ከ«ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ» ለውጦች መካከል ያለው ልዩነት

ከውክፔዲያ
Content deleted Content added
No edit summary
መስመር፡ 116፦ መስመር፡ 116፦
* Ethiopia: Anatomy of a Traditional Polity, John Markakis (2006)
* Ethiopia: Anatomy of a Traditional Polity, John Markakis (2006)
* In Search of the Historical DNA of the Eritrean Problem (Review of “The Eritrean Affair (1941-1963) by Ambassador Zewde Retta), Professor Negussay Ayele
* In Search of the Historical DNA of the Eritrean Problem (Review of “The Eritrean Affair (1941-1963) by Ambassador Zewde Retta), Professor Negussay Ayele

[[en:Wolde Giyorgis Wolde Yohannes]]
[[fr:Wolde Giyorgis Wolde Yohannes]]
[[he:וולדה גיורגיס

እትም በ20:59, 10 ኦገስት 2010

ፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ (፲፰፻፺፫ ዓ/ም - ፲፺፻፷፰ ዓ/ም) በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት በተላለያዩ ጊዜያት የፅሕፈት፤ የእርሻ፤ የአገር ግዛት እና ገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሁም የጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ በመሆን አገልግለዋል። በሥነ ፅሁፍም መስክ ላይ የድርሰት መፅሐፍቶችን ያበረከቱ እንደዚሁም በትውልድ አገራቸው ቡልጋ ቤተ ክርስቲያን ያሠሩ ትልቅ ሁለ ገብ ሰው ነበሩ። ወደፊት የንጉሠ ነገሥቱን መንግሥት የሚደመድመው የስድሳ ስድስቱ አብዮት በተፋፋመበት ወቅት፣ እኚህ ሰው ለሕክምና ወደ ሎንዶን መጥተው ሲታከሙ ቆይተው ሐምሌ ፳ ቀን ፲፺፻፷፰ ዓ/ም እዚያው አርፈው ኬንሳል ግሪን (Kensal Green Cemetery) በሚባል የመቃብር ሥፍራ ተቀበሩ። [1]

የወጣትነት ዘመናት

ፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደጊዮርጊስ ቡልጋ አውራጃ ውስጥ መስኖ ዘንባባ በሚባል ሥፍራ በ፲፰፻፺፫ ዓ/ም ከቤተ ክህነት ወገን ተወልደው በዘመኑ ስርዓት የግዕዝ እና አማርኛ ትምሕርታቸውን በዚያው በቤተ ክህነት አጠናቀቁ። ከዚያ ቀጥሎ መቼ፣ እንዴትና ለምን ለሚሉት ጥያቄዎች መረጃ ባይገኝም ሆኔም ቀሬ በንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ዘመን መሆኑ ነው፣ አዲስ አበባ ይመጡና በዳግማዊ ምኒልክ ትምሕርት ቤት ፈረንሳይኛ ቋንቋ አጥንተዋል። በዚህም የቋንቋ ዕውቀት በአስተርጓሚነት ሲያገለግሉ ቆይተው ኢትዮጵያ የዓለም መንግሥታት ማኅበር አባል ስትሆን በ ፲፱፻፲፰ ዓ/ም ወደ ማኅበሩ ፅሕፈት ቤት ዠኔቭ ይላካሉ።

ከዠኔቭ ሲመለሱ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ ጣልያንቤልጅግ እና ጀርመን ክፍል ኃላፊ ሆነው ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ በ፲፱፻፳፫ ዓ/ም በዚያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዲሬክቶርነት ማዕርግ ለሦስት ዓመት አገልግለዋል። [2]፲፱፻፳፮ ዓ/ም በፅሕፈት ሚኒስቴር ጠቅላይ ዲረክቶር ተብለው ለጥቀውም የንጉሠ ነገሥቱ የግል ፀሐፊ ሆነው እስከ ጠላት ወረራ ድረስ ሲያገለግሉ ቆዩ። ከንጉሠ ነገሥቱም ጋር የቅርብ ግንኙነታቸውና ወደፊት የሚይዙትም የ’ፈላጭ ቆራጭነት’ ሥልጣን የተመሠረተው በዚህ ጊዜ እንደሆነ ይገመታል።

