Jump to content

ሚንጊ

ከውክፔዲያ

ሚንጊ ማለት በደቡባዊው የኢትዮጲያ ክፍል በተለይም በኦሞ ወንዝ አካባቢ ኑሯቸውን ባደረጉ የኦሞ እና የሀመር ህዝቦች የሚዘወተር ባህላዊ ልማድ ነው። በባህሉ መሰረት ሚንጊ ናቸው ተብለው የተፈረጁ ልጆች ንጹህ እንዳይደሉ እና በማህበረሰቡም ላይም እርግማን ያመጣሉ ተብሎ ይታሰባል። ከዚህም የተነሳ የተለያዩ እርምጃዎች ህጻናቱ ላይ ይደርስባቸዋል። አንድ ህጻን ሚንጊ ነው የሚባለው ከታችኛው ጥርሱ ቀድሞ የላይኛው ጥርሱ ከበቀለ፣ ልጆቹ መንታ ሆነው ከተወለዱ እንዲሁም ከጋብቻ ውጪ የተወለዱ ልጆች ሲሆኑ ነው። ሳይንሳዊ ጥናት እና ምርምሮች እንደሚያሳዩት የህጻን ልጆች ጥርስ የአንዳንዱ የላይኛው ቀድሞ ሲበቅል የአንዳንዱ ደግሞ ታችኛው ቀድሞ ይበቅላል። ይህም በልጆቹ ጤንነት ላይ የሚያሳድረው ምንም አይነት አሉታዊ ተጽዕኖ የለም። መንታ ልጅ መውለድም ቢሆን እርግማን አይደለም።

የጎሳ መሪ የሆኑ ሰዎች በአካባቢያቸው ሚንጊ የሆነው ልጅ እንዳለ ካወቁ ቶሎ ብለው መጥተው ልጁን ወደ ጥልቅ ጉድጓድ ወይም ወንዝ በመወርወር ፣ አፉ ውስጥ ብዙ አፈር በመጨመር እንዲሁም ህጻኑን ጫካ ውስጥ በመጣል ህይወቱ እንዲያልፍ ያደርጋሉ። በዚህ ባህል እጅግ በጣም ለቁጥር የሚታክቱ ብዙ ህጻናት ተሰውተዋል። ሚንጊ ናቸው ተብለው ከሚፈረጁት ህጻናት ባለፈ የአካል ጉዳተኛ ሆነው የሚወለዱ ወይም ከተወለዱ በኋላ በለጋ እድሜያቸው የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ህጻናትም ይሄው እጣ ፈንታ ይገጥማቸዋል። በዚህ አሰቃቂ ሁኔታ የሚሞቱ ህጻናት ስርዓቱን የጠበቀ የቀብር ስነ ስርዓት እንኳን አይደረግላቸውም። ሚንጊ እንደሆኑ እንደታወቀ የጎሳው መሪ አካላት ወደ ቤታቸው በመሄድ ህጻናቱን ከእናታቸው እጅ ነጥቀው በመውሰድ ህይወታቸው እንዲያልፍ ያደርጋሉ።

መቼ እና እንዴት ተጀመረ?

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ይሄ ባህል መቼ እና እንዴት እንደተጀመረ በውል የሚታወቅ ነገር ባይኖርም ነገር ግን በተለያየ ምክኒያት ለአካባቢው ማህበረሰብ ጥንክሮ በመስራት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ማይችሉትን ለመቀነስ ታስቦ የተጀመረ ባህል እንደሆነ አንዳንዶች መላ ምታቸውን ያስቀምጣሉ። ከዚህ መላ ምት ያለፈ የተጻፈ እና የተሰነደ ስለ ባህሉ ታሪካዊ አመጣጥ የሚገልጽ የታሪክ መዝገብ የለም።

ሆኖም ግን ለረዥም ጊዜያት ሲተገበር እንደኖረ ግልጽ ነው። በዚህ ባህል ምንም የማያውቁ ህጻናት ገና ምንም ሳያውቁ እርግማን ታመጣላችሁ በሚል ሰበብ ህይወታቸው እንዲያልፍ ይደረጋል። እናቶችም ለዘጠኝ ወራት በሆዳቸው ተሸክመው፣ በብዙ ስቃይ አምጠው ወልደው፣ አጥብተው ያሳደጉትን ልጅ የጎሳቸው መሪዎች በጉልበት ነጥቀው ወስደው አይናቸው እያየ በሚዘገንን ሁኔታ ጭካኔ በተሞላው መንገድ ሲሞቱ ማየት ቀላል ነገር ሊሆንላቸው አይችልም። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ከፍተኛ የሆነ የሞራል ጉዳት እና ስብራት ይደርስባቸዋል። ሆኖም ባህሉ እጅግ ስር የሰደደ እና በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘ ስለሆነ ልጃቸውን በእምባ ከመሸኘት በስተቀር አማራጭ የላቸውም።

እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር ከ1936 - 1947 ዓ.ም ባለው ጊዜ ጣሊያን ኢትዮጲያ የኔ ግዛት ናት ባለችበት ወቅት በምስራቅ አፍሪካ የኢጣሊያ ግዛት ናቸው በተባሉ ቦታዎች ሁሉ ላይ መሰል ድርጊቶች እንዳይደረጉ አግዳ ነበር። በዚህ መቀትም ሚንጊ ናቸው ብሎ ልጆችን መፈረጅ እና ህይወታቸው እንዲያልፍ ማድረግ እንደ ትልቅ ወንጀል ይቆጠር እና ያስቀጣ ነበር። ከብዙ አመታት በኋላም በ2012 ዓ.ም የካሮ ህዝቦች ሚንጊ የሚለው ባህል መቀረት እንዳለበት ስምምነት አድርገው ነበር። ሆኖም ይሄው ስምምነት በተፈለገው ደረጃ መሬት ላይ ሊወርድ አልቻለም ነበር። አሁን ድረስም ከ680,000 ያላነሱ የማህበረሰቡ አካላት ይህንኑ ጎጂ የሆነ ባህል እንደሚተግብሩት ይታወቃል።

የማስቆም ሂደት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ላሌ ላቡኮ የተባለ የካሮ ጎሳ ተወላጅ ገና የአስራ አምስት አመት ልጅ እያለ ሚንጊ ነው ተብሎ በማህበረሰቡ የተወገዘ ህጻን ልጅ ሲገደል በማየቱ እጅግ በጣም አዝኖ ነበር። ላሌ ከዚህ ፣ማህበርሰብ ከተገኙ ሰዎች መካከል በሚሽነሪ ትምህርት ቤቶች የመማር እድል ያገኘ ልጅ ነበር። ካደገ በኋላም እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም አንዲት ህጻን ወላጆቿ በትዳር ሳይጣመሩ የወለዷት በመሆኗ ብቻ ልትገደ እያለ የሚችለውን ሁሉ በማድረግ ህይወቷን ያተረፋል። ከዚህም በኋላ ቀስ በቀስ እንደዚህ ሚንጊ የተባሉ ልጆችን ከሞት በማትረፍ እና ወደ ከተማ በመወሰድ ለህጻንቱ የሚሆን መጠለያ ስፍራ በማዘጋጀት ያሳድጋቸው ጀመር። ይሄ በጎ ስራውም ቀስ በቀስ እየተሰማ ሄዶ የዚህን ህዝብ ታሪክ እና የእርሱን መልካም ስራ የሚዘክሩ ሁለት ዶክመንታሪዎች ተሰርተዋል። የመጀመሪያው drawn from the water የሚል እና በ2012 የተሰራ ሲሆን ከዚህ በመቀጠልም በ2015 ዓ.ም ጆን ሮው (John Rowe) [1]በሚባል እውቅ ፊልም ፕሮዲዩሰር አማካኝነት omo child : the river and the bush የሚል ዶክመንታሪ ተሰርቶ ለእይታ በቅቷል። ዶክመንታሪዎቹም ሽልማትን አግኝተው ነበር። ከጊዜያት በኋላም ላሌ ከፕሮዲዩሰሩ John Rowe ጋር በመሆን የኦሞ ልጆች ድርጅትን ከፍተው ህጻናትን ከሞት ለማትረፍ እየሰሩ ይገኛሉ። በJohn ርowe አጋዥነት ለዚሁ አላማ በተሰራ መጠለያ ቤት ውስጥም ወደ 50 የሚደርሱ እድሜያቸው ከ 1 እስከ 11 የሆነ የእድሜ ክልልየሚገኙ ህጻናት ከሚንጊ ሞት ተርፈው ይኖራሉ።

  1. ^ http://realscreen.com/2015/11/20/exclusive-journeyman-acquires-omo-child-doc/