Jump to content

ቀደምት ሳይንሳዊ ፍልስፍናዎች

ከውክፔዲያ

ቀደምት ሳይንሳዊ ፍልስፍናዎች፤ በቀድሞው ወቅት ሳይንስ ሳይራቀቅ ቴክኖሎጂም ዓለምን በፍጥነት ከመቀየሩ በፊት የነበሩት የጥንት ፈላስፎች ለአሁኑ ዘመን የሳይንስ እድገት የራሳቸውን አሻር አሳርፈዋል። ታዲያ የጥንት ፈላስፎች ሲነሱ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት የግሪክ ፈላስፎች ሆነው ይገኛሉ። ሪናን የተባው ፀኃፊ እንዳለው፣ «ሶቅራጥስ ለሰው ልጅ ፍልስፍናን አበረከተ። አሪስቶትል ደግሞ ሳይንስ አበረከተ» ከሶቅራጠስ በፊትም ቢሆን ፍልስፍና ነበሩ። ከአሪስቶትልም በፊት ቢሆን ሳይንስ ነበር። ነገር ግን ከሶቅራጠስና ከአሪስቶትል በኋላ ፍልስፍናም ሆነ ሳይንስ ከፍተኛ እድገት አሳይቷል። ከነሱ በኋላ የተሰራው ሁሉ እነሱ በጣሉት መሠረት ላይ የተገነባው ነው” ሲል የቀደሙትን ፈላስፎች ሚና ያረጋግጣል። ለመጀመሪያ ጊዜ በግልፅ ለማይታወቁት ክስተቶችና ድርጊቶ ተፈጥሯዊ ማስረጃዎችን ማቅረብ የጀመሩት ኢዮኒያዊን ግሪኮች እንደነበሩ ታሪክ ይናገራል።

የተለዩ ገጠመኞችን ምክንያቶች ወይም መነሻዎች በፊዚክስ አማካኝነት ለማግኘት ሞክረው ነበር እንዲሁም በፍልስፍና አማካኝነት ለማድረግ የሞከሩት ደግሞ ለአጠቃላይ (ክስተቶች) ተፈጥሯዊ ንድፈ ሃሳብ በማግኘት ነበር። ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ640 እስከ 550 እንደኖረ የሚነገርለት እና “የፍልስፍና አባት” ተብሎ የሚታወቀው ታለስ የመጀመሪያ የከዋክብት ሳይንስ ተመራማሪን ሳይንሳዊ ፍልስፍና እናያለን።

እሱም አንድ ወቅት ሚልተስ በተባለ ስፍራ የሚኖሩ ተወላጆችን ያስደነቀው ፀሃይና ከዋክብት ከእሳት የተሰሩ ኳሶች ናቸው በማለት ነበር። ሰዎቹ ግን ፀሃይንና ከዋክበትን አምላኮች ናቸው ብለው ያምኑ ነበር። ከክርስቶስ ልደት በፊት 610-540 መካከል ይኖር የነበረው የዚህ ፈላስፋ ተማሪ የነበረው አናክሊማንደር ለመጀመሪያ ጊዜ ከዋክብትንና መልክዓ ምድርን የተመለከተ ቻርቶች ወይም ስዕች የሰራ ሰው ነው። በእሱ እምነት ዓም የተጀመረው እንደ አንድ ወጥ ክምችት ሆኖ ነው። ሁሉም ነገር ከዚህ የተገኘው የተቃራኒዎች መለያየት በሚለው ሂደት ነው። የከዋክብት ታሪክ እራሱን የሚደጋግምና ቁጥር ስፍር የሌላቸው አለማት እንደሚፈጠሩና ተመልሰውም እንዲጠፉ አስተምሮ ነበር። እንደሱ አባባል መሬት በራሷ ውስጣዊ ግፊት ሚዛኗን ጠብቃ የቆመችና የማትንቀሳቀስ አካል ናት። ፕላኔቶች በሙሉ በአንድ ወቅት ከፈሳሽ አካል የተሰሩ ነበሩ፤ ህይወት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው ከባህር ሲሆን ወደ ደረቅ መሬት የመጣውም የባህር ውሃ ሲቀንስ ነው። በዚህ ሁኔታ ደረቅ መሬት ላይ የቀሩት እንስሳት ቀስ በቀስ አየር የመተንፈስ ችሎታን በማዳበር ከዚህ በኋላ በምድር ላይ ለተፈጠሩት ህይወቶች መነሻ ሆነዋል የሰው ልጅም ከመጀመሪያ ጀምሮ አሁን የሆነውን ዓይነት ፍጡር የማያውቅ ከነበረና ከማደግ ይን ያህል ጊዜ የሚፈጅበት ከሆነ እስካሁን በህይወት መቆየት አይችልም ነበር ኪልም አትቷል። ከክርስቶስ ልደት በፊት በ450 ይኖር የነበረው አናክሊሜኔስ የተባለው ሌላው ተመራማሪ ደግሞ የነገሮችን የጥንት ሁኔታ ሊገለፅ አንድ ወጥ ጋዝ እንደነበረና ቀስ በቀስም ወደ ነፋስ፣ ጉም፣ ውሃ፣ መሬትና ድንጋይና እንደ ተለወጠ ይናገራል። እንደሱ አባባል የቁሳቁስ ሦስቱ ቅርፆች ማለትም ጋዝ፣ ፈሳሽና ጠጣርነት፣ የመቀዝቀዝ የተለያዩ ደረጃዎች ናቸው።

