አኩሪ አተር

ከውክፔዲያ
አኩሪ አተር

አኩሪ አተር (Glycine max) የአባዝርት አትክልት ዝርያ ነው።

በየጊዜው አኩሪ አተርን መመገብ ለሴቶች ጉዳት ባያደርግም፣ ለወንዶች ጤናማ እንደማይሆን በሰፊ ቢታወቅም በአንዳንድ አገር ባሕል አመጋገብ በብዛት ይጨመራል።

ከ20ኛዉ ክፍለ ዘመን አንስቶ በተለይ አሜሪካን ዉስጥ ወርቃማዉ ወይም ተዓምረኛዉ እህል የሚል ስያሜ አግኝቷል። አኩሪ አተር በፕሮቲን እና ቅባት ምንጭነቱ የሚወዳደረዉ የእህል ዘር የለም። ባለሙያ ካገኘም ለመጠጣትም ለመበላትም የሚችል የእህል ዘር ነዉ። ስለአኩሪ አተር ሲወሳ ብዙዎች የሚያስታዉሱት ለሕፃናት አካል ግንባታ ጠቃሚ መሆኑ ብዙ ጊዜ የተነገረለትን የአኩሪ አተር ወተት ሊሆን ይችላል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በኢትዮጵያዉያን የምግብ ጣዕም ለዛ ተላብሶ በተለያየ ምግብነት መቅረብ እንደሚችል እየታየ ነዉ።

አኩሪ አተር ወደኢትዮጵያ የገባዉ በ1950ዎቹ መሆኑን ነዉ በእህሉ ላይ ምርምር የሚያደርጉት ባለሙያዎች የሚያስረዱት። በአኩሪ አተር ላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተደረገዉ ዝርያ የማዉጣት ምርምርም 22 ዓይነት ዘሮች እስካሁን ተገኝተዋል። በኢትዮጵያ የአኩሪ አተር ብሔራዊ ምርምር ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ትዕዛዙ ደጉ ስድስት ዘርፎች ያሉት የምርምር ፕሮጀክት እህሎቹን እርስ በርስ በማዳቀል የሚፈለገዉን የጥራት ደረጃ እንዲይዝ ማድረግ፤ ምርትና በሽታ መቋቋም ላይ ያተኮረ ምርምርም ያካሂዳል። አኩሪ አተርን በሀገር ዉስጥ በ12 የምርምር ማዕከላት ላይ ከፍተኛ የዝናብ መጠን በሚያገኙ፤ መካከለኛ የዝናብ መጠን በሚያገኙ እና ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ምርምሩ ይካሄዳል። ምርምሩ በዚህ አያበቃም ሰብል ክብካቤን በሚመለከት መቼ መዘራት አለበት የሚለዉ እና የአመራረት ሥርዓት ማለትም አኩሪ አተር ከየትኛዉ እህል ጋር ተፈራርቆ ይዘራ፤ ከየትኛዉስ ጋር ተሰባጥሮ ይዘራ የሚለዉ ጥናትም የፕሮጀክቱ አንድ አካል ነዉ። አኩሪ አተርን ሰብልን ሊያጠቁ የሚችሉ አረም ሆነ ተባይ ወይም በሽታ የቱ እንደሆነም ክትትል ይደረጋል። ስለአኩሪ አተር ጥቅም የሚዘረዝሩ ዘገባዎች የመኖራቸዉን ያህል በተፈላጊነቱ ምክንያት በተለይ ደቡብ አሜሪካ ዉስጥ ደኖች እንዲጨፈጨፉ ምክንያት ሆኖ በሥነምህዳሩ ላይ ጫና እስካተለ የሚያወሱም አሉ።

