Love, Simon

ከውክፔዲያ
Jump to navigation Jump to search

Love, Simon (በአማርኛ "ከፍቅር ጋር፣ ሳይመን") 2018 እ.አ.አ የተለቀቀ በBecky Albertalli በተጻፈው Simon vs. the Homo Sapiens Agenda በተባለው መጽሐፍ መሰረት በGreg Berlanti የተዘጋጀ አሜሪካዊ የፍቅርና ወጣት ኮሜዲ-ድራማ ፊልም ነው። ዋና ዋና ተዋናዮቹ Nick Robinson, Josh Duhamel እና Jennifer Garner ናቸው። የፊልሙ ጭብጥ የሚያጠነጥነው ሳይመን ስፒየር (Simon Spier) በተባለ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ላይ ነው። ሳይመን እራሱን ይፋ ያላወጣ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ሲሆን ይህም እንዳይታወቀብት ሚስጥሩን ከቤተሰቡና ጓደኞቹ እንዲሁም ማንነቱን ለትምሕርት ቤት ሊያጋልጥው ካስፈራራው ሰው ጋር የሚያደርገውን ትግል ያሳያል። በተጨማሪም በበይነ መረብ ከተዋወቀው እና ፍቅር ካስያዘው ነገር ግን ማንነቱን የማያውቀውን የክፍል ጓደኛው ማን እንደሆን ለማወቅ የሚያደርገውንም ጥረት ያሳያል።

Love, Simon መጀመሪያ የታየው ፌብሪወሪ 27፣ 2018 እ.አ.አ በMardi Gras Film Festival ሲሆን በይፋ የተለቀቀው በዩናይትድ ስቴትስ ማርች 16 2018 እ.አ.አ ነው። የፊልም ተቺዎች በበኩላቸው ፊልሙ ባሉት "ደማቅ የፍቅር ስሜት፣ ለየት ለየት ያለ የተዋናዮች ቡድንና አብዮታዊ መደበኛነት" አሞግሰውታል። በተጨማሪም ፊልሙን "አስደሳችና ልብ የሚነካ" መሆኑን ገለጸዋል። በስመ ጥር የሆሊውድ ስቱዲዮ የተሰራ የመጀመሪያው በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ወጣት የፍቅር ሕይወት ታሪክ ላይ ያተኮረው ፊልም በዓለም ዙሪያ $65 ሚሊዮን ብር ገቢ አስገኝቷል።

ታሪክ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ሳይመን ስፒየር በአትላንታ፣ ጆርጂያ ክፍለ ከተማ የሚኖር የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪነቱን ያልገለጸ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ነው። ከቤተሰቡ ጋር ጠንካራና በፍቅር የተሞላ ግንኙነት አለው። አስቀድሞ የሚያውቃቸው ኒክ (Nick) እና ሊያ (Leah) እንዲሁም ቅርብ ጊዜ ከተዋወቃት አቢ (Abby) ጋር ጥብቅ ጓደኝነት መስርቷል።

አንድ ቀን ሊያ ሳይመንን የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የምስጢር መስጫ ድረ ገጹ ላይ በድብቅ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ስለሆነው አንድ የትምህርት ቤታቸው ተማሪ ጽፎ ስላየችው ጽሁፍ ትነገረዋለች። ስለተማሪው የሚታወቀው በኦንላይን ስሙ "Blue" (ብሉ) መባሉ ብቻ ነው። ሳይመን በኢሜይል ከብሉ ጋር መጻጻፍ ይጀምራል፣ እርሱም ለኢሜይሉ "Jacques" (ዣክ) የሚል ስም ይጠቀማል። ሁለቱም ስለራሳቸው ግላዊ መረጃ በመለዋወጥ ግንኙነት ይፈጠራሉ። ይሁን እንጂ እርስ በእርሳቸው የተላላኳቸው ኢሜይሎች በስህተት በሌላ ተማሪ እጅ ይገባል። የሳይመንን ሚሰጢር በእጁ ያስገባው ማርቲን (Martin) የሚባለው ተማሪ አቢን የሳይመን ጓደኛ በጣም ይወዳታል ነገር ግን ጓደኛ ሊያደርጋት አልቻለም። የሳይመንን ምስጢር እንደ ማስፈራሪያ በመጠቀም አቢን ጓደኛው እንድትሆን እንዲረዳው ይህን ካላደረገ ግን ምስጢሩን ለመላው ትምህርት ቤት እንደሚነግርበት አስፈራራው፡፡ ሳይመን በዚህ መሃል የክፍል ጓደኛው የሆነው ብራም (Bram) "ብሉ" ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ ይጀምራል።

