ገደረ

ከውክፔዲያ
Jump to navigation Jump to search

ገደረ ወይም ገደራት በግምት ከ3ኛው ክፍለ ዘመን በፊት በአክሱም የነገሰ የኢትዮጵያ ንጉሥ ነበር። የንጉሥ ገደረ ሠራዊት በደቡብ አረብ ስለመዝመቱ የሚናገሩ መረጃዎች ተገኝተዋል። ሆኖም የመንን በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ መግዛቱን ለማረጋገጥ አያስችሉም። በሳባ ቋንቋ ተጽፎ በየመን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ንጉስ ገደረ (ገደራት) ከሂምያር ቤተሰቦች ተቀናቃኝ ከሆነው ሓምዳ አኒድ ባላባት አል-ሃን፣ ናህፋን እና ከልጆቹ ሳይ-ሩውም፣ አውታር፣ እና ያሪም አይመን ጋር ወግኖ እንደነበርና ሆኖም ቆይቶ ወገንተኝነቱን ቀይሮ ከሂምያሮች ጎን እንደተሰለፈ ያመለክታል። የንጉስ ገደረ ዘመቻዎች ውጤቶች ባይታወቁም፡ ከሌላ ጽሑፍ በተገኘው መረጃ መሰረት፤ ናህፋን ወደ ሃበሻት (ሃበሻ) ሠራዊቱን እንዳዘመተና ከገደራት ጋር ባደረገው ውጊያ እንደቀናው መረጃው ይጠቁማል። በዚሁ ተመሳሳይ መረጃ መሰረት፡ የንጉሥ ገደረ ልጅ ባይጃ (በይጋ) በደቡብ አረብ ናይድና ዛፋር በተባሉ ቀጠናዎች ጦርነት ውስጥ እንደተሰለፈና ተሸንፎ ወደ ባሕር ጠረፍ ክልሎቹ እንዳፈገፈገ ያወሳል። የአክሱም ኃይላት ግን ዋዲ ሱርዱድ እና ዋዲ ሣሃም በተባሉት የስሜን የመን የባሕር ማዶ ቀጠናዎች እንቅስቃሴያቸውን ቀጥለው በጉራቲድ ነገስታት ኢልሳራህ ያህዱብ እና ያዚል ባይዪን በኃይል ተገፍተው እስኪለቁ ድረስ በአካባቢው ቆይተዋል። ንጉስ ገደረ በእርግጥ ደቡብ አረብን መግዛቱን የምያረጋግጥ ማረጋገጫ እስካሁን ባይገኝም የአክሱም ሠራዊት በደቡብ የመን ያደረገው ዘምቻና ቆይታ በወቅቱ በኢትዮጵያና በደቡብ አረብ ግዛቶችና ነገስታት መካከል ጠንካራ ግንኙነት እንደነበር ይረጋግጣሉ።

ዓዲ ገለሞ በተባለ በደቡብ ኤርትራ ከሚገኝ ስፍራ በቁፋሮ የተገኘው ከመዳብ በተሰራ ዘንግ ላይ የተገኘው የግዕዝ ጽሑፍ ላይ ገደረ፣ ነጋሲ አክሱም መሆኑን የሚናገር መልዕክት ይዟል። ይህ ንጉስ ገደረ ደቡብ አረብ ከዘመተው ገደረ (ገደራ) ጋር አንድ ስለመሆኑ እስካሁን ማረጋገጫ የለም። በ330 ዓመተ ዓለም አካባቢ በአካባቢው አግዱር የተባለ ንጉሥ ነግሶ እንደነበር ለምሳሌነት ማስቀመጥ ይገባል።

ምንጭ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]