የጠላት ወረራና ያስከተለው ስደት

የንጉሠ ነገሥቱ የግል ፀሐፊ አቶ ወልደ ጊዮርጊስ ፋሽሽት ኢጣልያ አገራችንን በወረረ ጊዜ ክንጉሠ ነገሥቱ ሳይለዩ፣ በማይጨው ዘመቻ ከአዲስ አበባ ወደደሴ አብረው ኅዳር ፲፰ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ/ም ይጓዛሉ ።[3] በኋላም ግንቦት ወር ፲፱፻፳፰ ዓ/ም በጂቡቲ እና በኢየሩሳሌም በኩል አድርገው ከሐይፋ ወደብ እስከ ጅብራልታእንግሊዝ የጦር መርከብ፣ ከጅብራልታር እስከ ሳውዝሃምፕቶን የእንግሊዝ ወደብ በመንገደኛ መርከብ ተጉዘው የአምስት ዓመት የስደታቸውን ዘመን አብረው ተሳትፈዋል።

በስደት ዘመን ንጉሠ ነገሥቱ ከቤተሰባቸው ጋር በባዝ ከተማ “ፌየርፊልድ ሃውስ” የስደት ዘመን እንዳሳለፉ ብዙ ተጽፏል። ከቤተ ሰቡም ጋር አብረው የነበሩ (ሠራተኞች፣ አገልጋዮች፣ መነኮሳት) ሌሎች ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንደነበሩ ‘ሉትዝ ሄበር’ (Lutz Haber) “ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በባዝ ከ 1928 – 1932 ዓ.ም” (The Emperor Haile Sellasie I in Bath 1936 – 1940) በሚል ጽሑፉ በሰፊው አስፍሮታል። በዚያ የስደት ዘመን ግን ፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ የት እንደኖሩ መረጃ ማግኘት ባይቻልም የንጉሠ ነገሥቱ የግል ጸሐፊ ስለነበሩ እምብዛም እንድማይርቋቸው ይገመታል። ሆኔም ቀሬ በታኅሣሥ ፲፱፻፳፱ ዓ/ም የፈረንጆች ገና ዕለት ንጉሠ ነገሥቱ በቢቢሲ ራዲዮ ለአሜሪካውያን ደጋፊዎቻቸው መልዕክት ሲያስተላልፉ፣ በስደት የዲፕሎማሲ ትግል ሲያካሂዱና ከዓለም መንግሥታት ማኅበር ጋር ‘የአእምሯዊ ግብግብ’ በገጠሙበት ጊዜ አጠገባቸው ሆነው ከሚያማክሯቸው ሰዎች አንዱ አቶ ወልደ ጊዮርጊስ እንደነበሩ ንጉሥ ነገሥቱ “ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ - ፪ኛ መጽሐፍ” ላይ ጠቅሰውታል።

ከድል እስከ ግዞት

<<የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሥልጣን በግዛቱ ውስጥ ያልተወሰነ ነው። ሥልጣኑ ሃይማኖታዊም ሆነ ሥጋዊ ጉዳዮችን ያጠቃልላል። በሥልጣኑ ይሾማል፣ ይሽራል መውሰድም፣ መስጠትም፤ ማሠርም፣ መፍታትም፤ መግደልም፣ መስቀልም ይችላል። ትንሹም ትልቁም ንጉሠ ነገሥቱ የእግዚአብሔር ተወካይ ነው ብሎ ስለሚያምን የእርሱን ትዕዛዝ ያለአንዳችም ሰበብ ወይም ማመካኘት በደስታ ይቀበላል።>> “ዝክረ ነገር” ከ ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል [4]

“በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የአስተዳደር ስልት፤ ለሥልጣን የብቃተ ቢስነት ወንጀል ወይም የማይካድ የሙስና ድርጊት ሲታይ የተለመደው ቅጣት ወደሌላ ሥራ መዛወር ሲሆን፤ ለንጉሠ ነገሥቱ ታማኝ አለመሆን ግን ያለምንም ጥርጣሬ በፈጣን ፍርድ በግዞት ዓለም መጥፋትን ያስከትላል።” ጆን ማርካኪስ (John Markakis)፣ “ኢትዮጵያ፥ የባህላዊ ሽከታ ሥነ አካል” (Ethiopia: Anatomy of a Traditional Polity)።[5] እዚህ አስተያየት ላይ ደግሞ ‘የንጉሠ ነገሥቱን ስም እና ተወዳጅነት የሚሻማ/የሚያሳማ ዝናም ያተረፈ ‘ባለ ሥልጣን’ የሚጠብቀው እንዲሁ ተመሳሳይ ቅጣት ነበር’ ብንል ከእውነቱ አንርቅም።

ስለፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ እምብዛም የተጻፈ ባይኖርም ያሉት ቅንጥብጣቢዎች ከሞላ ጎደል የሚያሳዩን በዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከላይ የሠፈሩትን ሁለቱንም ገጽታዎች መጀመሪያ በ”እንደራሴ” መልክ የተጠቀሙበትና በመጨረሻውም የግዞት ዓለምን የቀመሱባቸው ገጽታዎች መሆናቸውን ነው።

ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር አብረው በስደት በነበሩባቸው ዘመናት በታማኝነታቸው የንጉሠ ነገሥቱን እምነት አስገኘላቸው። የግል ጸሐፊነታቸው በኋላም የጽሕፈት ሚኒስቴርነታቸው ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ከማንም የላቀ አቀራረብ (ስለዚህም ተሰሚነትን) ስለሰጣቸው እንዲሁም የራሳቸው የዱኛ ችሎታ ከንጉሠ ነገሥቱ ቀጥሎ ሌላ ማንም ያልነበረውን የሥልጣን መብት ሰጥቷቸዋል። (ባህሩ ዘውዴ - የዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ ከ 1847 እስከ 1983)

ከስደት ሲመለሱ ‘ፀሐፌ ትዕዛዝ’ ተብለው የጽሕፈት ሚንስቴር ሆነው ይሾማሉ። በተለምዶው ስርዓት የጽሕፈት ሚኒስቴሩ የንጉሠ ነገሥቱን መንግሥታዊ መዝገቦች ጸሐፊ እና ጠባቂ ሲሆን፣ ዐዋጆች፤ ትዕዛዛት እና መንግሥታዊ ሰነዶችም በዚሁ ሰው በኩል ያልፋሉ። ይሄ ማለት ደግሞ ከላይ እንደሠፈረው፣ ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደመስቀል በ”ዝክረ ነገር” ላይ “ትንሹም ትልቁም ንጉሠ ነገሥቱ የእግዚአብሔር ተወካይ ነው ብሎ ስለሚያምን የእርሱን (የንጉሠ ነገሥቱን) ትዕዛዝ ያለአንዳችም ሰበብ ወይም ማመካኘት በደስታ ይቀበላል።>> ብለው ያስረዱንን ስርዓት ለዚህ ማዕርግ የበቃ ሰው የቱን ያህል ሥልጣን እንደነበረውና ዝንባሌው የራሱን ሥልጣን የማዳበርም ከሆነ ይሀንን ዓይነት መሠረት ይዞ የዝንባሌውን ዓላማ ስኬታማ ማድረግ እንዴት ቀላል እንደሆነ ይገነዘቧል።

፲፱፻፴፭ ዓ/ም ፣ ድል በተገኘ በሁለት ዓመቱ፣ ንጉሠ ነገሥቱ “የመንግሥታችችን ሚኒስቴሮች ሥልጣንና ግዴታዎች ለማብራራት” በሚል ዐዋጅ በራሳቸው ሰብሳቢነት የሚመራ የሚኒስቴሮች ምክር ቤት እና “ቃለ መሐላ” የሰጡ ሚኒስቴሮች መሾማቸውን ሲይስታውቁ የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት በፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ እንደሚመራና ምክር ቤቱም በኒሁ ሰው ‘ቁጥጥር’ ስር እንደሚሆን ታወጀ። እኒህ ሚኒስቴር በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ውስጥ “ከማናቸውም ባለሥልጣን ጋር በቀጥታ የመገናኘት ሥልጣን” እንደተሰጣቸው ዐዋጁ ለጥቆ አስታወቀ። እንግዲህ በዚህ አዋጅ መሠረት ፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ በንጉሠ ነገሥቱ ፍላጎት እና ዐዋጅ የዘውዱን የበላይነት ለማስከበር ሙሉ ሥልጣን ‘እንደራሴ’ መሆናቸው ተረጋግጧል። በሌላ መልክ ሲተረጎም፤ ፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ መስቀል በንጉሠ ነገሥቱ እውቀትም ይሁን ፍላጎት ‘በማስመሰል’ም ይሁን በትክክል የንጉሠ ነገሥት መንግሥቱን ዓላማ በማራመድ ኢትዮጵያን ለማልማት፤ በዘመናዊ መንገድ ለመምራት፤ ‘ለመፍለጥ ለመቁረጥ’፤ የራሳቸውን ባለሟሎች እና ወገኖች በማንኛውም ረገድ ለማዳበር፤ የራሳቸውን የሥልጣን መሠረት ለማስፋፍትም ሆነ የዝዘውድ ስርዓቱን ዘላለማዊ ለማድረግ ልዩና ቁልፋዊ ቦታ እንደነበራቸው እንገነዘባለን።

