ክርስቶስ

ከውክፔዲያ
Jump to navigation Jump to search

ክርስቶስ ማለት ከግሪክኛ ቋንቋ Χριστός ነው፤ ይህም ለመሢሕ (ከዕብራይስጥ ማሺያሕ ወይም «የተቀባ») ትርጒም ነው። በክርስትና እምነት እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ (ረቢ ይሆሹዓ) ስያሜ ይጠቀማል፤ «የተቀባ» ማለትም ወልድ (ከሥላሴ አንዱ) ሆኖ ለንጉሥነት ማለት ነው። «በእርሱ የመለከት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና» (ቈላስ. ፪፣፱) በአዲስ ኪዳን የተመሠረተ እምነት ነው። በትምህርተ ሥላሴ ዘንድ እሱ ብቻ መላው አምላክ ሳይሆን የፈጣሪው ክንድ ወይም አካል ነው፤ እንደ አብመንፈስ ቅዱስ ሆኖ ደግሞ በሌሎች ቦታዎች አለ።

ብሉይ ኪዳን ደግሞ «መሢሕ» የሚለው ቃል በዕብራይስጡ በመዝሙረ ዳዊት 2 እና በትንቢተ ዳንኤል 9 ይገኛል፤ በአዋልድ መጻሕፍትም በዕብራይስጥ ትርጉማቸው ባይተርፉም በተለይ በመጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤልና በመጽሐፈ ሄኖክ ውስጥ አምላክ በምድር እንደ ሰው ልጅ ሆኖ ለመጎብኘትና በመጨረሻ ለዘላለም ለመግዛት እንዳቀደ ይገልጻል። በተጨማሪ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ብዙ ሌሎች ጥቅሶች ስለ መሢሕ እንደሚነብዩ ይታመናል።

ክርስቶስ ቅድመ ዓለም ያለ እናት ከባሕርይ አባቱ ከአብ ፣ ድኀረ ዓለም ያለ አባት ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ የተወለደ፣ ሥጋን እና ነፍስን ከቅድስት ድንግል ማርያም ነሥቶ ሰው የሆነ የባሕርይ አምላክ ነው::የሰውን ልጅ ከባርነት ነጻ ለማውጣት ፣ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከባርነት ወደ ነጻነት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን ለማሸጋገር፤ ፍቅር ከዙፋኑ ስቦት የወረደ፤ አምላክ ነው ኢየሱስ ክርስቶስ::

ክርስቶስ ኢየሱስ ቸር እረኛ፣ አምላክ፣ ወልደ አምላክ፣ ሰውም አምላክም፣ ሲሆን በክርስቲያኖች መካከል ስለ ባሕርይው የተለያዩ አመለካከቶች አሉ::በጥንታዊት ቤተክርስቲያን ማለትም ከጉባኤ ኬልቄዶን በፊት አንዲት ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን በነበረችበት ወቅት ያለው አስተምህሮ 'ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው ፤አምላክ ነው፤ አምላክ ደግሞ አንድ ባሕርይ አለው፤ ክርስቶስም አንድ ባህርይ አንድ አካል አለው ይል ነበር:: ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ፣ ሰውም አምላክም፣ ትስእብት(ሥጋ) ከመለኮት ጋር ፍጹም ከተዋሐደ በኋላ እንደ ሁለት አካል ወይም ባህርይ አይቆጠርም ፤ብላ ታስተምር የነበረች አለማቀፋዊት ቤተክርስቲያን በጉባዔ ኬልቄዶን ከሁለት ተከፈለች::ይህም አንድ ባሕርይ እና ሁለት ባሕርይ በማለት ነበር::

ነገር ግን ማንም ክርስቲያን ቢሆን አሁን ላይ ያለው እምነት ክርስቶስ የዓለም መድህን፣ የእግዚአብሔር ልጅ ፣ የሕይወት መገኛ፣ ህብስተ ሕይወት፣ መንገድ እና መልካም እረኛ እንደሆነ፤ የሰውን ልጅ ድንቅ በሆነ ፍቅሩ ከሰይጣን አገዛዝ ነጻ ያወጣ ፣ በምድር አባት በሰማይ እናት የሌለው ፣ ሁለት ልደታት ያለው፣ ከብርሃን የተገኘ የዓለም ብርሃን ፣ ቅን ፈራጅ እና እውነተኛ ዳኛ እንደሆነ ይታመናል:: ክርስቶስ በክርስትና ዓለም ላሉ ሰወች መራራ ሞትን ሞቶ ሕይወትን የሰጠ ፣መራራ ከርቤን ጠጥቶ ጣፋጭ ወይንን(ደሙን) ያጠጣ፣ ራቁትን ሆኖ ፀጋን ያለበሰ፣ ተሰቅሎ ሰይጣንን ከፊታችን ጠርቆ ያስወገደ ፣ ተርቦ ሰማያዊ ሕብስትን ያበላ የሁሉም አዳኝ መሆኑ ይታመናል::

ክርስቶስ-«ሁሉም በእርሱ ሆነ፥ (በእርሱ ተፈጠረ)፥ ከሆነውም (ከተፈጠረውም) ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም። ዮሐ ፩፥፫።-ተብሎ እንደተጻፈ፤ ደግሞም በትንቢት ነብዩ ኢሳይያስ <<ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።>> ተብሎ እንደተተነበየ፤ በወንጌልም <<ቃል እግዚአብሔር ነበረ>> ተብሎ የምሥራች እንደተነገር፤ በዮሐንስ ወንጌል ሐዋርያው ቶማስ ጌታዬ አምላኬ ብሎ እንደመሰከረ፤ ክርስቶስ እግዚአብሔር መሆኑ በብዛት ባለንበት ዓለም ይታመናል::ነገር ግን ከዚህ የተለየ እምነት በአለማችን እንዳለም ይታወቃል::

: