አውራከፕት ና ኔኬስ

ከውክፔዲያ
አንዱ የአውራከፕት ቅጂ ስለ ኦጋም ጽሕፈት ሲያስረዳ

አውራከፕት ና ኔከስ (አይርላንድኛ፦ Auraicept na n-Éces «የጠቢባን መመሪያ») በአይርላንድ ሥነ ጽሑፍ ጥንታዊ የሆነ መጽሐፍ ነው። የተቀነባበረው ከ650 እስከ 1050 ዓም ያሕል ይሆናል።

መጽሐፉ ስለ አይርላንድኛ ወይም ጋይሊክኛ እና ስለ ኦጋም ጽሕፈት ጸባይና ታሪክ ነው።

በአውራከፕት ውስጥ አራት ንዑስ ጽሑፎች ተቀነባብረዋል፤ እነርሱም፦

ከዚያ በኋላ ያለው ተጨማሪ መረጃ በ1050 ዓም አካባቢ እንደ ተጻፈ ይመስላል። አራቱ ጽሑፎች ከመጨረሻ እስከ ፊተኛው ድረስ ሲገኙ፣ የፈርኼርትነ፣ አመርጊንና ፌኒየስ ክፍሎች በውነት እንደዚያ ጥንታዊ እንደ ሆኑ አይታሥብም።

የፌኒየስ ክፍል[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ይህ ክፍል (መስመሮች 1102-1639) እንዲህ ይጀመራል፦

«በፌኒየስና በያር ማክ ኔማና በጋይደል ማክ ኤጠር ዘንድ የዚህ መጽሐፍ መጀመርያ ይህ ነው። እነዚህ ሰዎቹ ናቸው፤ ይህም ዘመኑ ነው፣ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ የወጡበት ዘመን ነው። በዳክያ ተሠራ፣ ሌሎች ግን በሰናዖር ሜዳ እንደ ነበር ይላሉ። የሚጻፍበት ምክንያት፣ በሙሴ ከተሰጠና ከርሱ ጋር በኻይ ኻይንብሬጣኽ ከታወቀ በኋላ፣ እንደ መመሪያቸው እንዲመረጥላቸው በፌኒየስና በያርና በጋይደል ማክ ኤጠር ታላቅ ትምህርት ቤት ስለ ተጠየቀ ነው።»

ከዚህ በኋላ «ዋና ፊደላት» - የዕብራይስጥ ፊደልየግሪክ አልፋቤትየላቲን አልፋቤትኦጋም ጽሕፈት ይገልጻል (የእብራይስጥና የግሪክ ፊደሎች በትክክል ግን አያሳይም።) ከዚያ ጽሑፉ ስለ ጋይልክኛ ድምጾች፣ ክፍለ ቃላትና ቃላት ወዘተ. አንዳንድ ነጥቦች ያቀርባል። በነዚህም ውስጥ አንዳንድ ጥቅሶች ትኩረት ስበዋል። ስለ ባቢሎን ግንብ እንዲህ ያስተምራል፦

«የግንቡ እርግጥኛ ቁጥሮች ፭ ናቸው፦ 72 ብሔረሠቦች፣ ከነርሱ ጋር 72 አማካሪዎች፣ የተከፈሉባቸው 72 ልሳናት፣ እነዚያን ልሳናት ለመማር ከፌኒየስ ጋር የመጡት 72 ተማሪዎች፣ የግንቡም ቁመት 72 እርምጃዎች ነበር።»
«ግንቡ የተሠራው በ፯ አለቆች ሥር ነበር፦ ኤቦር ወልደ ሳላ፣ የግሪኮች ወላጅ ግሬጉስ ወልደ ጋሜር፣ የላቲኖች ወላጅ ላቲኑስ ወልደ ፋውኑስ፣ የስኮቶች ወላጅ ሪፋት ስኮት፣ ናምሩድ ወልደ ኩሽ ወልደ ካም ወልደ ኖኅ፣ እና ፋሌክ ወልደ ራግው ወልደ አርፋክስድ ወልደ ሴም።»

