Jump to content

የሲቢሊን መጻሕፍት

ከውክፔዲያ
(ከሲቢሊን መጻሕፍት የተዛወረ)

የሲቢሊን መጻሕፍትግሪክ የተጻፉ የትንቢት ግጥሞች ክምችት ነበሩ። በአፈ ታሪክ የጥንታዊ ሮማ ንጉሥ ታርኲኒዩስ ሱፐርቡስ ከአንዲት ሲቢል (ሴት ነቢይ) ገዝተዋቸው በሮማ መንግሥት ታሪክ ታላቅ አደጋ በተከሠተበት ወቅት እኚህ ትንቢቶች ይማከሩ ነበር።

የዛሬው ምሁሮች እኚህ መጻሕፍትና ዛሬ የታወቁት በክርስትና አባቶችም ከ2ኛ ክፍለዘመን እስከ 5ኛ ክፍለዘመን ድረስ በሰፊ የተጠቀሱት የሲቢሊን ራዕዮች አንድ አይደሉም ባዮች ናቸው።

የኩማይ ሲቢል - በ17ኛ ክፍለዘመን ሰዓሊው ዣክ ግራንቶም

መጻሕፍቱ ደግሞ ለግሪኮች ታወቁ። መጀመርያ የታዩ በገርጊስደብረ ኢዳ (ለጥሮአስ ትንሹ እስያ ቅርብ የሆነ) በአፖሎ ቤተ መቅደስ በ7ኛው ክፍለዘመን ዓክልበ እንደ ነበር ይታመናል። ደራሲይቱ የሄሌስፖንት ሲቢል ተባለች። ከዚያ ክምችቱ ከገርጊስ ወደ ኤሩትራይ (በምሥራቅ ትንሹ እስያ) እንዳለፈ የኤሩትራይ ሲቢልም ሥራ እንደ ተባለ ይታመናል። ይኸውም ክምችት ከዚያ እስከ ኩማይ ጣልያ ከዚያም እስከ ሮማ ከተማ እንደ ተጓዘ ይመስላል።

አይኔይድ ደራሲ ቪርጂል ዘንድ አይኔያስ ወደ ሢኦል ሳይጓዝ የኩማይ ሲቢልን አማከሮ ነበር። ንጉሥ ታርኲንዮስ ከኩማይ ሲቡል እንዴት እንደ ገዟቸው ዝነኛም አፈ ታሪክ ነበር። እርሷ ዘጠኝ የትንቢት መጻሕፍት ክምችት ለታርኲን ለመሸጥ ብታስብ እሳቸው ውድ በመሆኑ እምቢ ብለው ሦስቱን እንዳቃጠለች ይተረታል። ከዚያ በኋላ ስድስቱን ቀሪዎች መጻሕፍት ለፊተኛው ዋጋ ለመሸጥ አሰበች። ሁለተኛ እምቢ ብለው ሌላ ሶስት አቃጠለች። በመጨረሻ ሶስቱን የተረፉ መጻሕፍት እንዳይጠፉ ለዚህ ዋጋ ገዙና በሮማ በዩፒተር ቤተ መቅደስ አኖሯቸው።

መጻሕፍቱም ለ2 የሮማ ባለሥልጣናት አደራ ተሰጡ። ከ375 ዓክልበ. ጀምሮ አሥር ጠባቂዎች -- አምሥት ከባለሥልጣናት ወገንና አምሥት ከተራ ዜጎች ወገን -- ተሾሙላቸው። ከዚህ በኋላ (ምናልባት በሱላ ጊዜ 96-86 ዓክልበ.) ቁጥራቸው እስከ 15 ተጨመረ። የኚህ ጠባቂዎች ተግባር ከአስጊ ሁኔታዎች ለማለፍ ተገቢ ስርዓት ምን እንደ ሆነ ማማከር ነበር። ሆኖም ስርአቱን ብቻ እንጂ ምስጢራዊ ትንቢቱን እራሱን አልገለጹም ነበር።

የመጻሕፍቱ ተጽእኖ የምሥራቅ አማልክትን ለምሳሌ አፖሎ፣ «ታላቂቱ እናት» ኩቤሌ እና ኬሬስ፣ እንዲሁም የግሪኮች አረመኔ እምነት ወደ ሮማ አረመኔ ሃይማኖት አስገባ።

ግጥሞቹ በግሪክ ስለተጻፉ ጠባቂዎቹ ሁልጊዜ በሁለት የግሪክ አስተርጓሚዎች ይረዱ ነበር። የዩፒተር መቅደስ በ91 ዓክልበ. በተቃጠለበት ወቅት ግን ጠፉ። ስለዚህ የሮማ ላይኛ ምክር ቤት (ሴናት) በ84 ዓክልበ. ተልእኮዎች ተመሳሳይ ትንቢቶች አገኝተው እንዲተኩ ላኩዋቸው። በተለይም ትንቢቶች የተለቀሙ ከትሮይ ከኤሩትራይ ከሳሞስ ደሴት ከአፍሪካ (ማለት የዛሬ ቱኒዚያ) በጣልያም ከሲሲልያ ደሴትና ከቲቡር ነበር። አዲሱን ክምችት ወደ ሮማ ካመጡ በኋላ የሮማ ቄሶች እውነት የመሠላቸውን ለይተው ሌሎቹን ግን ከክምችቱ ጣሉ።

የሮማ ንጉሠ ነገሥት አውግስጦስ በ20 ዓክልበ. ወደ አፖሎ መቅደስ አዛውሮአቸው ተመርምረው አዲስ ቅጂ ተደረገ። እዚያ እስከ 397 ዓ.ም. ቆዩ። በዚያን ጊዜ የአሪዮስ ክርስትና ትምህርት አራማጅ የሆነ ስቲሊኮ እንዳቃጠላቸው ይባላል።

