አባል:Moresh~amwiki

ከውክፔዲያ
                                                                                                   ግጥም ምንም አይነት ቅርፅ አየያስፈልገውም?

በቅርቡ በአንድ የኤፍኤም ሬዲዮ የስነፅሁፍ ውይይት ላይ ተናጋሪው ስነ-ግጥም ስለሚባለው አንድ የስነፅሁፍ ንኡስ ክፍል ሲያስረዳ ግጥም ምንም አይነት ፎርም አያስፈልገውም ሲል የሰማሁ ይመስለኛል። የዚህ አባባል ጥቅሙ ቶሎ አልገባ አለኝ። እና ባይገባኝስ ታዲያ? ጊዜ ለማይገባቸው ፈዛዞች ቦታ የለውም። ለፖሊሶች ፣ ለሃኪሞች ፣ ለወዛደሮች ፣ ለሆስተሶች ፣ ለወታደሮች ወዘተ ምንም ዩኒፎርም አያስፈልግም ማለትም እንችላለን። ግን አንድ ጥቅም አለው አልኩ ደግሞ። አንዳንዴ እንድናየው የቀረበልን ስእል ይዘት አልገባ ብሎን ስንጠይቅና ረቂቅ /አብስትራክት/ ስለሆነ ነው ሲሉን በስራው ላይ ህይወት ዘርቶ ተመልካች ሊረዳው የሚችል የሆነ አንድ ቅርፅ ማስያዝ ሲያቅተው አብስትራክት ነው ይለናል እያልን በሰአሊያን እንደምናሾፈው ፣ ለግጥም ምንም አይነት ፎርም አያስፈልገውም ካልን ሌላ ባይጠቅም ምናልባት በምን አይነት አወቃቀር ነው የፃፍከው? የሚል ማብራሪያ ፈላጊ ሲመጣ እንደዚህ አይነት ማምለጫ ሊሆነን ይችላል አልኩ። ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን በእሳት ወይ አበባ የግጥም መድብሉ መግቢያ ላይ ስለሥነግጥም በፃፈው ንባብ ስነግጥም የራሱ ገፅታ ፣ የራሱ መለያ እንዳለው ሲነግረን ስነግጥም “አብዛኛውን ጊዜ የመሰረተ-ቋንቋውን ቅድመ-ድንጋጌና የራሱንም ስያሜ ይዞ … የአማካይ ሥነግጥሞቹን የመሰረት ድንጋጌ ሳያስቀር … እንደጦርነት ስትራተጂና እንደወይዛዝርት የአለባበስ ወግ …” /ገፅ 8/ የራሱን መስመር ይዞ እንደሚጓዝ ያስረዳንና ሥነግጥም በሥርአት ሊመራ እንደሚገባው ሲገልፅ ደግሞ “… የሥነግጥም ድንጋጌ ይሄው ብቻ መሆን አለበት ወይም ደግሞ ከዚህኛው የቋንቋ መሰረተ ድንጋጌ በተወረሰው አይነት ብቻ መሰራት አለበት ብሎ መወሰን ያው ከተወሰነ አእምሮ የሚወጣ ድፍረት ነው ብንልም ፥ በሌላው መልክ ደግሞ ቁጥሩን (ሜትሩን ወይም `ምቱን´) የተመደበ የስንኝ ስልት እና ቤት ባልደነገገው የቃላት መረን አሂዶ እነሆ ሥነግጥም ማለቱም የባሰ ፀያፍ ማሰኘቱ ሳይሳነን …” /ገፅ 11/ እያለ ይቀጥላል። ይሄ የፀጋዬ አገላለፅ ይመስለኛል በስነፅሁፉ ዓለም ተቀባይነት ያለው። ግጥም ምንም አይነት ፎርም አያስፈልገውም የሚለው ከላይ የጠቀስኩት ትከራካሪ ደግሞ ሌላ አተያይ እያቀረበልን ነው። በዚህ ፎርም-አልባ አቀራረብ የተፃፉ ግጥሞችን እናይ ይሆናል። የሆነ ሆኖ አንድ ነገር ትክክል ነው፦ አካባቢያችንን ፣ ራሳችንን ፣ስራዎቻችንን ወዘተ የምናይበት መነፅር የአንዳችን ከሌላችን ይለያል። ይሄ ልዩነት ለዘለአለም ይኑር የሚያስብል ነገር አለ። ምክንያቱም ከእኛ አዲስ ነገር የመፈለግ እና የመሰላቸት ባህርይ አንፃር ሲታይ ይህ ልዩነት ባይኖር ኖሮ የእለት ተእለት ኑሮ ተደጋጋሚ በመሆኑ ብቻ በፈቃደኝነት ከመኖር ምህዋር አንወጣም ነበር ትላላችሁ? ግን ሁሌም አካባቢያችን እና ድርጊታችን አዲስ እንዲመስለንና እንደገና እንድንወያይበት፣ እንድንመረምረው የሚያደርገን ከልምዳችን እና ከአቅማችን የተነሳ ነገሮችን የምናይበት እና የምንረዳበት የተለያየ አንፃር /Perspective/ እና አተያይ /Point of View/ መኖሩ ሳይሆን አይቀርም፤ ስለዚህም ነው ለዚህ ልዩነት እድሜ ይስጠው ያልኩት። ስለአተያይ ሳነሳ አንድ ነገር ትውስ አለኝ፤ እንዲያውም ጥሩ ምሳሌ ሳይሆን አይቀርም፤ ከፃፍኳቸው ግጥሞች አንዳንዶቹን አቶ ጌታቸው ወልደሰማያት ለሚባል የድሮ አለቃዬ እና ወዳጄ ሰጠሁት። አንድ የሰው ልጅ ጭካኔ ጫና የተሰማው አህያ የተከዘበትን ይፍረደኝ በሚል ርእስ የተፃፈ /ቁጥር ፬/ ግጥም አነበበና ሲመልስልኝ “እኔ የምልህ” ሲል ጀመረ አቶ ጌታቸው ፤ ቀጠለናም “ይሄ አህያ በእሱ (በእግዚአብሄር) አምሳል ሊፈጠር ይፈልግ ነበር እንዴ?” ሲል ጠየቀኝ። እንግዲህ ይህ ስለቁጥር ፬ ግጥም አንድ አተያይ ነው ፤ ሌሎች አንባቢያን ደግሞ ሌላ ይኖራቸዋል ፤ እኔ የራሴ አለኝ ፤ አህያው የራሱ አለው። በአንድ ነገር ላይ አራት አይነት አንፃሮች ተፈጠሩ ማለት አይደለም? ይህ ልዩነትም ይሆናል እንድንከራከር ፣ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩ ፣ አዳዲስ ግኝቶች ላይ እንድንደርስ እና ያላወቅነውን እንድናውቅ የሚረዳን። ያም ባይሆን ቢያንስ እንዲህ ስንነታረክ እድሜአችንም ሳናውቀው ይጓዛል። ጊዜ ሞልቶ የተርፈን አይደለን፤ኦሆ ደሞ ሌላ አጀንዳ … ወደ ጉዳዬ ልመለስ፦ ስለግጥም አፃፃፍ የማቀርበው አዲስ ሃሳብ የለኝም። እሱን ልተወውና አስተማሪዎቻችን ያሳዩንን ተከትዬ ለመፃፍ የሞከርኩ ይመስለኛል። እሱም ተሳክቶልኝ ከሆነ ነው። ይልቅ አንድ ነገር ቀላቅያለሁ፤ ስለግጥም እስከማውቀው ድረስ ቤት መደዳውን የሚመታ እና በፈረቃ የሚመታ /ከሁለቱም አይነት መቺ ይሰውራችሁና/ አይነት ያየሁ ወይም አለ ብዬ የተረዳሁ ይመስለኛል፤ ምሳሌ ልጥቀስ፦ • መደዳውን የሚመታ አይኔን ሰው ራበው የሰው ያለህ የሰው /ዮፍታሄ ንጉሴ/

