የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል (ኢትዮጵያ)

ከውክፔዲያ

የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል (ሳ.ቴ.መ.ማ.)፣ ኢትዮጵያ (English፡ Science and Technology Information Center) የሳይንስቴክኖሎጂ መረጃዎችን የመሰብሰብ፣ የመምረጥ፣ የመተንተንና እሴት አክሎ የማሰራጨት ኃላፊነት የተጣለበት የመንግስት ድርጅት ነው።

የአመሰራረት ታሪክ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔራዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃዎች ስብስብ ማዕከልን ለማቋቋም የመጀመሪያውን ሀሳብ የወጠነው በ1977 እ.ኤ.አ. የኢትዮጵያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን (ኢ.ሳ.ቴ.ኮ) ነበር። ኢኒስቲቲዩቱ የተመሰረተበት ዋነኛ ዓላማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃዎችን ለመሰብሰብ፣ ለማደራጀት እና ለማሰራጨት የሚያስፈልጉ የተለያዩ አገልግሎቶችንና መገልገያ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ነው። ዋና መቀመጫውን አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ ልዩ ስሙ ቡልጋሪያ ማዞሪያ ያደረገው የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል (ሳ.ቴ.መ.ማ) በማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 257/2004 የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃዎችን በማፈላለግ፣ በመሰብሰብ፣ በመመምረጥ፣ በማደራጀት፣ በመተንተን እና በጥናትና ምርምር እሴት ጨምሮ በማሰራጨት የሀገሪቱን የቴክኖሎጂ ሽግግር ሂደት የማፋጠን ተልዕኮን በመያዝ የተመሰረተ ነው።[1]

የማዕከሉ ስትራቴጂክ መሰረቶች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ በመንግስትና በሕዝብ የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በላቀ ብቃት ለማሳካት የተልዕኮ አፈፃፀም አቅጣጫ ጠቃሚ ኮምፓሶች የሆኑት ራዕይ፣ ተልዕኮ፣ እሴቶችና ተቋማዊ ፍልስፍናዎች (ስትራቴጂክ መሰረቶች) ያስፈልጉታል። በመሆኑም የማዕከሉ ስትራቴጂክ መሰረቶች እንደሚከተለው ቀርቧል።[2] ራዕይ

• በ2015 ዓ.ም የኢንፎርሜሽን ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ልዕቀት ማዕከል ተገንብቶ ማየት፤ ተልዕኮ

