Jump to content

ኤንመርካርና የአራታ ንጉስ

ከውክፔዲያ
የ11:05, 2 ጃንዩዌሪ 2023 ዕትም (ከInternetArchiveBot (ውይይት | አስተዋጽኦ) ተዘጋጅቶ)
(ለውጡ) ← የፊተኛው እትም | «የአሁኑን እትም ለመመልከት» (ለውጡ) | የሚከተለው እትም → (ለውጡ)

ኤንመርካርና የአራታ ንጉስ በጣም ጥንታዊ የሱመርኛ ትውፊት ነው። በታሪካዊ ሁኔታ ምናልባት በ3ኛ ሺህ ዘመን ክ.በ. ድርጊቶች ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይቻላል። ከ'ኡኑግ-ኩላባ' (ኦሬክ ወይም ኡሩክ) ንጉስ ከኤንመርካርና ስሙ ካልታወቀ ከአራታ ንጉስ መከከል ስለተደረገው ውድድር ከሚገልጹ ሰነዶች አንዱ ነው።

በሰነዱ መጀመርያ ክፍል የሚከተለው መረጃ ይሰጣል፦ «በዚያ ጥንታዊ ዘመን፣ ዕድሉ በተወሰነ ጊዜ፣ ታላላቆቹ መሳፍንት የ'ኡኑግ-ኩላባ' ኤ-አና ራሱን ከፍ እንዲያድርግ ፈቀዱ። በዚያን ጊዜ ብዛትና የዓሳ ጎርፍ፣ መልካም ገብስ የሚያመጣውም ዝናብ በ'ኡኑግ-ኩላባ' ተጨመሩ። የድልሙን አገር ገና ሳይኖር፣ የ'ኡኑግ-ኩላባ' ኤ-አና በደንብ ተመሰረተ።»[1] Archived ሴፕቴምበር 26, 2011 at the Wayback Machine

ኤ-አና ማለት 'የአገራት ሁሉ እመቤት' ለሆነች ለኢናና ክብር በኡሩክ የተሠራ መስጊድ ነበረ። እንዲሁም የአራታ ጌታ በኢናና ስም ራሳቸውን በዘውድ ቢጫኑም፣ ይህ ማድረጋቸው ግን በኡሩክ እንዳላት ጡብ መስጊድዋ ደስ አላሰኛትም።

እንዲህ 'ኢናና ከብሩኅ ተራራ በቅዱስ ልብዋ የተመረጠችው' ኤንመርካር ከዚያ አራታ እንዲገዛለት እናና እንድትፈቅደው ይጠይቃታል። የአራታ ሕዝብም የወርቅና የዕንቁ ግብር እንዲያቀርቡ፣ ከፈተኛው የአብዙ መቅደስ በኤሪዱ፣ የኤ-አና መቅደስም በኡሩክ ይሠራ ዘንድ፣ ይጠይቃታል። እንግዲህ የኢናና ምክር ለኤንመርካር አንድ ልዩ ተልእኮ የሱስንና የአንሻን ተራሮች አሻግሮ ከአራታ ንጉስ ግብርነታቸውንና ተገዥነታቸውን ለማስፈልግ ወደ አራታ እንዲልከው ነው።

ይህ ምክር ለኤንመርካር ተስማምቶት ተልእኮውን ይልካል። መልእክተኛውን ሲልከው ደግሞ ግብሩን ካልላኩለት በቀር አራታን ለማጥፋትና ሕዝቡን ለመበትን የሚል ዛቻ ይሰጣቸዋል እንዲህ ሲለው፦ «ኢናናም በማዕበሉ በጩኸት የተነሣችበት እንደ አጥፊው ጎርፍ ጥፋት እኔም ደግሞ የጎርፍ ጥፋት በዚያ እንዳላድርግ...»። ከዚያ በላይ ለመልእክተኛው 'የኑዲሙድ መዝሙር' ይሰጣል፤ ይህም ኤንኪ የተባለው አምላክ ኗሪ ያለባቸው አገሮች ሁሉ ወደ አንድ ቋንቋ እንዲመልሳቸው ይለምናል። (በሌላ ትርጉም ግን ኤንኪ የአገሮች ቋንቋ እንዲያደባለቅ ይላል።) እነዚህ አገሮች ስሞች ሹባርሐማዚሱመር፣ ኡሪ-ኪ (የአካድ ዙሪያ) እና የማርቱ አገር ይባላሉ።