ምስጢራዊና የሥልጣን አያያዝ፣ አጠቃቀም እና ‘ከመለኮት የተሠጠ’ መብታቸውን ከማንም ጋር መሻማት የማይፈልጉትስ ንጉሠ ነገሥት እንደዚህ ዓይነት ዐዋጅ ሲያስተላልፉ፣ ምን አስበው ኖሯል? በጊዜው አገራችንን ከፋሽሽት ጣልያን ለማላቀቅ አባቶቻችን እና እናቶቻችን የሚያደርጉትን ተጋድሎ ለመደገፍ ገብተው የነበሩት እንግሊዞች፤ ከድል በኋላ ኢትዮጵያን ቢያንስ በሥራቸው እንደቅኝ ግዛት ለማስተዳደር፤ ይሄ ባይሳካላቸው ደግሞ ሕዝቦቿንና ግዛቷን ከፋፍለው ለመበተን የሚጥሩበት ጊዜ ነበር። ታዲያ ለንጉሠ ነገሥቱ የዚህ አዋጅ መነሻ ምናልባት እንግሊዞች በዓላማቸው የቀናቸው እንደሆነ የሚያሳብቡበት (scape-goat) የዋህ ሰው ማዘጋጀታቸው ኖሯል?

የፀሐፌ ትእዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ አነሳስ፣ እድገት፣ ይሄን ያህልም ሥልጣን እስከመያዝ መብቃትና በመጨረሻውም ውስጡ ከተበላ በኋላ እንደሚወረወር የሙዝ ልጣጭ መደረግ ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን በአንባቢ እና የኢትዮጵያን የቅርብ ታሪክ በሚያጠና ሰው ጭንቅላት ላይ ያስነሳሉ።

በሥልጣን ዘመን

፲፱፻፴፬ - ፴፭ ዓ/ም የ”አንግሎ-ኢትዮጵያ ስምምነት” (Anglo-Ethiopian agreements of 1941-42) ድርድር ወሳኝና ቁልፍ የሆነ ሚና ተጫውተዋል። በተለይም በጊዜው ኦጋዴንን በእንግሊዝ መንግሥት ሥር ለማስተዳደር የሚካሄደውን ሴራ በመቃወም ያደረጉት ትግል በአንዳንድ የብሪታንያ ባለ ሥልጣናት አመለካከት እሳቸውን ያለአግባብ ‘ጸረ-ብሪታንያ’ እንዳስባላቸው ትልቁ የኢትዮጵያ ታሪክ ምሑር ሪቻርድ ፓንክኸርስት ገልጾታል። ይሄንን በተመለከተ እሳቸው “እኔ ለኢትዮጵያ የቆምኩ እንጂ ጸረ ማንም አይደለሁም።” ብለዋል።

፲፱፻፴፭ ዓ/ም የንጉሠ ነገሥቱን መንግሥት በአውራጃዎቹና በጠቅላይ ግዛቶቹ ላይ ‘ለማጠንከር’ በወሰዱት እርምጃ የአገር ግዛት ሚኒስቴርነትን ሥልጣን ከጽሕፈት ሚኒስቴር ጋር በመለጠቅ ያዙ። ይሔ ሚኒስቴር በአገሪቱ አጠቃላይ የጸጥታን ጉዳይ የሚቆጣጠርም ስለነበር ፀሐፌ ትዕዛዝን የበለጠ አስከባሪና ተፈሪነትን አስገኝቶላቸዋል። ሆኖም የአገር ግዛት ሚኒስቴርን በ፲፱፻፵፩ ዓ/ም ለቀው የፍትሕ ሚኒስቴርነትን ያዙ። የራሳቸውን ባለሟሎችም በየሚኒስትሩና በየ መንግሥት መሥሪያ ቦታዎች አሠማሩ።

