ማሪቱ ለገሰ
ማሪቱ ለየአምባሰል ንግስት” በመባል የምትታወቀው ታዋቂ የባህል ዘፋኝ ማሪቱ ለገሰ አስደናቂ የሙዚቃ ጉዞዋን የጀመረችው እ.ኤ.አ. ለብዙ አሥርተ ዓመታት የሚዘልቅ የተለያየ ዲስኮግራፊ ያለው፣ የሚያስደስት አድናቂዎች። እ.ኤ.አ. በ2015 በወሎ ዩኒቨርሲቲ በክብር ተሸላሚ ሆና በሙዚቃ ኢንደስትሪው ውስጥ የተከበረ ሰውነቷን አጠናክራለች። ባቲ፣ ትዝታ እና አምባሰል የነበራት አተረጓጎም አድናቂዎቿን በአድናቆት በመተው አድናቆትን አትርፈዋል።ገሰ የኢትዮጵያ ታዋቂ ዘፋኝ ስትሆን ብዙ ባህላዊ የሙዚቃ ስራወችን በማቅረብ ትታወቃለች።
የአምባሰሏ ንግስት ታላቋ ድምጻዊት ማሪቱ ለገሰ በያዝነው ሳምንት ከሩብ ክፍለ ዘመን የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ሀገሯ ገብታለች።አዲስ አበባ ስትገባም በርካታ አድናቂዎቿ ደማቅ አቀባበል አድርገውላታል።አስደናቂ ከሆነው የሙዚቃ ህይወቷ አንጻር ለማሪቱ የተደረገላት አቀባበል ቢያንስባት እንጂ አይበዛባትም።ለመሆኑ ግን ማሪቱ ለገሰ ማን ናት?
የክብር ዶ/ር አርቲስት ማሪቱ ለገሰ በደቡብ ወሎ ዞን በደሴ ዙሪያ ወረዳ ከድጆ 018 ቀበሌ አባባሌ መንደር በ1937 ዓ.ም ነው የተወለደችው። ገና ከልጅነቷ ጀምሮ ሙዚቃ የእሷ ልዩ ተሰጥኦ ነበር።በ1992 ዓ.ም ወደ አሜሪካ ከመውጣቷ በፊት ከጋዜጠኛ ደረጄ ሀይሌ ጋር ባደረገቸው ቃለመጠይቅ በልጅነቷ ዘፈን ባለበት ቦታ በሙሉ እየተጠራች ትዘፍን እንደነበር ተናግራለች።በሰርጉም በበአሉም ብቻ ዘፈን እና ጨዋታ ባለበት ቦታ ሁሉ እኔ አለሁ ትላለች ማሪቱ።ማሪቱ ከልጅነት ጀምሮ ወደ ደሴ ከተማ በመግባት በተለያዩ መጠጥ ቤቶች በግል ስትጫወት የቆየች ሲሆን በ1961 ዓ.ም የወሎ የአገር ባህል ተጫዋች ማህበር በ61 አባላት ሲመሠረት እርሷም የዚህ ማህበር አባል ነበረች።
በኋላ ላይ ደግሞ ዝነኛው ላሊበላ ኪነት ሲቋቋም ከመስራቾቹ ቀዳሚዋ ማሪቱ ነበረች።በወቅቱ ታዋቂው ከያኒ ቀለመወርቅ ደበበ ላሊበላ ኪነትን ሊያደራጁ ወደ ደሴ ሲሄዱ መጀመሪያ ከመረጧቸው አርቲስቶች መሀከል ዋናዋ ማሪቱ ናት።ከ1971 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ በወሎ ላሊበላ የኪነት ቡድን ውስጥ በመሆን በአምባሰል፣ አንቺ ሆዮ፣ በባቲ፣ በትዝታ ሙዚቃዎች ንግስት ሆና አገልግላለች።
ማሪቱ በዚያ ኪነት ውስጥ መሰንቆ ተጫዋች ከነበሩት ባለቤቷ እና ከሌሎች አርቲስቶች ጋር ብዙ ስራዎችን የሰራች ሲሆን በአንድ ወቅት ኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም ወደ ደሴ በሄዱበት ወቅት በኪነቱ እንቅስቃሴ ተደስተው ለቡድኑ አውቶቢስ ሸልመውት ነበር። ያ ወቅት ዛሬ እንደ ህዝብ መዝሙር የሚዘፈኑት እነ አምባሰል ፤ እሪኩም ፤ ከመከም ፤ ቃሮዬ ፤ አካሌ ውቤ ፤ ዞማዬ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማሪቱ አንደበት የተበረከቱበት ወቅት ነበር።ዘፈኖቹ በጣም ከመወደዳቸው የተነሳ በየቦታው ይደመጡም ነበር።
በአንድ ወቅት አባቷ ከሚኖሩበት ገጠር ልጃቸውን ለማየት ወደ ደሴ ሲመጡ በህዝብ ማመላለሻ አውቶቢስ ላይ የልጃቸውን ድምጽ ይሰማሉ።ይሄኔ ሮጠው አውቶቢሱን ያስቆማሉ።ምነው ሲባሉ ይቺ የምትዘፍነው የኔ ልጅ ናት አባትሽ ሊጎበኝሽ መጥቷል ነይ ውረጅ በላት ይላሉ ፤ ሹፌሩም ስቆ የሚዘፍነው ካሴት እንደሆነ ሲነግራቸው በል ዘፍና እስክትጨርስ እዚሁ ቁምልኝ ብለው ተሳፋሪውን ሁሉ አስቀዋል።
ደሴ ላይ የራሷ የባህል ቤት የነበራት ማሪቱ አዲስ አበባ ከመጣች በኋላም ያንኑ ስራ እየሰራች ሰኬታማ ሆና በህዝብም ተወዳጅ ሆና ነበር።ከሌሎች ታላላቅ አርቲስቶች ጋር በመሆንም በህዝብ ለህዝብ ስራ ላይ ተሳትፋለች።ከዚህም ጋር የተያያዘ ገጠመኝ አላት።ገጠመኙም እሷና ብዙነሽ በቀለ አሜሪካ ከደረሱ በኋላ አንድ ክፍል ይመደቡና ወደ ማረፊቸው ይገባሉ።ሲገቡም ክፍሉ ባዶ ሆኖ ያዩታል።እንዳይጠይቁ የቋንቋ እጥረት አለባቸው ፤ ዝም እንዳይሉም ሳይተኙ ሊያድሩ ሆነ።እንዲያው ቆመው ሲቆዝሙ የቡድኑ መሪ ካሳ ከበደ መጡ።ምን ሆናችሁ ነው ሲሏቸው ችግሩን ነገሯቸው።እሳቸውም ስቀው ማብሪያ ማጥፊያውን ሲጫኑት አልጋው ተዘረጋ።ማሪቱ እና ብዙዬም እንቅልፋቸውን ተኝተው አደሩ።
ማሪቱ የሰውም ሙዚቃ ደግሞ መዝፈን እና ልብስን ደግሞ መልበስ አትወድም።በተለይም በሀገር ባህል ልብስ ተጠቃሚነቷ ትታወቃለች።በመቶዎች የሚቆጠር የሀገር ባህል ልብስ እንዳለት ትናገራለች።በልጅ ሞት ሀዘን የደጋገማት ማሪቱ ሀገር ቤት ስትገባ የጠበቃት አቀባበል ግን አሁንም ብዙዎች እሷን እንደ እናታቸው እንደሚያዩአት ያመላከተ ነበር።ማሪቱ ወዳጇ ብዙ ነው።ከወዳጆቿ መሀከል ደራሲ አሌክስ አብርሀም አንዱ ነው።አሌክስ በአንድ ወቅት ስለ ማሪቱ የጻፈውን ግሩም ጽሁፍ እዚህ ጋር እንጨምረው።
ማሪቱ ለገሰ ዘፋኝ ናት እንዴ ?
