Jump to content

የፍርድ ቀን

ከውክፔዲያ
የ15:40, 21 ሜይ 2022 ዕትም (ከInternetArchiveBot (ውይይት | አስተዋጽኦ) ተዘጋጅቶ)
(ለውጡ) ← የፊተኛው እትም | «የአሁኑን እትም ለመመልከት» (ለውጡ) | የሚከተለው እትም → (ለውጡ)

የፍርድ ቀን በማይክል አንጄሎ ቡናሮቲ

የፍርድ ቀን የተባለው ስዕል የሚገኘው በቫቲካን ከተማ በሲስቲኒ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከመንበሩ በስተ ጀርባ በኩል ከሚገኘው ግድግዳ ላይ ነው። ማይክል አንጄሎ ቡናሮቲ ይህን ስራ ለመጨረስ አራት አመት ፈጅቶበታል። ማይክል አንጄሎ ይህን የፍርድ ቀን የተባለውን ስእል የሰራው ዘፍጥረትን በዚሁ ቤተ ክርስቲያን ጣሪያ ላይ በሰራ በሰላሳ አመቱ ነው። ስራው በጣም ትልቅ እና ግድግዳውን በሙሉ ያካተተ ነው። ስራው በ1537 ተጀምሮ በ 1541 ተፈጸመ ። የፍርድ ቀን ስሙ እንደሚያስረዳው ጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳን ጋር ዳግመኛ ለፍርድ ቀን እንዴት እንደሚመጣ እና ፍርድ እንዴት እንደሚሰጥ የሚያሳይ ሰዕል ነው። የፍርድ ቀን የተባለው ስዕል በካርዲናል ካራፋ እና በማይክል አንጄሎ መካከል ከፍተኛ የሆነ ቅራኔ አስነስቶ ነበር። ቅራኔውም የተነሳው የፍርድ ቀን በተባለው ስዕል ሲሆን ክሱም ሀፍረት የሌለው ቤተ ክርስቲያኑን እርቃነ ስጋቸውን በሆኑ ሰዎች ሞላው የሚል ነበር። በዚህም የተነሳ የአሳማ ቅጠል የሚባል እንቅስቃሴ በካራፋ እና ሞንሲኞር ሴሪኒኒ የማንቱዋ አምባሳደር አደራጅነት ስዕሉን ለማስጠፋት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ጀመሩ። የጳጳጹ ዋና አስተዳድሪ ቢያጂዮ ዳ ሴሴናም እንዳለው በዚህ በተባረከ እና በተቀደስ ስፍራ እርቃናቸውን የሆኑ ሰዎች ሀፍረተ ስጋቸውን ሳይሸፍኑ በሚያሳፍር ሁኔታ መታየታቸው እንዲህ ያለው ስዕል ለጳጳጽ መቀደሻ ስፍራ ሳይሆን የሚያስፈልገው ለህዝብ መታጠቢያ ቤት እና ለዝሙት ለመጠጥ መሸጫ ቤት ብቻ ነው ብለው ተናግረዋል። ማይክል አንጄሎም ይህን ክስ ከሰማ በኋላ ይስለው ከነበረው ስዕል መካከል ወደ ገሀነም ከሚገቡት አንዱን የሙታን አለቃ ወይም ዳኛ በመባል የሚታወቅ ሚኖስ የሚባል ሰው ስለነበረ የሴሴናምን ጭንቅላት ወይም መልክ በትክክል ስዕሉ ላይ አስቀመጠው። ስዕሉም የሚገኘው በስተቀኝ ከታች በኩል ነው። ስዕሉ ላይ ጆሮውን እንደ አህያ በማስረዘም ሞኝ መሆኑን ሲገልጽ እባብ ሰውነቱ ላይ ተጠምጥሞበት ብሉትን ሲነድፈው ያሳያል ሴሴናም ይህን ከተመለከተ በኋላ ለጳጳጹ ክስ ቢያቀርብም ጳጳጹም የኔ ግዛት ገሀነም ድረስ አይዘልቅም ብለው መልስ ስጥተውታል። በዚያም የተነሳ ስዕሉ ሳይጠፋ እንደዛው የመቅረት እድል አግኝቷል።

የማይክል አንጄሎ የፍርድ ቀን. ቅዱስ ባርቶሎሜ ከ12ቱ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር አንዱ የነበረ ቆዳው እንደ እንሰሳ ተገፍፎ ተዘቅዝቆ በስቅላት የተገደለ የተገፈፈበትን ቢላዋ እና ቆዳውን ይዞ በቆዳው ላይ ያለው ፊት የማይክል አንጄሎ ነው።