፲፱፻፵፰ ዓመተ ምሕረቱን የሕገ መንግሥት ረቂቅ ከሦስት አሜሪካውያን እና ከጊዜው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አክሊሉ ሀብተ-ወልድ ጋር አዘጋጅተዋል።

በንጉሠ ነገሥቱ የሳቸው ልዩ እና አቻ የሌለው ተሰሚነት እንዲሁም የያዙት ቆራጣዊ ሥልጣን የሚያስፈራቸውና የሚያሳስባቸው መሳፍንት፣ መኳንንትና ባለ ሥልጣኖች ቁጥር እያደር እይጨመረ መምጣቱ አልቀረም። ለጊዜው በንጉሠ ነገሥቱ አመለካከት (እንደዚህ የተጠላ ባለ ሥልጣን በንጉሠ ነገሥቱ ላይ ለማመጽ አይፈልግም እንዲያውም ጥላቻን ከንጉሠ ነገሥቱ ላይ ይመክታል) እና ግምገማ የዚህ ዓይነት ጥላቻ ፀሐፌ ትዕዛዝን እስከነአካቴው ጠቀመቸው እንጂ አልጎዳቸውም።


ግዞት

ሆኖም የውጭ ጋዜጠኖች ፀሐፌ ትዕዛዝን ‘የኢትዮጵያ አምባ ገነን’ ሲሉ ማንሳታቸው ለንጉሠ ነገሥቱ የሳቸው የዝና ተወዳዳሪ ሆኖ መታየት የፀሐፌ ትዕዛዝን ውድቀት ካስጀመሩት ምክንያቶች አንዱ ነው ተብሉ ይገመታል።

ሌላው ደግሞ ምክንያት የኤርትራን እና የኢትዮጵያን ‘ማኅበራዊ’ መንግሥት ይመለከታል። አምባሳዶር ዘውዴ ረታ፣ “የኤርትራ ጉዳይ” በተባለው መጽሐፋቸው እንደገለጹልን በመጋቢት ወር ፲፱፻፵፩ ዓ/ም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤርትራን በተመለከተ ጉዳይ ክርክር ሲደረግ የእንግሊዙ ልዑክ ያቀረበውን የመከፋፈል ኃሳብ በመቃወም የጊዜው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አክሊሉ ሀብተ-ወልድ መልስ ሲሰጡ ይሄንን በመቃወም ስለተናገሩት ንግግርና የእንግሊዝን መንግሥት ‘አስቀይመው’ ከሆነ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ምን ዓይነት እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ለመምከር ንጉሠ ነገሥቱ በሰበሰቡት ጉባዔ ላይ በጊዜው የግል ጸሐፊያቸው የነበሩት እና ዬንግሊዝ ደጋፊ የሚባሉት አቶ (በኋላ ፀሐፌ ትዕዛዝ) ተፈራ ወርቅ ኪዳነ ወልድ አክሊሉ ለብሪታንያ መንግሥት ልዑክ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ደጋፊ ፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ደግሞ የአክሊሉ እርምጃ ትክክል መሆኑን እና ምንም ዓይነት ይቅርታ መደረግ እንደሌለበት ተከራከሩ።

