ሲልቪያ ፓንክኸርስት
እመት ሲልቪያ ፓንክኸርስት ሚያዝያ ፳፰ ቀን ፲፰፻፸፬ ማንቼስተር በምትባለው የእንግሊዝ ከተማ ተወለዱ። እናታቸው ለሴቶች መብት እና የፖለቲካ ድምጽ ታጋይ የነበሩት ኤመሊን ፓንክኸርስ ሲሆኑ አባታቸው ዶክቶር ሪቻርድ ፓንክኸርስት ይባሉ ነበር። እመት ሲልቪያ የታወቁት የታሪክ ምሁር የፕሮፌሶር ሪቻርድ ፓንክኸርስት እናት ናቸው።
ግፈኛው ፋሺስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ መጀመሪያ ይሄው የሙሶሊኒ የፋሺስት ሥርዓት እና በጊዜው የነበረው የእንግሊዝ መንግሥት ኢትዮጵያን ለመቆራረስ የነበራችውን ዓላማ በመቃወም በወረራው ዘመናትም ለኢትዮጵያ ነጻነት፣ በሙሉ ቆራጥነት ባከናወኑት ከፍ ያለ ተጋድሎና ላስገኙት ውጤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለውለታ የሆነላቸው ሲልቪያ ፓንክኸርስት ከዚህም ባሻገር የልዕልት ፀሐይን ሆስፒታል ለማሠራት ያስፈለገውን ገንዘብ በማሰባሰብ፤ የኢትዮጵያ ሴቶች መብት እንዲከበርና የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ሸንጎም እንዲሻሻል ያደረጉት ጥረት ዓቢይ ተግባራት እንደነበሩ ታሪክ የሚያስታውሳቸው የኢትዮጵያ ታላቅ ወዳጅ ሴት ነበሩ። ኢትዮጵያ የፋሺዝም ሰለባ ከሆነችበት 1928 ዓ.ም ሚያዚያ ወር አንሥቶ ስለ ኢትዮጵያ የሚናገርና የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራን የሚያወግዝ ‹‹ዘኒው ታይምስ ኤንድ ኢትዮጵያ›› የተሰኘ ጋዜጣ በተከታታይ ማሳተማቸው ይታወቃል፡፡
በኋላም ግፈኛው ፋሺስት ኢጣልያ ተሸንፎ ነጻነታችን ከተመለሰ ወዲህ፣ እመት ሲልቪያ ጓዛቸውን ጠቅልለው ከልጃቸው ከሪቻርድ ጋር ኑሯቸውን አዲስ አበባ ላይ በ፲፱፻፵፰ ዓ/ም መሥርተው ሲኖሩ «ኢትዮጵያ ኦብዘርቨር» የተሰኘ ወርኃዊ መጽሔት ማሳተም ጀምረው ነበር፡፡ እመት ሲልቪያ ከጻፏቸው ሃያ መጻሕፍት ስምንቱ በኢትዮጵያ ዙሪያ ያተኮሩ ናቸው፡፡
እመት ሲልቪያ ፓንክኸርስት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንሥርዓት ሲጠመቁ ወለተ ክርስቶስ የተባሉ ሲሆን፤ በተወለዱ በ ሰባ ዘጠኝ ዓመታቸው የመስቀል ዕለት መስከረም ፲፯ ቀን ፲፱፻፶፫ ዓ/ም አዲስ አበባ ላይ አረፉ። ቀብራቸውም ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከነቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ከፍተኛ የመንግሥት ባልሥልጣናትና የውጭ ልዑካን በተገኙበት በትልቅ ክብር በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።
http://www.globalallianceforethiopia.org/files/Sylvia%20Pankhurst%20_Ethiopian%20Patriot_.pdf Archived ሜይ 4, 2012 at the Wayback Machine
- (እንግሊዝኛ) Wright, Douglas A. H.: P.R.O., FO 371/154836 Annual Report from Ethiopia for 1960
- (እንግሊዝኛ) Asfaw, Berihun; Sylvia Pankhurst: Citizen of the World; Emperor Haile Selassie, Sylvia E. Pankhurst & the Ethiopian independence