ሰባት አለቆች ነበሩ ካለ ቀጥሎ ስድስቱን ብቻ መዘርዘሩ የሚገርም ነው። ሌላ እጅ በጽሑፉ ውስጥ እንዳመለከተ፣ ላቲኑስ ወልደ ፋውኑስ በትሮያ ጦርነት ዘመን እንደ ኖረ ስለ ተባለ፤ በባቢሎን ግንብ ዘመን ነበር ማለቱ ትክክለኛ መረጃ አይመስልም። ከዚያ በቀር የፋሌክ ትውልድ ልክ አይደለም፤ እርሱ በኦሪት ዘፍጥረት መሠረት የራግው አባትና የኤቦር ልጅ ነበር። እንዲሁም አፈ ታሪካዊ ሰው ፌኒየስ ፋርሳ ወይም በሙሴ ዘመን ወይም በባቢሎን ግንብ ዘመን እንደ ኖረ ለማለት ጽሁፉ ከራሱ ጋር አይስማማም።

በዚሁ ክፍል ውስጥ ከሚሌሲያን በፊት በአይርላንድ ስለ ነበሩት ቋንቋዎች ናሙና ያቀርባል፤ እርሱ (ተባዕት)፣ እርሷ እና እርሱ (ግዑዝ) በጋይሊክኛ «እሤ፣ እሢ፣ እሠድ» ሲሆን በፊር ቦልግ ቋንቋ «ዊንዲዩስ፣ ዊንድሲ፣ ኦንዳር» እና በቱአጣ ዴ ዳናን ቋንቋ «ሞድ፣ ቶድ፣ ትራይጥ» እንደ ነበር ይመሰክራል። ይህ ሚሌሲያን ወደ አይርላንድ ከገቡ በኋላ ስለ ታወቀላቸው፣ የፌኒየስ ቃል እንደ ተቆጠረ አይሆንም። ነገር ግን ስለ «ሞድ፣ ቶድ፣ ትራይጥ» ብዙ አይነት ልዩ ልዩ ተጨማሪ ነጥቦች ይሰጣል፤ እነዚህም በጠቅላላ ብዙ ዓውደ ምንባብ አይሰጡም።

የአመርጊን ክፍል[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ይህ ክፍል (መስመሮች 1028-1101) እንዲህ ይጀመራል፦

«በአመርጊን ግሉንጌል ዘንድ የመመሪያው መጀመርያ ይህ ነው። የዚህ መጽሐፍ ቦታ፣ ቶኹር እንቨር ሞር በሂ ኤነኽግላይስ ኩዓላን ምድር ነው፤ ዘመኑም የሚሌሲየስ ልጆች ዘመን፣ ሰውዬው አመርጊን ግሉንጌል ወልደ ሚሌሲየስ። የተሠራበት ምክንያት፣ የሚሌሲየስ ልጆች ስለ ጠየቁት ነው።
ይህን ቋንቋ ማን ፈጠረ፣ የቱ ጋ ተፈጠረ፣ መቼስ ተፈጠረ? ይህ ከባድ አይደለም። ፌኒየስ በናምሩድ ግንብ ፈጠረው፣ ይህም ከግንቡ በየአቅጣቻው ከተበተኑት ፲ ዓመታት በኋላ ነበር። ወደዚያው ምድር የሄደው ሰው ሁሉ አንዱን ቋንቋ ይናገር ነበር እንጂ ሰው ሁሉ አንድ ዘር አልነበሩም፤ ለምሳሌ የፌኒየስ ተማሪ ካይ ካይንብሬጣኽ፣ ከትምህርት ቤቱ 72 ተማሪዎች አንዱ። እርሱ በልደት ዕብራዊ ነበር፣ ወደ ግብጽም ተላከ። ፌኒየስም በዚያ በግንቡ ቀረ፣ በዚያም ኖረ፣ ትምህርት ቤቱ ከውጭ አገር ካመጡዋቸው ብዙ ልሳናት አንድ ምርጥ ቋንቋ እንዲመርጥላቸው ጠየቁት፤ ቋንቋቸው ለሌሎች ሳይሆን ለራሳቸው ብቻ እንዲሆን፣ ወይም እንደገና ከነርሱ ጋር ለሚማሩት ሁሉ። ያንጊዜ ቋንቋቸው ከብዙ ልሳናት ተመረጠላቸው፣ ከነርሱም ለአንዱ ሰው ተሠየመ፣ እንግዲህ ስሙ በዚሁ ቋንቋ ላይ ነው። ያው ሰው ጋይደል ማክ አንግን ነበር፤ ጋይድል ወይም ጋይሎች ከርሱ ናቸው፣ ከጋይደል ማክ አንግን ማክ ግሉንፊንድ ማክ ላምፊንድ ማክ አግኖማይን ግሪካዊው። ይህ ጋይደል ማክ አንግን ማለት ጋይድል ማክ ኤጠር ነው፤ አባቱ ሁለት ስሞች አንግንና ኤጠር ነበሩትና።»