• በፈረቃ የሚመታ መሄዷን ሃሰት አድርጎ መኖር አለባት ይላል ወዬ እንድትለው ፈልጎ የሌለችውን ፀዳል እኔ አንዳንዴ ሁለቱንም አይነቶች ለአንድ ግጥም ተጠቅሜባቸዋለሁ። ምን ትዘባርቃለህ ስትሉኝ አብስትራክት ነው ብዬ ለማምለጥ ከፈለግሁ ኮስተር ብዬ ፣ አዲስ ስልት ብሞክር ምን አለበት? መቼም እናንተ ለውጥ አትወዱም እላችኋለሁ። ጉዳችሁ ፈላ ግን እንደዚያ ማለት አልፈለግሁም። እውነት ለመናገር በጀመርኩት ስልት መጨረስ አቅቶኝ ነው የቀላቀልኩት። ከጣመ ይቀጥላል ፣ ውበት/ዜማ አበላሽቶ ከሆነ ይቀራል። ለብልሽቱም አስተማሪዎቻችንን እና አንባቢዎቼን ይቅርታ እጠይቃለሁ። እነዚህን የለማጅ ግጥሞች እንድታነብቡ የፈለግሁት አንድም አስተያየታችሁን በመፈለግ ነው። ድክመቶቼ ላይ ትኩረት እንድታደርጉ አደራ እላለሁ። አለበለዚያ እንዴት መሻሻል ይቻላል? ደሞ ሌላ ምን ላውራ? አሃ፣ ግጥሞቹን ስፅፍ ትኩረቴን የሳቡ አንዳንድ ነገሮችን ትንሽ ማነሳሳት ፈለግሁ። አንዱ የመመሳሰል ነገር ነው። ከዚህ በፊት ከተሰሩ ስራዎች ጋር የሚቀራረብ ፣ የሆነ የእከሌ ተፅእኖ ያረፈበት ፣ ወደ እዚያ የሚጎተት ነገር ባይኖር ጥሩ ይመስለኛል። መልካም አረአያን መከተል አይገባም እያልኩ አይደለም ፣ ሲያልፍም አይነካኝ። ተመሳሳይነት ያለው ነገር እየቀረበ ሌላው ቢቀር ጊዜም ፣ ጉልበትም ፣ ወረቀትም መባከን የለበትም ለማለት ነው ነገሩ። አይመስላችሁም? ሙሉ በሙሉ ባይቻልም ስራዎችን ከዚህ ተመሳሳይነት ማፅዳት ይገባል ብዬ አምናለሁ። መቼም የምናቀርባቸው ነገሮች የህይወት ገጠመኞቻችን እና የአመለካከታችን ውጤቶች ናቸው። ሁላችንም ደግሞ የአንድ ምድር ነዋሪዎች እንደመሆናችን ፍላጎቶቻችን ፣ ምኞቶቻችን ፣ተስፋዎቻችን እና ሃዘኖቻችን የሚመሳሰሉባቸው አንፃሮች አሉ። ከዚህ በተጨማሪ መማሪያዎቻችንም ተመሳሳይ ስለሆኑ ከቀደምት ስራዎች ያገኘናቸው ልምዶች ይከተሉናል። ግጥም የምንወድ ሰዎች እነከበደ ሚካኤልን ፣ ፀጋዬ ገብረመድህንን ፣ ደበበ ሰይፉን ፣ መንግስቱ ለማን ፣ ገብረክርስቶስ ደስታን ፣ ፈቃደ አዘዘን ፣ ታገል ሰይፉን ወዘተ ፣ ከውጪም እንዲሁ የምናደንቃቸውን እናስባለን። ስንሰራም ድንገት በሃሳባችን መምጣታቸው አይቀርም። እኔን አጋጥመውኛል፤ ምሳሌ ልጥቀስ ፤ ከዚህ በታች ያለውን ግጥም ፃፍኩ፦ የግድግዳዬ ሸረሪት ጡነቻ ተሸክሜ ፣ አጥንቴ ከብዶኛል እንዳንቺ አልገሰግስ ፣ ሥጋ ተጭኖኛል ውሰጂኝ ጎትተሽ ፣ ሳቢኝ በገመድሽ አውጪኝ ከመቃብር ፣ አርጊኝ ጎረቤትሽ እያለ ይቀጥላል፤ ይሄው ይበቃል። ከዚያ ሳነብበው ፣ ስቀይረው ፣ ስበይደው ፣ ባነሳሁ ባየሁት ቁጥር ኦድ ቱ ኤ ናይቲንጌል /Ode to a Nightingale/ የሚል ርእስ ያለው John Keats የተባለ ፀሃፊ ግጥም ትዝ ይለኛል። ይሄ ሰውዬ ለምን በሃሳቤ መጣ አልኩ፤ አንድ የሚቀራረብ ነገር ሳይኖር እንዲህ እሱ ብቻ ተነጥሎ እንደማይመጣብኝ ገመትኩ፤ ተመሳሳይ እንዳይሆን አልኩና ለማረጋገጥ ያህል የKeatsን ግጥም ሳነብበው መንፈሱ የሚመሳሰሉ ነገሮች አሉት፦ Ode to a Nightingale … Here, where men sit and hear each other groan; Where palsy shakes a few, sad, last gray hairs, Where youth grows pale, and spectre-thin, and dies; Where but to think is to be full of sorrow And leaden-eyed despairs, Where Beauty cannot keep her lustrous eyes, Or new Love pine at them beyond to-morrow. Away! away! for I will fly to thee, … አሃ አልኩ ፤ ለዚህ ነው ለካ የመጣብኝ። እሱ ከወፍ እኔ ከሸረሪት ጋር እያወራን ነው፤ እርግጥ እሱ እመጣለሁ ነው ያለው ፣ እኔ ውሰጂኝ ነው ያልኩት ፤ ቢሆንም ይዘቱ ስለሚቀራረብ ፣ ግጥሙን ባየሁ ቁጥር እየዞረቺኝ አልለቅ ያለቺኝ የኬትስ መንፈስም በሰላም ታርፍ ዘንድ የግድግዳዬ ሸረሪት የሚለውን ግጥም ተውኩት። አንድ ሌላ ፀሃፊ የሚያስታውኝ እውን አይደለሽም በሚል ርእስ የፃፍኩት ግጥም አለ፤ እሱን ባየሁ ቁጥር እፊቴ ድቅን የሚለው ደግሞ አንድ ወቅት ከሱቅ እቃ የተጠቀለለበት የመፅሄት ቁራጭ ገፅ ላይ ያነበብኩት የፀሃፊው ስም የሌለበት ግጥም ነው፤ ያንን ቁራጭ ወረቀት ብፈልግ አጣሁት። ለማንኛውም ግን እውን አይደለሽም የሚለውንም በተመሳሳይ ምክንያት ተውኩት። እንግዲህ ከሁለቱ በቀር ሌሎቹን ስፅፍ በሃሳቤ የመጣ ገጣሚ የለም ፤ ስለዚህ ግጥሞቹ ከሌላ ጋር ተመሳሳይ እና ድግግሞሽ ናቸው የሚያስብል በቂ ምክንያት የለም አልኩ። የማላውቃቸው ግን የሚመሳሰሉ ሊኖሩ ይችላሉ ፣ እሱን አንባቢያን ናችሁ የምታውቁት። በኔ በኩል ለፅዳት ይህን ያህል ነው ያደረግሁት ፤ ባይበቃም በአንባቢያን አስተያየት የበለጠ ይጠራል የሚል እምነት አለኝ። ምን ቀረ? የመሚቀረው የአንበባበቢየያን አስተየያየት ነው ስለግጥም አጠቃላይ በባህርያትም ሆነ በእኔ ሙከራዎች ላይ አስ ተያየት እንድትሰጡ በአክብሮት እጋብዛለሁ የነኔ ግጥመሞች የሚከተሉት ናቸው


፩ እሱን ተወው!


