Jump to content

ወርጂ

ከውክፔዲያ
የ13:43, 12 ኖቬምበር 2023 ዕትም (ከAbaba RXZ (ውይይት | አስተዋጽኦ) ተዘጋጅቶ)
(ለውጡ) ← የፊተኛው እትም | «የአሁኑን እትም ለመመልከት» (ለውጡ) | የሚከተለው እትም → (ለውጡ)

ወርጂ የአርጎባ የአፋርና ጎሳ ነው።

ወርጂዎች

አረብኛ

አርጎብኛ

አፋርኛ

አማርኛ ቋንቋዎችን በዋነኝነት ይናገራሉ።

20,600 1996 Census

መልክዓ ምድር

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በኢትዮጵያ ውስጥ ከጀበርቲ ማህበረሰብ ጋር በኢኮኖሚ ተዋስኦው የሚመሳሰል ሌላ ህዝብ አለ፡፡ ይህ ህዝብ “ወርጂ” ይባላል፡፡ የወርጂ ህዝብ ንግድን የኢኮኖሚ መሰረቱ በማድረግ በኢትዮጵያ ውስጥ የተዋጣለት የነጋዴ ማህበረሰብ የሚባልበትን ቅጽል ለመጎናጸፍ ችሏል፡፡ ወርጂ በኢኮኖሚ ስምሪቱ ከጀበርቲ ጋር መመሳሰሉን በማየት ብቻ በርካቶች የጀበርቲ ማህበረሰብ አካል አድርገው ሲቆጥሩት ይታያል፡፡ በኔ ጥናት መሰረት ግን ወርጂና ጀበርቲ የተለያዩ ነገሮችን ነው የሚወክሉት፡፡ ጀበርቲ ማለት በጥቅሉ ሲታይ “ኢትዮጵያዊ ሙስሊም” እንደማለት ነው፡፡ ስያሜው በይበልጥ ነጥሮ ሲታይ ደግሞ በሰሜንና ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያና በኤርትራ የሚኖሩ ሙስሊም ማህበረሰቦችን ነው የሚወክለው፡፡ ከዚያ ወረድ ብሎ ሲታይ ግን ጀበርቲ ትውልዱ ከሼኽ ዒስማኢል ጀበርቲ እና ከሼኽ ሙሐመድ አል-ጀበርቲ ቤተሰቦች የተገኘ ሰው እንደማለት ነው፡፡ “ወርጂ” ግን ከጥንት ጀምሮ እንደ አንድ ብሄረሰብ ይታወቅ የነበረ ህዝብ ነው፡፡ የአጼ አምደ-ጽዮን ገድል በተጻፈበት ዘመን የወርጂ ህዝብ በታችኛው አዋሽ እና በአዳል መካከል ተስፋፍቶ ይኖር ነበር፡፡ እነዚህ ወርጂዎች በዚያ ዘመን ከብት አርቢዎች ነበሩ፡፡ በአጼ አምደ-ጽዮን ላይ በተደጋጋሚ ጊዜያት በማመጻቸው አጼው ከፍተኛ የቅጣት እርምጃዎችን እንደወሰደባቸው የአጼው ገድል በስፋት ያስረዳል፡፡ ግብጻዊው አል-መቅሪዚ በበኩሉ (1400-1444) ስለ ኢትዮጵያ ሱልጣኔቶች ታሪክ ሲጽፍ “ወርጂ” የሚባል አርብቶ አደር ህዝብ በኢፋት ሱልጣኔት ይኖር እንደነበረ ነግሮናል፡፡ ይህ ህዝብ እስከ ኢማም አሕመድ ኢብራሂም አል-ጋዚ ዘመን ድረስ ከየረር ተራራ በስተምስራቅ ጀምሮ እስከ ዛሬው የአፋር ክልል ምዕራባዊ ክፍል ድረስ ይኖር ነበር፡፡ ማህበረሰቡ በኢማም አሕመድ ዘመን ከአርብቶ አደርነት ወደ ከፊል አራሽነት እየተቀየረም ሄዷል፡፡ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተከሰቱት ታላላቅ ክስተቶች ግን የመላውን የምስራቅ አፍሪቃ ህዝቦች ዲሞግራፊያዊ ተዋጽኦ ከስረ-መሰረቱ ቀየሩት፡፡ በዚህም የተነሳ ከፊሉ የወርጂ ህዝብ በአፋር ህዝብ ተዋጠ፡፡ ከፊሉ ግን ከየረር ተራራ አቅራቢያ መኖሩን ቀጠለ፡፡ ይህኛው ክፍል እያደር ከኦሮሞ ህዝብ ጋር በጋብቻና በሞጋሳ ስልት እየተዛመደ ራሱን የኦሮሞ ህዝብ አንድ አካል አድርጎ መቁጠር ጀመረ፡፡ የአጼ ምኒልክ አያት የነበሩት ንጉሥ ሣህለ ስላሤ ወደ ደቡብ መስፋፋት በጀመሩበት ጊዜ በቅድሚያ ከወጓቸው ማህበረሰቦች መካከል አንዱ ይህ የወርጂ ህዝብ ነው፡፡ የዘመኑ ሙስሊሞች ርስት መያዝ አይፈቀድላቸውም በሚለው የሰለሞናዊያን ህግ መሰረትም ወርጂ መሬቱን አጣ፡፡ በዚህም የተነሳ ወደ ሌሎች ስፍራዎች እየፈለሰ በንግድ ስራ ላይ መሰማራት ጀመረ፡፡ የወርጂ ማህበረሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪክ ሰነዶች ከተጠቀሰበት ጊዜ አንስቶ በእስልምና ሃይማኖት ተከታይነቱ ነው የሚታወቀው፡፡ ጥንት ይኖርበት የነበረው መሬትም በተለያዩ ዘመናት የተነሱት የሸዋ፣ የኢፋት እና የአዳል እስላማዊ ሱልጣኔቶች አካል ሆኖ ነበረ፡፡ ይሁንና የህዝቡ መነሻ ከዐረቢያ ነው እየተባለ አልፎ አልፎ የሚነገረውን አፈ-ታሪክ ከሰነዶች ለማረጋገጥ አልቻልኩም፡፡