ከዚህ በኋላ የጋይሊክኛ አናባቢዎች ከሮማይስጥ አናባቢዎች እንዴት እንደ ተሻሉ ለማስረዳት ይሞክራል።

የፈርኼርትነ ክፍል[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ይህ ክፍል (መስመሮች 735-1027) እንዲህ ይጀመራል፦

«የፈኼርትነ መጽሐፍ መጀመርያ። የዚህ መጽሐፍ ቦታ፣ ኤማይን ማኻ። በኮንኾባር ማክ ነሣ ዘመን። ሰውዬው፣ ፈርኼርትነ ባለ ቅኔው። የተሠራበት ምክንያት ድካምና ያልሠለጠኑ ሰዎች ወደ ዕውቀት ለማምጣት ነው። »

ከዚያ በኋላ የጋይሊክኛ ቃላትና ስዋሰው ከሮማይስጥ ቃላትና ስዋሰው እንዴት እንደ ተሻሉ ለማስረዳት ይሞክራል። በዚህ መካከል አንድ ግጥም ስለ ፌኒየስ ፋርሳ ሚስት በላት እንደ ምሳሌ ይሠጣል፦

«በላት፣ የተመረዘው ኔል እናት፤
በሙሉ ከታሠረው ላቲኑስ ልጆች፤
በፀሐይቱ ብሩሕ ቀን ዓረፈች፤
የፌኒየስ ፋርሳይድ ሚስት።»

በዚህ ክፍል መጨረሻ ደግሞ እንዲህ ይላል፦

«እንግዲህ ለፊደል አስፈላጊ የሆነው መነሻው ከ፩፣ ፈጠራ ከ፪፣ ማኖሩ በ፫፣ ማረጋገጡ ከ፬ ጋር፣ በኅብረት መታሠሩ ከ፭ ጋር፣ ማጉለሉ ከ፮፣ አከፋፈሉ ከ፯፣ አገዛዙ ከ፰ ጋር፣ መከሠቱ በ፱፣ መሠረቱ በ፲። ፩ዱ በላይ እሱም ፌኒየስ ፋርሳይድ ነው፤ ፪ቱ ከርሱ ጋር ማክ ኤጠር፤ ፫ኛው ማክ አንግን፤ ፬ኛው ካይ፤ ፭ኛው አመርጊን ማክ ናዕንደ ማክ ነኑዋል፤ ፮ኛው ፈርኼርትነ፤ ፯ኛው ተማሪው፤ ፰ኛው ከንፋላድ፤ ፱ኛው ተማሪው፤ ፲ኛው መሠረቱ በአንድ እሱም ትሬፎካል።»

ይህ ዓረፍተ ነገር ከን ፋላድን (፯ኛው ክፍለ ዘመን ዓም የኖረ) በመጥቀሱ በኮንኾባር ማክ ነሣ ዘመን የተጻፈው አይቻለም።

የኬን ፋላድ ክፍል[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ይህ ክፍል (መስመሮች 1-734) በውነት በኬን ፋላድ (671 ዓም የሞተ) እንደ ተጻፈ ይታመናል። ስለ ጋይሊክኛ ጥያቄና መልስ ያቀርባል፤ ለምሳሌ፦

