Jump to content

ቀጭኔ

ከውክፔዲያ
የ08:36, 16 ኤፕሪል 2019 ዕትም (ከየውልሰው አስፋው ደፋር (ውይይት | አስተዋጽኦ) ተዘጋጅቶ)
(ለውጡ) ← የፊተኛው እትም | «የአሁኑን እትም ለመመልከት» (ለውጡ) | የሚከተለው እትም → (ለውጡ)
?ቀጭኔ

የአያያዝ ደረጃ
ሳይንሳዊ ደረጃ መስጫ
ስፍን: ጉንደ እንስሳ (Animalia)
ክፍለስፍን: አምደስጌ (Chordata)
መደብ: አጥቢ (Mammalia)
ክፍለመደብ: ሙሉ ጣት ሸሆኔ Artiodactyla
አስተኔ: የቀጭኔ አስተኔ Giraffidae
ወገን: ቀጭኔ Giraffa
ዝርያ: G. camelopardalis
ክሌስም ስያሜ
''Giraffa camelopardalis''
Linnaeus, 1758

ቀጭኔ በአፍሪካ የሚኖር ባለሙሉ ጣት ሸሆኔ ጡት አጥቢ አራዊት ሲሆን በምድር ከሚገኙ እንሰሳት በርዝማኔ የመጀመሪያውን ደረጃ ይዞ ይገኛል። ወንዱ ከ 4.4 እስከ 5.5 ሜትር ርዝማኔና 1,360 ኪሎግራም ክብደት ያስመዘግባል። እስካሁን በሪኮርድ የተያዘው የ 5.87ሜና የ2000ኪ.ግ ቀጭኔ ነው።[2] ሴቶቹ በጥቁቱ አነስ ብለው ይታያሉ።

ፈጣንና ባለ ግርማ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

እነዚህን ፍጥረታት በአራዊት ማቆያ ቦታዎች አንገታቸውን ከታጠሩበት አጥር በላይ ወጣ አድርገው የተመለከተ ሰው በአፍሪካ ቁጥቋጦዎች ነፃ ሆነው ሲሮጡ ያላቸውን ውበትና ግርማ መገመት ያስቸግራል። የቀጭኔ እንቅስቃሴ ትልቅ ግርማ ያለውና እንደ ውኃ ሙላት የሚፈስ ነው። በገላጣው የግጦሽ መስክ ላይ በሚጋልቡበት ጊዜ ቁመናቸው ትንሽ እንቅፋት ቢነካቸው ወድቀው የሚሰባበሩ ያስመስላቸዋል። ይሁን እንጂ እስከ 1, 300 ኪሎ ግራም የሚደርስ ክብደት ያላቸው ወንድ ቀጭኔዎች ቀልጣፋና ምንም የማያደናቅፋቸው ሯጭ ከመሆናቸውም በላይ በሰዓት እስከ 60 ኪሎ ሜትር ሊሮጡ ይችላሉ።

ይህች አስደናቂ ፍጡር የምትገኘው በአፍሪካ ብቻ ነው። እርጋታዋና ሰላማዊ ተፈጥሮዋ ዓይን ይስባል። የቀጭኔ ፊት በዓይነቱ ልዩ የሆነና ቆንጆ ሊባል የሚችል ሲሆን ረዥምና ጠባብ ጆሮዎች፣ ሁለት ትናንሽ ቀንዶች እንዲሁም ጠቆር ያለ ለስላሳ ጠጉር አላት። ዓይኖቿ በጣም ትላልቅና ጥቁር ሲሆኑ ረዣዥም በሆኑ ቅንድቦች ይጠበቃሉ። ቀጭኔ ያን በመሰለ ከፍታ ላይ ሆና ሩቅ ስትመለከት ፊቷ ላይ የየዋህነት ገጽታ ይታይባታል።

በጥንት ዘመናት ቀጭኔ ባላት አስደሳች ቁመና እንዲሁም ጨዋ፣ ዓይነ አፋርና ሰላማዊ ባሕርይ ያላት በመሆኑ በጣም ተወዳጅና ትልቅ ግምት የሚሰጣት ነበረች። በብሔራት መካከል ሰላምና በጎ ፈቃድ መኖሩን ለማመልከት የቀጭኔ ግልገሎች ለነገሥታትና ለገዥዎች በገጸ በረከትነት ይሰጡ ነበር። ጥንታዊ በሆኑት የአፍሪካ አለቶች ላይ ቀለማቸው የደበዘዘ የቀጭኔ ሥዕሎች እስከ ዛሬ ይታያል። [3]