በዚሁ መጽሐፍ ላይ ኤርትራና ኢትዮጵያ በ’ኅብረት መንግሥት’ አስተዳደር (federation) በተዋሃዱ ዓመት ባልሞላው ጊዜ በተነሳው የ’ኅብረት መንግሥት’ አለማስፈለግ ጉዳይ በ መስከረም ወር ፲፱፻፵፯ ዓ/ም በተደረገው የንጉሠ ነገሥቱ ውስጣዊ ጉባዔ ላይ ልዑል ራስ ካሳ በአንድ አገር ውስጥ ሁለት ዓይነት አመራር ሊኖር ስለማይችል በአንድ ሕጋዊ አስተዳደር ሁሉንም የኢትዮጵያ አካላት ማስተዳደር እንደሚያስፈልግ ሲያስረዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ አክሊሉ ሀብተ ወልድ ደግሞ ኢትዮጵያ ወዳም ሆነ ጠልታ ይሄንን ዓይነት አስተዳደር በሕግ የተቀበለችው ስለሆነ ይሄንን በጥንቃቄ መተግበር ግዴታዋ እንደሆነና ኅብረታዊ መንግሥቱን መለወጥ ካስፈለገም ሕጋዊ በሆነ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ታዛቢዎች የሚመሰከር የ’ውሳኔ ሕዝብ’ ድምጽ መሆን እንዳለበት ሲያስገነዝቡ፣ ፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ አክሊሉን በመደገፍ ‘ ኢትዮጵያ የኅብረታዊ መንግሥትን ለመደምሰስ እንዳልተዘጋጀችና እርምጃው የሚያስከትላቸውንም ክስተቶች በቅጡ ለማጥናት ጊዜ ያስፈልጋል።’ ብለው ካስረዱ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ ይሄንን ግምገማ እሳቸው ያስጀመሩት እና የሚገፋፉት ጉዳይ ነው በሚል ተርጉመው ፀሐፌ ትዕዛዙን በመቆጣት ‘’ለ እንደራሴያችን ራስ አንዳርጌ ወይም ለምክትሉ ደጃዝማች አስፍሃ የኅብረት መንግሥቱን መውደቅ የሚያፋጥን ምንም ዓይነት ትዕዛዝ እንዳልሰጠን ከሁሉ የበለጠ አንተ ታውቃለህ።” በማለት ገሰጿቸው ይሉናል።

እንግዲህ ባንድ በኩል ፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ ከንጉሠ ነገሥቱ በዐዋጅ በተሰጣቸው ሙሉ ሥልጣን ብዙ የሚፈሯቸውና የተከፉ መሳፍንት፣ መኳንንትና ባለሥልጣናት እንደጠሏቸውና የሳቸውን ከሥልጣን መውረድ በጉጉት ይጠባበቁ እንደነበር ተመልክተናል።

ቀጥሎም የንጉሠ ነገሥቱ የግል ፀሐፊ (ማለትም ለንጉሠ ነገሥቱ ቅርብነትና ተሰሚነትን እያገኙ የመጡት) እንዲሁም የ’እንግሊዝ ደጋፊ’ ይባሉ የነበሩት ፀሐፌ ትዕዛዝ አካለ ወርቅ ኪዳነ ወልድ ከወልደ ጊዮርጊስ ጋር ያደርጉትን ሙግት ተመልክተን ምናልባት የጽሕፈት ሚኒስቴሩ ዘላቂና ኃይለኛ ባላጋራ አጋጥሟቸው ይሆን ለማለት እንችላለን።

በሦስተና ደረጃ የኤርትራን የኅብረት መንግሥት በተመለከት የንጉሠ ነገሥቱ ተግሳጽ በሌሎች (ተቃዋሚዎቻቸው) ፊት ሲደርሳቸው ጆን ማርካኪስ “በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የአስተዳደር ስልት፤ ለሥልጣን የብቃተ ቢስነት ወንጀል ወይም የማይካድ የሙስና ድርጊት ሲታይ የተለመደው ቅጣት ወደሌላ ሥራ መዛወር ሲሆን፤ ለንጉሠ ነገሥቱ ታማኝ አለመሆን ግን ያለምንም ጥርጣሬ በፈጣን ፍርድ በግዞት ዓለም መጥፋትን ያስከትላል።” ያለን በፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስው ላይ እየተተገበረ መሆኑን እንገነዘባለን።

ወዲያውኑ ፀሐፌ ትዕዛዝ ከጽሕፈት ሚኒስቴርነታቸው ተሽረው መጀመሪያ የአሩሲ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ ሆነው እስከ ፲፱፻፶፫ ዓ/ም ከቆዩ በኋላ ወደ ገሙ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳድሪ ሆነው ተዛወሩ።

የስድሳ ስድስቱ አብዮት ኃይለ ሥላሴን ከሥልጣን ከማውርደኡ ከጥቂት ጊዜ ቀደም ብሎ ለሕክምና ወደ እንግሊዝ አገር ይሄዱና ሁለተኛውንና የመጨረሻውን የስደት ዘመን ጀምረው በተወለዱ በሰባ አምስት ዓመታቸው እዚያው እንግሊዝ አገር አርፈው ተቀበሩ።

