ሐና ወኢያቄም
ሐና ወኢያቄም | |
---|---|
የክርስቶስ ብቸኛ አያቶች | |
የሐና ትውልድ ዘመን | ፶ ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት |
የቅድስት ሐና እናት ስም | ሄርሜላ |
የቅድስት ሐናና የቅዱስ ኢያቄም አንድዬ ልጃቸው | እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም |
ቅድስት ሐና ያረፈችበት ቀን | የካቲት ፲፮ ፤ ፲፪ ዓመት ከክርስቶስ ልደት በኋላ |
የሚከበሩት |
በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በካቶሊክ ቤተክርስቲያን |
የንግሥ ቀን | ኅዳር ፲፩ |
ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን አባቶች እንደሚያስተምሩት አዳምና ሔዋን እግዚአብሔር አትብሉ ያላቸውን የዕፀ በለስን ፍሬ በሰይጣን ምክር ተታለው በበሉ ጊዜ ፣ ከተድላ ገነት ወጡ ፤ በፈጣሪ ፍርድም ተቀጡ ።
እግዚአብሔር አዳምና ሔዋንን ከገነት አስወጥቶ በአንጻርዋ (በትይዩ) በደብረ ቅዱስ አኖራቸው ፤ ስለምን ቢሉ ፣ ገነትን እያስታወሱና በሩቅ እያዩ እንዲያዝኑ ፣ በዚያውም ፣ "ወደ ቀድሞው ቤታችን ወደ ገነት ይመልሰን ይሆን? " እያሉ እንዲጸጸቱ ና ወደ ነበሩበት ለመመለስ እንዲተጉ በአጠቃላይ ገነት መንግሥተ ሰማያት እንዳልጠፋች ፣ ሕልም እንዳልሆነች በእርግጥ እንዳለች በአይምሮ እንዲቀረፅ ሲል አደረገው።
ከዕለታት አንድ ቀን አዳም ፣"እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ፣ ገነትን ያህል ቦታ ያጣሁት በአንቺ ምክኒያት እኮ ነው" ሲል ሔዋንን ተቆጣትና ፊት ነሣት ። በዚያም ጊዜ ሔዋን ደንግጣ ከአዳም ሸሽታ ሄደች ። አዳምም ብቻውን እያዘነና እየጸለየ ሳለ ፣ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ አዳም መጥቶ ፣ "ከሚስትህ ጋር ተጣልተህ፣እስዋንም አባረህ እንዴት ትጸልያለህ? ሂድና ታረቃት" አለው ። አዳምም ፣ "እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ፣ ገነትን ያህል ቦታ ያጣሁት በእርስዋ ምክኒያት ስለ ሆነ አልታረቅም" አለው ። መልአኩም ፤ "በእርስዋ ምክንያት ያጣኸውን ብታጣ ከፈጣሪህ ጋር መታረቂያህ እስዋ ናትና ታረቃት" አለው ። አዳም ግን ፣ "አይሆንም አለና ጸሎቱን ቀጠለ" ። መላኩም እንደገና ወደ አዳም መጥቶ ፣ "እግዚአብሔር የቂመኛን ጸሎት አይቀበልምና በመጀመሪያ ከሚስትህ ታረቅ" አለው ። አዳምም ለመልአኩ መልሶ ፣ "አንተው ሂደህ ብታመጣልኝሳ?" ብሎ ለመነው ። መላኩም አዳም ፈቃደኛ መሆኑን ሲያውቅ ፣"እንዳባረርሃት አንተው ሂድና አምጣት እንጃ፤ እኔ ምን ባይ ነኝ " ሲል መለሰለት ። በዚያን ጊዜ አዳም ሄዶ ከሔዋን ታረቀ ፣ መለሳትም ።