• ቴክኖሎጂን ለልማት ለመጠቀም በሚደረግ ጥረት ዘላቂ የኢንፎርሜሽን ምንጭ መሆን፤

እሴቶች

• የባለቤትነት ስሜት

• መደመር

• ተማሪነት

ተቋማዊ ፍልስፍና

• መረጃችን ለሀገራዊ ቴክኖሎጂ ምጥቀት፤

• ተቋማዊ ልዕቀታችን በሰው ኃይላችን፤

• እሴት በማከል እንተማለን፤


ተቋማዊ አወቃቀር ዳይሬክቶሬት

• የምርምርና ትንተና ዳይሬክቶሬት

• የእውቀት አስተዳደርና ስርጭት ዳይሬክቶሬት

• የኢንፎርሜሽን መሰረተ ልማት ዳይሬክቶሬት

	የኢትዮጵያ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ፖሊሲ

የኢትዮጵያ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ፖሊሲ በ2004 ዓ.ም የፀደቀ ሲሆን ሀገሪቷ ውጤታማ የሆኑ የውጭ ቴክኖሎጂዎችን ለማፈላለግ፣ ለመምረጥ፣ ለማስገባት እንዲሁም ለመጠቀም የሚያስችላትን ሀገራዊ የኢኖቬሽን ስርዓት ለመፍጠርም ያለመ ነው። የፖሊሲው ዓላማ ውጤታማ የሆኑ የውጭ ቴክኖሎጂዎችን በማፈላለግ፣ በመምረጥ እና በማስገባት በማምረቻና በአገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ የመማር፣ የማላመድ እና የመጠቀም ሀገራዊ አቅም ለመገንባት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕቀፍ መፍጠር ነው። የሀገሪቷን የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ችግሮች ጥናትና ምርጥ ተሞክሮ ያላቸው የሌሎች ሀገራት ሁኔታ ላይ የዳሰሳ ጥናት የተካሄደ ሲሆን በዚህም መሰረት አስራ አንድ ወሳኝ የፖሊሲ ጉዳዮች ተለይተዋል። እነዚህም፡- የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የሰው ሀብት ልማት፣ የማምረቻና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ምርምር፣ የፋይናንስ ሥርዓትና ማበረታቻ ሥርዓት፣ ብሔራዊ የጥራት መሰረተ ልማት፣ የዩኒቪርሲቲዎች፣ የምርምር ተቋማት፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማትና የኢንዱስትሪ ትስስር፣ የአዕምሯዊ ንብረት ሥርዓት፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ፣ የአካባቢ ልማትና ጥበቃ እንዲሁም ዓቀም አቀፍ ትብብር ናቸው። ሀገራዊው የኢኖቬሽን ሥርዓት አስተዳደር መዋቅር የፖሊሲውን አፈፃፀም ለመምራት፣ ለመደገፍ እና ለመከታተል እንዲያስችል ተዘርግቷል። የኢኖቬሽን ሥርዓቱ ዋና ዋና ተዋናዮችም፡- ሀገራዊው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምክር ቤት፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ሌሎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እንዲሁም የኢኖቬሽን ድጋፍና የምርምር ሥርዓት ናቸው።

የኢንፎርሜሽን ስርጭት[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል አንዱ ቁልፍ ተግባር እሴት የታከለባቸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃዎችን ማሰራጨት ሲሆን እነዚህን መረጃዎች ለማሰራጨት ማዕከሉ የተለያዩ የማሰራጫ ስልቶችን ይጠቀማል። ከስልቶቹ መካከል የቴሌቪዥን ስርጭት፣ ድረ-ገፅ ወይም የሳይበር እና የህትመት ሚዲያን ይጠቀማል። ማዕከሉ በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ቴክ-ሳይንስ የተሰኘ መጽሐፍን በሶስት ወር አንድ ጊዜ የሚያሳትም ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በሳምንት አንድ ቀን ለ30 ደቂቃ ቆይታ የሚያደርግ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አለው። ይህ የቴሌቪዥን ፕሮግራም በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢ.ቢ.ሲ) የቴሌቪዥን ጣቢያ የሚሰራጭ ነው። ሌላው መረጃ የማሰራጫ ስልት የሳይበር ሚዲያ ሲሆን ማዕከሉ የራሱ የሆነ ድረ-ገፅን (http://stic.gov.et/ Archived ጃንዩዌሪ 22, 2015 at the Wayback Machine ወይም http://stic.et Archived ኖቬምበር 17, 2019 at the Wayback Machine) ይጠቀማል። ይህ ድረ-ገፅ በየቀኑ ከዓለማችን የተሰበሰቡና እሴት የታከለባቸው የተለያዩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዜናዎችን የያዘ ሲሆን በተጨማሪም የተለያዩ የምርምር ጥናቶችንና ህትመቶችን የያዘ ነው።

የሳይንስና ቴክኖሎጂ አመላካቾች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የሳይንስና ቴክኖሎጂ አመላካቾች ስለ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ስርዓት፣ ዉስጣዊ መዋቅር፣ ከኢኮኖሚና ከማኅበረሰብ ጋር ስላለው ትስስር እንዲሁም ስርዓቱን የሚያስተዳድሩ አካላት፣ በውስጡ እንቅስቃሴ ለሚያደርጉ እና ስርዓቱ ተፅዕኖ ለሚያደርስባቸው አካላት ጥያቄዎችን የሚመልሱ ተያያዥነት ያላቸው መረጃዎች ናቸው። ይህ የሚያመላክተው በብሔራዊ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ስርዓት ላይ የሚመጣ ለውጥ በአምራችና አገልግሎት ሰጪ (የንግድ ተቋማት)፣ ተመራማሪዎች፣ የመንግስት ኤጀንሲዎች፣ በዘርፉ የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት መካከል ያለ ትስስርና ግንዛቤ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንደሚያመጣ ነው።