ከእንስሳት ሁሉ ቀጭኔን በቁመት የሚወዳደር የለም። ሙሉ ዕድሜ ላይ የደረሱ ወንድ ቀጭኔዎች ከእግራቸው ኮቴ አንስቶ እስከ ቀንዳቸው ድረስ ከ5.5 ሜትር የሚበልጥ ርዝመት አላቸው። በግብፃውያን ጥንታዊ ሥዕላዊ የአጻጻፍ ዘዴ ቀጭኔ በረዥም ቁመቷና አርቆ በመመልከት ችሎታዋ ምክንያት “መተንበይ” የሚለውን ግሥ ትወክል ነበር።

ቀጭኔ በአፍሪካ መስኮች በሚሰማሩት የሜዳ አህዮች፣ ሰጎኖች፣ አጋዘኖችና ሌሎች እንስሳት መካከል ስትቆም እንደ ማማ ሆና ትታያለች። ቁመቷና አርቆ የማየት ችሎታዋ ማንኛውንም አደጋ ገና ከሩቅ ለማወቅ ያስችላታል። ስለዚህ የቀጭኔ መኖር ለሌሎች እንስሳት የመረጋጋት ስሜት እንደሚፈጥር ጥርጥር የለውም። [4]

አስደናቂ የሆነ አፈጣጠር

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ቀጭኔ ከዝሆን በስተቀር ማንኛውም ሌላ እንስሳ ሊደርስ በማይችልበት ከፍታ ላይ የሚገኙ ረዣዥም ቀንበጠቦችን ለመብላት የሚያስችል አስደናቂ አፈጣጠር አላት። ልዩ የሆነ የመቆንጠጥ ችሎታ ያለው የላይኛው ከንፈሯና እንደተፈገለው የሚተጣጠፍ ችሎታ ያለው ምላሷ ሹል በሆኑ እሾሆች የታጠሩ ቅጠሎችን ለመቀንጠብ ያስችሏታል።

ቀጭኔዎች በቀን እስከ 34 ኪሎ ግራም የሚመዝን ዕፅዋት መመገብ ይችላሉ። የተለያዩ ዕፅዋትን የሚበሉ ቢሆኑም ይበልጥ የሚመርጡት በአፍሪካ ሜዳዎች የሚገኙትን እሾሃማ ግራሮች ነው። አንድ ወንድ ቀጭኔ ምግብ ለመፈለግ ምላሱን እስከ 42 ሳንቲ ሜትር መዘርጋት ይችላል። የቀጭኔ አንገት በጣም አስደናቂ የሆነ የመተጣጠፍ ችሎታ አለው። ይህም ላይኛዎቹን የዛፍ ቅርንጫፎች ለመቀንጠብ በምታደርገው እንቅስቃሴ ረዥሙን ራሷን እንደ ልቧ ለማዘንበልና ለማዟዟር ያስችላታል።

ለቀጭኔ ወደ ላይ መንጠራራት በጣም ቀላል ነገር ሲሆን ተጎንብሶ ውኃ መጠጣት ግን ይከብዳታል። ወደ ውኃ ጉድጓድ በምትቀርብበት ጊዜ የፊት እግሮቿን ቀስ በቀስ ከፍታ ካራራቀቻቸው በኋላ ወደ ውኃው ለመድረስ እንድትችል ሁለት ጉልበቶቿን አጠፍ ታደርጋለች። ቀጭኔዋ እንዲህ ባለው አመቺ ባልሆነ ሁኔታ እያለች ረዥም አንገቷን እስከ መጨረሻ ትዘረጋለች። ደግነቱ ግን ከምትመገባቸው ቅጠላ ቅጠሎች በቂ እርጥበት ስለምታገኝ ቶሎ ቶሎ መጠጣት አያስፈልጋትም።

የቀጭኔ አንገትና ትከሻ የቅጠል ቅርፅ ባላቸውና ቀጫጭን በሆኑ ነጭ መስመሮች ያጌጠ ነው። ቀለማቸው የተለያየ ሲሆን ከወርቃማ ዳለቻ አንስቶ እስከ ቡናማ እንዲያውም ጠቆር እስካለ ቀለም ይደርሳል። የቀጭኔ ዕድሜ እየገፋ በሄደ መጠን ቀለሟም እየጠቆረ ይሄዳል። [5]

