ድሽቃ
ድሽቃ ከባድ መትረየስ | |
---|---|
![]() | |
ዓይነት | ከባድ መትረየስ |
የተሰራበት ሀገር | ሶቭየት ኅብረት |
የአገልግሎት ታሪክ | |
የአገልግሎት ዘመን | ከ1938 እ.ኤ.አ. – አሁን |
ጥቅም ላይ የዋለው በ | ሶቭየት ኅብረት፣ ቻይና፣ ቬትናም፣ እና ሌሎች በርካታ የአፍሪካ፣ እስያ እና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት |
ጦርነቶች |
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የኮሪያ ጦርነት የቬትናም ጦርነት የሶቭየት-አፍጋን ጦርነት እና ሌሎች በርካታ ግጭቶች |
የምርት ታሪክ | |
የተነደፈው በ |
ቫሲሊ ዴግትያርዮቭ ጌኦርጊ ሽፓጊን |
አምራች | ቱላ የጦር መሣሪያ ፋብሪካ |
የተመረተው ብዛት | ከ1 ሚሊዮን በላይ |
ሌሎች ሞዴሎች |
DShKM (የተሻሻለ) ታይፕ 54 (የቻይና ቅጂ) |
ጠቅላላ ዝርዝር | |
ክብደት |
34 ኪ.ግ (የመሳሪያው ብቻ) 157 ኪ.ግ (ከጋሪው ጋር) |
ርዝመት | 1,625 ሚ.ሜ. |
የበርሜል ርዝመት | 1,070 ሚ.ሜ. |
የጥይት ዓይነት | 12.7×108ሚሜ |
የአሰራር ዘዴ | ጭስ ቅብብል |
የተኩስ ፍጥነት | በደቂቃ 600 ጥይቶች |
የጥይት አፈሙዝ ፍጥነት | 850 ሜትር/በሰከንድ |
ውጤታማ የተኩስ ርቀት | 2,000 ሜትር |
ከፍተኛ የተኩስ ርቀት | 3,500 ሜትር |
የጥይት አቀባበል | የ50-ጥይት ዝናር |
አነጣጣሪ | የብረት አነጣጣሪ |
ድሽቃ (DShK) የ1930 የሶቭየት ኅብረት ስሪት የሆነ ከባድ መትረየስ ሲሆን፣ ስያሜውም 'DShK' የንድፍ አውጪዎቹን የቫሲሊ ዴግትያርዮቭ (Degtyaryov) እና የጊዮርጊ ሽፓጊን (Shpagin) ስምና የመሳሪያውን ትልቅ ጥይት የሚያመለክተውን ክሩፕኖካሊቤርኒ (Krupnokaliberny) የሚሉትን ቃላት የመጀመሪያ ፊደላት በመውሰድ የተሰጠ ነው። በበርካታ ሀገራት ‘ዱሽካ’ (Dushka)፣ ትርጉሙም "ውዴ" በሚል ቅጽል ስም በስፋት ይታወቃል።
መሳሪያው በዋናነት ለፀረ-አውሮፕላን፣ ለቀላል ብረት-ለበስ ተሽከርካሪዎች እና ለእግረኛ ጦር ድጋፍ ሰጪነት ያገለግላል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ከ40 በላይ ሀገራት ጦር ውስጥ በስፋት አገልግሎት ላይ ይገኛል።
በ1920ዎቹ መጨረሻ የሩስያው ቀይ ጦር ከባድ መትረየስ ያስፈልገው ነበር። የመጀመሪያው ሙከራ በቫሲሊ ዴግትያርዮቭ የተነደፈው DK (ዴግትያርዮቭ ክሩፕኖካሊቤርኒ) ሲሆን በ1930 ተመርቶ ነበር። ይሁን እንጂ የጥይት አቀባበሉ ስርዓት ቀርፋፋና የተኩስ ፍጥነቱም ዝቅተኛ ስለነበር ብዙም ተቀባይነት አላገኘም።
በ1938 ዓ.ም. ጊዮርጊ ሽፓጊን ለDK መትረየስ አዲስ አይነት የጥይት አቀባበል ስርዓት (ዝናር ጎራሽ) በመንደፍ ችግሩን ፈታው። ይህ የተሻሻለው መሳሪያ DShK 1938 የሚል ስያሜ ተሰጥቶት በቀዩ የሶቭየት ጦር አገልግሎት ላይ ዋለ።
የDShK መትረየስ ወደ ኢትዮጵያ በስፋት የገባው በዋናነት በደርግ ዘመነ መንግሥት (1966–1983) ነው። በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶቭየት ኅብረት እና ከምስራቁ ብሎክ ሀገራት ጋር ባለው የጠበቀ ወታደራዊ ግንኙነት አማካኝነት ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያ ዕርዳታ ያገኝ ነበር።
DShK መትረየሶች ከታንኮች፣ ከጋሻ-ለበስ ተሽከርካሪዎች እና ከሌሎች የጦር መሳሪያዎች ጋር በመሆን ለሚከተሉት ዋነኛ ግጭቶች በብዛት ጥቅም ላይ ውለዋል፦
- የኦጋዴን ጦርነት (1977–1978): ከሶማሊያ ጋር በተደረገው ጦርነት የኢትዮጵያ ጦር በታንኮችና በተሽከርካሪዎች ላይ የጫናቸውን DShK መትረየሶች በስፋት ተጠቅሟል።
- የኤርትራ የነጻነት ትግል እና የእርስ በርስ ጦርነት: በወቅቱ በነበሩት ረጅም ጦርነቶች ውስጥ እንደ ዋና የድጋፍ መሳሪያነት አገልግሏል።[2]
ድሽቃ በጋዝ ግፊት የሚቀባበል ስሆን ጥይቱን ለማስወንጨፍ ውስጡ የሚሽከረከር ቦልት ይጠቀማል። የጥይት መጋቢው ዝናር ሲሆን ጥይቶቹ ከግራ በኩል ወደ መሳሪያው ይገባሉ።