እድሜህ መች አነሶ ነበር ለመብረር ጠፈር ለጠፈር የሰው ልጅ ቅም ቅም ኣያት አይደለህ የነሉሲ ምንጅላት አጋም ቀጋውን መንጥረህ የጠበቅካቸው ቤት ጠርገህ ተውከው እንጂ በነበር ፣ በርህን በላይህ ዘግተህ ብቀጠቅጥ ይቀጥቅጠኝ ፣ ብረት ላትበይድ ምለህ መጫኛ ነካሽ ፋቂ ፣ አንጥረኞች ወጊዱ ከነልጅ ልጆቻችሁ ፣ አንጦሮጦስ ውረዱ ልጆችህን አግልለህ ፣ ውጉዝ ከመአርዮስ የቅኔ ምንቸት ግባ ፣ የስራ ባህል አዲዮስ፤ ስታውሸለሽል ሰምበሌጥ ፣ በቄስ ግዝት ታግተህ በሽክና ስትጠጣ ፣ የበሬ ጫንቃ ጭምድደህ በአህያ ጀርባ ተማምነህ ፣ በሰፌድ በወስከምባ አቅም እሱኑ የሙጢኝ ብለህ ፣ ስትገፋ ድድሩን አለም መጓዝህ ሲገባህ ግዜ ፣ ቀኝ ኋላ ዙር ታጥፈህ ደሞ የራስክን ጥፋት ፣ ባይልልኝ ነው ትላለህ፤ እሱን ተወው አትቀልድ ፣ ምን አመጣው ሰበቡን ልኮህ ነበር ወደ ምድር ፣ አጎናፅፎ ጥበቡን ተመስገን ነው ይሄውም ፣ ለዚህ ዘመን መድረስህ አንድ የተስቦ ላሽ ፣ ከምድር ላይ ሳይመልጥህ



፪ ኤጭታዬን ኤጭ ብሎ


ብተወው ኤጭ ብዬ ሲቀደድ ጡት መያዣዬ መሳቄን እንጂ የፊቴን ማን ሊያየው ብዬ የውስጤን ኤጭታዬን ኤጭ ብሎ ፣ ሊያሳጣኝ ለጎረቤት አፍ አየሁት በቀሚሴ ላይ ፣ ብቅ ብሎ የጡቴ ጫፍ ለካ ለዚህ ነው እንዴ ፣ ወይኔ ልጅት በሞትኩት በነጋ በጠባ ቁጥር ፣ የቡና ወሬ የሆንኩት ´ኑ ብሉኝ ትላለች` ፣ እያለ እንደሚያማኝ ´ጡቷ አጎጠጎጠ` ፣ ሲዘፍንልኝ ገባኝ ደልቶት ሙቅ ያኝካል ፣ ላጤው ጎረቤቴ አውጥቶ ሲያሰጣኝ ፣ ድህነት ከቤቴ

፫ ምን አገኘህ?


ሰው ሲባል’ኮ ጭራቅ ነው ውደደው እንጂ አትመነው በሚለው ያንተ ስብከት ተለካና ያ ደግነት ቢያስብ እንደክርስቶስ ወስዶ የጥፋትክን ጦስ ስትረግጠው ዝም ቢልህ ትእግስቱን ጠርጥረህ እስኪመቸው ያደባል እያልክ ያልበላህ ቦታ ስታክ ስታማው ሄደ እንዲገባህ ሰባራ ሚዛንህ ትርፉ ጎርፍ ና ውሽት ቢሞላህ አይቀር እንደሁ ማለፉ


፬ ይፍረደኝ!


በራሴ አምሳል ተፈጥሬ በኖርኩ ትእዛዝ አክብሬ አጎንብሼ ፣ ከማንም በታች ውዬ ሸክም ምሱ ፣ ዱላ ቀለቡ ተብዬ ይሆን እንዴ ፣ እሱን ስላልመሰልኩ እኔ ራሴን ስለሆንኩ ለውለታዬ አሳር የሚከፈለኝ የጉድ ሸክም እየጫነኝ ወይ እሱ አልፎ ላያልፍለት በቃኝ ላይል ፣ የሀብት ጥማት ፍትወት ማቃሰት ሆኗል ስራዬ መዋተት በዳገት በቁልቁለቱ መንከራተት በፀሀይ በጨረቃ እድሜ ረዝሞ እጅግ ርቆ ህልሜ ይህ ከሆነማ ውለታዬ የዚች ምድር ድርሻዬ ይፍረደኝ እሱ ያረገው ትንፋሼን ሞቆ ያደገው


፭ ቀርቶ ከሰው ገላ


አንድ ሺህ እንደአንድ ፣ ህሊና ተያይቶ እንደዳማ መስመር ፣ ጠርዝ ደርዝ ሰርቶ ደሞ እንደመንገዱ ፣ ሳየው አይን ሞልቶ ሲራመድ ግራ ቀኝ ፣ በመንፈስ ተግባብቶ አሰብኩኝ ስለ’ኔ ፣ ቀርቶ ከሰው ገላ ስለማልግባባው ፣ ከራሴ እንኳን ጥላ


፮ ነፍስሽን እሷኑ ግደያት


በይ እስቲ ተጨነቂ ያቺኑ ነፍስሽን ጭመቂ አልጥም ሲልሽ ነገሩ ´ዶሮ ማታ` ማደሩ ነፍስሽን እሷኑ ግደያት መቼም ተመልካች የላት ግን አታስጊው ገላሽን የሚሸውድልሽን ሲነጋ ወልወል እያ’ረግሽ ወደ መንጋው ተመለሽ




፯ ምን እንመስል ይሆን? እስቲ አንዴ መዋለድ አቁሙ በስጋችሁ ላይ አድሙ ተዉ ስራ ጫወታ መራመድ መቆም መኝታ ምግብ አይዙር ባፋችሁ እንቅልፍ ይሁን እርማችሁ ጭጭ በሉ ፣ ድምፅ አታሰሙ አታዛጉ ፣ ህልም አታልሙ ሁላችንም እንደዚህ ስንሆን ምን እንመስል ይሆን?

፰ መቼ ዞር ብላ ፍቅሬ ብላ ስትመጣ ፣ ልታቅፈኝ እጇን ዘርግታ ያምረኝና ልጅነት ፣ አኩኩሉ ጨዋታ እንደተበደለ ልጅ ፣ ድንገት ኩርፍ እላለሁ ፊቴን ደመና አድርጌ ፣ ጀርባዬን እሰጣታለሁ ፍቅሬ ሽምቅቅ ብላ ፣ ምንም ሳታናግረኝ ስትሄድ ፊቷን አዙራ ፣ እኔን ለኔ ስ’ተወኝ ደንግጬ ብድግ እላለሁ ፣ ልሮጥ ወደ ተራራው እሷ መቼ ዞር ብላ ፣ ማቃሰት የኔ ነው ተራው



፱ የታለሁና? በለው ትለኛለች ፣ መቀነቷን አስራ ሽቅብ እያሳየች ፣ የማዶውን ጋራ እንደወንድ ቆጥራኝ ፣ ሀሞተ ኮስታራ ቅብሩን የማይመኝ ፣ ሞቶም የሚያቅራራ ውስጤን አታውቀውም ፣ በውስጧ ያለውን ድምጿን ከመስማቱ ፣ ቀድሞ የሞተውን መች እጠብቅ ነበር ፣ በለው እስክባል ላብ በላብ ሆኜ እንጂ ፣ በውጊያ መሃል