በሃሎዊን ግብዣ ላይ ሳይመን ከብራም ጋር ለመነጋገር ቢሞክርም ከሴት ተማሪ ጋር ሲሳሳም ያየዋል። ሳይመን ለኒክ አቢን የሚወድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነ የፍቅር ጓደኛ እንዳላት በመንገር ይዋሸዋል። ከግብዣው በኋላ ሊያ ለሳይመን አንድን ሰው እስከ ሕይወቷ መጨረሻ የምታፈቅር ሆኖ እንደሚሰማት ትነግረዋለች። ሳይመን ይህ የምታፈቅረው ሰው ኒክ ነው ብሎ ያምናል።

በአንድ ምግብ ቤት ውስጥ ሳይመን ከአቢና ከማርቲን ጋር ተገናኝቶ ለሚያሳዩት የቲያትር ትዕይንት ይለማመዳሉ። ከሳይመንና ከአስተናጋጃቸው፣ ላይል (Lyle)፣ በመሃል ጥሩ ግንኙነት ይፈጠራል። ሳይመን እርሱ "ብሉ" ሊሆን ይችላል ብሎ ያምናል። በኋላ በሌሊት ሳይመን ለአቢ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪነቱን ይነግራታል። እርሷም በአዎንታዊ ስሜት ትቀበለዋለች።

በትምህርት ቤት የኳስ ጨዋታ ላይ ሆነው ሳይመን ላይልን ያየዋል። ላይል "ብሉ" መሆኑን ሊጠይቅ እያሰበ ሳለ ግን ላይል አቢን እንደሚወድ ይደርስበታል። በዚህም የተናደደው ሳይመንን ማርቲን ምክር እንዲሰጠው ሲጠይቅ ሳይመን አዝወትሮ መነዝነዙ አበሳጭቶት "ደፍረህ የፈለግከውን አድርግ ወይም ተወው" ይለዋል። በዚህ መሰረት ማርቲን ያቀደውን ለማድረግ ይወስናል። ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ተሳታፊዎች ሁሉ ብሔራዊ መዝሙር መዘመራቸውን ማርቲን ያስቆማና ለአቢና ለተሳታፊዎች ሁሉ አቢን እንደሚወድ ይነግራቸዋል። አቢ ግን ለእርሱ እንደዚያ ዓይነት ስሜት እንደሌላት ትነግረዋለች። ይህንንም ተከትሎ ማርቲንን ሌሎቹ ተማሪዎቹ ያላገጡበታል።

ማርቲን በተፈጠረው ነገር ሰዎች እርሱ ላይ ማላገጣቸውን እንዲያቆሙና በበቀል ስሜት በገና ዋዜማ የሳይመን ኢሜይሎችን በምስጢር ድረ ገጹ ላይ በመለጠፍ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪነቱን ለመላው ትምህርት ቤት ያሳውቅበታል። የሳይመን እህት ኖራ (Nora) ወንድሟን ልታጽናናው ብትሞክርም ፍቃደኛ ሳይሆን በመቅረት የመኝታ ቤቱ በር ይዘጋባታል በዚህም ብቻ ሳያበቃ ከትምህርት ቤት ጓደኞቹ ለሚደርሱት መልዕክቶች ምላሽ መስጠት ያቆማል። በዕለተ ገና ሳይመን የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪነቱን ለወላጆቹ ይነግራቸዋል። ምንም እንኳ ቢገርማቸውም ይቀበሉታል።

