መልካሙ ተበጀ
መልካሙ ተበጀ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ የተውኔትና ዜማ ደራሲ፣ የቲያትር ተዋናይ እና ድምፃዊ ነው።
መልካሙ ተበጀ የተወለደው በ፲፱፻፴፰ ዓ.ም. በሲዳሞ ክ/ሀገር ክብረ መንግሥት በሚባል ቦታ ነው። መልካሙ የሙዚቃ ፍቅር ከሕፃንነቱ ጀምሮ አብሮት ያደገ ነው። ቤተሰቦቹ ለሥራ ጉዳይ ወደ ሐረር ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ሲዛወሩ አብሮ በመምጣት በአምኃ ደስታ ትምህርት ቤት ይገባል። በትምህርት ቤት በተለያዩ በዓላት በተለይም በወላጆች ቀን በሚያደርገው ተሳትፎ የሙዚቃ ስሜቱ ከእሱ አልፎ በተመልካች ዘንድ እየጎላ በመሄድ ነሐሴ ፲፭ ቀን ፲፱፻፶፯ ዓ.ም. በብሔራዊ ቲያትር የታዳጊ ኦርኬስትራ /ዳዊት ኦርኬስትራ/ በድምፃዊነት ተቀጠረ።[1]
መልካሙ ከግጥምና ዜማ ደራሲነቱ ባሻገር ቲያትርም የመድረስና በተዋናይነት የመሳተፍ ችሎታ ያለው ሲሆን ስለ ማህበራዊ ህይወት፣ ስለ ወጣትነት፣ ስለ ተፈጥሮ፣ ስለ ፍቅር እና ስለ ሌሎችም ብዙ የተጫወተ አንጋፋ ከያኒ ነው።[1]
መልካሙ እስካሁን ድረስ ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ዜማዎችን ተጫውቷል። ከእነዚህም ዜማዎቹ አንድ መቶ ሃምሳ ያህል የራሱ ድርሰቶች ናቸው። «የሲዳሞ ቆንጆ»፣ «በይ እንግዲህ ተለያየን»፣ «ቸብ ቸብ»፣ «ዳህላክ» እና «ሙዚቃ» የተሰኙ ዜማዎቹ እራሱ ደርሶ ከተጫወታቸው ዘፈኖች መካከል በዋቢነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።[1]
የድርሰት ችሎታውን ካስመሰከረባቸው ስራዎቹ አንዱ የሆነውና እራሱም በተዋናይነት የተሳተፈበት «ቢሮክራሲያዊ የከበርቴ አሻጥር» የተሰኘው ድርሰቱ ነው። መልካሙ በበርካታ የቴሌቪዥን ድራማዎች ከመጫወቱ ሌላ በፀጋዬ ገ/መድህን በተደረሰው «አቡጊዳ ቀይሶ»፣ በአያልነህ ሙላት በተደረሰው «ሻጥር በየፈርጁ» እና በሌሎችም ቲያትሮች ተሳትፎአል።[1]
ጅምር! ይህ አጭር ጽሑፍ መሠረት ወይም መዋቅር ነው። አሁን ሊያስፋፉት ይችላሉ! |