ከዚህም ጊዜ ጀምሮ ሁለቱም ሲጫወቱ ሔዋን አዳምን ፣ "እግዚአብሔር አምላካችን እንደተጣላን ይቀር ይሆን? አይታረቀንም ብለህ?" ስትል ጠየቀችው ። አዳምም ፣ "እግዚአብሔር መሐሪ ነውና ይታረቀን ነበር ። ዳሩ ግን አንቺ አለሽና ምን ይሆናል" አላት ። በዛም ጊዜ ሔዋን ፣ "ከእንግዲህ ወዲህ ካንተ ፈቃድ አልወጣም" አለችው ። ይህንንም ከተባባሉ በኋላ ሁለቱም እግዚአብሔርን ለመለመን ሱባኤ ገቡ ። አዳምና ሔዋን ሱባኤያቸውን ሲፈጽሙ እግዚአብሔር ተገለጠላቸውና ፣ "አዳም ሆይ ፤ከሰማየ ሰማያት ወርጄ ፣ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ እኔ አድንሃለሁ" አለው ። አዳምም ፣ "እግዚአብሔር ሆይ ፣ መቼ ነው የምታድነኝ?"ሲል ጠየቀው ። "አምስት ቀን ተኩል ሲፈፀም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ፣ በመንደርህ ተመላልሼ ፣ ተሰቅዬና ሞቼ አድንሃለሁ" ብሎ ተስፋ ሰጠው ፤ ቃል ኪዳንም ገባለት ።[1]። "አምስት ቀን ተኩል" በእግዚአብሔር አቆጣጠር ነው "አምስት ሺህ ከአምስት መቶ ዓመት" ማለት ነው ። አዳምም በዚህ ተስፋ እየተጽናና ዘጠኝ መቶ ሠላሳ ዓመት ከኖረ በኋላ አንቀላፋ (ሞተ) ዘፍጥ.፭፥፩-፭ ።
ለአዳም የተሰጠው ተስፋም ሲወርድ ሲዋረድ ቴክታና በጥሪቃ ከተባሉ የዳዊት ዘር ከሆኑት ከድንግል ማርያም አያቶች ደረሰ ። በዮሴፍ ሀረገ ትውልድ በኩል በአጭሩ ሲቆጠር አኪንም ኤልዮድን ወለደ ፤ ኤልዮድም አላዛርን ወለደ ፤ አላዛርም ማትያስን ወለደ ፤ ማትያስም ያዕቆብን ወለደ ፤ ያዕቆብም ዮሴፍን ወለደ ፤ ዮሴፍም በዕድሜ ሽምግልና እያለ አምላክን ለመውለድ ትንቢት የተነገረላትን ድንግል እንዲጠብቃት (እንዲያጫት) በእግዚአብሔር መልአክ ታዘዘ ማቴ.፩፥፲ ። ከዳዊት ዘር ሐረግ ትውልድ የተወለዱት የቅድስት ድንግል ማርያም ቅድም አያቶች ቴክታና በጥሪቃ በጣም የበዛ ሀብት ነበራቸው ። ነገር ግን ልጅ ስላልወለዱ በሀብታቸው ብዛት እምብዛም አይደሰቱም ነበር ። እግዚአብሔርን ግን ፍሬ እንዲሰጣቸው ሱባኤ እየገቡ ይጸልዩ ነበር ። በአንድ ወቅት ቴክታና በጥሪቃ ሱባኤ ገብተው ሳለ ራእዪ ያያሉ ፤ ራእዪውም አንዲት ነጭ እንቦሳ ጥጃ ከበረታቸው ስትወጣ ይህችም እንቦሳ ሌላይቱን እንቦሳ ስትወልድ ፣ እንዲሁ እየተዋለዱ እስከ አምስተኛይቱ እንቦሳ ይደርሳሉ ፤ አምስተኛይቱ እንቦሳ ግን ጨረቃ መሰል እንቦሳ ትወልዳለች ፤ ጨረቃይቱም ፀሐይን ትወልዳለች ። ይህንንም ራእዪ በዘመናቸው ለነበረው መፈክረ ሕልም (ሕልም ፈቺ) ሄደው ነገሩት ። እሱም ፣ "ደጋግ ልጆች ትወልዳላቹህ ። የጨረቃው ራእዪም ከሰው በላይ የሆነች ልጅ ትወልዳላቹህ ። የፀሐዩ ነገር በርቶ አልተገለጸልኝም እንደ ነብይና እንደ ንጉሥ የመሰለ ልጅ ከቤታቹህ ይወለዳል" ብሎ ነገራቸው ።
ከዚህም በኋላ ቴክታ ፀነሰች ፤ ወለደችም ስምዋንም ሄኤማን ብላ ጠራቻት ። ሄኤማን ማለት "ስለቴ ደረሰ ፤ እንደ ስለቴ ሆነልኝ" ማለት ነው ። ከዚያም ሄኤማን ዴርዴን ፣ ዴርዴን ቶና ፣ ቶና ሲካርን ወለዱ ፣ ሲካር ሄርሜላን ፤ ሄርሜላ ሐናን ወለደች ። ኢያቄምና ሐናም እንደ ሳሙኤል ወላጆች እንደ ሐናና ሕልቃና በእግዚአብሔር ፊት ደጋጎች ነበሩ ። ሁለቱ ጻድቃን ነበሩ ነገር ግን ልጅ ስላልወለዱ ልጅ እንዲያገኙ ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩ ነበር ፤ እንዲህ ሲሉ "ሴት ልጅ ብንወልድ በቤተ መቅደስ እየኖረች እግዚአብሔርን እንድታገለግል ፤ ወንድ ልጅ ቢወለድ እንደ ነብዩ ሳሙኤል የእግዚአብሔር ካህን ሆኖ ዕድሜው ሙሉ እንዲያገለግል ለእግዚአብሔር ስዕለት አርገን እናቀርባለን" ብለው ብፅዓት ገቡ ። ሐናና ኢያቄምም በሱባኤ ቆይተውና ስዕለታቸው ተናግረው ሐምሌ ፳፱ ቀን ወደ ቤታቸው ተመለሱ ። ሐምሌ ፴ ቀን ሁለቱም ሕልም አዩ ። ሐና ለኢያቄም ፥ "ፀመር (ግምጃ) ሲያስታጥቁህ ፣ የእጅህም መቋሚያም ለምልማ አብባና አፍርታ ፍሬዋን ሰው ሁሉ ሲመገብ አየሁ" ብላ ነገረችው ። ኢያቄም በበኩሉ ፣ "ርግብ ጸዐዳ (ነጭ ርግብ) ሰባቱን ሰማያት ሰንጥቃ ወርዳ በራስሽ ላይ ስታርፍ ፣ በቀኝ ጆሮሽም ገብታ በማሕፀንሽ ስታድር አየሁ" ብሎ ነገራት ። ስለዚህ በዚህ እግዚአብሔር በገለጸላቸው ራእዪ መሠረት ነሐሴ ፯ ቀን ሐና ፀነሰች ።
ሐና ድንግል ማርያምን በፀነሰች ጊዜ የመውለጃዋ ቀን እስኪደርስ የታዘዘ መልአክ ሕፃንዋን ከማንኛውም ክፉ ነገር ይጠብቃት ነበር ። ከተፀነሰችበት ቀን ጀምሮ ምንም ርኩሰት እንዳይነካት መልአኩ ጠበቃት ፤ በሐሳብም በሥጋም ድንግል ሆና ለዘላለም እንደምትኖር የተነገረላት ናትና ።
ሐና ቅድስት ድንግልን በፀነሰችበት ወራት ታላቅ ደስታ ተደረገ ። ብዙ በሽተኞችም የሐናን ልብስ እየዳሰሱ ተፈወሱ ፣ ብዙ እውሮችም ልብስዋን እየነኩ ዓይኖቻቸው በሩላቸው ። ተአምራቱን ያዩ ምቀኞች ሰዎች ግን ቀንተው ሐናን ሊጣሉዋት ወሰኑ በድንጋይም ሊወግሩዋት ተስማሙ ። የእግዚአብሔርም መልአክ ለኢያቄም ተገልጾ "ወደ አድባረ ሊባኖስ ተራሮች ይዘሃት ውጣ" አለው ። ኢያቄምም መልአኩ እንዳዘዘው ወደ ሊባኖስ ተራሮች ይዝዋት ወጣ ። በዚያም አንድ ዋሻ ውስጥ ሳለች ወለደች ። ድንግል ማርያም በተወለደችበት ሰዓት ዋሻው በረቂቅ ሰማያዊ ብርሃን ተሞላ ፤ የሰማይ መላእክትም እግዚአብሔርን ሲየመሰግኑ ተሰሙ ፣ በሊባኖስ ተራሮች ጫፍ ብርሃናት እንደ ችቦ ሲበሩ ከሩቅ ታዩ ።
በድንግል መወለድም የአዳም ተስፋው ሊፈፀም ዋዜማው ተጀመረ "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" ተብሎ የተነገረለት ተስፋ ሊፈፀም መሠረት ተጣለ ። ሊቃውንት ይህን አስመልክተው "አዳም ከገነት በተሰደደ ጊዜ የመዳን ተስፋው ባንቺ በኩል ይሆናል" ብለው የሚያመሰግኑበት ዘመን (ዘመነ ሐዲስ) ሊጀመር አዋጅ ተነገረ ።
"መሠረቶችዋ በቅዱሳን ተራሮች ናቸው" ሲል ዳዊት የተናገረው ድንግል ማርያም ከአብርሃምና ከዳዊት ዘር መወለድዋን ለመግለፅ ነው መዝ.፹፮፥፩ እንዲሁም በመዝ.፵፬፥፲፪-፲፯ ፣ በሰለሞን መኃይልም ፣ በራእዪም በትንቢተ ኢሳያስ ... በብዙ መጽሐፍት የተተነበየላት ናት ።
ከ፴፫ቱ የእመብርሃን በዓላት ሁሉ የልደት በዓሏ የበለጠ መሆኑን ራሷ ቅድስት ድንግል ማርያም ፣ በቀን ሺህ ጊዜ "ሰአሊ ለነ ቅድስት" እያለ ለሚጸልይ ለአንድ ባሕታዊ እንደነገረች የቤተክርስቲያን አባቶች ይተርካሉ (ትርግዋሜ ቅዳሴ ማርያም ምዕራፍ አንድ) ። ወስብሐት ለእግዚአብሔር ።
- ^ ይህ ታሪክ የተገኘው ከመጽሐፈ ቀለምንጦስ ዘሮም ፣ ከገድለ አቡነ አዳም ፣ ከአክሲማሮስ (ሄክሳሜሮን) ዘኢጲፋንዮስ ከተባሉ የሥርዓት እና የትውፊት መጻሕፍት ነው