የምርምርና ስርፀት ሰርቬይ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ምርምርና ስርፀት አንዱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አመላካች ነው። ይህ አመላካች አዲስ ግኝቶችን ለመፍጠር የሚያስችሉ የዕውቀት ክምችትን እድገት፣ ከግለሰቦች የሚገኝን፣ ከባህልና ከማኅበረሰብ የሚገኝን እውቀት የሚያካትት እንዲሁም የዕውቀት ክምችትን መጠቀምን የሚያጠቃልል ነው። የመጀመሪያው ብሔራዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አመላካች ዳሰሳ ጥናት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በ2010 እ.ኤ.አ. የተካሄደ ሲሆን በ2013 እ.ኤ.አ. ሳ.ቴ.መ.ማ ኃላፊነቱን ወስዶ ሁለተኛውን ብሔራዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አመላካች ዳሰሳ ጥናት በማከናወን የጥናቱን ውጤት በ2014 እ.ኤ.አ. አውጥቷል። ዳሳሳ ጥናቱ ሀገሪቱ በምርምርና ስርፀት ላይ ያላትን ኢንቨስትመንትና የሰው ኃይል አግባብ በአራት ዘርፎች ከፋፍሎ የሚያሳይ ጥናት ነው። የመንግስት ተቋማት፣ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የቢዝነስ ተቋማት እና የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጥናቱ የዳሰሳቸው ዘርፎች ናቸው። በ2014 እ.ኤ.አ. የታተመው ጥናት በዋነኛነት ሀገሪቱ ለምርምርና ስርፀት የምታወጣው ወጪ ከሀገሪቱ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ምን ያህል እንደሆነ ለመጠቆም ነው። ከጥናቱም የተገኘው ውጤት እንደሚያመለክትው የምርመርና ስርፀት ወጪ የሀገሪቱን አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት 0.6 በመቶ ነው። ይህም በአፍሪካ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት 1 በመቶ የሚሆነውን ወጪ ለምርምርና ስርፀት ማዋል ተብሎ የተቀመጠውን አቅጣጫ የሳተ ውጤት እንዳልሆነ ለመገንዘብ ተችሏል። በተጨማሪም በ2010 እ.ኤ.አ. ከተከናወነው ጥናት ውጤት ጋር ሲነፃፀር አመላካቹ (0.24 በመቶ) በ3 እጥፍ እድገት አሳይቷል።

የኢኖቬሽን ሰርቬይ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ኢትዮጵያ ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገርና የተጀመረውን የልማት ጎዳና ቀጣይነት ባለዉ መልኩ ለማስኬድ እውቀት መር ኢኮኖሚ ልትከተል ይገባል። በእውቀት መር ኢኮኖሚ ኢኖቬሽን ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ይህንንም በመገንዘብ በሀገሪቱ ውስጥ ያለዉን የኢኖቬሽን ደረጃ ለመገንዘብና ተቋማት ለኢኖቬሽን እንቅስቃሴዎች የሚያወጡትን ወጪና ከተለያዩ ተቋማት ጋር እውቀትንና ክፍሎትን ለማዳበር የሚያደርጉትን ግንኙነቶች ለመረዳት እንዲሁም ዘርፉን ለማስተዳደር የሚችል ፖሊሲ ለመቅረፅ በ2007 የመጀመሪያውን የኢኖቬሽን ሰርቬይ ለማካሄድ ታቅዷል። ይህንንም እንዲያከናውን የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል ሙሉ ሀላፊነት ተጥሎበታል። ማዕከሉ የንግድ ተቋማትን እንደዋነኛ የጥናት ክፍል በመውሰድ በአራት ዘርፎች ላይ፣ ከዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ የፌደራል ከተማ መስተዳድሮች ውስጥ በናሙና የተመረጡ ተቋማት በሚያመርቷቸው ምርቶች ላይ፣ ከአመራረት ሂደት አንፃር፣ ከተቋም አስተዳደር እና ከግብይት ስርዓት አንፃር የሚያከናውኗቸው ኢኖቬሽኖች ላይ ጥናት ሊያከናውን አቅዷል። ተቋሙ ጥናቱን በሀምሌ 2006 ጀምሮ በሰኔ 2007 ዓም የሚያጠናቅቅ ሲሆን አሁን ማለትም በሚያዚያ ወር ላይ የጥናቱ 90 በመቶ ተገባዷል።

