Jump to content

ሂሩት በቀለ

ከውክፔዲያ
1935 - 2015
ሂሩት በቀለ 1935 - 2015 ዓ.ም.

ሂሩት በቀለ ከ50ዎቹ መጀመሪያ እስከ 80ዎቹ መጨረሻ ድረስ በጊዜው ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ጥቂት ስመጥር የሴት አርቲስቶች መሐከል አንዷ ተወዳጅ ድምፃዊት የነበረች ስትሆን: በተጨማሪም የግጥምና የዜማ ደራሲ ነበረች። ሂሩት የተጫወተቻቸው ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃዋቿ እስከ አሁን ድረስ በህዝብ ዘንድ በጣም ተወዳጅና እንደውም ለብዙ አዳዲስ ወጣት ሴት አርቲስቶች መነሳሻና አቅም መፈተሻ የነበሩ መሆናቸው ግልጽ ነው።

የህይወት ታሪክ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ሂሩት በቀለ እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በእለተ ሰኞ መስከረም 28 ቀን 1935 ዓ.ም. ከእናቷ ከወ/ሮ ተናኜወርቅ መኮንንና ከአባቷ የመቶ አለቃ በቀለ ክንፌ በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ቀበና ተወለደች። እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስም ቀበና ሚሲዩን ት/ቤት[1] በመግባት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷ አጠናቃለች። ከዛም ቤተሰቦቿ ወደ አሰላ ለስራ በመዣወራቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አሰላ በሚገኘው በራስ ዳርጌ ት/ቤት ተከታትላለች::

የስራ ዝርዝር

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ሂሩት በትምህርት ቤት በነበረችበት ወቅት ለክፍል ጏደኞቿና ለሰፈሯ ልጆች ማንጎራጎር ታዘወትር ነበር:: ይህን ችሎታዋን የተመለከቱት ጏደኞቿም ወደሙዚቃው አለም እንድትገባ በተደጋጋሚ ያበረታቷትና ይገፏፏት ነበር:: በዚህ መሰረት እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1951 ዓ.ም. ከቅርብ ጏደኛዋ ጋር በመሆን ወደ ምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል[2] በመሄድ በድምፃዊነት ተፈትና ለመቀጠር በቃች:: ብዙም ሳትቆይ ለመጀመሪያ ግዜ በተጫወተችው “የሐር ሸረሪት” በተሰኘው ዜማ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትንና ተቀባይነትን አገኘች:: ይሄኔ ነበር የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ክፍል አይኑን የጣለባት። ጥሎባትም አልቀረ በ 1952 ዓ.ም. ላይ ከምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል እውቅና ውጪ የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ሂሩትን በመጥለፍ በጊዜው ኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ወደሚባለው የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ በመውሰድ በልዩ ኮማንዶዎች የ24 ሰዓት ጥበቃ እየተደረገላት ለበርካታ ወራቶች ተደብቃ ቆየች:: ከረጅም ወራቶች ያላሰለሰ ጥረት በኃላ የምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል ፍለጋውን ለማቋረጥ በመገደዱ: የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ክፍል ሂሩትን በይፋ በቋሚነት የሠራዊቱ የሙዚቃ ክፍል አባል አድርጎ ቀጠራት::

ሂሩት በቀለ በምስራቅ ጦር ግንባር ለሠራዊቱ የሙዚቃ ትርኢት ስታቀርብ

ሂሩት ከተጫወተቻቸው አያሌ ሙዚቃዎቿ መሀከል አንደ ህዝብ መዝሙር በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታወቀውና ከትንሽ እስከ ትልቅ በሀገር ፍቅር ስሜት እስከአሁን የሚያዜመው ኢትዮጵያ አንዱ ነው::

ሂሩት በፖሊስ ሰራዊት የሙዚቃና የትያትር ክፍል ውስጥ በቅንነት ለ35 ዓመት አገልግላለች:: በነዚህም 35 ዓመታት ውስጥ ከ­­­200 በላይ ሙዚቃዎችን የተጫወተችና ለህዝብ ጆሮ ያደረሰች ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በሸክላ የታተሙት ከ38 በላይ ሙዚቃዎች ሲሆኑ: በካሴት ደረጃ ደግሞ 14 ካሴቶች እያንዳዳቸው 10 ዘፈኖችን የሚይዙ ለሙዚቃ አፍቃሪዎቿ አበርክታለች::

ሂሩት በሙዚቃ አለም በቆየችባቸው አያሌ አመታት ውስጥ ከብዙ ስመጥር ድምፃውያን ጋር በመሆን ስራዋን ለህዝብ አቅርባለች: ከነዚህም መሀከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል: ማህሙድ አህመድ[3]: አለማየሁ እሸቴ[4]: ቴዎድሮስ ታደሰ: መልካሙ ተበጀ: ታደለ በቀለ: መስፍን ሀይሌ: ካሳሁን ገርማሞና ሌሎችም ይገኙበታል።