አኩሪ አተር ሀገር ዉስጥ በከፍተኛ ደረጃ የሚመረተዉ በቤንሻንጉል ጉምዝ እና በኦሮሚያ ክልል ነዉ። አኩሪ አተርን በብዛት ከሚያመርቱ ሃገራት ዩናትድ ስቴትስ፤ ብራዚል እና አርጀንቲና ቀዳሚዎቹ ናቸዉ። የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ተቋም በአኩሪ አተር ላይ አመራረትም ሆነ ምግብ ዝግጅት ላይ ምርምር ሲያካሂድ የቆየ መሆኑን የገለፁት በግብርና ምርምር ተቋሙ የምግብ ሳይንስ ተመራማሪ እና የብሔራዊ አስተባባሪ አቶ ቢላቱ አግዛ አኩሪ አተር በኢትዮጵያ በምግብነት ያን ያህል አልተለመደም ይላሉ።

ከአኩሪ አተር የተቀላቀለበት ኬክ

ከአኩሪ አተር ወተት ለማዘጋጀት ሲታሰብ እህሉን ከአንድ ቀን በፊት ለቅሞና አጥቦ ለ15 ደቂቃ ያህል መቀቀል ያስፈልጋል። ከዚያም አዉጥቶ ተዘፍዝፎ ያድራል። ከዚያም የራሰዉን አኩሪ አተር ልጣጩን በሚገባ በዉኃ አስለቅቆ በትንሽ በትንሹ እየቆነጠሩ ፈጭቶ እንደእህሉ መጠን ዉኃ ጨምሮ መቀቀልና መጭመቅ ነዉ። እንደባለሙያዉ ከሆነም ለአንድ ኪሎ አኩሪ አተር ስምንት ሊትር ዉኃ ያስፈልጋል።

ተፈጥሮን ተከትሎ የማይበቅል እህልም ሆነ በተፈጥሮ ሥርዓት ያላደጉ እንስሳትን መመገብ ለጤና አደገኛ መሆኑን በተግባር የተረዳዉ ምዕራቡ ዓለም በአሁኑ ጊዜ ፊቱን ከእንስሳት ተዋፅኦ ወደተክሎችና ሰብሎች አዙሯል። በዚህ ምክንያትም ከአኩሪ አተር የሚገኙ የምግብ ተዋፅኦዎች ተመራጭነትን እያገኙ ነዉ። ከአኩሪ አተር ወተት እና አይቡ እንደሚገኝ ሁሉ የአኩሪ አተር ሥጋም አለዉ።

የአኩሪ አተር አይብ

በአኩሪ አተር ዘር እና አመራረት ላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ ምርምር ሲደረግ ረዥም ዓመታት አስቆጥሯል። የምግብ ዝግጅቱን ተመለከተ የሚካሄደዉ ምርምር ብቻም አስር ዓመታት እንደቆየ አቶ ቢላቱ ገልጸዋል። የግብርና ምርምር ተቋሙ የአኩሪ አተርን ምግብነት ለማላመድ በጀመረዉ እንቅስቃሴ ለአምራቹቹ ብቻ የምግብ ዝግጅት ሥልጠና ከመስጠት የተቋሙ ሠራተኞችም አዉቀዉት ሙያዉን በማስፋፋት በኩል አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ በሚል አሰልጥኗል።

አቶ ቢላቱ እንደገለፁልን ኢትዮጵያ አኩሪ አተርን ብታመርትም ለዉጭ ገበያ ነዉ። በአንፃሩ የተዘጋጁትን የአኩሪ አተር ምርቶች ወደሀገር ታስገባለች። ከዚህም ሌላ በተለያዩ አካላት የአኩሪ አተር ምግብ አዘገጃጀትን የማስተዋወቁ ሥራ እንደሚከናወን ያመለከቱት የምግብ ምርምር ባለሙያ ይህ ወጥነት እንዲኖረዉ እየተሠራ መሆኑንም ሳይገልፁ አላለፉም። አኩሪ አተር ላይ የሚደረገዉ ምርምርም ሆነ የምግብ አዘገጃጀቱ ጥናት ዋና ዓላማ እህሉ ሀገር ዉስጥ ጥቅሙ ታዉቆ ኅብረተሰቡ ከሚገዙ ምርቶቹ ይልቅ በየቤቱ በቀላሉ ማዘጋጀቱን ለምዶ እንዲጠቀምበት ማድረግ እንደሆነ ነዉ ባለሙያዎቹ ያስረዱት። በተጨማሪም ከዉጭ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለም አመልክተዋል።