ደመቀ ከበደ

ከውክፔዲያ
Jump to navigation Jump to search

ጋዜጠኛና ደራሲ ደመቀ ከበደ ጎጃም-ሞጣ በ1976ዓ.ም ተወለደ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በሞጣ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት፤የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሞጣ ከፍተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። ለኪነ-ጥበብ ያለውን ልዩ ፍቅር ለማጎልበት በት/ቤት ክበባትና በአራት ዓይና ጎሹ የከያንያን ማህበር ከአባልነት እስከ መሪነት ተሳትፏል።ቤተሰቦቹ እንደአብዛኞቹ ቤተሰቦች ጎበዝ ተማሪነቱን አስተውለው ህክምና ወይም ምህንድስና እንዲያጠና ቢገፋፉትም የቋንቋ አስተማሪዎቹም ሆኑ የሃይስኩል ጓደኞቹ ባሳደሩበት ተፅእኖና በንባብ ፍቅር ባደረበት ስሜት ጋዜጠኝነትን አጥብቆ ወደደ። በተለይ ነጋሽ መሀመድን፣ መዐዛ ብሩን፣ በላይ በቀለንና ታደሰ ሙሉነህን እጅግ መውደዱ ለጋዜጠኝነት ልዩ ፍቅር እንዲያድርበት አድርጓል፤ ለበዓሉ ግርማ ደግሞ ፍቅሩ የትየለሌ ነው፡ እናም ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የሚወደውን ሙያ ለማጥናት ዩኒቨርሲቲ ገባ።


በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በጆርናሊዝምና ኮሙኒኬሽን በማዕረግ ተመርቋል። በዩኒቨርሲቲ ቆይታውም የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ህብረት (ጄኔራል አሴምብሊ) ሰብሳቢ፣የባህል ማዕከል የስነ-ዕሁፍ ዘርፍ ተጠሪ፣ የጆርናሊዝምና ኮሙኒኬሽን ክለብ መስራች ስራ አስፈፃሚ፣ የዩኒቨርሲቲው ጋዜጣና መፅሄት አዘጋጅ ሆኖ ከመስራቱም በላይ “የራስ ጥላ “ የተሰኘ መፅሀፍ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እያለ አሳትሟል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ባሳየው ከፍተኛ አፈፃፀም የ1999 ዓ.ም ከዓመቱ ምርጥ ተማሪዎች አንዱ በመሆን ከፕሬዝዳንቱ እጅ ሽልማት ተቀብሏል፡፡


ከዩኒቨርሲቲ ከወጣ በኋላም በሪፖርተር ጋዜጣ የባህልና ኪነ- ጥበብ አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል፡፡ በመቀጠልም በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት /አዲስ አበባ/ ከሪፖርተርነት እስከ ከፍተኛ አዘጋጅነት ያገለገለ ሲሆን በ2002 ዓም ከሬድዮ ፋና የዓመቱ ምርጥ ጋዜጠኞች አንዱ በመሆን ከዋና ስራ አስፈፃሚው የገንዘብና የምስክር ወረቀት ሽልማት ተቀብሏል፡፡


ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት የስልጠና ፕሮግራም ማሻሻያ ክፍል ተ/ኃላፊ ሆኖ ሰርቷል፣ አሁን በድርጅቱ የዜና ዋና አዘጋጅ/አስተባባሪ/ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡

ደራሲው በ2003 ዓ.ም በኢትዮጵያና በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በምልክት ቋንቋ፣ በብሬል፣ በኦዲዮ ሲዲና በቴክስት በማሳተም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ትያትር ሚኒስትሮች፣ ምሁራን፣ታላላቅ ሰዎችና አርቲስቶች በተገኙበት አስመርቋል። የመፅሃፉን ማስታዎሻነት ለታሪክ ተመራማሪውና ለኢትዮጵያ ጥናት ተቋም መስራች ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ለፊስቱላ ሆስፒታል መስራች ዶ/ር ካትሪን ሀምሊን፣ ለኦርኬስትራ ኢትዮጵያ መሰራችና ማሲንቆ ተጫዋች ሚስተር ቻርለስ ሳተን፣ ለኢትዮፒክስ ተከታታይ ሲዲ አሳታሚ ፍራንሲስ ፋልሴቶና በስማቸው ጎዳና ለተጠራላቸው ሚስተር ካላራቦስ ባምቢስ ሰጥቷል፣ በምረቃው እለት በክብር እንግድነት ከተገኙት ምሁራን አንዱ የነበሩት ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሼቴ ደራሲው ያዘጋጀውን የማስታዎሻ ስጦታ ለፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በክብር ሰጥተውለታል።


ይህንን “አንድ ክንፍ” የተሰኘ ሁለተኛ የግጥም መፅሀፉን በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ስነ-ፅህፍና ታሪክ ተመራማሪውና የኢትዮያ የአገር ሽማግሌዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ፣ የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲው ፕሮሬሰር ጥሩሰው መንገሻ፣ የአፍሪካ ሴት ደራስያን ህብረት እና የኢትዮያ ደራሲያን ማህበር ከፍተኛ አድናቆት ሰጥተውታል፡፡ ከአገር አቀፍ እስከ አለም አቀፍ ሚዲያዎችም ዘግበውታል። ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅም እንዲህ መስክረውለታል።


'“I have read many poetry books in different languages. I find DEMEKE, the young Ethiopian journalist, to be an interesting great poet. He creates his own original style and method of writing. For instance, like a mathematician, he weaves tables and parabolas in his poetry writing. Likewise, he uses Braille, sign language, on both text and audio. His style is overall an original way of writing poetry, uncommon in Africa, especially in Ethiopia. It is my great hope that Demeke will be producing many more interesting works. He is a promising young writer who will some day soon be recognized as a great poet. He is an inspiration to other young Ethiopians. I bless him.” Ephraim Isaac, B.D., Ph.D., D.H.L., D.Litt.'


ደራሲና ጋዜጠኛ ደመቀ ከበደ ለታዋቂ ዘፋኞች ከሰጣቸው የግጥም ስራዎች በተጨማሪ በርካታ ለህትመት የተዘጋጁ ስራዎችን አዘጋጀቶ የህትመት ብርሃን እንዲያገኙ እየተጠባበቀ ነው።

የከዋክብት ጉማጅ-አጫጭር ታሪኮች ሌዋታ- ረጅም ልቦለድ የመጀመሪያዎቹ መጀመሪያ- የታላላቅ ኢትዮጵያውያን ታሪክ ዘባሲል- ተረት፣ሳይንስ፣ሃይማኖትና ልቦለድ በአንድ ስንስል የተጣመሩበት ረጅም መፅሃፍ እና አሁን ደግሞ የህፃናትን ጉዳይ ቅድሚያ በመስጠት አደይ አበባ የተሰኘ ተከታታይ የልጆች አዝናኝና አስተማሪ መፅሃፍ አዘጋጅቶ በህትመትና በስርጭት አብረውት የሚሰሩ አካላትን እየጋበዘ ይገኛል።