ከላይ እንደገለጽኩት የወርጂ ህዝብ በጥንተ መሰረቱ እንደ አንድ ብሄረሰብ ሊቆጠር የሚችል ነው፡፡ ሆኖም ህዝቡ የራሱ ቋንቋ የነበረው ለመሆኑ በተጨባጭ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ እኔ ጸሐፊው “ወርጂ በጥንተ መሰረቱ እንደ ብሄረሰብ ሊታይ ይችላል” የምለው የጥንቱ ሰነዶች ከሌሎች ህዝቦች የተለየ እና አንድ ራሱን የቻለ ህዝብ አድርገው ስለሚቆጥሩት ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ወርጂ የኦሮሞ ህዝብ አካል ተደርጎ ነው የሚቆጠረው፡፡ የአፍ መፍቻ ቋንቋውም ኦሮምኛ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ በብዙ የኦሮሞ ጎሳዎች ውስጥ “ወርጂ” እየተባለ የሚጠራ ንዑስ ጎሳ አለ፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን የወርጂ ህዝብ ከሌሎች ኦሮሞዎች የሚለይበትን አንዳንድ መለያዎች ለማስጠበቅ የቻለ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ወርጂ የሚኖረው በሸዋ ክፍለ ሀገር ነው፡፡ በክፍለ ሀገሩ ከሚኖሩት በርካታ የኦሮሞ ማህበረሰቦች መካከል ሙሉ በሙሉ ሙስሊም የሆነው ወርጂ ብቻ ነው፡፡ በሌላ በኩል ወርጂዎች የትም ሆነው በኦሮምኛ ሲነጋገሩ በድምጽ አወጣጥ ስልታቸው በቀላሉ ሊለዩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በኦሮምኛ “dhufe” ከተባለ “መጣ” ማለት ነው፡፡ ወርጂዎች በኦሮምኛ ሲናገሩ ግን “ufe” ነው የሚሉት እንጂ dhufe አይሉም፡፡ በብዙ ስፍራዎች የገጠሙኝ የወርጂ ተወላጆች “dh” የተሰኘውን የኦሮምኛ ድምጽ በ“a” ስልት ነው የሚያስኬዱት፡፡ ይህ ለየት ያለ የአነጋገር ዘይቤ እንዴት እንደተፈጠረ ለማወቅ አልቻልኩም፡፡ አንድ ተመራማሪ በዚህ ዙሪያ ጥናት ቢያደርግ አዲስ ነገር ሊያሳውቀን እንደሚችል አምናለሁ፡፡

ጀበርቲ እና ወርጂ በጨረፍታ ሲታዩ ከላይ የቀረበውን ይመስላሉ፡፡ ይህንን ጽሑፍ የከተብኩት ከልዩ ልዩ አንባቢዎች ሲቀርቡልኝ የነበሩ ጥያቄዎችን በትንሹም ቢሆን ልመልስ ብዬ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ የበለጠ መረጃና ማስረጃ ያላቸው ወገኖቻችን ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡን እንጠብቃለን፡፡ ሰላም ብያለሁ!!

የመረጃ ምንጮች -- 1. አፈንዲ ሙተቂ፤ “አዳል-ስመ ገናናው ሱልጣኔት እና የኢማም አሕመድ ኢብራሂም አል-ጋዚ ዘመቻዎች”፤ (ለህትመት የተዘጋጀ መጽሐፍ) 2. አሕመዲን ጀበል፤ “ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች”፤ 2003፤ አዲስ አበባ

ወርጂ የኢትዮጵያ ብሔር ነው።