“የአንድ ጓደኛየ እናት ይሞታሉ …. ቆይቷል … ለቀስተኛው ድንኳኑን ሞልቶ እስኪወጣለት አልቅሶ ለቅሶም ቀዝቀዝ እያለ …ወደሰባተኛው ቀን አካባቢ ሁኖታል …. ዘግይቶ የመጣ ወዳጅ ዘመድ አልፎ አልፎ እያለቀሰ ሲገባ ብቻ ውስጥ ያለው ቤተሰብ ተቀብሎ ትንሽ ማልቀስና ተው ተው ተብሎ ዝም ማለት ካልሆነ በስተቀር …. ለቅሶው ወደማብቃቱ ነበር ! ታዲያ ወደአስር ሰአት ገደማ ይሆናል ከድንኳን ውጭ እንደቤተክርስቲያን ደውል የሚያስገመግም መረዋ ድምፅ አንጀት በሚበላ ዜማ ሙሾውን እያወረደ ወደድንኳኑ ቀረበ ….ለስራ አዲስ አበባ ከርማ ገና ወደደሴ የገባችውና መርዶውን ሰምታ እህል ውሃ ሳትል የመጣቸው የሟች ቅርብ ወዳጅ ማሪቱ ለገሰ ነበች እንግዲህ አልቃሸዋ… መንደርተኛው በዚች ሴት የሃዘን እንጉርጉሮ ልቡ ተነካ … እንኳን ቤተሰብ ሊያፅናና ሁሉም የየራሱን ብሶት ዘርግፎት ትኩስ ሞት አስመሰለው …. እስካሁን ያ ድምፅ ውስጤ አለ …!
የገረመኝ ይሄ አይደለም …ከወራት በኋላ የቀለጠ ሰርግ ላይ ማሪቱን እንደማንኛውም ታዳሚ ተጠርታ ተገኝታለች ….‹‹ማሬዋ አቦ እንደው ለሙሽሮቹ ክብር ›› ተብላ ማሲንቆ የያዘ ሰውየ አጅቧት ያ ተአምረኛ ድምፅ ዳሱን ሞላው ….ጫጫታው ባንዴ መርፌ ቢወድቅ ወደሚያሰማ ዝምታ ተቀየረ … ረጭጭ …. የማሪቱ ድምፅ ይሄው በእያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ደም ስር ውስጥ ዛሬም አለ … ያኔም ይነዝረን ጀመረ… የማሪቱ አምባሰል የሰርገኛውን መንፈስ ወሰደው …. እናም ማሪቱ የሰርግ ዘፈን አልነበረም በአንባሰል ዜማዋ ያንቆረቆረችው …ድብን ያለ የሃዘን እንጉርጉሮ እንጅ ….እየዘፈነች ከወራት በፊት እናታቸውን በሞት ወዳጡት ቤተሰቦች ሄደች …የሟች ሴት ልጅና የልጅቱ አባት … ማለትም የሟች ባለቤት ….
ልጅቱም ጥቁር ጥለት ያለው ነጠላ ለብሳ …አባትየውም ጥቁር ቆብ አድርገው ጥጋቸውን ይዘው ተቀምጠው ነበር ….ሰርገኛው መሃል ….ማሪቱ በሚያስደምም የአምባሰል ዜማዋ … አሁን ላይ የረሳሁትን ግጥም ብቻ ሃዘን ምናባቱ … ሟችም አፈር ይቅለላት የሚሉ ቃላት ያሉበት ….እያቀነቀነች ወደልጅቱ ቀረበች እናም ጥቁር ጥለት ያለው ነጠላዋን ከልጅቱ ላይ ገፋ የራሷን ባለ ባንዲራ ጥለት ነጠላ ልጅቱ ላይ ደረበችላት (እንግዲህ በዚህ ሁሉ ዘፈኑ አልተቋረጠም) ሌላ ሰውየም የአባትየውን ጥቁር ቆብ አወለቀ …. ከየት እንዳመጡት እንጃ ሃዘንተኛውን ልጅ ፀጉሯን ቅቤ ቀቡት …አባትየውንም ለወጉ ፀጉራቸውን በቅቤ ሽው ደረጓቸው መስሎኛል ……. ሰርገኛው እልልታውን አቀለጠው ……ግዲህ በወሎ ባህል ሃዘን በቃ የሚለው ጎረቤት ነው ….ሃዘንተኛው ከዛ በኋላ ጥቁር አይለብስም ራሱንም አይጥልም ! ማሪቱ ወዲያው ዜማውን ቀየረችው ሞቅ ያለ የቦረና ዜማ ….ከዛማ ምኑ ቅጡ ሰርግ ቤቱ በጭፈራና በእልልታ በአንድ እግሩ ቆመ !
ማሪቱ ለዎሎ ህዝብ ዘፋኝ አይደለችም!! በዘፈኗ ኑሮውን ብሶቱን ፍልስፍናውን ባህሉን ፍቅሩን ማንነቱን የከተበች ህያው ብራና እንጅ ….ማሪቱ ለገሰ ለመላው የኢትዮጲያ ህዝብ እነዛን ድንቅ ቅኝቶች ሳይዛነፉ ተፈጥሯዊ ለዛቸውን እንደያዙ በድምፅ ያቆየች የታሪክ ብራና ናት ….ማሪቱ ዘፋኝ አይደለችም …. እራሷ ዜማ ናት … ማሪቱ ብትጠና የማታልቅ እራሷ ትውፊት ናት ራሷ ባህል ናት ! እውነቱን እናውራ አይደል ….አንድ ሰው የትም ሳይወጣ ሳይወርድ ቁጭ ብሎ የማሪቱን ዘፈን ያድምጥ ዘፈን ሳይሆን የህዝቡን ደስታ … የህዝቡን ብሶት …የህዝቡን መከራ የህዝቡን ክፉና ደግ ዘመኖች ሁሉ መሃተም በሆነ ድምፅ ልቦናው ላይ ያትማል !
ማሪቱ ምናለች …
ውሸቴን ነው እንጅ እንደው ስግደረደር
እኔስ ለዎሎ ልጅ ውሃ ሸጨ ልደር
እኔስ ለጦቢያ ልጅ ውሃ ሸጨ ልደር ….
ያኔ በዛ ዘመን በወሎም ይሁን በመላው ኢትዮጲያ እንኳን ውሃ ወተት መሸጥ ነውር ነበር …እግር የጣለው ሰው ፎሌ ሙሉ ርጎውን ግፎና አንጀቱን አርሶ መርቆ ብቻ የሚሄድበት ዘመን …. ታዲያ ‹‹ውሃ ሻጭ ›› ማለት ትልቅ ፀያፍ ስድብ ነበር … ማሪቱ ይሄን ነው የምትነግረን ‹‹ለአገሬ ልጆች ስል ፀያፍ ልባል ምናምንቴ ልባል ›› አለች ! ስለህዝብ ስድብን ልሸከም አለች ! ስለአገር አንድነት … ተከባብሮ ተፋቅሮ ስለመኖር በዘፈኖቿ ብዙ ብዙ ብላለች …ጀግንነታችንን ‹‹ዘራፍ ›› ብላ የማይወርድበት ማማ ላይ ሰቅለዋለች ! ያውም ህዝቡ ውስጥ እንደህዝቡ እየኖረች … በእግሯ የስንት ሰአት የእግር መንገድ እየተጓዘች ….ግጥም ተፅፎላት ዜማ ተቀምሮላት በይ ተብላ ሳይሆን ….ድምፅ ተሸጦ ግጥም ተሸቅጦ በማይኖርበት እንደውም መዝፈን ‹‹አዝማሪ›› እያስባለ በህዝብ አስነቅሮ በሚያስተፋበት ዘመን ….ማሪቱ ለገሰ ፊደል ሳትቆጥር የአንድን ህዝብ እውነት በድምፅ ብራናዋ ላይ ቀርፃ ለትውልድ አኖረችው … !
