቤተክርስቲያን ታንፃል፡፡ በየወሩ በ4ኛው ቀንና በየዓመቱ ጥቅምት 4 በአክሱም ፅዮንና መርጦ ለማርያም ቤተክርስትያናት በዓላቸው ይከበራል፡፡[5]

እንደ ነገሥታቱ ገድል በ32ዐዎቹ ንጉስ አጽብሃ በየረር ተራራ ላይ የገነባው ቤተ መንግሥትና ከቤተመንግሥቱ በስተ ሰሜን አቅጣጫ የተገነባው ውቅር ቤተክርስቲያን በአባ ከሣቴ ብርሃን የመጀመሪያው ጳጳስ ተባርኮ ተመረቀ፡፡28

አብርሃና አጽብሃ የጀመሩትን ክርስትናን የማስፋፋት ሥራ በተከታዮችም ነገሥታት የቀጠለ ሲሆን በ6ተኛው ክፍለ ዘመን በአፄ ካሌብና በአፄ ገ/መስቀል የንግስና ዘመን በበለጠ ተስፋፍቷል፡፡ በ6ተኛው ክ/ዘመን በተለይ ዘጠኙ ቅድሳን ከመጡ በኋላ ክርስትናን የማሠራጨቱ ሥራ ይበልጥ ተስፋፍቷል፡፡[5]

በአክሱም ዘመነ መንግስት ዮዲት ጉዲት የተባለች በአክሱም ግዛት ያሉትን አብያተ ክርስቲያናትና ቄሶችን ማጥፋት በጀመረች ጊዜ የአክሱም ፅዮንን ጨምሮ አንዳንድ ታቦታት ወደተለያዩ ቦታዎች ተሰደዋል፡፡ ምናልባት እነዚህ የፀረ ክርስትና ሰዎች አጽብሃ ወዳሰራው ውቅር ቤተክርስቲያን ቢመጡም ታቦቱን የእምነቱ ተከታዮች እስከ 1838 ዓ.ም ድረስ ይዘው ሲሰደዱ እንደቆዩና በመጨረሻ ቡልጋ ውስጥ ከሚገኘው ኢቲሳ ተ/ሃይማኖት ገዳም የቅዱስ ሚካኤልን ጽላት እንዳመጡት ይነገራል፡፡[5]

በየካ ደብረ ሣህል የሚገኘው የታሪክ ማስታወሻ የጽላቱን አመጣጥ ታሪክ እንደሚከተለው ያስረዳል፡፡[5]

“ንጉስ ሣህለ ሥላሴ (1805 - 1840 ዓ.ም) በነገሱ በ32ኛው ዓመት አባ ተስፋ ሚካኤል የተፀውኦ ስማቸው አባ ኦፎንቻ የሚባሉ መነኩሴ የቅዱስ ሚካኤልን ጽላት ቡልጋ ከሚገኘው ኢቲሳ ተ/ሃይማኖት ገዳም አምጥተው ግንቦት 13/1838 አስገቡት::”

ንጉስ ሣህለ ሥላሴ የሸዋ ንጉሥ ሆነው የገዙት ከ1805-1840 ዓ.ም ሲሆን በዚህ ዘመን በሸዋ ግዛታቸው ውስጥ እየተዘዋወሩ አንድነትና ሃይማኖትን በማስተማር ባላቸው ፅኑ ዓላማ ሠራዊታቸውን አስከትለው በ1826 ዓ.ም አካባቢ ከኢቲሳ ወደ ደቡብ አቅጣጫ እንደሄዱና የቀራኒዮ መ/ዓለም ቤተክርስቲያን ደብርን በ1826 ዓ.ም ተከሉ፡፡[5]

በእሳቸው ዘመን ግንቦት 12 ቀን 1838 ዓ.ም በስደት ከቆየበት ኢቲሳ የቅዱስ ሚካኤል ጽላት መጥቶ ገባ፡፡ የቅዱስ ሚካኤል ውቅር ቤተክርስቲያን ጽላት ከተመለሰ በኋላ ለአካባቢው ሰውና ለንጉሥ ሣህለሥላሴ ሠራዊት አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡[5]

አፄ ምኒልክ የሸዋ ንጉስ ሆነው ሲነግሱ ከተማቸው አንኮበር ነበረች፡፡ አባታቸው የጀመሩትን ወደ ደቡብ አቅጣጫ የመስፋፋትን መንገድ በመከተል እሳቸውም ወጨጫ ተራራ ላይ በድንኳን ካምፕ አድርገው ከነሠራዊታቸው ሰፈሩ፡፡ ወጨጫ ላይ በድንኳን ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ እ.ኤ.አ በ1886 ወደ እንጦጦ መጡና ከተማቸውን ከተሙ፡፡[5]

ታዲያ ወጨጫም ሆነ እንጦጦ እያሉ የእንጦጦ ማሪያም ቤተክርስቲያን ከመተከሉ በፊት ወደ ዋሻ ሚካኤል ውቅር ቤተ ክርስቲያን እየተመላለሱ ያስቀድሱ ነበር ይባላል፡፡[5]

በ1878 ውቅር ቤተክርስቲያኑ በአንድ በኩል በመደርመሱ አፄ ምኒልክ ካህናቱን፣ ጽላቱንና ቅርሶቹን ይጐዳብኛል በማለት ታቦቱን ከውቅር ቤተክርስቲያኑ ውስጥ አውጥተው እዚያው አካባቢ ባሰሩት መቃኞ ውስጥ አስገቡት፡፡ በመቃኞ ውስጥ እያሉ ለ7 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው ጽላት በ1895 አሁን የካ ሚካኤል ተብሎ ወደሚጠራው ቦታ መቃኞ ተሰርቶለት ገባ፡፡ ውቅር ቤተክርስቲያኑ ግን ባለቤት የሌለውና ጠባቂ አጥቶ የከብቶች መዋያ በመሆን ሣርና ሙጃ በቅሎበት ይገኛል፡፡[5]

ከዓለት ተፈልፍሎ የተሰራ ጥንታዊ ቤተክርስቲያን
የዋሻ ሚካኤል ፍልፍል-ዓለት ውቅር ቤተክርስትያን፣ በመግቢያው ወደ ውስጥ ከተገባ በኃላ ውጫዊ ገጽታውን በከፊል የሚያሳይ ፎቶ

ማጣቀሻ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  1. ^ Bruce, Strachan. "Washa-Mikael Significant Heritage Site In Danger", February 25, 2010. Retrieved on 21 October 2017.
  2. ^ "Washa Mikael Church in Addis Ababa", Lonely Planet, Retrieved on 21 October 2017.
  3. ^ Bruce, Strachan. "Ongoing Conservation Efforts Yield Enriched Understanding of Washa Mik’ael", November 26, 2014. Retrieved on 21 October 2017.
  4. ^ "Washa Mikael Rock-hewn Church", Geocaching, November 21, 2016. Retrieved on 21 October 2017.
  5. ^ ግዛቸው አበጋዝ እና ሌሎች. "የዋሻ ሚካኤልን የቱሪስት መስህብ ለማድረግ የተደረገ ጥናት ", በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የቱሪዝም ልማትና የቅርስ አስተዳደር ዋና የስራ ሂደት፣ የቱሪዝም ጥናትና ልማት ኬዝ ቲም፣ አዲስ አበባ. 2006 ዓም.

ውጫዊ አገናኞች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  1. ጥር 1፣ 2000 እኤአ የተነሳ ፎቶ - ዋሻ ሚካኤል ቤተክርስቲያን(በ12ኛው ክ/ዘመን እና 1531 መካከል)፣ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት በየካ ከፍታማ ቦታዎች የሚገኝ
  2. ዋሻ ሚካኤል ፍልፍል-ዓለት ቤተክርስቲያን - WaWasha Mikael rock-hewn Church
  3. SEARCHING FOR GOD’S COUNTRY – by Bruce Strachan
  4. Washa-Mikael | An Overlooked African Treasure – by Bruce Strachan
  5. Ethiopia - Google book search results - WASHAMIKAEL CHURCH
  6. More than one-thousand years rock-hewn church in Addis Ababa
  7. Washa Mikael Church