፲ ጥሩ ሰው ስትረግሙ ‘እግረና አፈር’ ሲሉኝ አፈር ግባ አሉኝ ብዬ ጠልቻቸው ስለረገሙኝ ላልላካቸው ምዬ ስንት አመት ስወቅሳቸው ሲስሙኝ ሳዞርባቸው ፊቴን እማ አፀደን ጠልቻቸው ተመኝተዋል ብዬ ሞቴን ከሞቱ በኋላ ሰማሁኝ ሲመርቁህ እኮ ነው ሲሉኝ፤ እንዲህ ቅር ይላል አያችሁ ጥሩ ሰው ሲርቅ ካይናችሁ


፲፩ የሌለችውን እጄን መትቶ እየማለ ክዶ ጠጣሩን እውነት ሊሆን አይችልም እያለ የዚያችን ሴት ሙትነት መሄዷን ሃሰት አድርጎ መኖር አለባት ይላል ወዬ እንድትለው ፈልጎ የሌለችውን ፀዳል


፲፪ ደግነትሽን ላላግጥበት ሳጃጅልሽ ጭጭ በዪኝ ሞኝ ሁኚልኝ ተነጠፊ ቂል ሳደርግሽ በቃ ቻዪኝ በኔ መንገድ አትለፊ ሳታልልሽ አወቅሁ አትበይ ላላግጥበት ደግነትሽን ብራቮ! እያልሽ አርፈሽ ተበይ በቃኝ አትበይ እባክሽን




፲፫ በመጨረሻ እንኳን? የትልቋ አሮጊት ፣ የ’ማማ ጠጅቱ አርባቸው ሊወጣ ፣ ሲመረቅ ሃውልቱ ቤተሰብ ጎረቤት ፣ ተሰባስበን ቆመን ጨርቁ ተገለጠ ፣ ተላቀስን ጮኸን የመጨረሻውን ፣ ያሉትን ለማንበብ አይኔን ጣል ሳደርግ ፣ ወደ ሃውልቱ ግንብ “በሞት ጥላ ስር ባልፍ ፣ ካንተ ጋር እስከሆንኩ በጭራሽ አልፈራም!” ፣ የሚል ቃል አነበብኩ፡፡ ከሞት ጋር ግብግብ ፣ ነፃ ትግል ገጥመው አንድ ሆስፒታል ሳይቀር ፣ አዲሳባን ዞረው ሰላሳ ከረጢት ፣ ግሉኮስ ጨልጠው የቤተሰቡን ቅርስ ፣ ልቅም አ’ርገው ሸጠው አንድ የቀረ ሃብል ፣ ለሃኪም ሊከፍሉ ´ማነሽ አንቺ ቡቱ ፣ ነይ እስቲ አንዴ’ ሲሉ ሰው ሲፈልጉ ነው ፣ ግራ ቀኙን ሲያዩ ግጥም ያ’ረጋቸው ፣ ሞት አደላዳዩ፡፡ እማማ ጠጂቱ ፣ በ’ኔ ይሁንብዎ መቼም ያለፈ አልፏል ፣ እስቲ ላጫውትዎ በሞት ጥላ ስር ባልፍ ፣ እኔ አልፈራም ሲሉ ምን ማለትዎ ነው ፣ በቃሉ ሲምሉ? መቼም እሱ አይገርመው ፣ የሰው ልጅ ውሸት ብለው ነወይ እርስዎ ፣ እንዲህ የሚሉት? አለ ወይ ፍርሃት ፣ ከዚህ የበለጠ ቤት መኪና ሃብል ፣ ቅርሳቅርስ ያሸጠ? ስንዋሽ ኖረን ፣ ስንቀደደው በመጨረሻ እንኳን ፣ ምለን ላንተወው ከሄድን አይቀር ብለን ፣ ከተሸነፍነው አናጣም ምክንያት ፣ የምንፈጥረው

፲፬ ልኑር አልኑር ሳይገባኝ እንዲሁ በሞት ሽረት በከብትነት በሰውነት እኔ በእኔነቴ ከርሮ ጀርባ ለጀርባ ዞሮ ልኑር አልኑር ሳይገባኝ 51 አመት ይሙላኝ?

፲፭ ንገረኝ ምስህ ምንድነው ከቶ ፣ የሚያረካህ ትልቅ ካሳ የሚለውጥህ አንተን ፣ ሳትዝቅ በፊት አበሳ ለክፋትህ ሲወድህ ፣ ምን ይሆን ላንተ ትርጉሙ ስታንገላታው ዝም ሲል ፣ የማይሰማህ ህመሙ ቆጥሮህ እንዳልቃሻ ልጅ ፣ ስትነክሰው የሚስምህ ማስተማሩ ይሆን እንዴ ፣ ብቻ እደግልኝ ሲልህ የቱ ይሆን ወዳጅነት ፣ ከቶ አንተን የሚጥምህ ልትቀብረው የምትምሰው ፣ ንፍጥህን በጠረገልህ የህሊናው ሰፊ ግዛት ፣ የትግስቱ ጥልቅ ቀመር ከእለት እንጀራ ተሻግሮ ፣ ማየቱ የነገን ሃገር ለምን አይታይህም ተስፋው ፣ ሰው ትሆናህ ማለቱ ይገባሃል ብሎ አንድ ቀን ፣ ለጥርስህ ጣቱን መስጠቱ ንገረኝ በውነት ምንድነው ፣ የሚያወጣህ ከዚህ መንገድ ራስክን ሳትገድል በፊት ፣ ሸምቅቀህ በፀፀት ገመድ


፲፮ ብርዳም ምድጃ ነው! ደመና ሲያንዣብብ ፣ ቀዳዶት ካልወጣ እኔ አለሁ ካላለ ፣ ገስግሶ ካልመጣ ጀምበሯ ስትጠልቅ ፣ ከዋጠው ጨለማ የኋሊት ከሮጠ ፣ አብሮ ከሞተማ የኔና አንተን ፍቅር ፣ ፍቅር አትበለው ያላለቀ ስእል ፣ አንድ ጭብጥ የሌለው ችግር ዘራፍ ሲለው ፣ ተንኖ የሚጠፋ ባዶ ጥሩምባ ነው ፣ በደጁ የሚያናፋ እንኳን እኛን ሊያደምቅ ፣ ሊያሳየን ውጋገን ለራሱ እንኳ እንዳያልፍ ፣ የጨለማዋን ቀን ብርሃን የሌለው ፣ ፍሙ የከሰለበት ብርዳም ምድጃ ነው ፣ አመድ የሞላበት

፲፯ በብቅል ፂም ስንሳለቅ ጠለቀች ደሞ ጀንበር ወደ ጠጅ ቤት ልንበር ተቀምጠን ልናወጋ ቀኑን በፌዝ ልንዘጋ ስንገምድ የወሬ ፈትል አንድ ጋት ፎቀቅ ሳንል በብቅል ፂም ስንሳለቅ እድሜአችን ተቃጥሎ ይለቅ?