ያኔ እንደዛሬው የሙዚቃ ተንታኝ ባልነበረበት ዘመን በህዝቡ ልቦና ተመዝና ሚዛን የደፋች በተፈጥሮ ዜማን አብጠርጥረው በሚያውቁ አባቶቻችን መንፈስ ላይ ሃሴትን የዘራች ታላቅ ሴት ናት ማሪቱ ለገሰ!! …ያውም ሴት ልጅ አደባባይ ወጥታ ልትዘፍን ቀርቶ ቀና ብላ የባሏን አይን እያየች መናገሯ እንደብልግና በሚቆጠርበት ዘመን ነው የምላችሁ ! ሬዲዮው የሚነግረን እነሜሪ አርሜዲ ቀድመው አደባባይ ወጡ እያለ ነው አይደል …ዘጋቢ በሌለበት ታሪኳን በድምፅና ምስል ቀርፆ የጮኸ ሰው በሌለበት ሆነ እንጅ …. ያውም በድቅድቅ ጨለማ በባዶ እግሯ ስለዘፈን ጭው ካለ ገጠር ተሰዳ ከተማ የተከሰተች ሴት ጥራ ካላችሁኝ ቅድሚያ ማሪቱን ከመጥቀስ ወደኋላ አልልም …. ሙዚቃ ትውፊታችን ነው …ባህላችን ነው ካልን ከዚች ሴት በላይ የዘመኗን እውነት ዘመን በማይሽረው ዜማና ግጥም ያስቀመጠ ኢትዮጲያዊ ዘፋኝ ካለ ይሄው አምጡና ሚዛኑ ላይ አስቀምጡ !
ማሪቱ ለገሰ እንደታዋቂ እራሷን ላይ ሰቅላ በህዝቧና በራሷ መካከል የክብር አጥር የገነባች ሴት አልነበረችም …እንደውም ደሴ በነበረችበት ቀን ሰው ሞተበት ሲባል ነጠላዋን አዘቅዝቃ የእዝን ሻይና ዳቦ ይዛ ሃዘን ቤት ስትሄድ መንገድ ላይ ታገኙዋት ነበር …ይች ሴት እንዲህ በታላላቆቹ የሙዚቃ ሰዎች እንኳን የተመሰከረለትን ድምፅዋን ሳንቲም መሰብሰቢያ አላደረገችውም …እንዳላት ስምና ዝና ምንም ነገር አልነበራትም … አሁን ኑሮዋ በውጭ አገር ነው እንደምሰማው ግን እዛም ይሄ ነው የሚባል ሃብት ያፈራች ሴት አይደለችም … ይታያችሁ ልክ በሩጫው ለአስርት አመታት የክቡር ዶክተር አትሌት ሃይለ ገብረ ስላሴ ብቃቱ ሳይወርድ በሩጫው እንዳኮራን …ማሪቱ ለገሰ በትንሹ ከአርባ አመታት በላይ የድምፅዋ ለዛ እንዳለ ብቃቷ ትንሽ እንኳን ሳይወርድ ዛሬም እያስደመመችን አለች ! እኔ ሳልወለድ የዘፈነችውን ዘፈን ስሙና ከሳምንት በፊት የዘፈነችውን ዘፈን አድምጡ ከዛ ያልኩት እንዳልተጋነነ ይገባችኋል !
አምባሰልን ከማሪቱ ለገሰ በላይ ያሽሞነሞነው ድምፃዊ ካለ …ይሄው እከሌ አለ በሉና ጥሩ …ሰርፀ ፍሬስብሃት አንዴ ምናለ ‹‹ስለማሪቱ የአዘፋፈን ስልትና የድምፅ ቅላፄ እንደው ተአምር ነው ከማለት ውጭ የምለው የለም …›› አለ ….እኔም ዛሬ ስለተአምረኛዋ ማሪቱ ለገሰ አወራኋችሁ “
በ ኪሩቤል አንበሴ ተተርጉሞ የቀረበ
ጅምር! ይህ አጭር ጽሑፍ መሠረት ወይም መዋቅር ነው። አሁን ሊያስፋፉት ይችላሉ! |