Jump to content

መሐረቤን ያያችሁ

ከውክፔዲያ
(ከቀበቶ የተዛወረ)

መሓረቤን ያያችሁ

ይህ፡ ልጆች መሮጥ ከቻሉበት ዕድሜ ጀምሮ፡ በቡድን ሆነው ሊጫወቱት የሚችሉት ጨዋታ ነው። ቁጥራቸው በርከት ብሎ፡ ትልቅ ክብ ሰርተው መቀመጥ ሲችሉ፡ ጨዋታውን መጫወት ይችላሉ። አጨዋወቱም፦

ልጆቹ ትልቅ ክብ ይሠሩና፡ እርስ በርስ እየተያዩ ይቀመጣሉ። አንድ መሓረብ የሚያክል፡ ሊወርወር የሚችል ጨርቅ ይዘጋጃል። ከዚያም፡ አንድ ልጅ ጨዋታውን ይጀምራል፤ ወይም፡ አብሮዋቸው ያለው ትልቅ ሰው ጨዋታውን ይጀምራል። መሓረቡን በእጁ ይዞ፡ ከጀርባቸው ክቡን እየተከተለ፡ ረጋ ብሎ፡ አንዱን እግሩን ሁለት ጊዜ መሬት እየጣለ፡ ሁለተኛውን እያስከተለ፡ «መሓረቤን ያያችሁ» እያለ ይሮጣል። ልጆቹ፡ «አላየንም ባካችሁ» እያሉ ቸብ ቸብ እያደረጉ ይቀበሉታል። በዚህ መልክ አንድ ሁለቴ፡ ወይም እስኪዘናጉ ድረስ ይዞራቸዋል። «መሓረቤን ያያችሁ?» «አላየንም ባካችሁ!» «መሓረቤን ያያችሁ» «አላየንም ባካችሁ!» ከዘፈኑ እኩል ቸብ ቸብ ቸብ እየተደረገ ይዘፈናል። በመሓል፡ ሳያስታውቅበት፡ ከአንዱ ሕጻን ጀርባ፡ መሓረቡን ጣል ያደርግና፡ ምንም እንዳልተለወጠ በማስመሰል «መሓረቤን ያያችሁ» እያለ፡ ድምጹን እንኳን ሳይለውጥ፡ ሳያቋርጥ ይቀጥላል። እያንዳንዱ ልጅ፡ ከጀርባው መሓረቡ መጣል አለመጣሉን፡ በተለይ መሓረቡን የያዘው ተጫዋች በርሱ ጀርባ ደርሶ ሲያልፍ ነቅቶ መጠበቅ አለበት። ያም የተጣለበት ልጅ፡ ወድያውኑ እንደተጣለበት የባነነ እንደሆነ፡ ወድያው ተነስቶ መሓረቡን ያነሳና የጣለበትን ሰው አባርሮ አባርሮ፡ በመሓረቡ፡ ወርውሮ፡ ይመታዋል። ልጁ ቶሎ ካልባነነ ግን፡ ጣዪው ተጫዋች ስለሚርቅበት፡ ከጀርባው እየተከተለ ለመምታት ብዙ እየተከታተለ መሮጥ አለበት። እንዲያውም ከመነሳቱ በፊት፡ ከጀርባው መሓረቡ መጣሉን ሳያውቅ፡ ፈዝዞ ዝም ብሎ ከተቀመጠ፡ ሌሎቹ ልጆች ትንስ ይታገሱትና፡ «ዋለበት አደረበት ዘንዶ በቀለበት፤ ዋለባት አደረባት ዘንዶ በቀለባት» እያሉ በጭብጨባ እየዘፈኑ ይሳለቁበታል። ይሄኔ ከባነነ፡ ተነስቶ፡ መሓረቡን ይዞ የጣለበትን ልጅ ያሩዋሩጣል። ሁለቱ ሲሮጡ፡ በዚያ በክቡ ጀርባ መሮጣቸውን ትተው ወደሌላ አቅጣጫ አይሮጡም። ይሯሯጡና፡ ጣዪው የተጣለበት ልጅ ክፍት ቦታ ላይ ቀድሞ ደርሶ ከተቀመጠ፡ የተጣለበት ልጅ «መሓረቤን ያያችሁ» እያለ ይቀጥላል። ጣዪው ከተመታ ግን፡ እርሱው ራሱ «መሓረቤን ያያችሁ» እያለ ይቀጥላል።

የጨዋታው ጥቅም- ሲሮጡ ሰውነታቸው ይጠነክራል። በዘፈኑና፡ በልጆቹ አድራጎትም ይዝናናሉ። በተለይ በተለይ፡ ከጀርባቸው ምን እየተካሄደ እንዳለ፡ ሁል ጊዜ፡ ነቃ ብለው መጠበቅ እንዳለባቸው ይማራሉ።

መልካም ጨዋታ!