፲፰ አገኘሁት ሃገሬን ካርታ ላይ ስፈልጋት በዚያው ያደግሁባትን ሰፈሬን እንደው እንደምን አደርሽ ልላት ሳያት የልጅነት መንደሬን አሳ ጎረጓሪ ዘንዶ ያወጣ የለ አገኘሁት ራሴን ሲቆዝም ጨረቃ ድምቡል ቦቃ እያለ ከኤሊዋ ጋር ሲያዘግም

፲፱ ትዝታ ሆይ ነገ እንዳይታየኝ ፣ አንገቴን ጠምዝዘሽ ከተዘጋ ፋይል ፣ መዝገብ ቤት አሽገሽ አጮልቄ ባየው ፣ የማውቀውን ዓለም ቦታ ተለዋውጧል ፣ የነበረው የለም እንደ’ኔ ያጃጃልሽው ፣ ተጎልቶ ‘ሚቀር የገበያ ድንጋይ ፣ ካልሆነ በስተቀር

፳ ሳቅበት ወየው አንተን አያ’ርገኝ አለሁህ ስትለው ባገኝ እዚያው ቆመህ ሳቅበት አጉርሶህ ቆሎ ሲያርበት

፳፩ ይሄው አይደል የምታየኝ እየመሰለኝ ነውሬን ስጋ የሸፈንኩትን ግፌን ምን ብላኝ ይሆን እያልኩ የራሴን ነፍስያ እያፈርኩ ቢሰለቸኝ ከነፍሴ ትንንቅ በራሴው ሃራም መሳቀቅ ጣቴን አሹዬ ሰደድኩ ቋቅ ልላት ጎረጎርኩ ግን እሷ መች እሺ ብላ ተሰክታ ከልቤ ባላ፤ ብቻ ፣ ይሄው ነው ጥማት ውጤቱ ለስጋ ማድላት ቋቅ ያልኩበት ሲቆስል ገባኝ ሲፋተግ ፣ ውስጤ ሲባላ ተሰማኝ

፳፪ ቢላዋ ሲያነሳ ጥፊ ዘልለሽ ቅጠል በበጠስሽ ቀልብሰሽ ቢጢሌ ጭራሽን በኖርሽ አልሞኝ ብለሽ እያውለበለብሽ ምላስሽን ካልቀረ ሰይጣን መባልሽ የቃዬል ውላጅ ቅጣፊ ተርቦ ማሪኝ ይበልሽ ቢላዋ ሲያነሳ ጥፊ እየሞትሽለት ለሚያማሽ ለሰው ልጅ ከምትደፊ ፳፫ አለሁልህ! መሸጋገሪያ ስትሻ ወደ ብልጠትህ መድረሻ አቻዮ መሰላልህ የኔ ትከሻ አለልህ ግዴለህም! የትም አትሂድ ላታገኝ እንደ’ኔ ሃዲድ

፳፬ ነገም እንደዚህ ነኝ አጎቴ ካገር ቤት ፣ ጋራውን ተጉዞ ሲመጣ እናቴጋ ፣ ስልቻውን ይዞ “ያ ልጅሽ አደገ?” ሲላት ይሰማኛል እኔ እንደሁ ብቅ አልል ፣ ፂሙ ያስፈራኛል ባመቱም ሲመጣ ፣ መስከረም ሲጠባ “ያ ልጅሽ አደገ?” ገና እግሩ እንደገባ ደምጹን ከመስማቴ ፣ እኔም አልጋ ስሬን ዲዲ ዲዲ ብዬ ፣ አልተው መደበቄን እንዲሁ እነደሸሸሁት ፣ አንድ ቀን ሳይስመኝ ሞተ ሲሉኝ ጊዜ ፣ አጎቴ ናፈቀኝ፤ ሲወዱኝ አይገባኝ ፣ እንደማጣቸው ብጣራ ´ማይሰማ ፣ ቤት እንዳላቸው ነገም እንደዚህ ነኝ ፣ ከዛሬ አልማር ትተውኝ ሲሄዱ ፣ ለመነባረር


፳፭ ስንት አመት? ስንት አመት ወደድኩሽ ስንት አመት ወደድሺኝ አበባዬ ስልሽ ወለላዬ እያልሺኝ ሁልጊዜ አዲስ ዜና የኔና ያንቺ ነገር መቼ ሞት ያውቅና ቢነገር ቢነገር


፳፮ ንጉስ ፉአድ መች አዩት? ግርማ ሆስፒታል ተኝተው አላህ ይማርዎ ሲሏቸው በጨዋታቸው ተነስቶ የፍራንክ እንቶፈንቶ ኢትዮጵያም ብር የሚቆጥር ለካ አላት ብለው ሚኒስትር ሳቁ አሉ የሳኡዲ ንጉስ ታይቷቸው የቁጥሩ ማነስ ይሄንኑም ስራ ላይ ለማዋል ቀኑ እንደሚያልፍ ስንማማል መቼ አዩ ንጉስ ፉአድ መላቀቅ ሲያቅተን ከልማድ


፳፯ አሳ ባደረገኝ ካልጠፋ ውቅያኖስ ፣ ምድር ላይ መታመስ መጋፋት መጣበብ ፣ ያለቅጥም መርከስ እነዳሰቡ ውሎ ፣ እንደሳቡ ማደር ልብረድ ብሎ መጋል ፣ ልሳቅ ብሎ ማረር በፀሃይ በሃሩር ፣ በድርቅ መጠበስ አግባብ አይደለም አልኩ ፣ በፍፁም አይልም ደስ ከርካሳ ኮረኮንች ፣ አቧራ ሰለቸኝ እርጥቡ ለምለሙ ፣ ባህሩ ናፋቀኝ ተመኘሁ ውል አለኝ ፣ መሰንጠብ አማረኝ ኧረ ምን ነበረ ፣ አሳ ባደረገኝ ! የማያምረኝ የለ ፣ የማልመኘው ጀምሬ ወጥኜ ፣ የማልበትነው


፳፰ እስከማህፀኗ አፍ ምን ሰራሁበት ብዬ ዘመኔን ወደ ኋላዬ ብተረትረው እስከጫፍ እስከማህፀኗ አፍ አልታይ አለኝ ርቆ ራሱም ከቦታው ለቆ



፳፱ ማን አለህ እንደ’ኔ? በትካዜህ የሚስቅ በእንባህ የሚለቃለቅ የቆሽትህን ፍም የሚሞቅ ልብህን በቃር የሚፍቅ ማን አለህ ፈቃደኛ ከኔ በላይ ጓደኛ!

፴ ስንት ናቸው? በጨለመበት አብርተው በሞታቸው ዘርተው ብርሃን የዞረብንን መርተው የነደዱ ለብዙሃን ፈፅሞ ያላየናቸው ላባቸው ደማቸው ሲፈስ ቢቆጠሩ ስንት ናቸው ያለፉ ሆነውልን ፈውስ

፴፩ ትምህርቱ እኮ ነው የምፈራው ሌሊት ስጓዝ እየታየኝ የጋኔል መጋዝ ጥቁር አራጅ እየመስለኝ ነጭ ምሽት የሚያምረኝ ስላስተማረኝ ነው እኮ ነጩን በማር ፣ ጥቁሩን በእበት መርጎ ፴፪ ሳንገናኝም ልናልፍ? እኔ ወደ ቤቴ ሳይ አንተ ወደ አደባባይ እኔ ደጁን ሳማትር አንተ ቤትህ ስታድር ዜብራ ላይ ስንተላለፍ ሳንገናኝም ልናልፍ?


