Jump to content

ቋራ

ከውክፔዲያ
(ከጎርጎ የተዛወረ)

ቋራ ወይም ኮርች ወይም ጎርጎ (Erythrina abyssinica) ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ተክል ነው። ይህ ዛፍ የእሳትና የምስጥ ጥቃትን የመቋቋም አቅም አለው። ነጭና ለስላሳ የሆነው ግንዱ ጥሩ ጣውላ የሚወጣው ባይሆንም በቀላሉ ቅርፅ ሊወጣለት የሚችል ዓይነት ነው። በወንዝና ኩሬዎች ዳርቻም ስለሚበቅል ለአፈር ጥበቃና እርከን ሥራ ተመራጭ ነው።

ፍሬው መርዛማ ነው። ሆኖም ካልደቀቀ ወይም ካልተፈጨ በስተቀር በቀላሉ አይዋጥም። ቅጠሉ ደግሞ ለከብቶች የቆዳ በሽታ በመድኃኒትነት ያገለግላል።


የተክሉ ሳይንሳዊ ጸባይ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዋናው ግንዱ አጭር ሲሆን ጥቅጥቅ ያሉና በየአቅጣጫው የሚበተኑ ወፋፍራም ቅርንጫፎች አሉት። ቅጠላቸውን ከሚያራግፉ የዛፍ ዓይነቶች ይመደባል። ቅርንጫፉ ክብ፣ የዘውድ ቅርጽ ያለው ሆኖ ከ፮–፲፪ ሜትር የሚደርስ ስፋት ያለው ነው። ቅርፊቱ ቡናማ፣ ወፍራምና ሻካራ ሆኖ ከግንዱ ጋር የተጣበቀ ነው።

በአንድ ቅርንጫፍ ላይ ሦስት አንድ ላይ የተያያዙ ቅጠሎች ሲገኙ ከሦስቱ ትልቅ የሆነው ቅጠል መጠን እስከ ፲፭ ሣንቲም እርዝማኔ አለው። በቅጠሉ መሐል ያለው ግንድና የቅጠሉ ታችኛው ገፅ አመድማ ቡኒ መልክ ያለው ሆኖ በፀጉር መሰል ነገር የተሸፈነ ነው። የአበቦቹ መጠን አነስተኛ ሆኖ ጠመዝማዛ ቅርጽ አላቸው።የመሐለኛው ክፍል ቀለም ብርቱካንማና ደማቅ ነው። የእያንዳንዱ አበባ ርዝመት በአማካይ ፭ ሣንቲም ይሆናል።

ፍሬው ወፍራም ሽፋን (ቅርፊት) ያለው ሲሆን፣ ከ፬–፲፮ ሣንቲም ርዝመት እና ፀጉራማ ነው። ፍሬዎቹ ጥቅጥቅ ብለው የተቀመጡ ናቸው፤ በአንዱ ቅርፊት ውስጥ ከአንድ እስከ አስር የሚደርሱ አብረቅራቂ ቀይ ቀለም ያላቸው የዘር ፍሬዎች ይገኛሉ።

ቆርጦ በመትከል፣ ችግኝ በማፍራትና ዘሩን በመዝራት ማራባት ይቻላል። የዘሮቹ የመብቀል ብቃት አነስተኛ ነው። በቀዝቃዛ፣ ደረቅና ከነፍሳት ንፁህ በሆነ ቦታ ከሆነ ዘሩ ለረዥም ጊዜ ሳይበላሽ እንዲቆይ ማድረግ ይቻላል።

በብዛት የሚገኝበት መልክዓ ምድር

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ገላጣማ በሆኑት እንጨታማና የሣር ምድር እርጥበታማ፣ እርጥብ ቆላና ወይና ደጋ የአየር ንብረት ክልል ውስጥ በተለይ ከ ፭ መቶ እስከ ፪ሺህ ሜትር ከፍታ ባላቸው አካባቢዎች ይገኛል።


የተክሉ ጥቅም

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በዋናነት ለማገዶ ፍጆታ፣ ለተለያዩ ቁሳቁሶች መሥሪያ (ሙቀጫ፣ ከበሮ፣ የንብ ቀፎ) ቅርፊቱና ሥሩ ደግሞ ለመድሃኒትነት ያገለግላል። ለንብ ምግብነት፣ አፈር ጥበቃ፣ የአፈርን ናይትሮጂን መጠን ለመጨመር፣ ለጌጣ ጌጥ፣ ለአጥር ግንባታ፣ ፍሬው ለአንገት ሀብል መስሪያ፣ ቅጠሉ ደግሞ የከብቶች መድሀኒት ለማዘጋጀት ያገለግላል፡፡

  • አክርማ መጽሔት፤ ቁጥር ፲፰ (፲፱፻፺፱ ዓ/ም)፤ ገጽ ፲፮