የቤተሰብ ሕይወት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ቀጭኔዎች ከ2 እስከ 50 የሚደርሱ አባላት ባሉት መንጋዎች ተደራጅተው አንድ ላይ የሚኖሩ ማኅበራዊ ፍጥረታት ናቸው። አንዲት ነፍሰ ጡር ቀጭኔ ልጅዋን ከ420 እስከ 468 ለሚደርሱ እርግዝና ቀናት ከተሸከመች በኋላ ሁለት ሜትር ቁመት ያለው ግልገል ትወልዳለች። ግልገሏ በምትወለድበት ጊዜ ራስዋን ታስቀድምና ከሁለት ሜትር ከፍታ ላይ ወደ መሬት ትወረወራለች። ይሁን እንጂ በ15 ደቂቃ ውስጥ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባት እየተውተረተረች ትነሳና ጡት ለመጥባት ዝግጁ ትሆናለች። ከሁለት ወይም ከሦስት ሳምንት በኋላ በደመ ነፍስ ተመርታ የግራር ቀንበጦችን መለቃቀም ስለምትጀምር ብዙም ሳትቆይ ረዥም እርምጃ ያላትን እናትዋን ተከትላ ለመሄድ የሚያስችል ጉልበት ታገኛለች።

አንዲት የቀጭኔ ግልገል በጣም ውብ መልክ ሲኖራት የወላጆችዋ አነስተኛ ግልባጭ ነች። ቁመቷ ከቀጭኔ ርዝመት ጋር ሲወዳደር አጭር ብትሆንም ከብዙ ሰዎች ቁመት ግን ትበልጣለች። በእናቷ ጥንቃቄ የተሞላበት ጥበቃ ተማምና አላንዳች መሸበር አካባቢዋን የምትማትረው ግልገል ላያት ሁሉ ልዩ መስህብ አላት።

ግልገል ቀጭኔዎች በተወለዱበት ወራት በግልገል መዋያ ተሰባስበው ሙሉውን ቀን ዕረፍት በማድረግ፣ በመጫወትና በአካባቢያቸው የሚሆነውን ነገር በመመልከት ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ። የቀጭኔ ግልገል ለማመን በሚያዳግት ፍጥነት ያድ⁠ጋል። በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ አንድ ሜትር የሚያክል ቁመት ሲጨምር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ደግሞ በእጥፍ ያድጋል። በአንድ ሳምንት ብቻ 23 ሳንቲ ሜትር ያህል ሊያድግ ይችላል! እናትዬው ለልጅዋ ከፍተኛ ጥበቃ የምታደርግ ሲሆን ልጅዋ የተወሰነ ርቀት እንድትዘዋወር ብትፈቅድላትም ሩቅ የማየት ችሎታ ስላላት በዓይኗ ትከታተላታለች።

ቀጭኔ ግዙፍ አካል፣ ከፍተኛ ፍጥነት፣ ቅልጥፍናና የማየት ችሎታ ስላላት ከአንበሳ በቀር የሚያጠቃት ጠላት የለም። ቢሆንም ይህችን የምታምር ፍጥረት የሰውን ያህል በብዛት አድኖ የገደለ የለም። ቀጭኔ በሚያምር ቆዳዋ፣ በሚጣፍጥ ሥጋዋና አንዳንዶች ምትሐታዊ ኃይል አለው በሚሉት ረዥምና ጥቁር ጭራዋ ምክንያት እጅግ ተፈላጊ ስለሆነች በአሁኑ ጊዜ የዚህች ሰላማዊ ፍጡር የወደፊት ሕልውና ስጋት ላይ ወድቋል። በአንድ ወቅት በብዙ የአፍሪካ አካባቢዎች እንደ ልብ ትታይ የነበረችው ቀጭኔ በአሁኑ ጊዜ የምትገኘው በቂ ጥበቃ በሚደረግላት ፓርኮች ብቻ ሆኗል። [6]

[የግርጌ ማስታወሻ]

በአፍሪካ ገላጣ ምድር ላይ በሰፊው ተሰራጭተው የሚታዩት ትናንሽ ዓለታማ ኮረብቶች ኮፕጀስ ይባላሉ።

እግረ ረዥሟ ተአምራዊ ፍጡር

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የቀጭኔ አካላዊ ቅርጽና ግዝፈት ችግሮች ማስከተሉ አይቀርም ብሎ የሚያስብ ይኖር ይሆናል። በጣም ትልቅ ቁመትና ረዥም አንገት ስላላት የተስተካከለ የደም ዝውውር እንዲኖራትና ወደ ሁሉም የአካሏ ክፍሎች ደም እንዲደርስ ማድረግ የማይቻል ነገር ሊመስል ይችላል። ለምሳሌ ያህል ቀጭኔ አንገቷን ወደ መሬት ስታጎነብስ በስበት ኃይል ምክንያት ብዙ ደም ወደ ጭንቅላቷ ፈስሶ አንጎሏን ማጥለቅለቅ ነበረበት። ራሷን ቀና በምታደርግበት ጊዜ ደግሞ ደሟ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ልቧ ተመልሶ ራሷን እስከ መሳት ሊያደርሳት ይገባ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ነገር አይደርስም። ለምን?