  • ጥያቄ፦ ጋይደል በየቱ አገር ተወለደ? ከባድ አይደለም፤ በግብጽ ነበር። የትኛው ሥፍራ? ከባድ አይደለም፤ በኡካ ሜዳ በግብጽ ደቡብ-ምዕራብ ክፍል ነበር። ከትምህርት ቤቱ ማን ወደዚያ ሄደ? ከባድ አይደለም፤ ጋይደል ማክ ኤጠር ማክ ቶዕ ማክ ባራኻም፣ የእስኩቴስ ግሪካዊ። ...
  • ጥያቄ፦ ከ72ቱ ልሳናት የቱ በፌኒየስ መጀመርያ ታተመ? ከባድ አይደለም፤ አይርላንድኛ፣ እርሱ ከትምህርት ቤቱ ተመረጠ፣ ከልጅነቱ የታደገበት፣ ከትምህርቱ ቤቱ አዲሱ ነበርና፣ ከልሳናትም ሁሉ የሚግባባ በመሆኑ ምክንያት፣ እሱም መጀመርያው ከግንቡ የመጣ ነበር። ፌኒየስ ከእስኩቴስ ሳይመጣ ዕብራይስጥ፣ ግሪክኛና ሮማይስጥ ነበሩት፤ እና በግንቡ እነዚህን መመሥረት አልነበረበትም፤ ስለዚህም ምክንያት ነው መጀመርያ የታተመው።...
  • ጥያቄ፦ የጋይሊክኛ ቦታ፣ ጊዜ፣ ሰውና ምክንያት ምንድናቸው? ከባድ አይደለም፤ ቦታው፣ የባቢሎን ግንብ፣ በዚያው መጀመርያ ተፈጠረና። ጊዜው የአዳም ልጆች ግንቡን የሠሩበት ጊዜ ነው። ሰውዬው፣ ሳኻብ ማክ ሮኸምሁርኮስ እና ጋይደል ማክ እጠር ማክ ቶዕ ማክ ባራኻም፣ የ እስኩቴስ ግሪካዊ። ምክንያቱ ምንድነው? ከባድ አይደለም፤ የናምሩድ ግንብ መሥራቱ ነው። ሌሎች እንደሚሉ፣ ምክንያቱ ጋይደል ወደ ተወለደበት አገር ሄዶ እሱ መጀመርያ በጽላትና በድንጋይ ላይ «ካልካኔንሲስ» በተባለው ቦታ ስለ ጻፈው ነው። ጋይደል በዚያ ጋይሊክኛ ጻፈ። ...