ቢብሎሜትሪክስ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የሳይንስና ቴክኖሎጂ አመላካች ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ ሌላው ቢብሎሜትሪክስ ነው። ቢብሎሜትሪክስ የጥናታዊ ፅሁፍ ህትመቶችንና ማጣቀሻዎቻቸውን አህዛዊ ትንተናና ስታስቲክስን በመጠቀም የሚለካ ነው። ቢብሎሜትሪክስ ስታትስቲካዊ ትንተና በመጠቀም የማጣቀሻና የቃላት ድግግሞሽ ትንተና በማከናወን መረጃዎች አቅጣጫ ማግኘት ነው። የህትመቶችንና የማጣቀሻዎቻቸውን አህዛዊ ልኬትን በመጠቀም መለካት በመላው ዓለም ጥቅም ላይ እየዋለ ያለ አካሄድ ነው። ቢብሎሜትሪክስ የጥናቶችን አቅም ለመለካት ጥቅም ላይ ይውላል። ቢብሎሜትሪክስን የጥናቶችን አቅም ለመለካት ከሚጠቀሙ መካከል ዩኒቨርሲቲዎችና የመንግስት ላቦራቶሪዎች፣ ፖሊሲ የሚቀርፁ አካላት፣ የምርምር ዳይሬክተሮችና አስተዳደሮች፣ የመረጃ ልዩ ሙያተኞች እና ላይብረሪያኖች እንዲሁም የምርምር ባለሙያዎች ዋነኞቹ ናቸው። እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ የቢብሎሜትሪክስ ትንተና በሀገሪቱ የጥናት ባለሙያዎች አልተከናወነም። የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል በ2014 እ.ኤ.አ. የቢብሎሜትሪክስ ትነተና ለማከናወን ዕቅድ ይዟል።

የአይ.ሲ.ቲ ሲስተሞች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

• ዌብ መሰረት ያደረገ የሰው ኃይል አውቶሜሽን ሲስተም

በማዕከሉ ውስጥ የሚኖረው የሰው ኃይል አስተዳደር ስራ የተማከለና በአንድ መስኮት የሚከናወን ለማድረግ ምቹ የሆነ፣ የሰራተኞችን ማህደር በመያዝ ሰራተኞች የግል መረጃዎቻቸውን ማየትና ማስተካከል እንዲችሉ የሚረዳ ሲስተም ነው።

• ዌብ መሰረት ያደረገ የእውቀት አስተዳደርና ኢለርኒንግ ሲስተም

በማዕከሉ በሚገኙት ሰራተኞች ዉስጥ የሚኖርን እውቀት ተደብቆ እንዳይቀር እርስ በእርስ የመማሪያና የእውቀት መገበያያ መድረክ በመሆን የሚያገለግል ሲስተም ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ መንገዶች የተሰበሰቡ እውቀቶችን ከማዕከሉ ዉጪ ለሚገኙ ተጠቃሚዎች ለማጋራት አመቺ ስፍራ የሚፈጥር ሲስተም ነው።