የቀጭኔ የደም ዝውውር ሥርዓት በዓይነቱ ልዩ ለሆነው ለዚህች እንስሳ ቅርጽና መጠን እንዲያገለግል ሆኖ በታላቅ ጥበብ የተሠራ ነው። ልቧ ራሱ በጣም ትልቅ ሲሆን ደሙን ሦስት ሜትር ተኩል ገደማ ርቆ እስከሚገኘው እስከ አንጎላ ለመግፋት የሚያስችል አቅም አለው። በደቂቃ እስከ 170 ጊዜ የሚመታውና 7 ሳንቲ ሜትር ያህል ውፍረት ባለው ጡንቻ የተገነባው የቀጭኔ ልብ ከሰው የደም ግፊት በሦስት እጥፍ የሚበልጥ ግፊት ያመነጫል። ወደ አንጎል የሚሄደውን ደም የሚሸከመው ካሮቲድ የተባለው የደም ቧንቧና ከአንጎል ወደ ልብ የሚመለሰውን ደም የሚሸከመው ጀጉላር የተባለው የደም ቧንቧ እንዲህ ያለውን ከፍተኛ ግፊት መቋቋም የሚያስችል መጠን ሊኖራቸው ይገባል። በእርግጥም እነዚህ የደም ቧንቧዎች ከ2.5 ሳንቲ ሜትር በላይ ስፋት ያላቸው ከመሆኑም በላይ ጠንካራና የመለጠጥ ችሎታ ባላቸው ሕዋሳት የተገነቡ በመሆናቸው ከፍተኛ ጥንካሬና የመለመጥ ችሎታ አላቸው።

ቀጭኔ ከጭንቅላቷ ጎንበስ በምትልበት ጊዜ ወደ አንጎሏ የሚሄደውን የደም ፍሰት የሚቆጣጠሩ ልዩ መቆጣጠሪያዎች አሏት። አንጎልና አንገት በሚገናኙበት ቦታ ላይ ትልቁ ካሮቲድ የደም ቧንቧ ሬቴ ሚራቢሌ ተብሎ ከሚጠራ አስደናቂ የሆነ መረብ መሰል አካል ይገናኛል። በከፍተኛ ኃይል ተገፍትሮ የመጣው ደም እዚህ ጋር ሲደርስ በጣም በርካታ ወደሆኑ ትናንሽ የደም ሥሮች እንዲገባ ስለሚደረግ የደሙ ግፊት ተስተካክሎ በአንጎል ላይ ጉዳት የማያስከትል ይሆናል። ቀጭኔዋ ራስዋን ጎንበስ በምታደርግበት ጊዜ ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነው መረብ ይለጠጣል፤ ራሷን ቀና በምታደርግበት ጊዜ ደግሞ ይኮማተራል። ይህም የስበት ኃይል የሚያሳድረው ተጽዕኖ ሚዛኑን የጠበቀ እንዲሆን ማድረግና የደም ግፊቷ በእጅጉ ቀንሶ ራሷን የምትስትበት ሁኔታ እንዳይፈጠር ለመከላከል ይረዳታል።

የሳይንስ ሊቃውንት በጣም አስደናቂ ርዝመት ያለው የቀጭኔ አንገት ያሉት አከርካሪዎች ቁጥር ከአይጥ ወይም ከብዙዎቹ አጥቢ እንስሳ ጋር እኩል መሆኑን ሲያውቁ በጣም ተደንቀዋል! ይሁን እንጂ የቀጭኔ አከርካሪዎች በጣም ረዣዥሞችና እርስ በርሳቸው ልዩ በሆነ ሁኔታ የተሰካኩ በመሆናቸው እንደ ልብ ሊተጣጠፉ ይችላሉ። ቀጭኔ አንገቷን መጠምዘዝና ማጠፍ ስለምትችል ሁሉንም የአካሏን ክፍሎች ለመላስም ሆነ ረዣዥም የዛፍ ቅርንጫፎች ላይ ለመድረስ ትችላለች። [7]

  1. ^ Antelope Specialist Group (1996). Giraffa camelopardalis. 2006 IUCN Red List of Threatened Species. IUCN 2006. Retrieved on 05 May 2006.
  2. ^ San Diego Zoo giraffe fact sheet Retrieved 14 August 2006.
  3. ^ ኬንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
  4. ^ ኬንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
  5. ^ ኬንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
  6. ^ ኬንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
  7. ^ ኬንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው