Jump to content

የፋራን ምድረ በዳ

ከውክፔዲያ
የ06:17, 23 ጁን 2013 ዕትም (ከCodex Sinaiticus (ውይይት | አስተዋጽኦ) ተዘጋጅቶ)
(ለውጡ) ← የፊተኛው እትም | «የአሁኑን እትም ለመመልከት» (ለውጡ) | የሚከተለው እትም → (ለውጡ)

የፋራን ምድረ በዳ (ዕብራይስጥ מדבר פארן /ሚድባር ፓእራን/) በመጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቀስ ቦታ ነው።

ስሙ መጀመርያ የሚታየው በኦሪት ዘፍጥረት 14፡6 ሲሆን፣ የኤላም ንጉሥ ኮሎዶጎምርና ከሱ ጋር ሌሎቹ ነገሥታት «የሖር ሰዎችንም በሴይር ተራራቸው በበረሀ አጠገብ እስካለች እስከ ኤል ፋራን ድረስ መቱ።» ከዚህ የፋራን ሥፍራ በሰዶምገሞራ አካባቢ እንደ ተገኘ ይመስላል። የአብርሃም በኲር ልጅ እስማይል እና እናቱ ሀጋርቤርሳቤ ከተሰደዱ በኋላ በፋራን መኖርያ አገኙ።

በኋላ በሙሴ ዘመን የእስራኤል ልጆች ከግብጽና ከከነዓን መካከል ለ40 ዓመት ሲቆዩ፣ ከሠፈሩባቸው ምድረ በዳ ቦታዎች መካከል ይቆጠራል (ኦሪት ዘኊልቊ 10:12)። በኦሪት ዘዳግም 1:1 እንደገና፣ «በዮርዳኖስ ማዶ በምድረ በዳ፥ በዓረባ ውስጥ በኤርትራ ባሕር ፊት ለፊት፥ በፋራንጦፌልም በላባንም በሐጼሮትም በዲዛሃብም መካከል ሳሉ፥ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ የነገራቸው ቃል ይህ ነው» በማለት ይጀመራል። በኋላ በምዕራፍ 33 ደግሞ «እግዚአብሔር ከሲና መጣ፥ በሴይርም ተገለጠ፤ ከፋራን ተራራ አበራላቸው...» የሚልን በረከት እናነባለን።

እንደገና በዳዊት ጊዜ ዳዊት በፋራን ምድረ በዳ ሸሸገ (1 ሳሙኤል 25፡1)። በተጨማሪ በ1 ነገሥታት 11:17-18 ዘንድ የኤዶምያስ ሰው ሃዳድ ከኤዶምያስ ወደ ግብጽ በሸሸበት ወቅት፣ በምድያምና በፋራን አገሮች እንዳለፈ ይነግራል።

ከነዚህ ጥቅሶች ሁሉ የተነሣ ብዙ ጊዜ ይህ ምድረ በዳ በሲና ልሳነ ምድር ውስጥ ወይም እስከ ዮርዳኖስ ጨው ባሕር ድረስ ያለው ምድረ በዳ መሆኑ ይታስባል።

በሌላ ልማድ ግን የፋራን ሥፍራ በመካ (በአሁኑ ሳዑዲ አረቢያ) ዙሪያ ነበር የሚል አስተሳሰብ አለ። በተለይ በእስልምና እስማይልና ሀጋር ስደት ያገኙበት አገር ፋራን በመካ ዙሪያ ነበር። በዚህ ትምህርት «ፋራን» ማለት ሄጃዝ ወይም ምዕራቡ አረቢያ ነው። በመካ አካባቢ የተገኙ ኮረብቶች ወይም ተራሮች «የፋራን ተራሮች» እንደ ተባሉ የሚሉ አንዳንድ ጥንታዊ ምንጮች አሉ።