Jump to content

ለማ ገብረ ሕይወት

ከውክፔዲያ

ለማ ገብረ ሕይወት በሀገር ባሕል ዜማ የታወቀና በተለይም ኃይለኛ የሆነ ድምፅ የነበረው ኢትዮጵያዊ ድምፃዊና የዜማና መጽሐፍ ደራሲ ነበር።

የህይወት ታሪክ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ለማ ገ/ሕይወት በ፲፱፻፲፰ ዓመተ ምሕረት በቡልጋኮረማሽ ልዩ ስሙ ሰንበሌጥ ማርያም ነው የተወለደው። የቄስ ትምህርቱንም እዚያው ቡልጋ ውስጥ የከሰምን ወንዝ ተሻግሮ መስኖ ማርያምተከታትሏል። በጠላት ወረራ ጊዜ ጥሩ ድምጸኛ በመሆኑና በአካባቢው ሽለላ፣ ቀረርቶ እና ፉከራ የሚችለው እንዳልነበር የሚነገርለት ለማ፣ አርበኞችን እየዘፈነ እየሸለለ ያዝናና እና ያበረታታ እንደነበር ተዘግቧል።[1] ለማ ከ፲፯ ዓመት ዕድሜው እስከ ፲፱፻፵፪ ዓ.ም. ድረስ በጦር ሠራዊትና በክብር ዘበኛ ወታደርነት ተቀጥሮ አገልግሏል።

ለማ በ፲፱፻፵፪ ዓ.ም. በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ተቀጥሮ የሙዚቃ ንባብና ባሕላዊ እንዲሁም ዘመናዊ መሣሪያዎችን መጫወት ተምሯል። ከዚያም በ፲፱፻፵፰ ዓመተ ምሕረት አዲሱ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ለንጉሠ ነገሥቱ ፳፭ተኛ የዘውድ በዓል ሲመረቅ ከቀረቡት ዘፋኞች አንዱ እርሱ ነበር። በዚሁ ቴአትር የኦርኬስትራው ኃላፊ እና ተዋናይም በመሆን ለብዙ ዘመናት አገልግሏል። የኢትዮጵያንም ባሕላዊ ሙዚቃ በአሜሪካ፤ በሶቪዬት ኅብረት እንዲሁም በሌሎች የወዳጅ አገሮች እየዞረ የማስተዋወቅ ግዴታውን ተወጥቷል።

ለማ በሙያው ተደንቆና በሕዝብ ዘንድም በመታወቁ ተደስቶ የኖረ ሰው ነበር። የለማ ልዩ ስጦታው በሽለላ ላይ ያዘነበለ ነው፣ ከዘፈኖቹ የበለጠ ታዋቂነት ያገኘው ግን ከውጭ ባሕላዊ ግፊት ወይም ተጽእኖ ነፃ በሆኑት ባሕላዊ የሠርግ ዘፈኖቹ ነበር። ድምፁ ያለ ድምፅ ማጉያ የጎላ ነው። «የዜማ ፍቅር የያዘኝ በሕፃንነቴ ወራት በደን ከብቶችን በምጠብቅበት ወቅት እንደ ቀረርቶ የመሳሰሉትን ሳንጎራጉር ነበር» ሲል እራሱን አስተዋውቋል።[2]

ለማ ሚያዝያ ፲፬ ቀን ፲፱፻፹፮ ዓመተ ምሕረት፣ በተወለደ በ ፷፰ ዓመት ዕድሜው አዲስ አበባ ላይ አረፈ።

የሥራዎች ዝርዝር

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ለማ ብዙ ዜማዎች ደርሷል። ከእነርሱም መካከል «ያዘው ጎበዝ» የተባለው እና የሠርግ ዘፈኖቹም በሕዝብ ዘንድ በጣም ይወደዳሉ። ለማ ከድምፃዊነቱም በላይ «አይረሳም» በሚል አርዕስት ስለ ኢትዮጵያ አርበኞች ታሪክ በግጥም የሚታወስ መጽሐፍ ደርሷል።[2]

  1. ^ Encycopaedia Aethiopica ጌታቸው ደባልቅ፤ የአርባ ቀን መታሰቢያ(1986)
  2. ^ "ናሽናል ቢብሊዮግራፊ ቡድን፣ የአንጋፋ አርቲስቶች መዝገበ የሕይወት ታሪክ፣ መጋቢት ፳፻፣ ገጽ 28-29". Archived from the original on 2011-09-29. በ2010-12-17 የተወሰደ.

http://www.youtube.com/watch?v=Hvs6Xwc6-gc