የጋይሊክኛና የሮማይስጥ ጸባይ በማነጻጸሩ መካከል አንዳንድ ጥቅስ ደግሞ ስለ አፈ ታሪክና ስለ ኦሪት ዘፍጥረት ይነካል፦

  • «በዚያው፣ በናምሩድ ግንብ መሥራት የሆነው። ያው ናምሩድ በጊዜው ከአዳም ዘር ጀግናው ነበር፤ ናምሩድ ወልደ ኩሽ ወልደ ካም ወልደ ኖኅ። ያንጊዜ እስከ ኒኑስ ወልደ ቤሉስ ድረስ በዓለም ላይ ንጉሥ አልነበረም፤ እስከዚያ ድረስ አለቆችና አማካሪዎች ብቻ ነበሩ። እንግዲህ ግንቡ በተሠራበት ወቅት በዓለሙ 72 አማካሪዎች ነበሩ። ከ72ቱም አንዱ ናምሩድ ነበረ። ኃይለኛ ሰው ነበር፣ በማደን ዝነኛ፣ ማለት ለአጋዘንና ለጥንቸል ማደን፤ ደግሞ ዐሣማአዕዋፍን ማጥመድ። እንደዚህ የሰዎች ብዛት ይከተሉትና በሥራዊት በዛ፤ በዚህም ከአማካሪ ሃይለኛ ሆነ። እንዲህ እነዚያ 72 አማካሪዎች በአንዱ ዕቅድ ግንቡን እንዲሠሩ ያዋሀዳቸው እሱ ሆነ፤ ከአባቱ ወንድም ልጅ ልጅ፣ ማለት ከአያቱ ወንድ ልጅ ልጅ ልጅ፣ ከፋሌቅ ወልደ ራግው ወልደ አርፋክስድ ወልደ ሴም ጋር። እርሱም እስከዚያ ድረስ ከ72ቱ አማካሪዎች አንዱ ነበር። ስለዚህ ፋሌቅ አንዱ አማካሪና የሁላቸው ወላጅ እንደ ሆነ ይላሉ። እዚህ አንድ ጥያቀ፣ ግንቡ የተሠራባቸው 72ቱ አማካሪዎች ስሞች ሲሆን፣ ጽሑፎቹ ግን ከነርሱ ከተገነኑ ከ17 ሰዎች በቀር አይዘርዝሩዋቸውም፤ እነርሱም ፋሌቅ፣ ናምሩድ፣ ኤቦር፣ ላቲኑስ፣ ሪፋት ስኮት፣ ናብጎዶን፣ አሦር፣ ኢባጥ፣ ሎንግባርዱስ፣ ቦድቡስ፣ ብሪቱስ፣ ጌርማኑስ፣ ጋራጥ፣ ስኪቲዩስ፣ ጎቲዩስ፣ ባርዳኒዩስና ሳርዳይን ናቸው። ያም ሆነ ይህ ከማየ አይኅ በኋላ መጀመርያው ንጉሥ እንደ ተፈጥሮ ናምሩድ ሆነ። መጀመርያው ንጉሥ እንደ ጥበቡ ያው ፋሌቅ ነበረ። እንደ ሥልጣኑ ግን፣ ኒኑስ ወልደ ቤል ወልደ ፕሎስክ ወልደ ፕሉሊሪስ ወልደ አጎሞሊስ ወልደ ፍሮኖሲስ ወልደ ጊትሊስ ወልደ ቲራስ ወልደ አሦር ወልደ ሴም ወልደ ኖኅ ነበረ። ... እግዚአብሔርም አደናግራቸው፣ አንዱ «ድንጋይ አምጣልኝ» ሲል ሌላው እንጨት ያምጣው ነበር፤ ማለት ሬንጁ የተሠራበት ዕንጨትና ድንጋይ ሲጠያይቁ ነበር። ከነዚህ ድርጊቶች ትንሽ በኋላ መምኅራን ከእስኩቴስ መጥተው በግንቡ ላይ የነበሩትን ብዙ ልሳናት ለመማር ፈለጉ፤ የአዳም ልጆች ብዙ ልሳናት ከተበተኑበትና ከተፈጠሩበት ቦታ በዚያ በፍጹምነት እንደሚቅሩ ስለ መሠላቸው ነበር። ስለዚህ ወደ ሰናዖር ሜዳ ወደ ግንቡ ቦታ፣ ወደ ኡክና ሜዳ ወደ ዶራም ሜዳ በሰናዖር ሜዳ ስሜን- ምዕራብ በኩል ሄዱ፣ የግንቡ ሥፍራ ልዩ ስያሜ ነበር። የመምህራን ቁጥር 75 ነበር፤ አንዱ ለየቋንቋና ሦስት ጠቢባን፣ አንዱ ጠቢብ ለያንዳንዱ ከሦስት ዋና ዋና ልሳናት፣ ማለት ዕብራይስጥ፣ ግሪክና ላቲን። 74 ልሳናት፣ እያንዳንዱ ቋንቋ፣ ከዚያ ተበተኑ።
ፌኒየስ ፋርሳይድ የአለቆቻቸው ስም ነበር፤ እሱም ከስሜኑ ከእስኩቴስ እንኳ ሳይመጣ በዋና ዋና ልሳናት ጠቢብ ነበር። የእኒዚህ ሦስት ልሳናት ብልጫ የተነሣ በነርሱ ከተጻፉት ጽሑፎች ብዛት ነው፤ ከልሳናትም ሁሉ ስለ ተደባለቁ ነው፤ ወይም እንደገና በመስቀሉ ሳንቃ ላይ ከነርሱ ፫ ስለ ተጻፈው ጽሑፍ ይሆናል። ፌኒዩስ በግንቡ ለቋንቋ ፍጹምነትን ስላላገነ፤ ትምህርት ቤቱንና ደቀ ማዛሙርቱን ወደ ውጭ አገር ወደ ምድር ከተሞችና ግዛቶች በየበኩሉ ቋንቋዎቹን እንዲማሩ በተናቸው፤ እንዲህ ሰባት ልሳናት እየተማሩ ፌኒየስ በምግብም በልብስም ያሳደጋቸው ነበር። ፌኒየስም በግንቡ ቀረ፣ እዚያም ተማሪዎቹ ከየአቅጣቻው እስከመጡለት ድረስ ኖረ፤ በዚያም ዘመን ላይ የዓለምን ዘሮች በግንቡ ያስተምራቸው ነበር። እንግዲህ በመጽሐፉ ይዘት ፌኒየስ እራሱ በዚያ በግንቡ እንደ ቀረና በዚያ ኖረ ብሏል። ለሎች ጸሐፊዎች እንደሚሉ፣ ግሪኮች ከያዋን ወልደ ያፌት ወልደ ኖኅ ልጆች ተነሥተው ፌኒየስም ከነርሱ ተነሥቶ ሲሆን በግንቡ መሥራት ከነርሱ ማንም አልነበረም። ...
  • ጥያቄ፦ የፌኒየስ ትውልድ ምንድነው? ከባድ አይደለም። ፋርሳይድ ወልደ ባዓጥ ወልደ ማጎግ ወልደ ያፌት ወልደ ኖኅ። ወይም፣ ፌኒየስ ፋርሳይድ፣ ወልደ ዮጋን ወልደ ግሉንፊንድ ወልደ ላምፊንድ ወልደ ኤጠር ወልደ አግኖማይን ወልደ ቶዕ ወልደ ቦንብ ወልደ ሰምህ ወልደ ማር ወልደ ኤጠኽት ወልደ አውርጠኽት ወልደ አቦድ ወልደ አዎይ ወልደ አራ ወልደ ያራ ወልደ ኤስሩ ወልደ ስሩ ወልደ ቦዓጥ ወልደ ሪፋት ወልደ ጋሜር ወልደ ያፌት ወልደ ኖኅ። በተረፈ ፌኒየስ እስኩቴሳዊ ነው፤ እስከርሱም ድረስ የእስከቴስና የጎጦች ትውልዶች ደረሱ። ሁላቸውም ከኖኅ ዘር ነበሩ። ግንቡ መቸም ሳይሠራ በዓለም ውስጥ የነበረው ቋንቋ ዕብራይስጥ ነው፤ እርሱም ከዕለተ ደይን በኋላ የሚሆነው ነው፤ አንዳንድም የሰማይ ልጆች ቋንቋ እንደ ሆነ ይል ነበር።... ፌኒየስ ፋርሳይድ ማክ እውገኒየስ፣ ያር ማክ ነማ እና ጋይደል ማክ ኤጤር እነኚህን ልሳናት የመረጡት ሦስት ጠቢባን ናቸው፤ በዮቴናም ወይም አቴና ከተማ ተፈጠሩ።»

