Jump to content

ተለፒኑ

ከውክፔዲያ
(ከቴሌፒኑ የተዛወረ)

ተለፒኑ ከ1488 እስከ 1483 ዓክልበ. አካባቢ ከንግሥቱ ወንድም ከ1 ሑዚያ በኋላ በሐቱሳሽ (በሐቲ አገር ወይም የኬጥያውያን መንግሥት) የገዛ ንጉሥ ነበር።

ንግስቱ ኢሽታፓሪያ ስትሆን እርሷ የሑዚያ ዋና እኅትና የአሙና ልጅ ነበረች። ሑዚያም ንጉሥ ሲሆን እኅቱንና ባሏን ለመግደል አስቦ ተለፒኑ ግን ሤራውን አግኝቶ ሑዚያን ከዙፋኑ አባረረው፣ ተለፒኑም ንጉሥ ሆነ፣ ነገር ግን ሑዚያን ይቅርታ ብሎት ሑዚያ በኋላ በሌላ ሰው እጅ ይገደል ነበር።

ይህን የምናውቀው ተለፒኑ በጻፈው የተለፒኑ ዐዋጅ በተባለው ሰነድ ይተረካል። በዚህ አዋጅ የቀደሙት ኬጥያውያን ነገሥታት ዘመኖች ከላባርና (ከ1582 ዓክልበ.) ጀምሮ ይተርካል። በተለይ ስለአወራረሳቸውና ከባቢሎን ውድቀት (1507 ዓክልበ.) ጀምሮ አያሌ ነገሥታት ወይም ወራሾች በአጭር ዘመን ውስጥ እንደ ተገደሉ ይተርካል። በግድያ የመጡት ነገሥታት የአማልክት ቂም እንዳገኙ ያጠቁማል። የራሱን ዘመን እንዲህ ይገልጻል፦

«[...] አሙናም ደግሞ አምላክ ሊሆን ሲል፣ የንጉሣዊ ዘበኞች አለቃ ዙሩ በምስጢር ከገዛ ቤተሠቡ ልጁን ታሑርዋይሊን፣ «የወርቃማው ጦር ሰውዬ» የተባለውን፣ ልኮ እርሱ የቲቲያን (የአሙና በኲር) ቤተሠብ ከነልጆቹ ገደላቸው።
መልእክተኛውንም ታሩሕሹን ልኮ እርሱ ሐንቲሊን (የአሙና ፪ኛ ልጅ) ከነልጆቹ ገደላቸው። ሑዚያም ንጉሥ ሆነ፣ ተለፒኑም ዋና ኢኅቱን ኢሽታፓሪያን አገባ። ሑዚያ እነሱንም ሊገድላቸው ይፈልግ ነበር፣ ሆኖም ጉዳዩ ስለ ተገለጸ ተለፒኑ አባረራቸው።
ወድሞቹ አምስት ነበሩ፣ ቤቶችንም ሠራላቸው፤ ይኑሩ፣ ይብሉ፣ ይጠጡ አለላቸው፤ ማንም አይበድላቸው! ተደጋግሜ እናገራለሁ፣ እነሱ በደሉኝ፣ እኔስ አልበድላቸውም።
እኔ ተለፒኑ በአባቴ ዙፋን ስቀመጥ፣ በሐሡዋ ከተማ ላይ ዘመትኩ፤ ሐሡዋንም አጠፋኋት። ሥራዊቴ ደግሞ በዚዚሊፓ ከተማ ነበሩ፣ ዚዚሊፓም ድል ሆነ።
እኔ ንጉሡ ወደ ላዋዛንቲያ ከተማ በመጣሁ ጊዜ፣ ላሓ ጠላት ሆነ እሱ ከተማውን ለአመጻ አስነሣሣው። አማልክቱ በእጄ ውስጥ ሰጡት። ከመኳንንት ብዙዎች፦ የሺህ አለቃ ካሩዋ፣ የእልፍኝ አስከልካዮች አለቃ ኢናራ፣ የዋንጫ ተሸካሚዎች አለቃ ኪላ፣ የ[...] አለቃ ታርሑሚማ፣ የምርኳዝ ተሸካሚዎች አለቃ ዚንዋሸሊ፣ እና ሌሊ፤ በምስጢር ወደ ምርኳዝ ተሸካሚ ታኑዋ ልከው ነበር።
እኔ ንጉሡ ሳላውቀው፣ ሑዚያንና ወንድሞቹን ገደላቸው። እኔ ንጉሡ ስሰማው፣ ታኑዋን፣ ታሑርዋይሊንም፣ ታሩሕሹን አምጥተው ጉባኤው መሞት ፈረደባቸው። እኔ ንጉሡ ግን ለምን ይሙቱ? ዓይናቸው ይሠውሩ! ብዬ፣ እኔ ንጉሡ በውነት ገበሬዎች አደረግኋቸው። የጦርነት መሣርያ ከጫንቃቸው ወስጄ ቀንበር ሰጠኋቸው!»

በዚሁ ታሪክ፣ ዙሩ «የንጉሥ ዘበኞች አለቃ» ሲባል ይህ ማዕረግ ለንጉሥ ወንድም እንደ ተሰጠና ዙሩ ታዲያ የአሙና ወንድምና የ1 ዚዳንታ ልጅ እንደ ነበር ይታመናል። ልጁም ታሑርዋይሊ «የወርቃማው ጦር ሰውዬ» ደግሞ ወደፊት ንጉሥ ሆነ። ዙሩ ቀዳሚ ወራሾቹን ቲቲያንና ሐንቲሊን ያስገደላቸው ለአሙና ሦስተኛው ልጅ ሑዚያ ወራሽነት እንዲያገኝ እንደ ነበር ይታስባል።

ተለፒኑ ከቀዳሚዎቹ ይልቅ ሩኅሩኅ ይመስላል፤ ለሑዚያ ይቅርታ ሰጠ፣ በኋላም ሑዚያ ሲገደል ለሑዚያ፣ ቲቲያና ሐንቲሊ ገዳዮች ይቅርታ ሰጥቶ የእርሻ ሥራ አስገደዳቸው ይላል።

ይህንን ሁሉ በቅድሚያ እንደ መሠረት ከተረከ በኋላ፣ የዐዋጁ ድንጋጌ እንዲህ ይላል፦

«በመላው ንጉሣዊ ቤተሠብ ውስጥ ደምን ማፍሰስ ተራ ነገር ሆኗል! ንግሥትም ኢሽታፓሪያ ዓርፈዋል። በኋላ ልዑል አሙና ለዕረፍት መጣ። የአማልክት ሰዎች [አረመኔ ቄሳውንት] ፦ በሐቱሳሽ አሁን ደምን ማፍሰስ ተራ ነገር ሆኗል! እያሉ ነው። እኔ ተለፒኑ በሐቱሳሽ ጉባኤ ጠራሁ። ከዚህ ሰዓት ጀምሮ፣ በሐቱሳሽ ማንም ሰው የንጉሣዊ ቤተሠብ ልጆችን አይበድላቸው ወይም ጩቤ አይዝባቸው!
ልዑል አልጋ ወራሹ - በኲር ልጅ ብቻ ንጉሥ ሆኖ ይጫን! በኲር ልዑል ባይኖር፣ ሁለተኛው ወንድ ልጅ ንጉሥ ይሁን። ነገር ግን ማንም ልዑል ወንድ ልጅ ባይኖር፣ የታላቅዋን ሴት ልጅ ባለቤት ወስደው እሱ ንጉሥ ይሁን!»

ተለፒኑ በራሱ በኩል ንጉሥ የሆነው ንግሥቱ የአሙና ልጅ በመሆንዋ ስለ ነበር፣ ይህን መርህ እንደ ሕግ ለማጽናት አስቦ ነበር። በአንድ መስመር ተለፒኑ «በአባቴ ዙፋን ስቀመጥ» ስላለ፣ ማለቱ የንግሥቱ አባት ይሆናል።

በዐዋጁ መጨረሻ ሁለተ ተጨማሪ ሕግጋት ስለ መግደልና ስለ ጠንቋይ ቀምረው ይሰጣሉ፦

« የግድያም ጉዳይ እንዲሚከተል ነው፡ ማንም ሰው ቢገደል፣ የተገደለው ሰው ወራሽ እንዳለ ሁሉ ይደረግበታል። ይሙት ካለ ይሞታል፤ ይካሥ ካለ ግን ይካሣል። ንጉሡ በውሳኔው ውስጥ አይገባም።»
« በሐቱሻ ግዛት ውስጥ ስለሚደረግ ጥንቆላ ጉዳይ፦ እነዚህን ጉዳዮች በመግለጽ ትጉበት። ማንም በንጉሣዊ ቤተሠብ ውስጥ ጥንቆላ ቢሠራ ኖሮ፣ ይዙትና ወደ ንጉሡ ግቢ አስረክቡት። ለማያስረክበው ሰው ግን መጥፎ ይሆናል።»

የኬጥያውያን ሕግጋት ቋንቋ ለዚህ ጽላት ተመሳሳይ ሲሆን መጀመርያው እንደ ሕገ መንግሥት የወጣው በተለፒኑ ዘመን እንደ ሆነ ታስቧል። የኬጥያውያን ጉባኤ ወይም «ፓንኩሽ» (እንደ መኳንንት ምክር ቤት) በዚያ ተመሠረተ።

ተለፒኑ ደግሞ ከኪዙዋትና ታላቅ ንጉሥ ኢሽፑታሕሹ ጋራ ስምምነት እንደ ተዋወለ ይታውቃል። የተለፒኑ ሴት ልጅ ሐራፕሺሊ ወይም ሐራፕሼኪ ስትሆን የአሉዋምና ሚስት ሆነች፣ ነገር ግን በተለፒኑ ላይ ስላመጹ እሱ ወደ ማሊታሽኩር አሳደዳቸው። የተለፒኑ መጀመርያ ተከታይ የዚዳንታ ልጅ ዙሩ ልጅ ታሑርዋይሊ እንደ ሆነ ይመስላል። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ግን አሉዋምና ተከተላቸው። አሉዋምና ከታሑርዋይሊ እንደ ቀደመ የሚል አስተሳሰብ ደግሞ ብዙ ይታያል።

ቀዳሚው
1 ሑዚያ
ሐቲ ንጉሥ
1488-1483 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
ታሑርዋይሊ