አባል:እስክንድር መርሐጽድቅ

ከውክፔዲያ

የአዲስ አበባን ቁልፍ የዛሬ 30 ዓመት ተረክቤ ነበር

በእስክንድር መርሐጽድቅ

ደርግ በ1979 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ረፐብሊክ (ኢሕዲሪ)ን ለመመስረት በሀገር አቀፍ ደረጃ ተፍ ተፍ ካለባቸው ዝግጅቶች መካከል የስነ-ጽሑፍ እና የጥያቄና መልስ ውድድሮች ይገኙበታል። ለዚሁ የበቆጂ ከተማ በፊናዋ ስትዘጋጅ በሁለቱም ዘርፎች ከቀበሌ 02 አንደኛ በመውጣት ከ01ዱ ተወካይ ሻረው ሙሉነህ ጋር ለመጨረሻው ውድድር መስከረም 2/1980 ዓ.ም. በ14ኛው የአብዮት በዓል ቀን ስቴዲየም ውስጥ የከተማም፣ የገጠርም ሕዝብ ግጥም ብሎ በሞላበት ፍጥጫው ተጀመረ።

የግጥም ውድድሩን በሰፊ የነጥብ ልዩነት በአንደኛነት ሳሸንፍ የጥያቄና መልሱ ላይ አንገት ለአንገት የመያያዝ ያህል ልንላቀቅ አልቻልንም። ኋላ ላይ ለሁለታችንም አንድ አንድ ጥያቄ እየቀረበ ስንመላለስ ቆይተን የመጨረሻዋ የለየችን ጥያቄ ቅድሚያ ለሻረው ቀረበች።

"ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት የታወጀው መቼ ነው?" ሲባል ሻረው ዝም አለ። የተያዘለት ጊዜ ተጠናቀቀና፣ "እሺ እስክንድር?" ስባል በሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍሎች የፖለቲካ ትምህርት የሸመደድኋትን ከአዕምሮዬ አውጥቼ ጠያቂው ስሜን ጠርቶ የአባቴን ስም ሊያስከትል ሲል፣ "ሚያዝያ 12/1968 ዓ.ም." አልኩ። ይኼኔ አስራት ተፈራ የተባለ የቀበሌያችን ሊቀ-መንበር ከየት መጣ ሳልለው አንገቴ ላይ ተጠመጠመ። አንድ ሰውዬ ግን 10 ብር አንጠልጥለው ወደ እኛ ሲሮጡ በደስታ ተንቀጠቀጥሁ። መድረክ ላይ ወጥተው ያደረጉት ግን ሞራሌን የነካ እና ዛሬም ድረስ ሳስበው "የሰው ነገር" ያሰኘኛል። ሰውየው ለካ በወቅቱ ከቤተሰብ ጋር በሥራ አጋጣሚ በተከሰተ ግጭት ቂም ይዘው ነበር። እናም፤ 10ሩን ብር ወስደው ሁለተኛ የወጣው ሻረው ግንባር ላይ ለጠፉት። በድርጊቱ እኔ እና ሕዝቡ መሀል የነበሩት ወላጆቼ ክው ብለው ሲቀሩ ሕዝቡ የሽሙጥ ጩኸት አሰማ። (በነገራችን ላይ፤ እንዲህ አይነት አጋጣሚ አሁን ያለሁበት መ/ቤትም ገጥሞኝ ነበር፤ "የመዋቅር ማሻሻያ" ሲሠራ ቱሪስቶች ነበሩና ጉብ ያሉት)

"የመዋቅር ማሻሻያ" ሲባል ሁሌ አንድ ነገር ይታወሰኛል። የማሻሻያ ኮሚቴ አባላት የራሳቸውን ፍራሽ በመዋቅሩ ያደላድላሉ፤ የሚጠሉትን ሰው ክፍል ያፈርሳሉ ወይም ደረጃውን ከመምሪያ ወይም ከዳይሬክቶሬት ወደ ቡድን ዝቅ ያደርጋሉ። ይህ ሳይበቃቸው ጓደኞቻቸውን ወይም አለቆቻቸውን በሀሳብ የተገዳደሩትን ሀቀኞች ወይም ምስኪኖች በራሳቸው ተነሳሽነት ወይም በነዚያ አሳሳቢነት ጥጋቸውን ያስይዙላቸዋል። ከኮሚቴው መሀል፣ "ኧረ ይኼ ነገር ትክክል አይደለም" የሚል ካጋጠመ ወይ፣ "የማታውቀው ነገር ስላለ ነው" ይሉታል፤ አሊያም መፈብረክ በተካነ አነካኪነታቸው ጥፋት ፈጥረው ይፈነግሉታል። ምክንያቱም፤ ሀገሩ ኮሚቴ ግመልን ያጎበጠበትና ንጉሡ በላይ ዘለቀን ገድለው ባንዳን የሾሙበት መሆኑን እናውቃለንና!