፴፫ ታገሱን አምና የሞቱትን ፣ ኮሎኔል መቃብር አየት አደረግኩት ፣ ዙሪያዬን ሳማትር ‘ህያው ሆኖ ‘ሚኖር ፣ ከሞትስ የሚቀር ከቶ እሱ ማነው?!’ ፣ የሚል ዛቻ ነገር ጽፈው ሃውልቱ ላይ ፣ ጠቃቅሰው ከቃሉ ከመቃብር ሰፈር ፣ በእልህ ይጮሃሉ፤ ባክዎት ኮሎኔል ፣ እንዲህ አይቆጡ ከሞትዎ በላይ ፣ ደም ብዛት አያምጡ ማናባቱ ለቅቆት ፣ ከቶ ማነው እሱ! አንድበአንድ ይመጣል ፣ ጥቂት ይታገሱ




፴፬ መቼ ጉዳዩ ሆነና! ከሩቅ አለሁ እያለ ፣ ሲጠቅሰን የፀጉሯ ሽበት ዘርግቶ ለፀሃይ ሰጥቶ ፣ ገትሯት ከዘመን ችሎት ስልጡኗ ጎረቤታችን ፣ የልጇን እየለበሰች እርሱት ያለጊዜው ነው ፣ ኢግኖር ኢት ፕሊስ ትላለች ወይ እርሱት ብሎ ነገር ፣ እሱ መቼ ዘንግቶ ቆጣሪው መች ይቆምና ፣ መች ላፍታስ አንቀላፍቶ የት አውቆ ችላ ማለት ፣ ሊያመልጠው የእሷ ገመና ብንረሳው ባንረሳው ፣ መቼ ጉዳዩ ሆነና

፴፭ መንገዳችሁን ቀጥሉ እነማ ናቸው ክፉ ፣ የሻጥር ሸማኔዎች ሳይነግዱ የሚያተርፉ ፣ የጭቃ ውስጥ እሾሆች ብቅ ይበሉ ለአንድ አፍታ፣ አንዴ ውጡ በሏቸው ባይያዝም ባይጨበጥም ፣ ተለዋዋጭ መልካቸው ለበቀል መስሏቸው ጥሪው ፣ ለክፋታቸው ቅጣት ሽንታቸው በእግራቸው ሲወርድ ፣ እየታያቸው ስቅላት እነሱን ጸጸት ይቅጣቸው ፣ ይፈሩ በምህረታችሁ ቀጥሉ መንገዳችሁን ፣ አንዳይለመድ ብላችሁ

፴፮ እንዴት ነህ? እኔ ቢራ ስይዝ ፣ አንተ ደጅ እየቆምክ ስትፖልስ ማምሸት ፣ ብርድ እየኮመኮምክ ከተማ ገጠሩን ፣ ሃገሩን ማዳረስ ከቶ እንዴት ይዞሃል ፣ ጧት ማታ መፖለስ ፴፯ መድሃኒት አውሱኝ ለፍቶ ስላገኘ ፣ ሰርቶ በጥረቱ ላቡን ጠብ አድርጎ ፣ ስለተባለ አንቱ የሚያንጨረጭረኝ ፣ አይኔን የሚያቀላ ስሬን የሚገትር ፣ ደሜን የሚያፈላ ነገር ዞሮብኛል ፣ የሆነ ድግምት መድሃኒት አውሱኝ ፣ ገድዬ ሳልሞት

፴፰ ምልክቱ እሱ ነው ያርባ ቀን እጣችሁ ፣ ጧት ያነሳችሁት ለአሳር መሆኑን ፣ በደንብ የምታውቁት ስትዋዋሉ ነው ፣ ስትጀምሩ ትዳር ሁሉን እኔ አውቃለሁ ፣ ከሚላችሁ ሰው ጋር

፴፱ ከመቼው? ምን ተጫወትንና ፣ ነገር እንዲህ ገባን ፍቅር አለቀና ፣ ጠላቴ ተባባልን የኔና አንተ ነገር ፣ እንዲህ ሆኖ ሊቀር ምን እርባና ሰጠን ፣ ከመላቀስ በቀር ምን እንባላለን ፣ ልጅ አይሉን አዋቂ እራፊ ጨርቅ እንጂ ፣ ሳይለብሱት አላቂ



፵ በሚጥምህ ቀጥል! ደሞ ጠለቀችልህ ጀምበር ወደ መኝታህ ልትበርር ብዙ ተባዙ በሚል ልሳን ላንተ በሰጠው ሥልጣን ሲዋለዱ አይተህ ላሞቹ በበረታቸው ሲንቻቹ ኮረጁኝ ብለህ ሞያህን በቁጣ ወድረህ ጦርህን ደሞ ልትወጋ እየበረርክ ስንት ትውልድ አስቆጠርክ የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ ያንተ መለኪያ መስፈሪያ ምድሪቱን ሙሏት ያለው ነው አልፋ ኦሜጋህ የሆነው በምርምር ጥበብ ቅመራ የሰው ልጅ ምን እንደሰራ መቼም ዞር ብለህ አታየው አንዴ የሰይጣን ሥራ ብለኸው፤ ግን ልክ ነህ ወዳጄ! ሳይንስ የሚባለውን ፀገም መዋለድ በለው ይታረም ማን ይችልሃል ፈር መቅደድ የማህፀን ውስጥ መንገድ አንደናት ጡት የሚያምርህ የጧት ማታ መዝሙርህ እሱ ነው ያንተ ስኬት የልብህ ትኩሳት ማግኔት ፈረንጅ ምን እንዳረጋት ምድሪቱን ፈጽሞ አትያት አንተ የራስህን ምድር ጀንበር ስትጠልቅ ወጥር የሰው ልጅ ዘሩ እንዲራባ ወደ ላቦራቶሪህ ግባ ደሞ ለመፈላፈል ፋሺን ከቶ ማን እንዳንተ ማሺን! ወንድሜ! ያምርብሃል ብትፎክር ስራህ አለ አይደል ምስክር ንገረው! “ኑኑዬ ጨቅላዋ”ን አዘፍን ቆስቁስ! ፈረስህ ያስካካ ፈንን ሳይንስን ተወው ይሰደድ እለፍ! በለው ጦስህን ይውሰድ መሰልጠን መሰይጠን እያልክ እሰው ጥበብ ላይ አስታውክ ወንድሜ! አንተ ፍትወትህ ላይ አተኩር አልሞት ያለህን ገላ አንኩር ምን ችግር ሃያ ቢሞሉ? በኦክስፋም ስንዴ ያድጋሉ አንተ በፍትወትህ ግብግብ እየስወለድክ ቀበሌ አስመዝግብ ማንም የፈለገውን ቢያማህ አንተ ወደ ሚጥምህ ስጋህ ያባትህ አይደል ጥሬ ስጋ ብልት አማርጠህ ውጋ ስማኝ! ይፈጸም ዘንድ ቃሉ ብዙ ተባዙ መባሉ የፍጡር ነውና ማክበር አሜን! በል ተቋለፍና ተሳረር


፵፩ አረም ለብሼ ልምጣ?! ድድ ማስጫ ተገትሬ ፣ ላንተ አቃቂር ሳወጣ ቀኑ በላዬ መሽቶ ፣ አመቱ ዞሮ ሲመጣ አንተ በ’ኔ ታርመህ ፣ ጺምህን ላጭተህ ስትወጣ አቃቂሩም አልቆብኝ ፣ አረም ለብሼ ልምጣ?


፵፪ አይሻልም ወይ ቢደፋኝ? ይድፋኝ! ብዬ ተበድሬ ፣ የሆነ ገንዘብ ለችግሬ በቃሌ መገኘት አቅቶኝ ፣ መንገድ በመቀየሬ ገንዘቡን ማጣቱ አንሶት ፣ ይቅር ይበልህ አለኝ ደሞ ምህረት ለምኖ ፣ ውለታ ሊያከናንበኝ፤ ስንቴ በእዳ ልዘፈቅ ሰዎች፣ በብድሬ ላይ ብድር እሱ ማረኝ አልማረኝ ፣ መጠየቄ እንደሁ አይቀር ነገ በሲኦል ችሎት ፣ በሁለት ጥፋት ከምዳኝ ይቅር ይበልህ ሳይለኝ ፣ አይሻልም ወይ ቢደፋኝ?