የመሬት መንቀጥቀጥ የሚከሰተው ደግሞ ፈሳሽ የነበረው የመሬት አካል በሚጠጥርበት ወቅት ነው። ህይወትና ነፍስ አንድ ናቸው። ከማንኛውም ቦታና በማንኛውም ነገር ውስጥ እንቅስቃሴ ኃይል ይገኛል ብሏል። ሌላው እና አስገረሚው ግሪካዊ ፈላስፋና ከ500-428 ይኖር የነበረው አናግዛጎራስ የሰውን ልጅ የማሰብ ችሎታ በተመለከተ የፊት እግሮችና እጆች መንቀሳቀቀስ በሚያቆምበት ጊዜ በሚፈጥር የኃይል ሂደት የተገኘ ነው ሲል አስተምሮ ነበር። በመጨረሻ አንድ ኤምፔኮክሌስ የተባውና ከክርስቶስ ልደት በፊት በ445 ሲሲሊ በምትባል ደሴት ይኖር የነበረ ሌላ ተመራማሪ ደግሞ የአዝጋሚ ለውጥን ፅንሰ ሃሳብ አንድ እርምጃ አስኪዶት ነበር። እሱ እንዳለው አካላት የሚፈጥሩት አስቀድሞ በነበረ መመሪያ ሳይሆን በምርጫ ነው። ተፈጥሮ በተለያዩ ህይወት ያላቸው አካላት ላይ ብዙ ሙከራዎችን ታደርጋለች። የተለያዩ አካላትን በተለያዩ መልኮች ታዋህዳለች። ውህደቱ የአካባቢውን ፍላጎት የሚያሟላ ከሆነ አካሉ በህይወት መኖሩን ዘሩን ማራባት ይችላል። ውህደቱ ካልሰመረ ደግሞ አካሉ ታርሞ ይጣላል። ጊዜ እያለፈ በሄደ ቁጥር የተለያዩ ህይወት ያላቸው አካላት አካባቢዎችን እየተለማመዱበት ይካሄዳሉ ሲል ሳይንሳዊ ፍልስፍናውን በየጊዜ ተናግሮ ነበር።

እንግዲህ እነዚህ ጥንታዊ ፈላስፎች የሳይንስ ብልጭታ ባልነበረበት ወቅት ፍልስፍናዊ ትንታኔዎችን በማዳበር ለሳይንሳዊ ንድፈ ሃሳቦችን ማደግ የማይናቅ ጥንታዊ ድርሻቸውን በአግባቡ ተወጥተው አልፈዋል።