ኮንግ-ፉጸ

ከውክፔዲያ
ኮንግ-ፉጸ በ1 ዓም ያሕል እንደ ተሳለ።

ኮንግ-ፉጸ ወይም ኮንፉክዩስ (ቻይነኛ፦ 孔夫子) 558-487 ዓክልበ. የኖረ ቻይናዊ ፋላስፋ ነበረ። ፍልስፍናውና ትምህርቱ «የኮንግፉጸ ትምህርት» በተለይ በቻይና፣ በኮርያ፣ በጃፓንና በቬትናም አገር ባህሎች ላይ ጥልቅ ያለ ተጽእኖ አሳድሮዋል። በእርሱ ፍልስፍና፣ የግለሰብና የመንግሥት ግብረገብ፣ የኅብረተሠባዊ ግንኙነቶች ትክከለኛነት፣ የወላጆች ክብር፣ ፍርድና ቅንነት ልዩ ትኩረት አገኙ።

ኮንግ-ፉጸ በሉ ክፍላገር የተወለደ ሲሆን፣ በክፍላገሩ ውስጥ የፖለቲካ ሰው ነበር። በ509 ዓክልበ. የአንድ ከተማ ከንቲባ ከመሆኑ በኋላ፤ የክፍላገሩ ወንጀል ሚኒስትር ሆነ። ነገር ግን በፖለቲካ ረገድ በሙሉ ስኬታማ አልነበረም። ከክፍላገሩ ሦስት ታላላቅ ኃይለኛ ቤተሠቦች ወገኖች፣ ሁለቱ አምባዎቻቸው እንዲፈርሱ በመጨረሻ ተስማሙ፣ እንጂ ሦስተኛው እምቢ ብሎ ለኮንግ-ፉጸ እቅድ አልተከናወነለትም። ስለዚህ በ505 ዓክልበ. ኮንግ-ፉጸ ከሉ ክፍላገር ሸሽቶ ለጊዜው በስደት ኖረ።

ከዚያ እስከ 491 ዓክልበ. ድረስ ወደየክፍላገሩ ቤተ መንግሥት ጎብኝቶ የፖለቲካ ፍልስፍናውን ያስተምር ነበር፤ ሆኖም ሁላቸው ምክሩን ስላላስገቡ ይህ ደግሞ በጣም ስኬታም አልነበረም። በ491 ዓክልበ. ወደ ሉ በክብር ተመልሶ ከዚያ እስከ ዕረፍቱ ድረስ ወይም ለ4 ዓመታት ዕውቀቱን ለ77 ደቃ መዛሙርት (ተማሪዎች) ያስተምር ነበር።

ኮንግ-ፉጸ ከዘመኑ በፊት የኖሩ ስድስት ዋና ማስተማርያ መጻሕፍት አቀነባበራቸው። እነዚህም «ስድስቱ ጽሁፎች»፦

  1. የሰነዶች ጽሑፍ (ሻንግሹ) - ከንጉሥ ያው ዘመን (2100 ዓክልበ) ጀምሮ እስከ 635 ዓክልበ. ድረስ የነበሩት አለቆች ሰነዶች ያቀርባል።
  2. የበልግና የመጸው ዜና መዋዐሎች (ቹንጭዩ) - የሉ ክፍላገር ታሪክ 730-489 ዓክልበ.
  3. የሥነ ሥርዓቶች ጽሑፍ (ሊጂ) - ለሕዝብና ለመንግሥት የሚገቡ ደንቦች
  4. የቅኔ ጽሑፍ (ሺጂንግ)
  5. የለውጦች ጽሑፍ - (ኢ ቺንግ) - ጥንታዊ የቻይና ንግርተኛ ዘዴ
  6. የሙዚቃ ጽሑፍ (ዩዌ ጂንግ) - በ221 ዓክልበ. የኮንግፉጸ ትምህርት መጻሕፍት በተቃጠሉበት ጊዜ በሙሉ ጠፍቶ አሁን «አምስቱ ጽሑፎች» ናቸው።

በተጨማሪ የኮንግ-ፉጸ ጥቅሶች አናሌክትስ (ሉንዩ) በተባለ ጽሑፍ ተቀነባብረዋል።

ከኮንግፉጸ ሕይወት በኋላ ትምህርቶቹ ተከታይነት አገኙ፤ በ148 ዓክልበ. የሃን ሥርወ መንግሥት የኮንግ-ፉጸ ትምህርት ይፋዊ አደረጉት። ወደ ማዕረግ ለመሾም ዕጩዎቹ በዚህ እምነት መጻሕፍት ይፈተኑ ነበር። ከ212 እስከ 1360 ዓም ድረስ ግን ልዩ ልዩ የቻይና ግዛቶች ዳዊስም ወይም ቡዲስም የመንግሥት ሃይማኖት አድርገው ነበር። እንደገና 1360-1903 ዓም ዘመናዊው የኮንግፉጸ ትምሕርት በቻይና ይፋዊ ሆነ።

ዳዊስም ሃይማኖት ዘንድ፣ የእምነቱ መሥራች ላው ድዙ በ539 ዓክልበ. ያሕል ዳው ዴ ቺንግ እንደ ጻፈ፣ እንዲሁም አንዴ ከኮንግ-ፉጸ ጋራ እንደ ተገናኙ ይታመናል። በዘመናዊ ዳዊስም በኩል፣ ላው ድዙና ኮንግ-ፉጸ ሁለቱ እንደ አማልክት ይከብራሉ።

በተለይ በፓኪስታን የሚታወቅ ከእስልምና የወጣ ክፍልፋይ አሕማዲያ እስልምና እንዳለው፣ ኮንግ-ፉጸ እና ላው ድዙ ሁለቱ የአላህ ነቢዮች ነበሩ።