ከበዓል ዕረፍት በኋላ ፍቅረኛሞች የሆኑት ኒክ እና አቢ ተበሳጭተው ሳይመንን ስለ ነገራቸው ውሸቶች ያፋጥጡታል። እርሱም ያደረጋቸውን ነገሮች በሙሉ ማርቲን እያስፈራራው የሰራቸው ጥፋቶች መሆኑን ይነግራቸዋል። ሊያ የምትወደው ኒክን ሳይሆን ሳይመን መሆኑን ትነግረዋለች። ጓደኞቹ ከተጣሉት በኋላ ሳይመን ከብሉ የመጨረሻ ኢሜይል ይደርሰዋል። በኢሜይሉ ውይይታቸው ብሉ ይፋ በመውጣቱ ማዘኑን ይገልፃል። ከዚያህ በኋላም መጻጻፋቸውን መቀጠል እንደማይፈልግ ነግሮ የኢሜይል መለያውን ያስወግዳል። ሳይመን ጓደኞቹን ብቻ ሳይሆን ፍቅር ያስያዘው ምስጢራዊውን ሰው ስላጣ በጣም ያዝናል።

በትምህርት ቤት መመገቢያ ክፍል ውስጥ ሳይመንን እና ግልጽ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ የሆነ ኢታን (Ethan) በተባለ ሌላ ተማሪ ላይ ሁለት ተማሪዎች ያላገጣሉ። በሳይመን እና በኢታን መካከል የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪነታቸውን መግለጻቸውን ተከትሎ ያጋጠሟቸውን ችግሮች በመወያየት ጥሩ ግንኙነት ይፈጠራሉ። ሳይመን ሊያን ይቅርታ ይጠይቃታል። በምስጢር መስጫ ድረ ገጹ ላይ ጓደኞቹን በይፋ ይቅርታ ይጠይቃቸዋል እንዲሁም ብሉ ከእርሱ ጋር የትምህርት ቤት ካርነቫል በዓል ላይ እንዲገናኙ ይጠይቀዋል።

ከትምህርት ቤቱ የሙዚቃ ዝግጅት በኋላ ሊያ፣ ኒክ እና አቢ ከሳይመን ጋር እርቅ ያወርዱና ከእነርሱ ጋር ወደ ካርነቫሉ እንዲሄድ ይጋብዙታል። ሳይመን ብሉን ለመጠበቀ ፌሪስ መንኩራኮሩ ላይ ይቀመጣል። ሳይመን የፌሪስ መንኩራኮር ላይ ለመቆየት የገዛቸው ትኬቶች በሙሉ ሲያለቁ ማርቲን ላጥፋው ጠፋት ካሳ ሌላ አንድ ዙር ትኬት ለሳይመን ይገዛለታል። ዙሩ ከመጀመር በፊት ብራም ከሳይመን ጎን በመቀመጡ ብሉ እርሱ መሆኑን ለሁሉም ግልጽ ያደርጋል። ሳይመን ከሴት ተማሪ ሲሳሳም ያየው በስካር መንፈስ የተሰራ ስህተት እንደነበረ ይነግረዋል። አንድ ላይ ፌሪስ መንኩራኮሩ ላይ ተቀምጠው ይሳሳማሉ ይሄንንም ክስተት ቆመው ሲመለከቱ የነበሩት ጓደኞቻቸው ደስታቸውን በጨብጨባ ይገልጣሉ።

የሳይመን ሕይወት ቀስ በቀስ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ይመለሳል። እርሱና ብራም ፍቅረኛሞች ይሆናሉ።