• የመረጃ ማነፍነፊያ ሲስተም

ይህ ጎልጉል የተሰኘው የመረጃ ማነፍነፊያ (Search Engine) ሲሆን መንግስት ትኩረት በሰጠባቸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች መረጃዎችን ኢንዴክስ በማድረግ የተጠቃሚዎችን የመረጃ ጥማት ለማርካት የተበለፀገ ሲስተም ነው።

• የብሔራዊ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዲጂታል ላይብረሪ ሲስተም

መንግስት ትኩረት በሰጠባቸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ መስኮች ዙሪያ የሚገኙ መጽሐፍትን ተጠቃሚዎች ባሉበት ቦታ ሆነው በኢንተርኔት እንዲያገኙ የሚያስችል ሀገራዊ ይዘት የተላበሰ ሲስተም ነው።

• ዌብ መሰረት ያደረገ የአዕምሯዊ ንብረት ሲስተም

በቴክኖሎጂ ሽግግሩ መንግስት ትኩረት በሰጠባቸው የትኩረት መስኮች የተሰበሰቡ የፓተንት መረጃዎች ለስራ ፈጣሪዎችና ተመራማሪዎች በሚያመችና ቀላል በሆነ ሀገራዊ ይዘትን በተላበስ መንገድ ማግኘት እንዲቻል የተበለፀገ ሲስተም ነው።

• የOCR (ኦፕቲካል ካራክተር ሪኮግኒሽን) ሲስተም

በህትመት መልክ የሚገኙ አማርኛን ጨምሮ በሌሎች ቋንቋዎች ያሉ ማንኛውም አይነት መረጃዎች ስካን ከተደረጉ በኋላ በቀላሉ በኮምፒውተር አማካኝነት መረዳትና መነበብ እንዲሁም ኤዲት መደረግ እንዲችሉ የሚያግዝ ሲስተም ነው። • የማዕከሉ ድረ-ገፅ

በማዕከሉ የሚገኙትን ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂያዊ እውቀቶችና ትኩስ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዜናዎችን ተደራሽ ለማድረግ ማራኪ ገፅታን ተላብሶና የተጠቃሚዎችን ፍላጎት መሰረት አድርጎ በአማርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ድረ ገፅ ነው።

• የማዕከሉ የውስጥ መገናኛ ኢንተርናል ፖርታል

ይህ የዉስጥ ለዉስጥ መገናኛ በማዕከሉ ዉስጥ የሚገኙ ሰራተኞች የማዕከሉን መተዳደሪያ ሕግና ደንብ፣ ፖሊሲና መመሪያዎች እንዲሁም ማስታወቂያዎች በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችል፣ የማዕከሉን ወቅታዊ የስራ ሂደትና የሰራተኞች የአፈፃፀም ደረጃ የሚያሳይ ሲሆን በተጨማሪም ሰራተኞች እርስ በእርስ የሚኖራቸውን የስራ ግንኙነት በይበልጥ ለማጠናከር የሚያግዝ ሲስተም ነው።

• ዌብ መሰረት ያደረገ BSC ሲስተም

ይህ አውቶሜትድ የውጤት ተኮር ምዘና ሲስተም የማዕከሉን፣ በማዕከሉ ውስጥ የሚገኙ የስራ ሂደቶችን፣ የቡድን መሪዎችና ግለሰቦች ስራዎቻቸውን የሚያቅዱበት፣ አፈፃፀማቸውን የሚመዘግቡበትና የአፈፃፀም ምዘና ሪፖርት ማግኘት የሚችሉበት ያለምንም ሰው ጣልቃ ገብነት በኮምፒውተር አማካኝነት የሚከወን የተማከለ ሲስተም ነው።