ሂሩት በቀለ ከ1987 ዓ.ም. በኃላ እራስዋን ከሙዚቃ አለም በማግለል ጌታን እንደግል አዳኟ በመቀበል ሙሉ ጊዜዋንና ህይወቷን ለመንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት ከ28 ዓመት በላይ በአገር ውስጥና በውጭ አገር በመዘዋወር ስለጌታችን እየሱስ ክርስቶ ታላቅነት ላልሰሙ በማሰማት አያሌ ወገኖች የእግዚህአብሄርን መንገድ እንዲከተሉና ወደ ህይወት እንዲመጡ ምስክርነት በመስጠት: በጸሎት በመትጋት ጌታን በዝማሬ እያገለገለች ትገኛለች::

ሂሩት በቀለ የመሰረተ ክርስቶስ ቤተክርስትያን አባል ስትሆን: ሶስት የመዝሙር አልበሞችንም ለክርስትያን ወገኖቿ አቅርባለች::

የግል ህይወት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ሂሩት በቀለ በሙዚቃ አለም በነበረችበት ጊዜ ከፍተኛ አድናቆትንና ዝናን ያተረፈች እንዲሁም ደግሞ በመንፈሳዊ ህይወቷ ደሰታንና የመንፈስ እርካታን ያገኘች ቢሆንም: የግል ህይወቷን በተመለከተ ግን ያላትን ትርፍ ግዜ ሁሉ ከልጆቿና ከቤተሰቧ ጋር ማሳለፍ እጅግ አድርጎ ያስደስታት ነበር::

ሂሩት ከሙዚቃ ስራዋና ከመንፈሳዊ ህይወቷ በተጨማሪ፥ በጨዋታ አዋቂነቷ በቅርብ የሚያውቋት የስራ ባልደረቦቿ: ጏደኞቿና ቤተሰቦቿ ይናገራሉ::

ሂሩት በቀለ ባደረባት የስኳር ህመም ምክንይት በአገር ውስጥና በውጪ አገር ለረጅም ጊዜ ህክምናዋን ስትከታተል የቆየች ቢሆንም የጌታ ፈቃድ ይፈጸም ዘንድ ግንቦት 4, 2015 ዓ.ም. በተወለደች በ 80 አመቷ ወደምትወደውና ሁሌም ወደምትናፍቀው ወደ የሰማይ አባቷ በክብር ሄዳለች::

ሂሩት በቀለ የ7 ልጆች እናት፣ የ10 ልጆች አያት እና የ7 ልጆች ቅድመ አያት ነበረች።

ሂሩት በቀለ በሙያዋ ላበረከተችው አስተዋጽዎ ከአገር ውስጥና ከውጭ ሀገር በርካታ ሽልማትና የእውቅና ምስክር ወረቀት ያገኘች ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ለመጥቀስ ያህል:

1ኛ) ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ እጅ ከወርቅ የተሰራ የእጅ አምባር እና የምስጋና ደብዳቤ

2ኛ) ከኢትዮጵያ ፖሊስ ሰራዊት ኮሚሽነር የከፍተኛ ስኬትና የላቀ አስተዋጽዎ ሽልማት ከምስክር ወረቀት ጋር

3ኛ) በሙዚቃው ዓለም ላበረከተችው ተሳትፎ ከፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ የብር ዋንጫና የምስጋና ደብዳቤ

4ኛ) በሙዚቃው ዘርፍ ለእናት ሐገሯ ላበረከተችው ከፍተኛ አስተዋጽዎ ከቀድሞዎ የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃማርያም እጅ ሰርተፍኬት

5ኛ) ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በኢትዮጵያና በሱዳን ህዝቦች መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማደስ ላበረከተችው አስተዋፅኦ የእውቅና የምስክር ወረቀት

6ኛ) ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላበረከተችው የሙዚቃ አስተዋፅዖ ከኢትዮጵያ አብዮታዊ ጦር የፖለቲካ አስተዳደር የምስጋና ደብዳቤና ሽልማት

7ኛ) ከፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ የቲያትር እና ሙዚቃ ክፍል የ25-ዓመታት ከፍተኛ ስኬት እና የላቀ አስተዋፅኦ የምስክር ደብዳቤ ከፍተኛ ሽልማት ጋር

8ኛ) ከቀድሞ የሰሜን ኮርያ ፕሬዘዳንት ኪም ኢል ሱንግ እጅ ከወርቅ የተሰራ ሜዳልያ

9ኛ) ከኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽነር: ለፖሊስ ሃይል ስፖርት ፌስቲቫል ላበረከተችው አስተዋፅኦ የእውቅና ሰርተፍኬት

10ኛ) ከመሰረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን: ላበረከተችው አስተዋፅኦ ልዩ እውቅና እና የምስጋና ሰርተፍኬት

11ኛ) ከወንጌል ብርሃን አለማቀፍ አገልግሎት ቤተክርስቲያን: በሃይማኖታዊ ህይወት ላሳየችው ትጋትና አስተዋፅኦ የምስጋና ሰርተፍኬት ይገኙበታል

12ኛ) ከጠቅላይ ምንስትር አብይ አህመድ እጅ የህይወት ዘመን ግልጋሎት ሜዳልያ ይገኙበታል

  1. ^ Kebana Adventist School
  2. ^ https://en.wikipedia.org/wiki/Ethiopian_National_Defence_Force_Band
  3. ^ https://en.wikipedia.org/wiki/Mahmoud_Ahmed
  4. ^ https://en.wikipedia.org/wiki/Alemayehu_Eshete