ሮቢን ሁድ

ከውክፔዲያ
ሮቢን ሁድ 1912 እ.ኤ.አ. ስዕል

ሮቢን ሁድእንግላንድ አገር አፈ ታሪክ የታወቀ ወንበዴ ወይም አርበኛ ነው። በፍላጻም ሆነ በሰይፍ፣ እሱና ቡድኑ «ከሀብታሞች ሠርቀው ለድኆች ይሰጡ ነበር» ይባላል። በዘመናት ላይ ትውፊቱ ተቀይሮ አሁን በበርካታ ፊልሞች ውስት ታይቷል።

በታሪካዊ መዝገቦች በኩል፣ ተመሳሳይ ስም መጀመርያ የተገኘው ከ1224 እና 1236 እ.እ.አ. መሃል በዮርክሺር ክፍላገር ሰነዶች ላይ አንድ «ሮበርት ሆድ» የተባለ ሰው ነበር። ስሙ ደግሞ «ሖበሆድ» እና «ሮበርት ሁድ» ተብሎ ይጻፋል። በ1224 እ.እ.አ. ለቤተክርስቲያን ዕዳ ስለነበረው ሕገ ወጥ ተባለ፣ ንብረቱም ተያዘ ። ሆኖም ወንበዴ እንደሆነ የሚል ሰነድ አልተገኘም።

ከ1261 እና 1300 እ.እ.አ. መካከል፣ «ሮቢን ሁድ» የሚባል ወንበዴ ይታወሳል። ከቅድመኖቹ ታሪክ ጸሐፊዎች አንዱ (ጆህን ዘፎርዱን) እንዳለው፣ ይህ ሮቢን ሁድ ደሞ የሳይሞን ደ ሞንትፎርት ወገን ደጋፊና ተዋጊ ነበር። በተረፈ ሮጀር ጎድበርድ የሚባለው ወንበዴ በእውነት የሳይሞን ደ ሞንትፎርት ተከታይና ደጋፊ መሆኑ ስለሚታወቅ፣ «ሮቢን ሁድ» የርሱ መጠሪያ እንደ ሆነ ይታሥባል።

እንዲሁም በ1323 እ.እ.አ. አንዱ የንጉሥ 1 ኤድዋርድ ሠራተኛ «ሮቢን ሁድ» እንደተባለ ይታወቃል፤ ነገር ግን ወንበዴ ወይም አርበኛ እንደ ሆነ የሚል የለም።

በ1370 እ.እ.አ. ያህል የተጻፈው ግጥም «ፒርስ ፕላውማን» መጀመርያ «የሮቢን ሁድ ቅኔዎች» ይጠቅሳል። በ 1402 እ.እ.አ. ይሄ ምሳሌ፣ «ብዙ ሰዎች ስለ ሮቢን ሁድ ተናግረው ቀስቱንም ከቶ አልሳቡም» ይዘገባል። ከዚህ ትንሽ በኋላ፣ «ሕዝብ ወደ ቅዳሴ ከመሔድ ይልቅ የሮቢን ሁድ ትውፊትና ዘፈን መስማት ይወዳሉ» የሚል ቅሬታ ታትሞ ይገኛል። የተጻፉት ግጥሞች እራሳቸው ከ1450 እ.እ.አ. ጀምሮ ታውቀዋል። በነዚህ ታሪኮች ሮቢን የእንግላንድ ንጉሥና የኖቲንግሃም አለቃ ጠላት ነው። በ1500 እ.እ.አ. የተቀነባበረው «የሮቢንሁድ ታሪክ» ንጉሡን «ኤድዋርድ» ይልዋል።

በ1521 እ.እ.አ. «የሮቢን ሁድ መቼት ንጉሥ 1 ሪቻርድመስቀል ጦርነት ተመልሰው በጀርመን አገር ሲታሥሩ ሆነ» የሚል ሀሣብ መጀመርያ ቀረበ። ይህ የሪቻርድ ወንድም ሉዑል ጆህን በእንደራሴነት እንግላንድ በገዙበት ዓመት ወይም በ1193 እ.እ.አ. ነበር ማለት ነው።

በቅድመኞቹ ትውፊቶች ዘንድ ሮቢን ተራ ሰው ቢባል፣ ከ1569 እ.እ.አ. ጀምሮ ከመክውንንት መደብ እንደ መጣ ይነገራል።

ደራሲው ሰር ዋልተር ስኮት 1819 እ.እ.አ. በጻፉት ልቦለድ «አይቫንሆ» ውስጥ፣ ሮቢን ሁድ የሳክሶኖች ቅሬታዎች አርበኛ፣ ጠላቶቹም ጆህን እና የኖቲንግሃም አለቃ የኖርማን ወገን ባለሥልጣናት መሆናቸው ግልጽ ይደረጋል። ይህም የትውፊቱ ዘመናዊ አስተያየት ሲሆን ባብዛኛው ግዜ በፊልሞች ሲታይ እንደዛ ነው። ከተሠሩት ተከታታይ ድራማዎች አንዱም The Adventures of Robin Hood (1955 እ.እ.አ.) በኢትዮጵያ ተሠራጭቷል።