ሥነ ጽሑፍ

ፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ ለአማርኛ ቋንቋ ካበረከቷቸው ድርሰቶች

  • የወንድ ልጅ ኩራት ስለሀገር መሞት
  • የዓለም ጠባይ ሐሴትና ብካይ
  • ከሥራ በኋላ ሥራ ስትፈቱ እንቆቅልሽ ተጫወቱ
  • ሥነምግባር
  • አምስት መንገዶች

የተባሉ ይገኙባቸዋል። ከዚህም ሌላ በተወለዱበት ቡልጋ ውስጥ የቅድስጌ ማርያምን ቤተ ክርስቲያን በግል አሠርተዋል።

ከድርሰቶቻቸው

ከአምስት መንገዶች (፲፱፻፶፬ ዓ/ም)

የሰው አሳብና የውሻ ጅራት ዘወትር ወደ ላይ ነው፡፡ ነገር ግን ውሻ በትር ሲመዘዝበት ጅራቱን እንዲሸጉብ፤ ሰውም ላይ ላዩን እላለሁ ሲል አንድ ዓይነት አደጋ ሲወድቅበት ጭብጥ እንኳ አይሞላም፤ ከአዳም መወለዱን የሚያምን ሁሉ ይህን ሊክድ አይችልም፡፡

ሰው ሃይማኖት ካለው በመከራም ላይ ቢወድቅ መከራም ቢወድቅበት ዘወትር በላይ ከመሆን በቀር በምንም አይጨነቅም፡፡ ስለዚህ ዮሐንስ አፈ ወርቅ የሚባለው መንፈሳዊ ሊቅ በዘጠነኛው ድርሳኑ አንተ ሰው በዓይኖችህ ፊት የሃይማኖት መጠኗን አትናቅ፤ ናቂ የሆነ ዓይን በሃይማኖት ላይ ሊገለጽ አይቻልም፤ አባ፣ አባ ብታውቁባት ጐንደርም ዋልድባ ናት፤ እንደሚባለው ሰው ቢያውቅበት ሳይንስም ሃይማኖት አለበት፡፡

ሰውየው፤ ሰውየውን ውሻህን በቀበሮ ለውጠኝ ቢለው የሚያደምጠውን ትቼ የሚያለምጠውን የምለውጠው ምኔ ሞኝ ነው? አለው ይባላል፡፡ ሰው ዐዋቂ ከሆነ ዘንድ በሃይማኖት ረገድ አለዐዋቂ ይሆን ዘንድ ምኑ ሞኝ ነው? በሳይንስ ምርመራ ያገኘው ጥበብ በጣም ከፍ እያለ ሲሔድ በእግዚአብሔር ላይም ያለው እምነት በበለጠ አኳኋን ከፍ ከፍ ማለት አለበት፡፡

ስለዚህ በሳይንስ ረገድም የሚደረገው አስተያየት ለመልክአ ሃይማኖት የጠራ መስተዋት ሳይሆነው አለመቅረቱ የታወቀ ነው፡፡

ዱሮ አንድ ተማሪ መንገድ ሲሔድ ያገኙት ሰዎች ወዴት ትሔዳለህ? ቢሉት፣ ለትምህርት ወደ ዘጌ እሔዳለሁ፤ በስቲያውም ቡና ለቀማ አለ ይባላል፤ የሳይንስም ምርመራ እንዲሁ ነው፡፡ ሥጋዊ ጥበብን እንመረምራለን ሲባል፣ መንፈሳዊውም አብሮ ይገኛል፡፡


ሁሉም ከመሬት ተፈጥሮአል

ማንጠልጠያ የሌለው ከበሮ ከተጋደመበት ሲጐስሙት ድምፁን ማሰማቱ አይቀርም፡፡ ሃይማኖት የሌለው ሰው ግን ምን ድምፅ አለው፡፡"" ቢኖረውስ ምን ፍሬ ነገር ሊያሰማበት ነው ቢሆንም ከሃይማኖተ ውጭ አፍ እላፊ አላደርግም፡፡ "ሽንብራ ዱቤ አይገኝም በዱቤ" እንደ ተባለው የሃይማኖት ፍሬ ያለሃይማኖት በዱቤ ያለመገኘቱ እየታወቀ እንዴት ሰው ያለ ሃይማኖት ይኖራል፡፡ ይህማ እንደ እንስሶች መሆን አይደለምን፤ እንዳያውም እንስሳት ሃይማኖት ቢኖራቸውም ባይኖራቸውም ምን ቸገራቸው፡፡ ቢጠመዱም፤ ቢታረዱም፤ ቢገረፉም፤ ቢገፊፉም፤ ጣጣቸው የሚያልቀው በዚሁ በታችኛው ዓለም ስለሆነ ከሞት በኋላ ነፃ ናቸው፡፡