፵፫ ንዴት ለቀቅ አርገኝ! ልይበት መንገዱን ፣ ንዴቴ ገለል በል ሳልጠጣ አታስክረኝ ፣ ፎቀቅ ብለህ ኮፈል አንጎል አታድርገኝ ፣ ደም ስሬን ገታትረህ አቦ አታንተባትበኝ ፣ ምላሴን ቆልፈህ ፍሜን እያራገብክ ፣ ጭራ አታስበቅለኝ ላስብበት ዘዴ ፣ በፈጠረህ ተወኝ አይኔን እያጨለምክ ፣ አትንዳኝ በነሲብ ተወኝ ብዬሀለሁ ፣ ወላሂ ለአዚብ ! እውነት ከእኔ ሆና ፣ ደሜን እያፈላህ ለሽንፈት አትዳርገኝ ፣ ልቀቀኝ በአላህ

፵፬ ብትሆን ነው ሺህ ዘመን ስትለበለብ ፣ በእቶን እሳት ተከ’በህ ስትሆን መዘባበቻ ፣ የሚደርስ አምላክ የሌለህ መድረስ አቅቶት ብለህ ፣ ያገርህ አድባር አዋይ ሰማየ-ሰማያት ደርሶ ፣ ጸሎትህ ያጣው ተቀባይ ከፍጥረትህ ነው ሚስጥሩ ፣ ከተላክህበት አላማ ካንተ ተምሮ ዓለም ፣ ላላየ ዞሮ እንዲያሰማ ቢያደርግህ እንጂ ምሳሌ ፣ የምጽአቱ ማስረጃ የሃጢአት ዋጋ መክፈያ ፣ የሲኦል እሳት ምድጃ አጥፍተህ እኮ አይደለም ፣ ብታጠፋስ ከማን ብሶ የሚግትህ የመከራ አይነት ፣ እሬቱን በማር ለውሶ ሆድ ባዶ ይጠላል አይደል ፣ በዚህም ቢሆን ተጽናና መቼስ ማልጎደኒ እያልክ ፣ ይሁና ፣ ይሁና

፵፭ የኔ ሰው ሲንጠራሩ ይሰማል ፣ ሌሊቱ ሲነጋ ኦ! ኦ! ኦ! ኦ! ፣ ሲሉ ከዶሮዎቹጋ ቆፍጣና ኮስታራ ፣ ልበ ኩሩ ናቸው ፈለጠኝ ቆረጠኝ ፣ በሽታ አያውቃቸው የእድሜአቸው ርቀት ፣ ምልክት የሌለው ተፅፎ የቀረ ፣ የሄ ነው የሚለው “ምኒሊክ ዘወዲቱን ፣ እያሱን አውቃለሁ ይመስገን አምላኬ ፣ ሁሉን አይቻለሁ የማር ጠጅ ስቤ ፣ ጮማ ቆርጫለሁ አሁንም ገና ነኝ ፣ በደንብ እኖራለሁ ጎብጬ ብታየኝ ፣ እንዲህ አቀርቅሬ አርጅተሃል አልከኝ ፣ ደፈርከኝ አጅሬ?!” ይሉኛል የኔ ሰው ፣ በየጨዋታችን አቦል ጀባ ሊሉ ፣ ሲመጡ ቤታችን፤ ሰሞኑን ግን ጠፉ ፣ ደርሶ ያለወትሯቸው ያለንጋት ቡና ፣ እንዴት አስቻላቸው? “እኒያ ሽማግሌ ፣ ከቶ ምን ነካቸው? እንደዚህ አይጠፉም ፣ ደርሶ በጤናቸው ዘመድ እንኳ የለ ፣ ውሃ ´ሚያቀምሳቸው መጋኛ ምናምን ፣ ሽው ቢልባቸው ሚስት አገቡ ልበል? ፣ አይሞትም ልባቸው” አለቺኝ እናቴ ፣ ሂድና ጥራቸው ኑ! ቡና ጠጡ ፣ ትላለች በላቸው፤ እሺ ብዬ ወጣሁ ፣ ሄድኩ ወደቤታቸው አባባ! ብዬ ጮህኩ ፣ ቆሜ ከደጃቸው መልስ ስላጣሁኝ ፣ በሩን ደበደብኩት እጄን አሾልኬ ፣ ከውስጥ ከፈትኩት ገባሁ ወደጓዳ ፣ ወደ መኝታቸው ወደ ጨላለመው ፣ ጓዳ ጎድጓዳቸው ውድምድም ብሎ ፣ የእሳት ምድጃቸው በቀፋፊ ጠረን ፣ ተሞልቷል ጎጇቸው በጭላንጭል ብርሃን ፣ ታየኝ መኝታቸው ብቸኛ ጓደኛ ፣ የቅርብ ወዳጃቸው በጣም ተጠግቼ ፣ ቀርቤ አስተዋልኩት በእጄ ደባበስኩት ፣ ጨርቁን ገላለጥኩት አሮጌ ብርድ ልብስ ፣ ባናው ተከምሯል እሳቸው ግን የሉም ፣ ባዶውን ተንጋሏል ኧረ ምን ነካቸው ፣ ወዴት ተሰወሩ? የት ተነስተው ሄዱ ፣ ጎረቤት ሳይነግሩ? ኖረው ካረጁባት ፣ ካፈጁባት መንደር የት ሄዱ ይባላል ፣ የማይመስል ነገር ከአልጋቸው ግርጌ ፣ ትልቅ በርሜል ቆሟል አቤት! ምን ያክላል ፣ ለአንድ ሠርግ ይበቃል ላንተ ሰርግ ይሆናል ፣ ያሉኝ ይሄንን ነው? ምናለ ቢሰጡን ፣ እቤት ብነወስደው እሳቸው እንደሆን ፣ በጣም አርጅተዋል እዚህ ተገትሮ ፣ ምን ይጠቅማቸዋል? እያልኩ ብቻዬን ፣ በርሜሉን ዳሰስኩት ዙሪያውን አቅፌ ፣ ስፋቱን ለካሁት ጉልበቴን ልፈትሽ ፣ ላነሳው አስቤ ገና ጎንበስ ስል ፣ ትንፋሼን ሰብስቤ ያልጠበቅሁት ነገር ፣ እይኔ ላይ ተተክሎ አንጥሮ መለሰኝ ፣ ጥፋ ከዚህ ብሎ:: ጠምዝዞ የሚጥል ፣ ካልጋ ላይ አውርዶ ምን ጉድ አነቃቸው ፣ ግራ አጋቢ መርዶ ጎረቤት መጣራት ፣ እንዴት አቃታቸው? የሚያወጡት ምስጢር ፣ ኑዛዜም የላቸው? ድረሱልኝ የለ ፣ ጤናዳም አቅምሱኝ ከፈን ግዙ የለ ፣ አፍታቱኝ ገንዙኝ እግራቸውን አጥፈው ፣ ወድቀው በጀርባቸው ያሸለቡ መስለው ፣ ዱሮ እንደማውቃቸው ደህና ሁኑ ልጆች ፣ አባባ ትልቁ ከነኩራታቸው ፣ ዓለምን ሲለቅቁ

፵፮ ተረኛ ነኝ ሲለምነኝ ከርሞ ፣ ስንቀው ከርሜ እደጄ ላይ ቆሞ ፣ በኩራት ታምሜ ትቶኝ እልም አለ ፣ ለካ አልቋል ትግስቱ ብለምነው ቆሜ ፣ ሲናፍቀኝ ፊቱ አኬሩ ዞረና ፣ እባክህ ወንድሜ የኔ ተራ ሆነ ፣ በእሱ ቦታ ቆሜ

፵፯ ደግሞ ከኔውም ብሶ ውዝ ውዝ አ’ርጎ ጭራውን ፣ በሞከረ ሊግባባኝ መሰደቢያ አደረግሁት ፣ ከኔውም ብሶ ለማኝ ቡቺ እንኳን በደጃፉ ነው ፣ ምን ሊባል ይሆን የ’ኔ ሳካልል ከአጥናፍ አጥናፍ ፣ በህይወት ሙሉ ዘመኔ እንጀራ በስሏል ባሉበት ፣ ጭራዬን ስረጭ ለሆዴ ከዚህ በላይ መቁለጭለጭ ፣ መቁላላትስ አለ እንዴ? ከቶም የራሴን ጉድፍ ፣ አስቀምጬ በሙዳይ ደግሞ ከኔውም ብሶ ፣ ቡቺን ጭራ አትቁላ ባይ