እናም፤ መጨረሻ ላይ ማዘጋጃ ቤቱ 15 ብር፣ የአጠቃላይ ሳይንስ /General science/ መጽሐፍ እና የማርክስ፣ ኤንግልስና ሌኒን ታሪኮችን የያዙ ሦስት መጻሕፍት ሸለመኝና ወደ ቤት እንዳዘንሁ ሄድሁ። ቤት ስደርስ መላ ቤተሰባችን፣ "አኮራኸን!" ብለው በየተራ ይስሙኝ ጀመር። ከዚያም፣ "ቁጭ በል" ተብዬ፣ "ዛሬ ሕዝብ ፊት ስላኮራኸን አዲስ አበባ ገብተህ እንድትማር ወስነናል" ብለው የከተማዋን ቁልፍ ሸለሙኝ። ከዚያ በኋላማ ማን ይቻለኝ፤ እንኳን አዲስ አበባ መማር፤ ሄዶ መምጣትም በጓደኞቻችን ዘንድ ያስኮራ እና ያስከብር ነበረና እየበረርሁ፣ "አዲስ አበባ ልማ...ር ነው" ብዬ ከተማዋን "እንቁልልጬ" አልኳቸው። ይኸው ከዚያ ጊዜ ጀምር አዲስ አበባን ላለፉት 30 ዓመታት በያዝኩት ቁልፍ ስቆልፋት እና ስከፍታት እየኖርሁ እገኛለሁ።

የፈተና ነገር ካነሳሁ በ1973 ዓ.ም. ቀልጦልኝ የነበረውን ጭብጨባ ላክልላችሁ። 1972 ዓ.ም. ክረምት ላይ በርካታ ህጻናት በበላቸው አካሉ አማርኛን እና በአስቴር ሳህሌ ሒሣብን በመጀመሪያው ዙር የመሠረተ-ትምህርት ዘመቻ ተምረን ነበር። ያ ሁሉ ውሪ ፈተና ተሰጠውና ውጤቱ ሲመጣ አንደኛ በመውጣቴ የት/ቤቱ ተማሪዎች ግራና ቀኝ እያጨበጨቡልኝ ደብል እንድመታ ተደርጌ አንደኛን ሳልማር ከዜሮ ወደ ሁለተኛ ልዛወር ችያለሁ። ፎቶው በዚያ ዓመት አዲስ አበባ ስገባ አንድ ልደት ላይ የተነሳሁት ነው።

ነገርን ነገር ያነሳዋል አይደል? "ልደት" ስል አንድ ነገር ታወሰኝ። ያኔ በቆጂ ልደት የሚከበረው እነ ጋሽ አምቤ ወይም ቤተ ፎቶ ቤት ተሂዶ ነው። ህጻኑን/ኗን ጠረጴዛ ላይ ያወጡና ከፊት ሻማ እየተበራ ፎቶ ገጭ ነው። ሻማዎቹ እንደ ቅልጥጤዎቹ አዲሳቦች ብዛታቸው በዕድሜ ልክ አልነበረም፤ ለሁሉም አንድ ብቻ'ጂ! እሷም እንዳታልቅ የጋሽ አምቤ ልጆች እነ ገነት እና ጌጤ እንዲሁም ደሱ ቶሎ ለማጥፋት ሲያጠዳድፉን ለጉድ ነበር፤ አንዷ ሻማ ለመቶ ምናምን ውሪዎች ልደት ታገለግል ነበረና! አሴ እና ከርሱ በኋላ የመጡት ግን ለፎቶ ቤቷ በነሱ እግር ሲተኩ በየቤቱ እየሄዱ ማንሳት እንደጀመሩ አውቃለሁ። ዛሬማ ሁሉ ነገር የግሎባላይዜሽንን ጠበል ተጠምቆ እንኳን በቆጂ እልም ያለው ገጠርም ፎቶውን በሞባይል ስልኩ፤ ልደቱን ደግሞ በብዙ ወይም በዕድሜው ልክ በተፈበረኩ ሻማዎች ኬክም ይሁን ዳቦ ቆልሎ የሀገር ውሪ እያንጫጫ ያደለው ውስኪና ሻምፓኙን፤ እነ እማማ ጌጤ ደግሞ ጠላቸውን እያራጩ ማሳለፉ ላይ ደርሰዋል።

ግን ግን፤ አነ ጋሽ አምቤ የአብዮቱንም፣ የየልደቱንም ፎቶዎች አሁን ይኖሯቸው ይሆን? ካሉ ልጆቻቸው አውሱንና ትዝታዎችን እየጻፍን ዘና እናድርግባቸው።

የፎቶ ነገር ሆኖ አንድ ነገር አስታውሼ ልቋጭ፡፡ ያኔ ፎቶዎቹ ከስቱዲዮ ውጪ ሲነሱ አንሺው ከአናት የሚመጣውን ብርሐን ለመከላከል በኮት በመሸፈን ነበር፡፡ እንደዚያ የተነሳው ፎቶ የሚታተመው (በዚያን ጊዜ አባባል ‹‹የሚታጠበው››) ጨለማ ቤት ውስጥ ፊልሙ ከካሜራው ወጥቶ በዚያው ጨለማ በኬሚካል ተነክሮ ነው፡፡ ከዚያ፤ በመቆንጠጫ ፀሐይ ወይም ነፋሻ ቦታ ላይ እንደ ልብስ ይሰጣል፡፡ የአስቸኳይ ለከፈለ ደግሞ ፊልሙ በከሰል ላይ ሙቀት ተሰጥቶት ይደርስለታል፡፡ ኋላ ላይ ደግሞ ከለር ፎቶ ሲመጣ ለተነሺ ደርሶ የሚሰጠው ከአንድ ሳምንት ወይም ከ15 ቀናት በኋላ ነበር፡፡ ምክንያቱም፤ የሚታጠበው አዲስ አበባ ተወስዶ ነውና! እዚያ ደግሞ ማሽናቸው አንድ ሊሆን ይችላልና ወረፋ እስኪደርስ አንድ ሳምንት ሊወስድ ይችላል፡፡ ማሽኖቹ እንዲህ እንደዛሬ በሰከንድ እያከታተሉ የሚያወጡም ስላልነበሩ ቆይታውን ያራዝሙታል፡፡