ከዚህም ላይ ልብ የሚመታና በስሜት ላይ መገረምን የሚጥል ቃል በማግኘቴ ሲከነክነኝ ይኖራል፡፡ እሱ እኮ ነገረኛ ነው፡፡ ተጠራጥሮ ያጠራጥራል፡፡ "የሰው ልጆችና የእንስሳ እጣ ነው፡፡ ድርሻቸውም የተስተካከለ ነው፡፡ ሰውም ከእንስሳ ብልጫ የለውም፡፡ ነገሩ ሁሉ ከንቱ ነውና፡፡ ሁሉም ወደ አንድ ቦታ ይሔዳል፡፡ ሁሉም ከመሬት ተፈጥሮአል፡፡ ሁሉም ወደ መሬት ይመለሳል፡፡ የሰው ልጆች ነፍስ ወደ ላይ እንድትወጣ፤ የእንስሳም ነፍስ ወደ ምድር በታች እንድትወርድ ለይቶ የሚያውቅ ማነው" ይላል፡፡

አባብሎች

- ደስ መሰኘትና መከፋት ሲዘዋወሩ ስለሚኖሩ ደስ ያለው እንደሚከፋው፣ የከፋው ደስ እንደሚለው አይጠረጠርም፡፡ - በዕድሜ መሰንበትና ፈተናን ሁሉ አልፎ ወደ ደህና ቀን መድረስ ብዙ ጊዜ መታደልና መክበር ነው፡፡ - በእናት ማኅፀን የተፀነሰ ፅንስ ቀኑ ሲደርስ በማኅፀን ታግዶ እንደማይቀር ሥራም በትጋት ከተጀመረ የሠራተኛው አሳብ ከወሰነው ጊዜ አያልፍም፡፡ - ፍልስፍና አድራሻ የለውም፤ ያለ ዕረፍት ሲሄድ የሚኖር የምርመራ አሞራ ከመሆኑም የተነሳ ከሁሉ ይደርሳል፡፡ - ማወቅ ወጣም ወረደ ለመደነቅ ብቻ አይደለም፤ ስህተት የሌለበት ሙሉ ሰውን ለመሆንም ነው እንጂ፡፡ - ሥጋ በመንፈስ እየተንቀሳቀሰ፣ መንፈስ በሥጋ እየተዳበሰ ግዙፍነትንና ረቂቅነትን ለመግለጽ፣ መንፈስ ወደ መንፈሳዊነት፣ ሥጋም ወደ ሥጋዊነት እያዘነበለ፣ በአንድ ሰው አካል ሁለት ኃይል ሲሠራ ይኖራል፡፡ (ብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ፣ 1935)

ማጣቀሻ

  1. ^ http://en.wikipedia.org/wiki/Wolde_Giyorgis_Wolde_Yohannes
  2. ^ Gebissa, Ezekiel (translation) : “My Life & Ethiopia’s Progress, vol two (1999) pg 16
  3. ^ Mockler, Anthony: “Haile Selassie’s War” (2003) pg 73
  4. ^ Markakis, John: “Ethiopia Anatomy of a Traditional Polity” (2006 ed), pg 252
  5. ^ Markakis, John: “Ethiopia Anatomy of a Traditional Polity” (2006 ed), pg 255

ዋቤ ምንጮች

  • ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ፣ አንደኛ መጽሐፍ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (፲፱፻፳፱) ዓ/ም
  • The Emperor’s Clothes, Gaitachew Bekele (1993)
  • My Life & Ethiopia’s Progress – Volume Two, Research Associates (1994)
  • A History of Modern Ethiopia, Bahru Zewde (2001)
  • Haile Selassie’s War, Anthony Mockler (2003)
  • Ethiopia: Anatomy of a Traditional Polity, John Markakis (2006)
  • In Search of the Historical DNA of the Eritrean Problem (Review of “The Eritrean Affair (1941-1963) by Ambassador Zewde Retta), Professor Negussay Ayele

[[he:וולדה גיורגיס