ከዚህ ቀጥሎ 72ቱን ልሳናት የተናገሩትን 72 ብሔረሠቦች ይዘርዝራል። እነዚህ ስሞች ግን የተገኙ ከብሉይ ኪዳን ሳይሆን ከባለ ቅኔው ሉክረጥ ሞኩ ኺያራ ግጥም ነው፤ እሱም የወሰዳቸው ከኢሲዶር ዘሰቪላ መጽሐፍ ኤቲሞሎጊያይ ሲሆን በቀድሞ የሮሜ መንግሥት ክፍላገሮችና ሌላ መናርያዎች ዝርዝር ነው። ከነዚህ 25 የተላቁት መሪዎች ስሞቻቸውን ለኦጋም 25 ፊደላት የሰጡ ናቸው፣ እነርሱም፦ ባቤልሎጥፈርዖን፣ ሳልያጥ፣ ናብጋዶን (ናቡከደነጾር)፣ ሄሮድዳዊት፣ ታላሞን፣ ካይ ካልያፕ፣ ሙይርያጥ፣ ጎትሊ፣ ጋሜር፣ ስትሩ፣ ሮቤልአኻብ፣ ኦይሰ፣ ኡሪጥ፣ ኤሡ፣ ያቂም፣ እጥሮቅዮስ፣ ዊሜሊኮስ፣ ዩዶንዮስ፣ አፍሪም እና ኦርዲኔስ እንደ ተባሉ ይላል። ሆኖም «ሌሎች አልፋቤት በአካያ፣ የኦጋምም ፊደላት በአመርጊን ማክ ሚሌሲዩስ በአይርላንድ እንደ ተፈጠሩ ይላሉ።»

ተጨማሪው ክፍል[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የውጭ መያያዣ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]