አፈሙዙ በአየር እንዲቀዘቅዝ ወንፊት ያለው ሲሆን፣ በቀላሉ ወልቆ ሊቀየር የሚችል ነው። ይህም ተከታታይ ተኩስ በሚኖርበት ጊዜ ግለትን ለመቆጣጠር ይረዳል። የማነጣጠሪያው ስርዓት ቀላል የብረት ማነጣጠሪያ ያካተተ ሲሆን፣ ለፀረ-አውሮፕላን ተኩስ ልዩ አነጣጣሪዎችም ሊገጠሙለት ይችላሉ።
ለመንቀሳቀስ እንዲመች፣ መሳሪያው ብዙውን ጊዜ በሁለት ጎማዎች ባሉት ጋሪ ላይ ይተከላል፤ ይህም በእግረኛ ጦር ሰራዊት እንዲጎተት ያስችለዋል። በተጨማሪም በታንኮች፣ በብረት-ለበስ ተሽከርካሪዎች እና በጭነት መኪናዎች ላይ በቀላሉ ሊገጠም ይችላል።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት DShK በቀዩ ጦር አገልግሎት ላይ የዋለ ሲሆን፣ በጦርነቱ ጊዜም በጠቅላላው 9,000 ፍሬ ተመርቷል።በተለይም እንደ GAZ-AA የጭነት መኪና፣ IS-2 ታንክ፣ ISU-152 በራሱ የሚንቀሳቀስ መድፍ እና T-40 ወንዝ ገቢ ታንክ ባሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እንደ ፀረ-አውሮፕላን መሳሪያነት በስፋት አገልግሏል። ልክ እንደ PM M1910 Maxim፣ እግረኛ ወታደሮችን ለማጥቃት በሚውልበት ጊዜ DShK ባለ ጎማ ጋሪ ላይ ይተከል ነበር፤ በዚህ ሁኔታ አጠቃላይ ክብደቱ 157 ኪ.ግ ይደርስ ነበር።
ከ1945 ዓ.ም. በኋላ DShK ለምስራቁ ብሎክ ሀገራት እና ለሌሎች የሶቭየት ኅብረት ወዳጅ ሀገራት በስፋት ተሰራጭቷል። በኋላም DShKM የተባለው የተሻሻለው ሞዴል ተመርቷል። መሳሪያው በቬትናም ጦርነት፣ በሶቭየት-አፍጋን ጦርነት እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ በተካሄዱ በርካታ ግጭቶች ውስጥ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።
እ.ኤ.አ. በ2022 ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ በከፈተችበት ወቅት፣ የዩክሬን ጦር ኢራን ሰራሽ የሆኑትን የሻሄድ-136 ድሮኖችን (ሰው አልባ አውሮፕላኖችን) ለመመከት የDShK መትረየሶችን ተጠቅሟል። እነዚህ ድሮኖች እንደ 'MANPADS' ባሉ የአየር መከላከያ ሚሳኤሎች በቀላሉ የማይመቱ በመሆናቸው፣ DShK መትረየሶች ከመብራቶች (ሰርችላይቶች) ጋር ተጣምረው ጥቅም ላይ ውለዋል። ከሶቭየት ዘመን የቀሩ በርካታ DShK መትረየሶች በመኖራቸው፣ ይህ ዘዴ ድሮኖቹን ለማውደም ወጪ ቆጣቢ ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ አስተማማኝነት ካላቸው መንገዶች አንዱ ሆኗል።
ድሽቃ ከደርግ ውድቀት በኋላም በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ዋና የጦር መሳሪያ ሆኖ ቀጥሏል።
- በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት (1989–1991): በሁለቱም ወገኖች በኩል በስፋት ጥቅም ላይ ውሏል።
- በትግራይ ጦርነት (2012–2016): በጦርነቱ ውስጥ በተሳተፉት በሁሉም ኃይሎች (የመከላከያ ሠራዊት፣ የህወሓት ኃይሎች፣ የኤርትራ ሠራዊት እና የክልል ኃይሎች) በኩል በስፋት ጥቅም ላይ ውሎ ነበር። ከጦርነቱ የወጡ በርካታ ምስሎችና ቪዲዮዎች ድሽቃ መትረየሶችን ያሳያሉ።
- በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ያሉ ግጭቶች: በአሁኑ ወቅት(2017) በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች በሚታዩ ግጭቶች ውስጥ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎችም ሆነ በተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች በኩል በብዛት ከሚታዩ የጦር መሳሪያዎች አንዱ ነው።
- DShK 1938: የመጀመሪያው ኦሪጅናል ድሽቃ
- DShKM: ከጦርነቱ በኋላ የተሻሻለ ሞዴል ሲሆን፣ ይበልጥ አስተማማኝ የሆነ የጥይት አቀባበል ስርዓት አለው።
- Type 54: የቻይና ቅጂ ሲሆን፣ በበርካታ ሀገራት በስፋት ተሰራጭቷል።
- M2 Browning machine gun – የአሜሪካ አቻው የሆነው ከባድ መትረየስ
- Kord machine gun – የDShK ዘመናዊ የሩሲያ ተተኪ
- PK machine gun – ሌላው ታዋቂ የሶቭየት መትረየስ
- 12.7×108mm – የሚጠቀመው የጥይት ዓይነት
- List of machine guns – የመትረየሶች ዝርዝር