መልእክተኛው በአራታ ይደርስና ይህን መልእክት ለንጉሡ ተናግሮ ለጌታው ለኤንመርካር መልሳቸውን ይጠይቃቸዋል። የአራታ ንጉሥ መልሰው ለኡሩክ እጅ መስጠት ከቶ አይቻልም ይላሉ፣ ምክንያቱም ኢናና እራሷ ለማዕረጋቸውና ለሥልጣናቸው መርጣቸዋለችና። ተልእኮው ግን ወዲያው እናና በኡሩክ ንግሥት ሆና እንደ ተቀባች ከዚያም በላይ አራታ ለኡሩክ እንዲሰግድ ለማድረግ ቃልዋን እንደ ሰጠች ይገልጽላቸዋል።

በዚህ ዜና ጭፍግግ ገብተው በመጨረሻ የአራታ ንጉስ መልሳቸውን ይሰጣሉ፦ የኡሩክ ሠራዊት ለሳቸው እኩል ስላልሆነ ከኡሩክ ጋር ጦርነት ለማድረግ የተዘጋጁ ቢሆኑም፤ ኤንመርካር ግን የትልቅ መጠን ገብስ ወደ አራታ ቢልክላቸውና ኢናና እራሷ አራታን እንደ ተወች ብታስረዳው የዛኔ እጃቸውን ይሰጡታል ይላሉ።

ተልእኮ ይህን መልስ ይዞ ወደ ኤንመርካር ተመለሰና በማግሥቱ ኤንመርካር እንዲያውም ገብሱን ወደ አራታ ይልካል። ደግሞ ተልእኮውን በተጨማሪ ዕንቁ ለመጠይቅ ይልከዋል።

የአራታ ንጉስ ግን እምቢ ብለው በዚያ ፈንታ ኤንመርካር እራሱ ዕንቁ ወደሳቸው እንዲልክ ይጠይቃል። ኤንመርካር ይህን ሰምቶ ለአሥር አመት የተጌጠ በትር ያዘጋጃል። ከዚያ በኋላ ይህን ወደ አራታ በመልእክተኛው እጅ ይልካል። ይህ የአራታን ንጉሥ ያስፈራል፤ አሁን ኢናና በእውነት እንደ ተወቻቸው ያያሉና። ነገር ግን ጥያቄውን ለመወሰን ከሁለቱ ከተሞች ሁለት ጎበዞች አንድ በአንድ ላይ እንዲታገሉ የሚል ሀሣብ ያቀርባሉ። የኡሩክም ጌታ ይህን ሀሣብ ሲቀበል በተጨማሪ እንዳያጠፋቸው የአራታ ሕዝብ ለከፍተኛው መቅደሱ ዕንቁና ወርቅ እንዲገብሩ ይጠይቃል። መልእክተኛው በቃሉ ብዛት ለማስታወስ ተቸግሮት ኤንመርካር በዚያን ጊዜ ጽሕፈት ይፈጥራል። ስለዚህ ተልእኮው ጽሕፈቱን ይዞ እንደገና 'ሰባቱን ተራሮች' ይሻገራልና ለአራታ ንጉስ ያቀርበዋል። የአራታ ንጉስ ጽሕፈቱን ለማንበብ ሲሞከሩም ኢሽኩር (የአውሎ-ንፋስ አምላክ) ስንዴና ሽምብራ ለማብቀል ዶፋ ዝናብ ይሰጣል። ይህ ስንዴና ሽምብራ ወደ ንጉሥ ሲያመጡ፣ እሳቸው ኢናና የአራታን ቅድምትነት እንዳልተወች ያስረዳል ብለው ኅይለኛ ጎበዛቸውን ጠሩ።

ከዚህ በኋላ የሰነዱ ሸክላ ብዙ ቀዳዳ ስላለበት በቀላል አይታነብምና የሚከተለው ታሪክ ግልጽ አይደለም። በመጨረቫ ግን ኤንመርካር እንዳሸናፈ ምናልባትም ኢናና በአራታ ዙፋን ላይ እንዳስቀመጠችው ይመስላል። የአራታም ሕዝብ ግብራቸውን ለኤ-አና እና ለከፍተኛ አብዙ ግንብ ያቀርባሉ።

የውጭ መያያዣ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]