ማይክል አንጄሎ የራሱን መልክ በቅዱስ ባርቶሎሜ ከኢየሱስ 12 ደቀ መዝሙር ከነበሩት አንዱ የነበረ በህይወቱ እያለ ቆዳው እንደ እንሰሳ የተገፈፈ እና ተዘቅዝቆ በስቅላት የተገደለ ነው። ቆዳው የተገፈፈበትን ቢላዋ እና የተገፈፈ ቆዳውን ይዞ ። በተገፈፈው ቆዳ ላይ ያለው መልክ የማይክል አንጄሎ ቡናሮቲ መልክ ነው። ይህንንም ያደረገው ይህን ስዕል ሲስራ ምን ያህል መከራ እና ስቃይ ይደርስበት እንደነበር ለማሳየት ያደረገው ነው። ማይክል አንጄሎ ከሞተ በኋላ ግን ሀፍረተ ስጋቸውን ለመሸፈን ተስማሙ። ከዚያም የማይክል አንጄሎ ተማሪ ከነበረው ዳኒኤሌ ዳ ቮልቴራ ጋር ውል በመዋዋል ሀፍረተ ስጋቸውን በጨርቅ መሸፈን ተያያዙት። በ 1993 ስእሎቹ እድሳት ሲደረግላችው ወግ አጥባቂዎች በጣም በመከራከር ቀደም ሲል ዳኒኤሌ ሸፍኗቸው የነበሩትን ስእሎች ቀድሞ ማይክል አንጄሎ እንደሰራቸው ማስመለስ ችለዋል። አንዳንዶቹንም ለታሪክ በማለት ጨርቅ እንደለበሱ ትተዋቸዋል። የማይክል አንጄሎ ስራዎች አሳፋሪ በሚል በሌላ ሰአሊ በመበላሸታቸው ዋናውን የማይክል አንጄሎ ስራ በማንም ያልተነካውን በማርቼሎ ቬኑስቲ የተሰራውን በካፖዲሞንቴ ሙዚየም ውስጥ ኔፕልስ ማየት ይቻላል። ሳንሱር ሁልጊዜ ማይክል አንጄሎን ይከታተለው ነበር ይባላል። ማይክል አንጄሎ በአንድ ወቅት የሚያሳፍር ስራ ፈጣሪ የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶት ነበር። ብዙ የማይወደደው የአሳማ ነገር በመባል የሚታወቀው የጸረ እንደገና መወለድ እንቅስቃሴ በዘመኑ የነበሩትን ቅርጽ እና ስእሎች በሙሉ ሀፍረተ ስጋ መሸፈን የተጀመረው በማይክል አንጄሎ ስራዎች ነው።

የሲስቲኒ ቤተ ክርስቲያን ስእሉ በ1993 እድስት ተደርጎለታል። በባህል ቅርጽ እና ቫቲካን ሙዚየም ፋብሪዚዮ ማንሲኔሊ የበላይ ተቆጣጣሪነት ስራው ተፈጽሟል እድሳቱም ይህን ያመለክታል።

የፀሐይ ምልክት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ስራው ከሚጠይቀው ሙያዊ ግዴታ ባሻገር ማይክል አንጄሎ መሰረታዊ ስር ነቀል ለውጦችን ተጠቅሟል በተለይ ስለ ፍርድ ቀን በወቅቱ ሌሎች ሰአሊዎች ከተጠቀሙት ይልቅ። በመጀመሪያ በስእሉ ላይ የሚታዩት ሰዎች በሙሉ ፊታቸውን ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መሀል አዙረው ነው የሚታዩት። በወቅቱ የተለመደው ባህላዊ አሰራር ገነት መሬት እና ገሀነምን ወደ ጎን መስራት ነበር። ሁለተኛው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ጡንቻማ እና ጺም የሌለው አድርጎ በብርሀን እንዲከበብ ማድረጉ ነው። አንዳንድ ሰዎች ይህን ሁኔታ ከግሪኮች የፀሐይ አምላክ ከነበረው አፖሎ ጋር ያመሳስሉታል። ይህን ስራ ከማግኘቱ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ስራውን የሰጡት ጳጳጽ ክሌሜንት VIIኮፐርኒከስን ስለ ሕዋ ፀሐይ እና ጭፍሮቿ የተጻፈውን ጽሁፍ ያጠኑ ነበር። ስለዚህም አንዳንድ ሰዎች ፀሐይ የሕዋችን መካከል ናት ብለው ያስቡ ስለነበር ጌታችን ኢየሱስን እንደ ፀሐይ መካከል አድርጎ ሰራ ይላሉ።

ማመሳከሪያዎች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

http://www.crucifixion.com/visual/theology/johndixon/terror.htm Archived ኦገስት 14, 2007 at the Wayback Machine

ይህን ይመልከቱ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

http://en.wikipedia.org/wiki/Doom_%28painting%29

ወደ ውጭ የሚያገናኙ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

http://commons.wikimedia.org/wiki/Category:Sistine_Chapel_-_Michelangelo%27s_Last_Judgment_%28unrestored%29 ስእሉ ከመታደሱ በፊት

http://commons.wikimedia.org/wiki/Category:Sistine_Chapel_-_Michelangelo%27s_Last_Judgment_%28restored%29 ስእሉ ከታደስ በኋላ