፵፰ ህሊናዬን ሸጬ አንገቴን አጥፌ ፣ ባዳምጠው ሆዴን አነጋጥጦ አገኘሁት ፣ ሊሰለቅጥ ልቤን እየጠራኝ ኖሯል ፣ በሃይል ተከፍቶ ጩኸቱን ጨመረ ፣ ሳየው ተደስቶ አውቆታል ማለት ነው ፣ እንደምወደው ልቤን ሸቃቅዬ ፣ እንደምሞላው


፵፱ ደግነት ዋጋው ይሄው ነው ልሙትልህ ስላልሺው ፣ ርሃቡ ጭራሽ ጨምሮ ቢዘረጋብሽ እግሩን ፣ እንዳሸነፈሽ ቆጥሮ አይግረምሽ ልጅቷ ፣ ጨክኖ ቢቆረጥምሽ አየሁ አይልም ከርሱ ፣ ጨርሶ ሳያጣጥምሽ ደግነት ዋጋው ይሄው ነው ፣ አፈር ስሆንልህ ባይ ከእሾህ የተጠጋ አጋም ፣ አርፈሽ ህመምሽን ቻይ





፶ እንኳን ጭማሪ ልመኝ የገበያው አንድ አይቀረኝ ያየሁት ሁሉ እያማረኝ መቼም አይጠፋ አሳቢ የጠየቁትን አቅራቢ አንድ የሩቅ ወዳጄ ደርሶ ቢጋብዘኝ ሞትን ደግሶ ለካ አይንም ይበላል እንዴ ሳልቀምሰው ሞላና ሆዴ አመሰገንኩት ከልቤ በአይኔ ብቻ ጠግቤ አላርፍ ያለች ጣት እያልኩ እግዜር ይስጥልኝ ተማርኩ


፶፩ አለ ወይ ነገር ከስሙ? የሰጡኝን መድሃኒት ፣ ሎሚ ነው ብዬ በልቼ የደፈቀኝን ህመም ፣ ሆድ ቁርጠቴን ከልቼ እምቧይ ነው ቢሉ ቋቅ ያለኝ ፣ አለው ወይ ነገር ከስሙ ከእሳት ወሃ ሊያረገኝ ፣ ዞሮ ሚመጣው ህመሙ



፶፪ መጫወቻ ታደርገው? ምንስ ራስ መበደል ፣ ሆኖ ቢገኝ እምነቱ ቀኝህን ሲመታ ግራህን ፣ የፈጣሪ ትምህርቱ ይቅር በሏቸው እንጂ ፣ በክፋት መንገድ አትሂዱ ምህረት ቢሆን ልመናው ፣ ጠላቶቻችሁን ውደዱ ይባርክህ ብሎ ቢተውህ ፣ ስትረግጠው እጅ ቢነሳ እመ አምሳል ፍጥረቱን ፣ ፈነጨህበትሳ !?

፶፫ የደሴዋ ነጋዴ ጭራሽ እንዳልሞትን ፣ በክተን በሃጢአት አንድ ተስፋ አገኘሁ ፣ የሰው ምልክት እህል መቅመስ አምሮኝ ፣ ጎራ ባልኩበት እዚች ከተማ ፣ አንድ ሆቴል ቤት ጠይም ሴት ወይዘሮ ፣ ብቅ ብላ ከጓዳ ምግብ አቅርባልኝ ፣ ጠላ ስትቀዳ ጊዮርጊስ ዳሽን ሜታ ፣ በ´ያይነቱ እያላት ጠላ እንደሚሻለኝ ፣ ማ ነገረሽ ብላት “ሚካኤል ነው ዛሬ ፣ ፀበል አይሸጥም ቢራው ነግ ይደርሳል ፣ ለኔ ያለው አይቀርም ታቦት የለም እንዴ ፣ ኸመጡበት አገር ተኛጋ ክብር ነው ፣ ቀኑ ነው ሚዘከር ከወየት ነዎ እርስዎ? የመልአኩ እንግዳ ይጠጡማ ጌታው” ፣ ብላኝ ወደ ጓዳ፤ መኖሩንስ አለ ፣ በኔም አገር ታቦት የሰው ልጅ ለፍራንክ ፣ የሚናከስበት ቀላቅሎ የሚሸጥ ፣ ሸክላ ከበርበሬ አጋንንት ያለበት ፣ ሲኦል ነው ሃገሬ

፶፬ ዛት ኢዝ ዴሞክራሲ የሚያወዛውዘው ፣ ጣቱን ወደ ላይ ጸብ ቢጤ ፈልጎ ፣ ቦክስ ከሰማይ እንዲኖር በምድር ላይ ፣ ሰው ራሱን ችሎ ነው የተፈጠረ ፣ ሲጀመር ሀ! ብሎ ቃሉ ካልተስማማው ፣ ቀሬታ ካለው ጥረህ ግረህ ብላ ፣ በላብህ ያለው የፈጣሪው ጥፋት ፣ መስሎ ከታየው ዛት ኢዝ ዴሞክራሲ ፣ ምን እንበለው?


፶፭ ዱቤ ካለባችሁ ዱቤዬን ሳልከፍል ፣ ሳጥኔ ገብቼ ጉድ ባይ ይቺን አለም ፣ ተሰነባብቼ እነማ እንዳዘኑ ፣ ማ ደስ እንዳለው ከመራቄ በፊት ፣ ስሰልላቸው ካልቃሾቹ መሃል ፣ ድምፁ ጎላ ብሎ ሲጠርበኝ ሰማሁት ፣ የሰፈሬ ጀብሎ ልትሄዱ አካባቢ ፣ ዱቤ ካለባችሁ ሂሳብ ማወራረድ ፣ አትርሱ ባካችሁ




፶፮ እኔ ልሙት! ብዬ እስክምል ባይሳካም ምኞትህ ፣ የካብከው ቢናድብህም የጨበጥከው ቢበተን ፣ ትንቅንቅ ቢበዛብህም ቢርቅብህ ያሰብከው ፣ አቀበት ቢሆን መንገድህ ቀጥል ብያለሁ ቀጥል ፣ አውጥቼ ለውሻ አልሰጥህ ገስግስ እያቆራረጥክ ፣ ተነስ እትበል ዳዴ ተንጠልጥለህ ገደል ላይ ፣ እንቅልፍ ያምርሃል እንዴ ዝለል ተወገር ልቤ ፣ ደልቅ ይሰማኝ ድምፅህ እኔ ልሙት! ብዬ እስክምል ፣ አርፌ እስካሳርፍህ

፶፯ እንደምን አላችሁ ስላለ ጥላሁን ፣ ውበትን አየኋት ላያት ተነስቼ ፣ ዘመኔን ኳተንኳት እኔ ደከምኩ እንጂ ፣ ነጭ አጥንቴ ወጣ እስዋ ከኔ አጠገብ ፣ መቼ ተቀምጣ ስኩል ስቀባባት ፣ ስጫጭራት ኖሬ ቀለሙ ተሟጥጦ ፣ ቢደርቅም ብእሬ እንኳን ሙሉ አካሏን ፣ ስዬ ላሳያችሁ አንድ ጣቷም የለኝ ፣ ይቅርታ ባካችሁ ሰው ከንቱ ይደክማል ፣ እንዲል ታውቃላችሁ ጫፏን ካገኘሁት ፣ ሙሏት ራሳችሁ ልብ ይመኛል እንጂ ፣ ወትሮም ይቺን ዓለም የጀመራት እንጂ ፣ የጨረሳት የለም