በ2ኛው ክፍለዘመን ደራሲ የትራሌስ ፍሌጎን መጽሐፍ የጉዶች መጽሐፍ ወይም መታሠቢያ ውስጥ ከሲቡላውያን መጻሕፍት 70 መስመሮች ተጠቀሱ። ይህ ጥቅስ ስለ አንድ ፍናፍንት ልደትና ስለ ጣኦቶች መሥዋዕት ሥርአት ይናገራል።

በታሪክ ከተመዘገቡት ምክሮች መኻል ፦

  • ዓክልበ. 407: መጻሕፍቱ ከአንድ ጨነፈር የተነሣ ተማከሩና ሌክቲስቴርኒዩም የተባለው ሥነ ሥርዓት ለአማልክታቸው ጣኦት ተመሠረተ።
  • ዓክልበ. 303: እንደገና ከጨነፈር በኋላ ደግሞ ብዙ ወታደሮች በመብራቅ ስለ ተመቱ መጻሕፍቱ ተማክረው አንድ ቤተ መቅደስ ተሠራ።
  • ዓክልበ. 301: ከሌላ ጨነፈር ቀጥሎ ተማክረው መልሱ ጣኦቱን አይስኩላፒዩስ ወደ ሮማ ከኤፒዳውሮስ (በግሪክ) እንዲያመጡ ሆነ። ሆኖም የሮማ ሴናት በጦርነት ተይዞ ከአንድ ቀን ጸሎት በቀር ስለ አይስኩላፒዩስ ነገር ምንም አላደረገም።
  • ዓክልበ. 246: «የአበባ ጨዋታዎች» (Ludi Florales) በመጻሕፍቱ ምክር ተመሠረቱ።
  • ዓክልበ. 224: የካርታጌና አለቃ ሃኒባል የሮማ ጭፍራ በካናይ ፍልሚያ ሲያጠፋ፥ መጻሕፍቱ ተማክረው እንደ ምክራቸው ሁለት ግሪኮችና ሁለት ጋውሎች በሮማ ገበያ በሕይወታቸው ተቀበሩ።
  • ዓክልበ. 212: በካርታጌና ጦርነት ጊዜ የሮማ አበጋዝ ስኪፒዮ አፍሪካኑስ ከመጻሕፍቱ ምክር የተነሣ የኩቤሌ ጣኦት ከፔሢኖስ አምጥቶ አምልኮቷን በሮማ አስገባ።
  • ዓክልበ. 71: «በሮማ ሦስት ቆርኔሌዎሶች ሊገዙ ነው» ከሚል ከአንዱ ትንቢት የተነሣ ፑብሊዩስ ቆርኔሌዎስ ሌንቱሉስ ሱራ አንድ ሤራ አደረገ።
  • ዓክልበ. 63: 12 በጥሊሞስ ወደ ግብጽ ዙፋን እንዲመለሱ ሮማውያን ሥራዊቱን መላካቸውን ሲማከሩ፣ መብራቅ በድንገት የዩፒተር ጣኦት መታ። ስለዚህ የሲቢሊን መጻሕፍት ተማክረው «ከግብጽ አንድ ንጉሥ መቸም እርዳታ ቢለምንሽ፣ ወዳጅነትሽ አይቀርለት እንጂ ጣርና አደጋ እንዳያገኙሽ ሥራዊት ከቶ አትሥጪው» የሚል ትንቢት በመገኘቱ ይህ ቃል የበጥሊሞስን መመለስ በጣም አቆየ።
  • ዓክልበ. 52: «በጳርቴ ላይ ማሸነፍ የቻለው ንጉሥ ብቻ ይሆናል» ስለሚል ትንቢት ቄሣርሮማ ሬፑብሊክ ላይ ንጉሥነትን በቶሎ እንደሚይዝ ያለ ጭምጭምታ ተፈጠረ።
  • 7 ዓ.ም.: በርማ ንጉሠ ጢባርዮስ ቄሣር ዘመን (የክርስቶስ ልደት አካባቢ) የሮማ ቲቤር ወንዝ ሲጎርፍ አንዱ ቄስ መጻሕፍቱ እንዲማከሩ አስቦ ጢባርዮስ ምስጢራዊ ስለቆጠራቸው እምቢ አለ።
  • 263 ዓ.ም.: ሮማውያን በፕላኬንቲያ ፍልሚያአላማኒ ጀርመኖች ከተሸነፉ በኋላ መጻሕፍቱ ተማከሩ።
  • 304 ዓ.ም.: ከሚልቪያን ድልድይ ፍልሚያ አስቀድሞ የተቃዋሚ አለቆች ማክሰንቲያስቆስጠንጢኖስ ሲያዘጋጁ ማክሴንቲዩስ የሲቢሊን መጻሕፍት አማከሩና ቆስጠንጢኖስ እምነታቸውን ከአፖሎ ወደ ክርስቶስ አዛወሩ። በፊልሚያውም የማክሴንቲዩስ ድል መሆኑ ስመ ጥሩ ድርጊት ነው።
  • 355 ዓ.ም.: የሮማ ንጉሥ ዩሊያኖስ ከሃዲ በጳርቴ ላይ ዘመቻ ሊያደርግ ሲል መጻሕፍቱን አማከረ። ከሮማ የደረሰውም መልስ በዛኛው አመት ጠረፍ መሻገሩን በግልጽ ደገፈው።

የውጭ መያያዣ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]