ኦኩስ ወዩስ
ኦኩስ ወዩስ (ሮማይስጥ፦ Ochus Veius) በጣልያናዊ መኖኩሴ አኒዩስ ዴ ቪቴርቦ ጽሑፍ ዘንድ (1490 ዓ.ም. የታተመ)፣ ከአባቱ ኮሜሩስ ጋሉስ ቀጥሎ በጣልያን ሀገር ለ50 ዓመት የነገሠ ነበር (2370-2320 ዓክልበ. ግድም ማለት ነው)።
አኒዩስ እንዳለው፣ ይህ የታወቀ ከቤሮሶስ ሳይሆን ከጥንታዊ የጣልያ ዜና መዋዕሎች በማግኘቱ ነበር። የአኒዩስ ታሪክ በአውሮፓ መምህሮች ዘንድ ለጥቂት ዘመን ተቀባይነት ቢያገኝም፣ በኋላ ግን ምንጮቹን ሁሉ በሐሠት እንደ ፈጠራቸው የሚል ክስ ወጣና የአኒዩስ መጽሐፎች እንደ ውሸት ተነቁ።
አኒዩስ እንዳለው ይህ «ኦኩስ ወዩስ» ደግሞ «ኦኩስ ኩሩሊስ» ይባል ነበር፤ ስሙም «ወዮኩስ» በተባለ ተራራ ሊታይ እንደሚቻል አለ። 50 አመት ከነገሠ በኋላ ካሜሴኑስ (የኖህ ልጅ ካም) ከአፍሪካ ወጥቶ የጣልያን መንግሥት እንደ ያዘ የሚል ወሬ ጨመረ። ከዚህ በላይ ስለ ኦኩስ ወዩስ ብዙ ሌላ መረጃ አይሰጥም። ሆኖም በቤሮሶስ ነው ተብሎ ባቀረበው ጽሑፍ (አሁንም ሐሣዊ ቤሮሶስ የሚባል) ስለኮሜሩስ (ጋሜር) ዘመነ መንግሥት እንዲህ ይላል፦
- ኮሜሩስ ወደ እስኩቴስ ጉብኝት አድርጎ ተመልሶ እንደ እስኩቴስ አደራረግ ሠረገላ ለመሥራት የጣልያን ከተሞቹን አስተማራቸው። እንዲሁም በሳካኛ (የእስኩቴስ ቋንቋ) ሠረገላ «ወዩስ» ይባላል፣ ጋሪም «ወያስ» ይሉታል፣ ከጋሪዎችም የተሠራ ከተማ ትንሽ ቢሆን «ወይቱላ»፣ ትልቅ ቢሆን «ኡሉርዱም»፣ መዲናም ቢሆን «ኩ ኦኮላም» ይሉታል፤ እስከ ዛሬም ድረስ እስኩቴሳውያን ጋሪና ሠረገላ እንደ መኖርያ ቤት ይጠቅማቸዋል።
ከአኒዩስ በኋላ፣ በ1629 ዓ.ም. ኩርቲዩስ ኢንጊራሚ የተባለ ጣልያናዊ ወጣት በቤተሠቡ እርሻ ላይ ብዙ ጥንታዊ የኤትሩስካውያን መዝገቦች እንዳገኘ ብሎ በሮማይስጥ ትርጉም አሳተማቸው፤ በነዚህ ደግሞ ከአኒዩስ ታሪኮች ጋር የሚስማማ ብዙ ነገር ነበር። ስለ ኦኩስ ወዩስ እንዲህ አለው፦ «የጎሜሩስ ልጅ ኦኩስ ወዩስ ተከተለው። ሕዝቡ የኖሩባቸው ብዙ ጋሪዎችና ኡሌርዳዎች ሠራ፤ በ50ኛው አመት ግን ካሜሰስ ከብዙ ሰዎች ጋር ከግብጽ መጥቶ ኦኩስን ተዋጋና መንግሥቱን ያዘ።» ዳሩ ግን በቅርብ ጊዜ ውስጥ የአውሮጳ ሊቃውንት የኩርቲዩስ መጽሐፍ ደግሞ ሐሣዊ እንደ ሆነ አሳመኑ፤ እስካሁንም እንደ ሐሣዊ ታሪክ ይቆጠራል።
ቀዳሚው ኮሜሩስ ጋሉስ |
የኮሜራ (ጣልያን) ንጉሥ 2370-2320 ዓክልበ. ግድም (አፈታሪክ) |
ተከታይ ካም «ኤሴኑስ» |