ቴክኖሎጂ ትንተናና ትንበያ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል ስር ከሚገኙት ዋና ዋና የስራ ሂደቶች ዉስጥ አንዱ ሲሆን በዋነኝነት ቴክኖሎጂዎችን ከማህበረ-ኢኮኖሚያዊ፣ ከባህል፣ ከዝግጁነት፣ ከአካባቢ፣ ከስጋት፣ ወደፊት ከሚያስከትሉት ተፅዕኖ እና ከሌሎች ዕይታዎች አንፃር በማየት ላይ ትኩረት ያደርጋል። የቴክኖሎጂ ትንተናና ትንበያ ስራን ለማከናወን የተለያዩ ደረጃዎች የሚታለፉ ሲሆን መረጃ ማሰባሰብ፣ መለየት፣ የቴክኖሎጂዎችን ቅድመ ትንተናና ትንበያ መረዳት እና የማጠቃለያ ሃሳብ ማስቀመጥ ከደረጃዎቹ መሀከል የሚገኙ ናቸው። ከትንተናና ትንበያ የሚገኘው መረጃ ለፖሊሲ አርቃቂዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የፈጠራ ባለሙያዎችና ልዩ በሆኑ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመረጃ ምንጭነት ያገለግላል።


ኢሳይንስ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ኢሳይንስ በእያንዳንዱ የሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ገፅታ ላይ ትልቅ ሚና የሚጫወት መስክ ነው። ለማንኛውም አይነት ፈር ቀዳጅ ለሆኑ ሳይንሳዊ ጥናቶችና ግኝቶች ከመጀመሪያ ፅንሰ ሃሳብ ጀምሮ የተለያዩ በስርዓት የተቀረፁ ሙከራዎችን ለማካሄድ፣ መረጃዎችን በስርዓት ለመሰብሰብ እንዲሁም ተጓዳኝ የሆኑ መረጃዎችን ለመተንተን የሚያገለግል አስቻይ መሳሪያ ነው። ማንኛውም አይነት የሳይንሳዊ ፅንሰ ሃሳብም ሆነ መላምት ፍላጎት መጠነ ሰፊ የሆነ መረጃ መሰብሰብ መቻል አለበት። ይህንንም ለማጎልበትና ለማሳካት የሚያግዙ ሲስተሞችን ባደጉ የኮምፒውቲንግ ስርዓቶች ለመደገፍ ኢሳይንስ ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። ኢሳይንስ ሳይንቲስቶች የስራቸውን ውጤት ለማከማቸት፣ ለማብራራት፣ ለመተንተን፣ የግንኙነት አውታራቸውን ለመዘርጋት እንዲሁም የራሳቸውን መረጃ ለሌላ ተመሳሳይ ቡድን ለማካፈል የሚያስችል አሰራርና ሂደትን በውስጡ ያዘለ ነው። የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል የመረጃ ማዕከል እንደ መሆኑ ኢሳይንስን ተግባራዊ ማድረጉ የመረጃ የመሰብሰብና ማሰራጨት ስራዎች በዋናነት ለማቀላጠፍ ያስችላል። እንዲሁም የመረጃ ማዕከሉ በውስጡ የምርምር ስራዎችን የሚሰራ ስለሆነ የምርምር ስራዎችን በተሻለ ጥራትና አቅም እንዲሰሩ ኢሳይንስ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው። ከሳ.ቴ.መ.ማ. ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት

• የኮሪያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንፎርሜሽን ተቋም [1] Archived ማርች 16, 2015 at the Wayback Machine

• የቻይና ሳይንሳዊና ቴክኒካል ኢንፎርሜሽን ተቋም [2] Archived ማርች 16, 2015 at the Wayback Machine

• የማሌዢያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንፎርሜሽን ተቋም [3]

• የፊሊፒንስ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንፎርሜሽን ተቋም [4] Archived ሜይ 7, 2015 at the Wayback Machine

  1. ^ "Archive copy". Archived from the original on 2018-09-23. በ2015-04-30 የተወሰደ.
  2. ^ "Archive copy". Archived from the original on 2015-07-21. በ2015-04-30 የተወሰደ.